Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ቀዳሚና ተከታይ!

ሰላም! ሰላም! በቀደም ዕለት እንዲያው ግራ ግብት ብሎኝ የሆድ የሆዴን  የማጫውተው ሰው ብፈልግ አጣሁ። ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ሥራ ሥራ እያለ ቀልቡ ከእሱ ጋር የለም። ባሻዬ የተጣላ ሲያስታርቁ፣ ቀብር ሲደርሱና ዕድሩን ሲመሩ ጊዜ አጡ። የነገሩን ዙሪያ ባስስ ባስስ ባዶ ሆነብኝ። እናንተ ሆናችሁብኝ እንጂ ሰው በሞላበት አገር ሰው አጣሁ ብሎ ማውራትም እኮ ያሳፍራል። ኋላ ዘወር ስል አንድ መጽሐፍ አዟሪ ‹‹መጽሐፍ›› ብሎ ‹‹ወዳጄ ልቤ›› የሚል አስነበበኝ። ባሻዬ፣ ‹‹እግዜር የሚናገርለት ሰው ቢያጣ ድንጋይ ያናግራል…›› የሚሉት ነገር ትዝ ብሎኝ መዥረጥ አድርጌ ከኪሴ ብር አወጣሁና መጽሐፉን ገዛሁት። ግን አታስዋሹኝ እስካሁን አላነበብኩትም። በቆምኩበት ለአንድ የሚከራይ ቤት ድለላ የቀጠርኳቸውን ሰዎች እየጠበቅኩ በቆምኩበት ከልቤ ጋር ጨዋታ ያዝኩ። ከማሻሻጥ ወደ ኪራይ ድለላ ከገባሁ ወዲህ ኑሮዬ ብቻ ሳይሆን፣ አስተሳሰቤም እየተለወጠ ነው ስላችሁ መጪውን አዲስ ዓመት በጉጉት እየተጠባበቅኩ ነው፡፡ መጠበቅ ነው!

‹‹እሳትስ ይነዳል እንጨት ካልገደዱ፣ ሰው ከርሞ ይርቃል ልብ ነው ዘመዱ›› ተብሎ አይደል? ታዲያ ከብቸኝነቴ ብሶ ከልቤ ጋር ጨዋታ መያዜ ይባስ ብቸኛ አደረገኝ። ወጪ ወራጁን ስታዩት ልቡን ልብ የሚልም ጠፍቷል። እንዲያውም ካነሳነው አይቀር ሰው ልቡ የሚመክረውን ከመስማት የሰው ምክር እየሰማ መስሎኝ መከራ እየመከረ ያስቸገረው። እውነቴን እኮ ነው። ልብ ይስጠን ነው መቼም። ታዲያ አጫውተኝ ያልኩት ልቤ በጥያቄ ላይ ሌላ ጥያቄ እያስከተለ ሕመሜን አባሰው። ‹‹ምነው ሰው ነፍሱርቃኗን ቀረች?›› ይለኛል። ‹‹ኧረ ተወኝ?›› ስለው፣ ‹‹ምነው ፍቅር ቀዘቀዘች?›› ይለኛል። ‹‹እኔ ምን አውቄ?›› ስለው፣ ‹‹ምነው እንዲህ እነ አቶ ውሸት፣ እነ ወይዘሮ ሐሜት፣ እነ ባሻ ምቀኝነት፣ እነ አጅሬ ፍቅረ ንዋይ ናኙ!?›› ይለኛል። ‹‹ጉድ ነው!›› እላለሁ አፍ አውጥቼ። ታዲያ ከልቤ አስጥሉኝ ብዬ አልጮህ። ለነገሩ ብንጮህም የሚጥለን እንጂ የሚያስጥለን ጠፍቷል። ወይ ልቤና እኔ!

መቼም መኖር ደግ ነው። በመቆየት ብዙ አየን። ያደላቸው ደግሞ ላላዩት ጭምር ያያሉ። እሱን ‹‹ፀጋ›› ብሎ ማለፍ ሳይሻል አይቀርም። የምር ግን እያዩ የማያዩ፣ እየሰሙ የማይሰሙ ሰዎች ቁጥር አልበዛባችሁም? እኩል ኖረን ታሪክ ስንተርክ የምንደባደብ ሰዎች አገሩን ሞላነው ምነው? በቀደም አንድ ወዳጄን እንዲህ ብለው ቁም ነገሩን ስቶ፣ ‹‹ተው እንጂ አንበርብር! ታክሲ የሚሞላው አንሶ መንገዱን አትሙላው። የት ልንሠለፍ ነው?›› ብሎ አፌዘ። ዘመን መቼም ብዙ ምዕራፎች እንዳሉት አውቃለሁ። ግን እንዲህ ያለ የምናነሳ የምንጥለው ነገር ሁሉ በፌዝ የታጀበ የሚያደርግበት ምዕራፍ እንዳለው አልጠረጥርም ነበር። ብዙ ጊዜ እኮ ቁም ነገሩን የምንስተው ፌዝ እየደባለቅን ሆኗል። ፌዝ ሲበዛ ደግሞ ጭካኔ ይከተላል፡፡ አይመስላችሁም? እኔን ከመምሰል አልፎ እውነት እየሆነብኝ ነው፡፡ ያስብላል!

ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ይኼን ትችት ሰምቶ፣ ‹‹አሁንስ አበዛኸው!›› አለኝ። ለምን አበዛሁት? ስንት ያበዙት እያሉ አንተስ እኔን መገሰፅን ለምን አበዛኸው?›› ስለው፣ ‹‹ቆይ አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ? የትውልዱ እጥር ምጥን ያለች የኑሮ ዘይቤ መፈክር ምንድናት?›› ብሎ ጠየቀኝ። ‹‹ፎካሪዎቹ እንጂ እኔ ምን አውቄ?›› ስለው፣ ‹‹አታካብድ ትባላለች›› ብሎ ወደ ትንታኔው ገባ። ‹‹እንግዲህ ይኼ ትውልድ የከበደ ነገር ላይወድ፣ ላይቀበል፣ ላይደራደር ወደዚህ የዓለም ታሪክ ምዕራፍ የመጣ እስኪመስል ማካበድ አይወድም። ሌላው ቀርቶ የተቆለለ ተራራ፣ እግዚኦ የሚያስብል ደመና ሲያይ አይወድም። ዘመኑም ይኼን አውቆ ከመቼውም ጊዜ በላይ ሲበሉት ቀላል፣ ሲለብሱት ቀላል፣ ሲነካኩት በቀላሉ፣ ሲያላምጡት በቀላሉ፣ ሲውጡት በቀላሉ የሚወራረዱ ነገሮችን የሚያመርት አዕምሮ አስነስቷል…›› አለኝ። ሳስበው ተዋጠልኝም አልተዋጠልኝም ያለው እውነት አለው። እያዩ ያለ ማየት፣ እየሰሙ ያለ መስማት ጉዳይም ከዚህ ጋር እንደሚያያዝ ታየኝ። አቃለን አቃለን ይኼው ቀለን የምንኖረውን ቤት ይቁጠረን። እውነቴን እኮ ነው። ብቻ የዚህ ዓለም የቅሌት መዝገብ የተከፈተ ቀን እንደለመደብን ከዓለም ሁለተኛ፣ ከአፍሪካ አንደኛ ሆነን እንዳንገኝ ፀልዩ አደራ፡፡ አያያዛችን አያምርማ፡፡ አይደል እንዴ!

የዚህ አቃሎ የመቅለል የዘመኑ ‹‹ፎርሙላ›› ትዝ ብሎኝ ልቤን ‹‹ሳይለንት›› አድርጌ ሳስብ ሳለሁ ማንጠግቦሽ ደወለች። ‹‹ወዬ?›› ስላት፣ ‹‹ሽሮ አልቆብኛልና እስካስፈጭ ከባልትና ሁለት ከረጢት ምጥን ሽሮ ገዝተህ እንድትመጣ…›› አለችኝ። ባለሙያዋ ሚስቴ መቼስ ሁሌ አይሞላላትም። ነገሩ እኮ ግራ አጋቢ ሆኖ የምንበጣበጠው፣ ሁሌም ሙሉ የሆነላቸው ሰዎች ስለበዙብን መሰለኝ። እናም ወደ ጨዋታዬ ስመለስ ደንበኞቼ መዘግየታቸውን ተረድቼ እዚያው አካባቢ ባልትና ቤት ፍለጋ ጀመርኩ። ለሠፈሩ እንግዳ መሆኔን ስረዳ አንድ ልጅ እግር አውደልዳይ ጠራሁና እዚህ አካባቢ ሽሮ የሚሸጡ አሉ ብዬ መጠየቅ። የአጠያየቄ ክፋት። ዘመኑ ነው!

እሱ ታዲያ ሰባት ቤቶች ቆጠረልኝ። እንዳልተግባባን ልብ በሉ። ‹‹እንዴ ይኼ ሁሉ ባልትና ቤት? በዚህ አካባቢ ያለ ሰው አተር ለቅሞ አስፈጭቶ ቤቱ ማዘጋጀቱን ትቶት ነው?›› ስል፣ ‹‹ኧረ ባልትና እዚህ ሠፈር የለም። እኔ እኮ ሽሮ ብቻ የሚሸጡ ምግብ ቤቶችን ያሉኝ መስሎኝ ነው…›› አለና እርሜን አወጣሁ። ወይ ሽሮ? እኮ ለሽሮም ሠልፍ? ድሮ እኮ ሬስቶራንት በላሁ ተብሎ ጉራ የሚነዛው በእነ ላዛኛ፣ ቴላቴሊ፣ ፒዛ፣ ቺክን አሮስቶ፣ መንዲ ምናምን ነበር። ድሮ እኮ አሁን ነው ዝም አትበሉ ‹‹ፕሊስ›› እንዲህ ባዕድ አገር እንደ ገባ ሰው በሽሮ ቤት ጋጋታ ስመሰጥ ደንበኞቼ ከየት መጡ ሳልላቸው ከች ብለው፣ ‹‹ላረፈድንበት እዚህ ቆንጆ ሽሮ ቤት አለ። ምሳ እንጋብዝህ…›› ብለው ይዘውኝ ላጥ። ከወንዱ የሴቱ ብዛት። ደግሞ ከሁሉ ከሁሉ የቢሉ ቢለዋነት። ደግሞ ደግሞ ከሁሉ ከሁሉ ኑሮ ከበደን ብለን የምንጮሃት ጩኸት። እኔ  ነገራችን ተምታታብኝ!

ተምታቶብኝ አልቀረሁም፡፡ ልክ ሥራዬን እንደ ጨረስኩ ወደ ቤቴ ገሰገስኩ። ማንጠግቦሽ አኳኋኔን ዓይታ ገና ሳትጠረጥር፣ ‹‹ሠራተኛ ላመጣ ነው…›› አልኳት። ውዷ ባለቤቴ እንደ ሰው ሬስቶራንት ለሬስቶራንት ባትንጎራደድ፣ እንዲያው ለአንድ ወር እንኳ ሠራተኛ ወጥ ሠርቶ አቅርቦላት ትብላ ብዬ ነበር። ‹‹አይደረግም!›› ብላ እሪ አለች። እኔም ፍንክች አልል አልኩ። ወዲያው አፈላልጌ አንዲት ለሥራ የተፈጠረች የምትመስል ወደ ቤት ይዤ ስገባ ባሻዬ ተቀምጠዋል። ክስ እንደ ቀረበ ወዲያው ገብቶኛል። ለባሻዬ ሁሉንም ነገር አስረድቼ ከአንድ ወር በላይ አትቆይም ብዬ አግባብቼ ሳበቃ የቀጠርኳትን ልጅ ከማንጠግቦሽ ጋር አስተዋወቅኳቸው። ሁሉን ነገር ተነጋግረው እንዳበቁ የደመወዙ ነገር ሲነሳ፣ ሠራተኛዋ ‹‹ማሳሰቢያ አለኝ?›› አለችን። ባሻዬ አሉ ብያችኋለሁ። ማንጠግቦሽ እንዳኮረፈች ናት። ለዘንድሮ ኩርፊያ!

ሠራተኛዋን፣ ‹‹በይ ተናገሪ፤›› ስንላት፣ ‹‹በመጀመሪያ የፊልም አፍቃሪ እንደሆንኩ እንድታውቁልኝ እፈልጋለሁ። ፊልም ማየት ስጀምር ይኼን አምጪ ይኼን ጣይ እንድባል አልፈልግም። ሌላው አንድም የቃና ፊልም እንዲያመልጠኝ አልፈልግም። በአጭሩ እዚህ ቤት የምሠራው የማታካብዱ ከሆነ ብቻ ነው። ሪሞት መደበቅ፣ ፊልም ሲጀምር ዜና እንስማ ብሎ ቻናል መቀየር አይቻልም። በዚህ ከተስማማን ስለምትከፍሉኝ ደመወዝ እንነጋገር…›› ስትል ማንጠግቦሽ በእጇ ያገኘችውን ይዛ ተነሳች። ቤቱ ተደበላለቀ። በገዛ እጄ ሳይቸግረኝ ሚስቴም እንደ ብዙዎች ሚስቶች ወጣ ብሎ መብላት ቢያቅታት፣ ቤቷ ሠራተኛ ሠርቶላት ትብላ ብዬ ሌላ ሁከትና ግርግር አስነስቼ አረፍኩት። ባሻዬ በደከመ አቅማቸው ማንጠግቦሽን እጅ እግሯን ሲይዙልኝ እኔ በመጣሁበት እግሬ ዘመናይ ቅምጥልን ይዤ ውልቅ። ከእሷ ብሶ ያቺ ዘመናይ፣ ‹‹ባለቤትህ ጤነኛ አትመስለኝም…›› አትለኝ መሰላችሁ በፊልም አክተሮች ዘይቤ። ‹‹ምን?›› ብዬ ቱግ ስል፣ ‹‹አቦ አታካብድ ካልሆነ ይቀራል እኮ…›› ብላኝ ትታኝ ሄደች። አጠገባችን ያሉትን ሳናከብር በስክሪን ለምናያቸው ሰዎች ነፍሳችንን ካልሰጠን የሚያሰኘን አባዜ ወስዶ ወስዶ የት እንደሚጥለን እንጃ ብቻ፡፡ እውነትም እንዴት ተቃለናል ዘንድሮ፡፡ ቀላል!

በሉ እንሰነባበት። ማንጠግቦሽ ከዚያን ቀን ወዲህ ይኼው እስከ በቀደም ማታ አኩርፋኝ ረጅም ዓረፍተ ነገር አውርታ አታውቅም ነበር። እኔም ይበለኝ ብዬ ተቀብዬው ነበር። ውዷ ባለቤቴ ማንጠግቦሽ ግን እንዲህ የዋዛ ሰው አትምሰላችሁ። ይኼው ውላ አድራ ሹክክ ብላ ትናንትና ማታ አንገቴ ሥር ገብታ፣ ‹‹እኔ እኮ የምሠራው አልጣፍጥህ ያለ መስሎኝ፣ የሰለቸሁ መስሎኝ፣ ፍቅራችን የቀዘቀዘ መስሎኝ ነው ሠራተኛ እንቅጠር ስትል ያኮረፍኩህ…›› ብላ እንባ እየተናነቃት ስትዳስሰኝ አመሸች። ዛሬ በሰንበቱ እኔና ባሻዬ ማልደን ተነስተን ቤተስኪያን ስመን ስንመለስ ማታ የሆነውን አጫወትኳቸው። ‹‹እግዜር እኮ መርቆ የፈጠረህ ሰው ነህ አንበርብር። በዚህ ጊዜ እንዲህ ያለ ነገር የት አለ?›› አሉኝ። እንዲያ ሲሉኝ ግር አለኝ። ‹‹እንዴት እንዲህ ያለ ነገር ሲሉ?›› አልኳቸው። እሳቸው መልስ አያጡ፡፡ መልስ በኪሱ!

‹‹ሰው እኮ ለእርቅ እንቢ ያለበት ዘመን ነው። በዚህ ሳምንት ብቻ የተጣሉ ስድስት ባልና ሚስቶች ሸምግያለሁ። አንዳቸውም አልታረቁም። ፍቅር እያደር ቀዝቅዛ ቀዝቅዛ በረዶ የምትሠራበት ዘመን ላይ ደረስን ብዬ ይኼው ዛሬ እግዚኦ ስል የነበረው ስለዚሁ ነበር…›› አሉኝና እጄን ይዘው ድምፃቸውን ቀነስ አድርገው ሰው ሰማኝ አልሰማኝ ብለው ሲያበቁ፣ ‹‹የሁሉም ነገር መሠረቱ እኮ ፍቅር ነው አንበርብር። ግን አየህ ሰው አልገባውም። እኛ የገባንም እያስተማርን አይደለም። ‹‹ሰላም ሰላም ይላል ትንሹ ትልቁ፣ ሰላም አይደለም ወይ የሕይወት መረቁ…›› ፍቅር ፈላጊና የሚፋቀር ሲኖር ያን ጊዜ ሳይዘመርለት ሰላም ራሱ በመካከላችን ነው። የሰው ፍቅር ሲኖርህ እኮ ነው የሥራ ፍቅር የሚኖርህ። የቤተሰብ ፍቅር ሳይኖርህ የአገር ፍቅር ከየት ይመጣል? ለራስህ ፍቅር ሳይኖርህ ለምታገለግለው ሕዝብ እንዴት አድርገህ መልካም አስተዳደር፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ማስፈን ትችላለህ? ንገረኝ እንጂ…›› ሲሉኝ እኔ ተለጉሜ አዳምጣለሁ። ‹‹በፍቅር የመጣ በዓይናችን የመጣ የምንልበት ዘመን ቢያደርግልን ልቤ ተመኘ። ኧረ ፍቅር ሙገሳ አንሶታል ጎበዝ። እስኪ የማይረባ ነገር ማራገብ ትተን ሰላምና ፍቅርን የምናራግብበት ጊዜ እናድርገው። ሰላምና ፍቅር ለማግኘት ውስጣችንን ብናቀለው እኮ ይሻለናል..›› ያለኝ ምሁሩ ልጃቸው ነበር፡፡ እኔ ደግሞ ሰላም ከሩቅ ሳይሆን አጠገባችን ነው እላለሁ፡፡ ቅርባችን ያለውን ሰላም ከሩቅ አንፈልግ፡፡ ቀዳሚና ተከታዩን እንወቅ፡፡ መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት