የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) በዓለም ዋንጫ የምድብ ሁለት ማጣሪያ ጨዋታ ዚምባቡዌን አሸነፈች፡፡ በሚቀጥለው ዓመት በኳታር ለሚዘጋጀው የዓለም ዋንጫ ጨዋታ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታቸውን እያደረጉ የሚገኙት ዋሊያዎቹ ለድል የበቁት በመጠናቀቂያ ሰዓት ላይ የተገኘውን የፍጹም ቅጣት ምት አስቻለው ታመነ በማስቆጠሩ ነው፡፡ 1ለ0 በሆነ ውጤት የመጀመሪያውን ሦስት ነጥብ በባህር ዳር ስታዲየም ላይ አግኝተዋል፡፡
ከቀናት በፊት የመጀመሪያ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታውን ከጋና ጋር አድርጎ ግብ ጠባቂ በሠራው ስህተት 1ለ0 የተረታው የዋሊያው ስብሰብ፣ በጨዋታ የበላይነት ቢኖረውም ግብ ማስቆጠር ተስኖት ነበር፡፡
በተመሳሳይም ዚምባቡዌን በባህር ዳር ስታዲየም የገጠመው ብሔራዊ ቡድኑ ግብ ማስቆጠር ሲቸገር ተስተውሏል፡፡
ዋሊያዎቹ በምድብ ሰባት ከጋና፣ ከደቡብ አፍሪካና ዚምባቡዌ ጋር ተደልድለዋል፡፡ ምድቡን ደቡብ አፍሪካ በአራት ነጥብ ስትመራ፣ ጋናና ኢትዮጵያ በተመሳሳይ በሦስት ነጥብ ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ ዚምባቡዌ በአንድ ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ናት፡፡ ኢትዮጵያ የምድብ ሦስት ጨዋታዋን ከመስከረም 26 እስከ 29 ባሉ ቀናት ውስጥ ደቡብ አፍሪካን በባህር ዳር ስታዲየም ታስተናግዳለች