‹‹የዓለማየሁ እሸቴ ዘፈኖች በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወጣቶችም ሆኑ አዛውንቶች ዓውደ ሕይወታቸውን እንዲቃኙ ያደረጉ፣ የማነቃቂያ ምንጭም የሆኑላቸው ናቸው፡፡››
የበኩር ድምፃዊ ዓለማየሁ እሸቴ ዜና ዕረፍትን ተከትሎ ዕውቋ የሥነ ሙዚቃ (ሙዚኮሎጂ) ባለሙያ ትምክሕት ተፈራ (ዶ/ር) በማኅበራዊ ትስስር ገጽዋ የከተበችው ጽሑፍ ነው፡፡
የዓለማየሁ ሙዚቃ ትሩፋቶች ከልጅነትና ታዳጊነት አልፎ እስከ ልሂቅነት በሕይወት መንገድ ለውጥ እንዲመጣ ማድረጋቸውም ይወሳል፡፡ በዓለማየሁ ሙዚቃ ሥራዎች ላይ በርካታ ጥናቶችን አዘጋጅታ በጆርናሎች ያሳተመችው ትምክሕት (ዶ/ር) ለአብነት በማሳያነት ያቀረበቻቸው ዘፈኖቹን እንደሚከተለው ሰድራዋለች፡፡
አዲስ አበባ ቤቴ፣ ጭሮ አዳሪ ነኝ፣ ሕይወቴ አባቴ ነው፣ ማን ይሆን ትልቅ ሰው? መማር መመራመር፣ ተማር ልጄ፣ ትምህርት ቤቴ እና እናት እንጀራ እናት፡፡ እነዚህን ጥቂቶቹን ዘፈኖች በዘመን አይሽሬ ቅኝት አግዝፋዋለች፡፡
ከስድስት አሠርታት በፊት የተጀመረው ሙዚቃዊ ሕይወቱ ዓለማየሁ እስከ 400 የሚደርሱትን ሥራዎቹን ማቅረቡንም አውስታለች፡፡
በተለይ ‹‹ወርቃማ ዘመን›› ተብሎ በሚታወቀው የ1950ዎቹ እና 60ዎቹ ዐረፍተ ዘመን ገንነው ከተነሱት ድምፃውያን ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚሠለፈው ዓለማየሁ ዘፈኖቻቸውን በሸክላ ካሳተሙ የመጀመርያዎቹ ድምፃውያን አንዱ ነበር፡፡ በአምሃ እሸቴ ሪከርዲንግ የተቀረፁት ሁለቱ ሥራዎች ‹‹ትማረኪያለሽ›› እና በሱዳንኛ ያቀነቀነው ‹‹ያታራ›› ናቸው፡፡
የሙዚቃ ባለሙያው ሠርፀ ፍሬስብሐት ‹‹በኢትዮጵያ ሙዚቃ የሪኮርዲንግ ታሪክ ውስጥ የተሳኩና ጥራታቸው ከፍ ያሉ ከ400 በላይ ምርጥ ሥራዎችን ያበረከተው ዓለማየሁ እሸቴ፣ ‹ጌሪ ኮፐር›፣ ‹ኢትዮጵያዊው ኤልቪስ›፣…›› እየተባለ በአድማጮቹ የአድናቆት ቅጽሎች መወደሱን ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ሙዚቃ ዓለም አቀፍ ተወዳጅነትን እንዲያገኝ ያደረገ ድንቅ ድምፃዊ እንደነበር ያስታወሰው ሠርፀ፣ ዓለማየሁ በአለባበሱና በአዘናነጡ፣ ከፀጉር አቆራረጥ ሥልቱ በመነሳትም፡-
‹‹ዓለማየሁ ቴክሱ
ነጭ ነው ፈረሱ
ፊት ለፊት ይታያል
ፒያሳ ሲደርሱ›› የሚባለው ግጥማዊ ብሂልን መቀዳጀቱንም ያሳያል፡፡
በ1933 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ የተወለደው ዓለማየሁ እሸቴ፣ በፖሊስ ሠራዊት ኦርኬስትራ በ1955 ዓ.ም. ተቀጥሮ ለስድስት ዓመታት አገልግሏል፡፡ በእነዚያ ዘመናት ያቀነቀናቸው ዘፈኖች ተቃውሞና ፖለቲካ አዘል እንደነበሩ የትምክሕት ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ ከነዚያ ዘፈኖች መካከል ያበጠው ይፈንዳ፣ ስቀሽ አታስቂኝ፣ ሲያውቁልሽ አታውቂ፣ ወልደሽ ተኪ እናቴ ይጠቀሳሉ፡፡
የፖሊስ ባንድ ባልደረባ የነበሩት የኮሎኔል ግርማ ኃይሌ ድርሰትና ቅንብር የሆነው ‹‹ወልደሽ ተኪ እናቴ›› በዘመኑ የነበረው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት፣ ጭቆና፣ ጉቦ፣ ኢፍትሐዊ አስተዳደርን በሰምና ወርቅ መንገድ የተገለጸውን ነው ዓለማየሁ ያቀነቀነው፡፡
ሃይ ዘራፍ እያሉ እያረረ አንጀቴ
እኔስ አልረባሽም ወልደሽ ተኪ እናቴ
አጋምና ቀጋ ለኔ ተስማምቶኛል
ቅቤማ ከጠጣሁ እንጥል ይወርደኛል
በስቃይ ወልደሽኝ በስቃይ አድጌ
መቼም አልተሻሻልኩ ልኑር ከሰው ግርጌ
ዮሜሳን ለሆዴ መች ይገዛልኛል
እንቆቆ እየተጋትኩ ዶሮ ማታ ይሉኛል
ቅቤውም ይትረፍረፍ ጮማም ይቆረጥ
እማማ እኔና አንቺ ሽሮ እናሯሩጥ፡፡
ዓለማየሁ ከፖሊስ ሠራዊት የኦኬስትራ ከለቀቀ በኋላ ባንዶች በሮሃ፣ ሸበሌ፣ አይቤክስ፣ ሶሊኮስ ባንድና በሙላቱ አስታጥቄ ባንድ በርካታ የሙዚቃ ሥራዎችን ማበርከቱን ገጸ ታሪኩ ያሳያል፡፡
በትውልድ ቅብብሎሽ ገዝፈው ከተገኙት ሥራዎቹ የሆነው ስለ ትምህርት የተጫወተው ‹‹ተማር ልጄ›› ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2015 በጀርመን ሽልማት ያገኘበት የዚህ ዘፈን አንዱ አንጓ የመማርን ልዕልና ያንፀባርቃል፡፡
‹‹ተማር ልጄ ተማር ልጄ
ወገን ዘመድ የለኝ ሀብት የለኝ ከጄ
ስማኝ ልጄ ሌት ፀሓይ ነው
ላልተማረ ሰው ግን ቀኑ ጨለማ ነው››
ራሱ ዓለማየሁ በ1966 ዓ.ም. ደርሶ ሙዚቃዊ ቅንብሩ የግርማ በየነ ሆኖ ከዓለም ግርማ ባንድ ጋር የተጫወተው ‹‹ማን ይሆን ትልቅ ሰው?››ም በግዝፈት ይነሳል፡፡
ያንዱ ቤት ሲጎድል አንዱ እየተረፈው
ክፉና በጎውን ዘመን ሲያሳልፈው
እኔ ግን መራመድ ከቶ አልቻልኩም ገና
ቱሃን ደሜን መጦ ጨርሶታልና
የአሥር ሳንቲም ቆሎ ኩርሽም አደርግና
አንድ ጣሳ ውኃ ጥጥት አደርግና
ተመስገን እላለሁ ኑሮ ይባልና
መኖር በዚህ ዓለም ከፍላጎት ጋር ነው
ልናዘዝ በቁሜ ያጣ እንደሞተ ነው
እየየ ወይኔ የዋኔ ጭፋሮ
እዚያው ፈላ ሞላ ላምናም ለዘንድሮ
ጊዜው ጎዳኝ እንጂ እኔ ሰው ዓላማ
ያህያ ልጅ በቅሎ ወርቅ ተሸልማ
እውነት ስትጠፋ ፍርዱ ሲጓደል
ሕጉ ላለው ሆነ ቂም ለመበቀል
ግን ለፍቶ የሚሠራው ዋጋውን አይጣ
ቢሮ ለስም ደርሶ ይቅር ገባ ወጣ
እጅ እግሩን አጣምሮ ትራስ ተንተርሶ
የበሉት እንጀራ ይወጣል ደም ጎርሶ፡፡
በአፍሪካ አሜሪካውያንም ሆነ በደቡብ አፍሪካ የሚታየውን የነጮች የበላይነትና የጥቁሮች መረገጥን የሚኮንነው ‹‹ጥቁር ግስላ›› ዓለማየሁን ካስከበሩት ሥራዎቹ መካከል ይጠቀሳል፡፡ በፊሊፕስ ሪከርድስ በ1965 ዓ.ም. የተለቀቀውና ከሸበሌ ባንድ ጋር የተጫወተውን ሙዚቃ ዓለማየሁ የጻፈው ሲሆን፣ ሙዚቃውን ያቀናበረው ደግሞ ግርማ በየነ ነው፡፡
ሽጉጥ መትረየሱን አንግቶታል
ያ ጥቁር ግስላ ደም ሸቶታል
ነጭ እባብ መሬቱን እያገላበጠ
ሠርተው እንዳይበሉ ሁሌ እያሯሯጠ
ሆዱን አደምብቶ ለሌሎቹ ተርፎ
ግስሎቹን ሁሉ ጨረሳቸው ነድፎ
ጥቁር እንደ አራዊት የተቆጠረበት
ምን ይሆን ምክንያቱ እንወቅ ምናለበት?
ብሎ በማለቱ በግር ተሰቀለ፡፡
ረዥም ጊዜ በዘለቀበት የልብ ሕመም ምክንያት ነሐሴ 27 ቀን 2013 ዓ.ም. በ80 ዓመቱ ያረፈው ዓለማየሁ እሸቴ፣ ሥርዓተ ቀብሩን ለማስፈጸም የሚመለከታቸው አካላት የተካተቱበት ኮሚቴ መቋቋሙ ተሰምቷል፡፡ ሪፖርተር ለኅትመት እስከገባበት ዓርብ ምሽት ድረስ ቀብሩ መቼ እንደሚፈጸም አልታወቀም፡፡
የሙዚቃው ፈርጥ ዓለማየሁ እሸቴ በአንድ ወቅት የሸገር ጨዋታ እንግዳ በነበረ ጊዜ ያነሳው የድሮውንና የአሁኑን ኪነታዊ ገጽታ ያነፃፀረበት ግዙፍ ሐሳብ እዚህ ላይ ይጠቀሳል፡፡ ‹‹ቀደም ሲል የነበረው ትውልድ፣ በኛ ዘመን የነበረው አድማጭ ነበር፡፡ ምን ተናገረ ምላሱ ምን ትንፍሽ አለ ብሎ ነው የሚከታተለው፡፡ ደራስያኑም በዚያኑ ዘመን እየተጨነቁ ነበር ግጥሞቹን የሚጽፉትና የሚሰጡን እኛም እንደዚያው ስሜታችን ስለሚነካ ተጨንቀን ነበር የምንዘፍነው፡፡ አድማጩ ግጥሙን ስለሚከታተል ደስ ብሎን እንዘፍናለን፡፡ አሁን የማየው እንደዚያ ገንቢ የሆነ የኅብረተሰብ ቁስል የሚነካ ነገር አይመጣም በግጥም፡፡ የመፍራትም ነገር አለ፡፡ በበኩሌ መፍራትን አልወድም በጭራሽ፡፡ በኢትዮጵያ በኛ ደረጃ አርቲስት ተብሎ መባል የሚገባው ሰው ብዙኃኑ ሲራብ፣ የሚራብ፣ ሲደሰት የሚደሰት ጀግንነቱን ታሪኩን በግልጽ የሚናገር እንጂ አንቺን ስለወደድኩኝ ወይም ስለምትረጂኝ ወዳንቺ ጎንበስ የምል ከሆነና የብዙኃኑ ሐቅ የምሸቅጥ ከሆነ ዘፋኝ ተብዬ መባል አይገባኝም፡፡››