Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርሲጨምር እንጂ ሲቀንስ የማይታየው የኑሮ ውድነት አፋጣኝ መፍትሔ ይሻል

ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ የማይታየው የኑሮ ውድነት አፋጣኝ መፍትሔ ይሻል

ቀን:

በሙሉቀን ካሳ

በአገራችን በተከታታይ ዓመታት ከፍተኛ የሆነ የኑሮው ውድነት እየታየ ነው፡፡ የማኅበረሰቡ የዕለት ተዕለት መሠረታዊ ፍላጎት የሆኑት ሸቀጣ ሸቀጦች፣ ቁሳቁሶች፣ የምግብ ነክ ዋጋ ጭማሪዎች የነዋሪውን ህልውና እየተፈታተኑት ነው፡፡ ትናንት የተገዛ ዛሬ ጨምሮ ያድራል፣ ጧት የገዛነው ከሰዓት በኋላ ይጨምራል፡፡ ነዋሪውን እንዲህ ግራ ግብት እስኪለው የሚታየው የዋጋ ንረት ምን ማድረግ እንዳለበት እስኪጠፋ ድረስ ያስጨነቀ ጉዳይ ነው፡፡

ቸርቻሪው ነጋዴ ሲጠየቅ እኔም በውድ ገዝቼ ነው ያመጣሁት፣ የለም ከምል ብዬ ነው ሲል ይደመጣል፡፡ አከፋፋዩ ሲጠየቅ ከላይ ከአምራቹ ነው የጨመረው ይላል፡፡ አምራቹ ደግሞ ሲጠየቅ ጥሬ ዕቃ የለም፣ ጥሬ ዕቃው የሚገባው ከውጭ ነው፣ መንግሥት ደግሞ ዶላር ቶሎ ቶሎ ሊሰጠን አልቻለም፣ በስንት መከራ አግኝተን ያስገባነው ዕቃ እንኳን በውድ ዋጋ ገዝተን ነው ያመጣነው ነው የሚል ሰንሰለታዊ ምክንያት እንጂ መፍትሔ ያስቀመጠ አካል አልተገኘም፡፡

በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ እንኳን የአንዳንድ ዕቃዎች ጭማሪ ብንመለከት ጤፍ በኪሎ ከ35 ብር ወደ 55 ብር በመግባት፣ በኪሎ ከ20 ብር በላይ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ሌሎች ጥራጥሬና መሠረታዊ ምግብ ነክ ነገሮች እንዲሁ በተነፃፃሪ ዕለት በዕለት ሲጨምሩ እንጂ ሲቀንሱ አይታይም፡፡ ባለፍነው አንድና ሁለት ወራት ውስጥ እንኳን የአትክልትና የፍራፍሬ ዋጋ ብናይ ቀይ ሽንኩርት ባለፈው ነሐሴ ወር 15 ብር በኪሎ የነበረው፣ አሁን እጥፍ ጨምሮ ከ30 ብር በላይ ሲገባ፣ ሙዝ በኪሎ ከ20 ብር እስከ 25 ብር ይሸጥ የነበረው ከአሥር ብር በላይ ጭምሪ በማሳየት 35 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡ በተለይ የሁሉም ማኅበረሰብ የዕለት ፍጆታ የሆነው ዘይት ከፍተኛውን የዋጋ ጭማሪ ሲደረግበት ቆይቷል፡፡ በአምስት ሊትር ላይ እንኳን ብናይ ከ200 እስከ 300 ብር ድረስ ጭማሪ በማሳየት ከ600 በላይ ለመሸጥ በቅቷል፡፡ ሌሎቹን መጠናቸው ይበዛም ይነስም መጨመር እንጂ መቀነስ የማይታይባቸው ሆነዋል፡፡

የዕለት ምግብ የሆኑት ዳቦና እንጀራ ዋጋቸው የማይቀመስ ከሆኑ ሰንብተዋል፡፡ ባለፈው ዓመት የኑሮ ውድነት ጋር ተያይዞ የዳቦ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ በመጨመሩ ምክንያት፣ በተለይ ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች ዳቦን በርካሽ ዋጋ እንዲያገኙ ታስቦ የተከፈተው ሸገር ዳቦን ለነዋሪው ከሚቀርብለት የማይቀርብለት ቀን ይበልጣል፡፡ በይመጣል ተስፋ ለመግዛት ከሌሊቱ 11፡30 ሰዓት ጀምሮ አውሬ እያባረረ የሚሠለፈው ዳቦ ፈላጊ ማኅበረሰብ ማየት የችግሩንና የኑሮውን አረንቋ ማሳያ የሚሆን ነው፡፡ በዚያው ልክ ሳይደርሰውና ሳያገኝ አዝኖ የሚመለሰው ዳቦ ፈላጊ ቁጥሩ ቀላል እንዳልሆነ ሄዶ መታዘብ ይቻላል፡፡

በተከታታይ ዓመታት ውስጥ የአገራችን የዋጋ ንረቱና ግሽበት ከአንድ አኃዝ ተሻግሮ ከ20 እስከ 28 በመቶ እንደደረሰ የየወሩ የብሔራዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ ያሳያል፡፡ ይኼ ከፍተኛ ደረጃ የሚባለው የዋጋ ንረት ወይም ግሽበት እንደ አካባቢውና ሁኔታ ከፍታና ዝቅታ ቢታይበትም፣ በተለይ በከተሞችና የግጭት ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ይበልጥ ግዥበቱና የመሠረታዊ ፍጆታዎች የዋጋ ንረት ከፍ ብሎ እንዳለ የስታትስቲክስ መረጃውን ማየት በቂ ነው፡፡

የዋጋ ንረቱን እንዲህ እንዲባበስ ያደረጉት በርካታ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ፡፡ በተለይ በዚህ ሁለትና ሦስት ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ በእርስ በርስ ግጭትና ጦርነት ውስጥ መሆኗ ዋነኛው ነው፡፡ በይበልጥ የዋጋ ንረቱ የሚያያዘው ሰላም ከማጣት ጋር ነው፡፡ በጦርነቱና ግጭቱ ምክንያት በርካታ ገበሬዎች አምርተው መብላትና ያመረቱትን ወደ ገበያ ማቅረብም አልቻሉም፡፡ ግጭቱ ባስ ባለባቸው አካባቢዎች ራሱ ገበሬው ሀብትና ንብረቱ ተዘርፎ፣ አሊያም ወድሞና ጥሪቱን አጥቶ ደርሶ ተረጂ ሆኖ እናየዋለን፡፡

በትግራይ እንኳን የተካሄደውን ጦርነት ብናይ በስምንት ወራት ውስጥ እስከ 100 ቢሊዮን ብር ድረስ ለክልሉ መሠረተ ልማትና ድጎማ እንደወጣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በሰኔ ወር ለፓርላማ ተናግረዋል፡፡ ይህ ገንዘብ ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት ወይም ፕሮጀክቶች ለመጨረስ ውሎ ቢሆን ኖሮ፣ ምን ያህል አሁን ያለውን የዋጋ ንረት ወይም አቅርቦት ሊያሻሽል እንደሚችል መገመት የሚቻል ይመስለኛል፡፡

ሌላው የሚነሳው የኑሮው ውድነትን ካባባሱት ውስጥ የምርት እጥረት መከሰት ነው፡፡ የምርት እጥረትን በሁለት መንገዶች ማየት የሚቻል ይመስለኛል፡፡ አንደኛው የምርትና ምርታማነት ከገበያው ላይ መቀነስ ነው፡፡ ይኼም አምራቹ ኃይል በቂ ምርት ወደ ገበያ አለማስገባት ወይም ገበያው በሚፈልገው ልክ ማቅረብ አለመቻል ነው፡፡ ይህም አቅርቦትና ፍላጎት እንዳይመጣጠን አድርጎታል፡፡ የምርት እጥረቱ ሲኖር ደግሞ የግዥ ፍላጎት እየናረ ስለሚሄድ ለዋጋ መናር ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ የምርት አቅርቦት እጥረት ሲኖርና የጊዜ ፍላጎት ሲንር ነጋዴው ደግሞ ይህንን አጋጣሚ ለመጠቀም የዋጋ ጭማሪ አድርጎ ይሸጣል፡፡

በሁለተኛ ደረጃ እጥረት እንዲከሰት የሚያደርጉት ሰው ሠራሽ ምክንያቶች  ናቸው፡፡ ስግብግብ ነጋዴዎች ከገበያ ውስጥ ምርቱን በመደበቅ ወይም አምራቹ እንዲቀንስ በማድረግ የሚፈጥሩት ነው፡፡ ሰው ሠራሽ የዋጋ ንረት አሁን ትልቅ ፈተና ሆኖ ይታያል፡፡ ዕቃውን ከደበቁት በኋላ በገበያ በከፍተኛ ደረጃ እየተፈለገ እንደሆነ ሲያውቁ ዋጋውን ከፍ አድርገው መጣ ይሉናል፡፡ በዚህ ተግባር ላይ የሚሰማሩት ነጋዴዎችና ደላሎች አቅማቸው ከፍ ያለ በመሆኑ፣ መዋቅራቸው ከአምራቹ እስከ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት ድረስ ኔትወርካቸው የተዘረጋ ነው፡፡ ይኼም አሁን የሚታየው የዋጋ ንረት በከፊል አርቴፊሻል ወይም ሰው ሠራሽ እንዲሆን አድርገውታል፡፡

በዚህም ደሃውን ማኅበረሰብ በልቶ እንዳያድር እያደረጉት ይገኛሉ፡፡ በተለይ የዕለት ጉርሱን ለመሸፈን የሚሯሯጠውንና ደመወዝተኛ የሆነው ማኅበረሰብ የዋጋ ንረቱ ዱብ ዕዳ ከመሆኑም በላይ፣ ህልውናውን ተፈታትኖት ቆይቷል፡፡ እነዚህ ነጋዴዎች የሚፈጥሩት ጫና እንዲህ ጨምሯል ወይም ዕቃዎች ተወደዋል ብለን የምናልፈው ብቻ አይሆንም፡፡

በዋነኛነት መነሻ አድርገው አሻጥር የሚፈጥሩት የፖለቲካ አለመረጋጋቱንና የኢኮኖሚውን መዋዠቅ ዓይተው ስለሆነ፣ የመንግሥትንና የአገርን ህልውና አደጋ ላይ ለመጣል የሚያደርስ ተግባር ጭምር ያላቸው ናቸው፡፡

በሦስተኛ ደረጃ የሚነሳው የዋጋ ጭማሪ የብር የመግዛት አቅም ወይም ምንዛሪው  በተደጋጋሚ መውረድ ነው፡፡ አሁን እንኳን ብንመለከት በባንክ እስከ 44 ብር ድረስ ሲመነዘር፣ በጥቁር ገበያ ደግሞ እስከ 70 ብር ድረስ እየተመነዘረ ይገኛል፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ የብር ምንዛሪ በተለያዩ ጊዜ በተደረገ ቅነሳ ከ54 በመቶ በላይ እንዲወርድ ሆኗል፡፡ አገራችን ደግሞ ደሃ እንደ መሆኗ ልባሽና ምግብ ነክ ሳይቀር ከውጭ የምታስገባ ናት፡፡ ይህም በዓለም ገበያ ያለው የብራችን ምንዛሪ ዝቅ በማለቱ፣ ከውጭ የሚገቡ ዕቃዎች ሁሉ ዋጋቸው በከፍተኛ ደረጃ እንዲንር አድርጎታል፡፡ የገቢና የውጭ ዕቃዎች እስከ 90 በመቶ ድረስ ልዩነት እንዲፈጥር ሆኗል፡፡

ሌላው በአራተኛ ደረጃ የዋጋ ንረቱን ያባባሰው የመንግሥት የላላ ቁጥጥር ነው፡፡ ዛሬ በጥቁር ገበያ ምንዛሪ እንዲህ እንዲንር ያደረገው ደካማ የክትትልና የሕግ ክፍተት መኖር ነው፡፡ በስታዲዮምና በብሔራዊ ባንክ አካባቢ አለፍ ያልን እንደሆነ የ‹‹እንመንዝርላችሁ›› ጥያቄው የሚያሳልፍ አይደለም፡፡ ባንኮችንም የዚሁ የምንዛሪ አሻጥር ውስጥ መገኘታቸው ደግሞ ይበልጥ አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡ በሕጋዊ መንገድ ዶላር ወይም ሌላ የውጭ አገር ምንዛሪ ለማግኘት የሚጠባበቁትን በመተው፣ ከባንኩ ሠራተኞችና ከደላሎች ጋር በመመሳጠር ከገበያ በላይ ለባለሀብቶች የሚሸጡበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

በሌላ በኩል አንድ ነጋዴ ምርት ደብቆ ሲገኝ የሚወሰድበት ዕርምጃ የላላ መሆኑ   ተደጋጋሚ ጥፋቶች ተበራክተው ታይተዋል፡፡ ምርት ደብቆ ወይም ከገበያ በላይ ሲሸጥ  የተገኘ ነጋዴ የሚወሰድበት ዕርምጃ ምናልባት እስካሁን የምንሰማው ተወረሰ የሚል ዜና፣ አለበለዚያም ከዚህ በላይ እንዲሸጥ በሚዲያ የሚወርድ የካቢኔ ትዕዛዝ ይሆናል፡፡ ማንም ነጋዴ እንዲህ በማድረጉ በፍትሕ ተጠይቆ ሲቀርብ ወይም ሲፈረድበት አይሰማም፡፡ ይኼ ደግሞ ሕገወጥነት እንዲስፋፋና እንዲበራከት አጋጣሚ በመፍጠሩ፣ ለዋጋ ንረቱ ትልቅ አስተዋጽኦ ሲያደርግ የቆየ ነው፡፡ እነዚህና ሌሎች ምክንያቶች ተጨምረው የገዥ አቅምና ገበያ አለመጣጠን ሆነዋል፡፡

ይህም ሆነ ይህ በዚህን ያህል ለዋጋ ንረቱ አስተዋጽኦ ያደረጉትን ካነሳን መፍትሔውስ ምንድነው ዋና ጥያቄ ነው፡፡ ይህንን የማኅበረሰቡ የራስ ምታት የሆነው የዋጋ ጭማሪና የኑሮው ውድነት አፋጣኝ መፍትሔዎችን በማስቀመጥ፣ ከዚህ አዙሪት ነዋሪው እንዲወጣ ማገዝ ያስፈልጋል፡፡ ይኼንን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት በተለይ መንግሥት የአጭር የጊዜና የረዥም ጊዜ ተከታታይነት ያላቸውን ሥልቶች መቀየስ ይጠበቅበታል፡፡

በአጭር ጊዜ መፍትሔዎች መንግሥት ጣልቃ በመግባት ምርቶቹን ከአምራቹ ወይም ከውጭ በማስመጣት ወደ ተጠቃሚው በቀጥታ እንዲደርሱ ማድረግ ይገባል፡፡ የአስመጪና የጅምላ አከፋፋይ የዋጋ ንረቱ ዋና ተዋናይ ሰንሰለት መቁረጥ ይገባዋል፡፡ በሸማች ወይም በቸርቻሪዎች በኩል በጣም በአነስተኛው ትርፍ ተመን ለተጠቃሚው ማድረስ፣ አንዱ በዝቅተኛ ዋጋ ለማድረስ ተጠቃሽ መፍትሔ ይሆናል፡፡

በሁለተኛ የግብርና የቀረጥ ቅነሳ ማድረግ ነው፡፡ የማኅበረሱ የዕለት ፍጆታ ውስጥ ዕቃዎችንና ምግብ ነክ ነገሮች ላይ ታክስ ማሻሻያ ያስፈልጋል፡፡ ከውጭ የሚገቡትን ዕቃዎች ሙሉ ለመሉ ከቀረጥ ነፃ ማድረግና የአገር ውስጥ አምራችም እንዲሁ ከቀረጥና ከግብር ቅነሳ ወይም የተለየ ድጋፍ ማድረግ ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ በዚህ ሰሞን መንግሥት ከውጭ የሚገቡት የምግብ ነክ ዕቃዎች ላይ ያደረገው የቀረጥ ቅነሳ፣ በሌሎችም ላይ በማድረግ ዋጋ የማረጋጋቱ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡

በሦስተኛ ደረጃ የዋጋ ንረት እየፈጠሩ ያሉ ነጋዴዎች ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር ማድረግ ይገባል፡፡ የንግድ ሱቆችን ከማሸግ ጀምሮ፣ የንግድ ፈቃድ ከመቀማትና በሕግ እስከመጠየቅ ያለው አሠራር መበረታታት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ በአንዳንድ መሠረታዊ የማኅበረሰቡ ሸቀጣ ሸቀጥና ምግብ ነክ በሆኑት ላይ ዝቅተኛ የመሸጫና የመግዣ ተመን ማበጀት ሌላኛው መፍትሔ ይሆናል፡፡

ስለዚህ መንግሥት የጀመረውን የስግብግብ ነጋዴዎች አሻጥር በመግታት ተጠያቂ ማድረግ ይገባል፡፡ ሰሞኑን በአዲስ አበባ አስተዳደር ካቢኔ ያሳለፋቸው  መፍትሔ ሊጠናከሩ የሚገባቸው ናቸው፡፡ የቤት ኪራይ ጭማሪ ቢያንስ ለሦስት ወራት ያህል ዕገዳ በማድረግ የክረምቱን ጊዜና የተከራዩን ሥጋት ይቀንሳል፡፡ ግን በዋናነት የከተማውን ነዋሪ እያማረረ ያለው ከመሠረታዊ ሸቀጥና ምግብ ነክ በላይ የቤት ዕጦት መሆኑ ይታወቃል፡፡ የአጭር ጊዜ መፍትሔ ቢሆንም፣ የቤት እጥረቱ እስካልተቀረፈ ድረስ ችግሩ ተባብሶ የሚቀጥል በመሆኑ ዘላቂ መፍትሔ ማሰቡ የሚበጅ ነው፡፡ አቅም ያለው ቤቱን የሚሠራበትን ሁኔታ ከሥር ማመቻቸትና፣ አቅም ለሌለው ማኅበረሰብ ቤቶችን ሠርቶ በዝቅተኛ ክፍያ ተደራሽ ማድረግ፣ እንዲሁም በፍጥነት ተሠርተው የሚያልቁ ቤቶችን ሠርቶ መስጠት በደንብ ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

በአራተኛ ደረጃ አምራች ኃይሉን በማበረታታት እንደ ዘይትና ስኳር ያሉ የማኅበረሰቡ አንገብጋቢ ጥያቄዎች የያዙና በምርት ሒደት ላይ ያሉ ድርጅቶችን፣ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል በማድረግ ቶሎ ወደ ምርት እንዲገቡ ማድረግ ነው፡፡ እንደ እነዚህ ያሉ ድርጅቶች ፋይዳቸው ብዙ ነው፡፡ በአንድ በኩል ሥራ አጦችን ሥራ በማስያዝ ሲያግዙ፣ በሌላም በኩል በውጭ ምንዛሪ የሚመጣውን ሸቀጣ ሸቀጥና ዕቃዎች በአገር ውስጥ መሸፈን ስለሚያስችሉ ምንዛሪን በመቀነስ ሚናቸው የላቀ ይሆናል፡፡

አምስተኛ የአካባቢን ሰላም በማስጠበቅ ምርት ካለበት አካባቢ እጥረት ወዳለበት ተደራሽ እንዲሆን ማድረግ፣ ትኩረት ተሰጥቶት መሠራት ያለበት ሌላኛው ጉዳይ ነው፡፡ አንዳንድ አካባቢዎች እንደ ጤፍና የእህል ዘሮች በብዛት ስለሚመረቱ ዋጋቸው ዝቅተኛ ይሆናል፡፡ በሌላ አካባቢ ደግሞ ቅመማ ቅመም ወይም አትክልቶች መሰል እንዲሁ ቅናሽ ሆነው ይታያሉ፡፡ በሰላምና በደኅንነት ሥጋት ምክንያት ሳይጓጓዙና ወደ ገበያ ሳይደርሱ የቀሩትን ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ምርት አቅርቦትን ማሳለጥ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ምርቶች ከፍተኛ እጥረት ወደ ተከሰተበት አካባቢ በተለይ በከተሞች ላይ በማሠራጨት የዋጋ ማረጋጋት ሥራ መሥራት ከፍ ያደርጉታል፡፡

ስድስተኛ የምርት እጥረቱን በዘላቂነት ለመቅረፍ ከዝናብ ጠባቂ አምራችነት መውጣት ዓይነተኛ መፍትሔ ነው፡፡ 85 በመቶ ገበሬ ይዘን በዓመት አንዴ በኋላቀር አስተራረስ እየተመረተ ራሳችንን በምግብ ልንችል አንችልም፡፡ በመሆኑም ቴክኖሎጂ በመጠቀም በዓመት ሁለትና ሦስት ጊዜ አምራችነት የሚደረገው ጥረት ከወሬ ወደ መሬት ቶሎ መወረድ አለበት፡፡ ለዚህ የሚበቃውን የመስኖ መሬትና የውኃ መያዝ ሥራዎች መጠናከር አለባችው፡፡ እንዲሁም እጥረት በሚታይበት በግብርናው ላይ አሁንም ከፍተኛ የሰው ኃይልና ሀብት በማቅረብ ምርታማነት መጨመር፣ ለባለሀብቱም ሆነ ለገበሬው ዘላቂ መፍትሔ ሰጥቶ እንዲበረታታ ማድረግ ይገባል፡፡

ሰባተኛ የዋጋ ግዥበትን ለመቀነስ ማንኛውም አገር የሚጠቀምባቸው ፖሊሲዎችን ማክሮ ኢኮኖሚ (macro Economic policy) መተግበር ነው፡፡ ሰሞኑን የብሔራዊ ባንክ ገዥ ያወጣቸው መመርዎች ትልቅ ሚና አላቸው፡፡ አንደኛው የወሰደው የገንዘብ ፖሊሲ (monetrey policy) ዕርምጃ ሲሆን፣ በገበያ ላይ ያለውን ገንዘብ ለመቆጣጠር ነው፡፡ በዚህም በገበያ የበዛውን ገንዘብ በተለያዩ መንገዶች ከገበያ ውስጥ ለመሰብሰብና ለመቆጣጠር፡፡ ሁሉም ባንኮች በብሔራዊ ባንክ የሚያስቀምጡት የመጠባበቂያ ገንዘብ ከአምስት በመቶ ወደ አሥር በመቶ ከፍ እንዲል ተደርጓል፡፡ ባንኮች የገንዘብ እጥረት ሲገጥማቸው ከብሔራዊ ባንክ የሚወስዱትን ገንዘብ መጠን ወለድም ከ13 በመቶ ወደ 16 በመቶ ከፍ እንዲል አድርጓል፡፡ ከውጭ ምንዛሪና ንግድ ባንኮች የሚያገኙትንም ምንዛሪ ላይ ማሻሻያ በማድረግ ግሽበቱን ለመከላከል በገበያ ላይ የተሠራጨውን ገንዘብ ለመሰብሰብ ዓይነተኛ ሚና አላቸው፡፡

ሁለተኛው መንግሥትን ገቢና ወጪ (fiscal policy) መቆጣጠር ነው፡፡ መንግሥት ገቢና ወጪውን በማመጣጠንና በመቆጣጠር ኢኮኖሚው ላይ ለውጥ በሚያመጣ መንገድ መተግበር ይገባዋል፡፡ ለኪሳራና ለወጪ የሚዳርጉ አሠራሮችን በመተው አፋጣኝ እመርታ በሚሰጡት ላይ ኢንቨስት በማድረግ ግሽበቱን ለመቆጣጠር ጥረት ማድረግ ይገባል፡፡

ሦስተኛው የጉልበት (Wage) ፖሊሲ ይጠቀሳል፡፡ ምርት እንደዚህ በቀነሰበት ጊዜ ሠራተኛውንና ገቢንም አብሮ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት በሚታይበት ወቅት ቀጣሪው አካል ደመወዝ ቢጨምር ገበያውን ከማረጋጋት ይልቅ የባሰ ያንረዋል፡፡ ለዚህም የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እንደሚሉት የሠራተኛ ደመወዝ ከመጨመሩ በፊት፣ ከፍተኛ ምርት ወደ ገበያ ማስገባትና ይኼንን መቆጣጠር ተገቢ ይሆናል፡፡

በአጠቃላይ እነዚህን ፖሊሲዎችን አስተሳስሮ በማስኬድ የኑሮ ውድነቱንና ግሽበቱን ለመግታት ዓይነተኛ ሚና ይኖራቸዋል፡፡ የገንዘብ ፖሊሲ፣ የመንግሥት ወጪና ገቢ ማመጣጠንና የሠራተኛ ገቢ ከምርት ዕድገት ጋር አብረው ተሳስረውና ተደጋገፍው ካልሄዱ ኢኮኖሚውን መቆጣጠር አዳጋች እንደሚሆን ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡

ስምንተኛ የዚህ ጽሑፍ መፍትሔ እየጨመረ የመጣውን የብር ምንዛሪ መቀነስ ማስተካከል ነው፡፡ ብር ከሌሎች ገንዘብ አንፃር የመግዛት አቅሙ በከፍተኛ ደረጃ ወርዷል፡፡ መንግሥት ባለፈው ሁለትና ሦስት ዓመታት የብር ምንዛሪ እስከ 54 በመቶ ድረስ እንዲሽቆለቆል ማድረጉ ስህተት ነው ባይ ነኝ፡፡ በዓለም ገበያ እዚህ ግባ የማይባል ምርት ሳናቀርብ ወደ ውጭ የምንሸጠው ከምናስገባው ጋር ሳይመጣጠን የብር ምንዛሪያችንን መቀነስ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ አመዝኗል፡፡ እንዲህ ዓይነት ፖሊሲ መከተል የሚጠቅማቸው በዓለም ገበያ ላይ ከፍተኛ ሽያጭ (Export) የሚያደርጉ አገሮችን ነው፡፡ ምንዛሪን ቢቻል መቀነስ አለዚያም ባለበት ለመግታት መሞከር ዓይነተኛ መፍትሔ ይኖረዋል፡፡

የምንዛሪውን እጥረት ችግር ለመቅርፍ የአገር ውስጥ አምራችን ማበረታታት፣ አላስፈላጊ ግዥዎችንና የውጭ ምንዛሪን የሚሻሙ ተግባራቶችን መግታት፣ የቴክኖሎጂ ኩረጃዎች መደገፍ፣ የጥቁር ገበያውን መቆጣጠርና መሰል ጥናት የተደገፈ መፍትሔ መውሰድ የተሻለ መፍትሔ ያመጣል፡፡

በመጨረሻም ትልቅ መፍትሔ የሚሰጠው ከምንም በላይ ለአንድ አገር የኢኮኖሚ መረጋጋት ዋናውን ሚና የሚጫወተው ሰላም ነውና ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ጦርነት ቶሎ ማስወጣት ያስፈልጋል፡፡ ሰላም እስካልመጣ ድረስ የአገሪቱ የዋጋ ንረትም ሆነ ግሽበት ማስተካከል የሚቻል አይሆንም፡፡ የዕለት ተዕለት የወጪ መናርና የነዋሪ እሮሮ ይጨምራል፡፡ አሁን በጦርነቱ ምክንያት እየወደመ ያለው ንብረትና ለጦርነቱ እየወጣ ያለው የአገር ሀብት ቀላል እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ ሰላም ደግሞ ለዚህ ሁሉ መፍትሔ ስለሚያመጣና ቅድሚያ የሚሰጠው በመሆኑ፣ በአፋጣኝ ኢትዮጵያን ከደኅንነት ሥጋት ነፃ ማውጣት ትልቅ መፍትሔ ያመጣል እላለሁ፡፡

በአጠቃላይ መንግሥትና ኅብረተሰቡ አብሮ በመሥራት አሁን እንደ አገርና ማኅበረሰብ የገጠመውን የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት ላይ በጋራ በመሥራት ችግሩን መቅረፍ ሁሉም አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይገባል እላለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...