Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርብሔራዊ ባንክ ምነው ዘራፍ ማለት አበዛሳ?

ብሔራዊ ባንክ ምነው ዘራፍ ማለት አበዛሳ?

ቀን:

በጌታቸው አስፋው

አንተስ ቀልደኛ ነህ አትበሉኝና ኢትዮጵያውያን በተለይም በሰሜኑ ክፍል ያለነው ኢትዮጵያውያን ዘራፍ ማለት እንወዳለን፡፡ ስለጦር ሰበቃና ስለጀግንነት ሽለላ ማለቴ አይደለም፡፡ ወንድማማቾች እርስ በራሳችን ልቡ ያበጠበት ገፊና ትዕግሥተኛው ተገፊ ሆነው ምሬት ሲበዛ፣ ጦር የሰበቁበትን የህልውና ሕግ ማስከበር ዘመቻ መከላከያ ሠራዊታችን ሕይወቱን እየሰዋ የአገር መከታ የሆነበትን ጉዳይ ማለቴ አይደለም፡፡ አባቶቻችን በጦር በጎራዴ ዘመናዊ መሣርያ የታጠቁ ፈረንጆችን አሸንፈው የሚሸልሉበትን ማኅበራዊና ሞራላዊ እሴታችን የሆነውን የሽለላና ቀረርቶ ዘራፍ ማለትም አይደለም፡፡

የህልውና ዘመቻው አካል እንጂ ዳር ቆሜ የምቀልድበት አይደለሁም፡፡ የአያቶቼና የአባቶቼ ደምፍላት አልበገር ባይነት በእኔ የደም ሥር ውስጥ ስለሚዘዋወርም፣ ሽለላውንና ቀረርቶውን አሳንሼ አላየውም፡፡ የጻፍኩት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከጥቂት ወራት ጀምሮ ‹‹ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ›› እንዲሉ በጥሬ ገንዘብ ፖሊሲ ችግር ምክንያት የዋጋ ንረት የሚሉት የኢኮኖሚ ሁኔታ ክስተት ሥጋችንን ግጦ በአጥንታችን ካስቀረን በኋላ፣ ዘራፍ ስለሚልበት (በንጉሡ ዘመን ቢሆን ኖሮ የጠቅል አሽከር የሚል ተቀፅላም ይኖርበት ነበር) የመመርያዎች ጋጋታ እንደ ባለሙያ የተሰማኝን ለመተንፈስ ነው፡፡

- Advertisement -

አሻጥረኛ ነጋዴ የለም ባልልም ከአሻጥረኛ ነጋዴው በላይ የብሔራዊ ባንክ ቸልተኝነት፣ ከባለሙያዎች ጋር አለመመካከር፣ ወደ ባንክ ስታስገቡም ስታስወጡም አሳዩኝ፣ ትዕዛዙ አልሠራ እስኪለው ቆይቶ ቆይቶ ወደ ትክክለኞቹ የፖሊሲ መፍትሔዎች እስኪመለስ በዋጋ ንረት ኑሯችን ተናጋ፡፡

ገና የብር ዓይነት ቅያሪው አምና ከተደረገበት ቀን ጀምሮ በርካታ ኢኮኖሚስቶች ስለብር የውጭ ምንዛሪ ተመንና የጥሬ ገንዘብ ፖሊሲው ሙያዊ አስተያየቶች ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡ እኔ ራሴ በሪፖርተር ጋዜጣ በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ ከዋጋ ንረትና ከብር ምንዛሪ ተመን መውደቅ ጋር አያይዤ የንግድ ባንኮች እንቅስቃሴንና የጥሬ ገንዘብ አስተዳደሩን አስመልክቶ፣ አራትና አምስት ጽሑፎችን በጋዜጣ አውጥቻለሁ፡፡ በተለይም መስከረም 16 ቀን 2013 ዓ.ም. በሲራራ ጋዜጣ የንግድ ባንክ አመራሮች ሽቅብ ብሔራዊ ባንኩን እየዘወሩት ነው እንዴ? በማለት በርካታ ጉዳዮች ላይ አስተያየት ሰጥቻለሁ፡፡ ለባለሙያዎች ምክረ ሐሳብ ጆሮ ሳይሰጥና አደባባይ ወጥቶ ሳይሞግት፣ በጓዳ በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ ብሔራዊ ባንኩ በርካታ መመርያዎችን ለንግድ ባንኮች አስተላልፏል፡፡

አንድ ኩንታል ጤፍ ከአምስት ሺሕ ብር በላይ አውጥቷል፣ አንድ ኪሎ ዘለላ በርበሬ አራት መቶ ብር አውጥቷል፣ አንድ ኪሎ ሥጋ በአንዳንድ የካዛንችሱ ጨርጨርን በመሳሰሉ ሥጋ ቤቶች አንድ ሺሕ ብር አውጥቷል፡፡ የዕንቁላሉ፣ የወተቱ፣ የጎመኑ፣ የቃሪያው፣ የሽንኩርቱ፣ የዳቦው፣ ስንቱን ቆጥሬ ስንቱን ልተወው ዋጋዎች ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሦስትና አራት እጥፍ ሆነዋል፡፡ ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ ነው እንግዲህ ብሔራዊ ባንኩ መመርያ በመመርያ እያንበሸበሸን የሚገኘው፡፡ የዋጋ ንረት እንደሆነ አንዴ ከተሰቀለ አይወርድም፡፡ ወደፊት የዋጋ ንረት ቢከሰትም ባይከሰትም የሕዝቡ በተለይም የደመወዝተኛው የመግዛት አቅም እንደሆነ አንዴ ተዳክሟል፡፡ ለመሆኑ መመርያ ፖሊሲ ነው ወይስ አስተዳደራዊ ጉዳይ ብቻ ነው? በእርግጥ ትንሽ ትልቅ ሳይባል ከትዕዛዝ ደብዳቤ አንስቶ መመርያ፣ ደንብ፣ አዋጅ ሁሉም እንደ ፖሊሲ ሊወሰዱ ይችላሉ፡፡ ሆኖም ግን ሁሉም ቢሆኑ ያስፈለጉበት ገፊ ምክንያት ምን እንደሆነ፣ ምን ውጤት እንደሚያመጡ በባለሙያ በሚገባ ከተተነተኑ በኋላ ነው ሕግ ሆነው ተፈጻሚ የሚሆኑት፡፡ አስፈላፈጊ ሲሆንም በፓርላማም ሆነ በሕዝብ ሊመከርበት ይገባል፡፡

የብሔራዊ ባንኩን ዓመታዊ ሪፖርቶች በየጊዜው ስለምከታተል ጽሑፎቼን በሙሉ በመረጃ አስደግፌ ነው የምጽፈው፡፡ በተለይም ስለቁጠባ ወለድ መጣኝና ስለብድር ወለድ መጣኝ አንዱን አክባሪ ሌላውን አደህይ መሆኑን ብዙ ጊዜ ጽፌያለሁ፡፡ የዋጋ ንረት መንስዔ ብሔራዊ ባንኩ የሚያሠራጫቸው ብርና ሳንቲሞች የወረቀት ምንዛሪዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ ንግድ ባንኮች ከአንዱ ሰው የሒሳብ ደብተር ወደ ሌላ ሰው የሒሳብ ደብተር ቁጥሮችን በመጻፍ ብቻ የሚፈጥሯቸው፣ በተለይ በጥሬነት ደረጃ (Liquidity Level) ከምንዛሪዎቹ እኩል የሚቆጠረው ተንቀሳቃሽ ተቀማጭ (Current Account)፣ አኃዛዊ (Digital) ጥሬ ገንዘቦች እንደሆኑም በመረጃ አስደግፌ ብዙ ጊዜ ጽፌያለሁ፡፡ እንደ ቴሌ ብር፣ ኤም ብር፣ ክሬዲት ካርድ፣ ዴቢት ካርድ፣ ወዘተ. የሩቅ ለሩቅ ጥሬ ገንዘቦች (Virtual Money) በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች መገበያየትም የጥሬ ገንዘብ ትርጉምን እንደሚያሰፉም ጽፌያለሁ፡፡

ብሔራዊ ባንኩ በገበያ ውስጥ የጥሬ ገንዘብ መብዛትንና ማነስን የሚቆጣጠርባቸው አራትና አምስት መንገዶች ሲኖሩ፣ ከእነዚህም ውስጥ ከዋነኞቹ በቀዳሚነት የሚጠቀሱት ንግድ ባንኮች ለሚያበድሩት ብድር መጠባበቂያ ተቀማጭ በብሔራዊ ባንክ የሚያስቀምጡት የተቀማጭ መጣኝ (Reserve Ratio)፣ የወለዶች ሁሉ ገዥና የንግድ ባንኮችን ወለድ አተማመን የሚገራው ብሔራዊ ባንኩ ለንግድ ባንኮች የሚያበድርበት የተቀናሽ ወለድ መስኮት (Discount Window)፣ ብሔራዊ ባንኩ ቦንድ በመሸጥና በመግዛት ገበያ ውስጥ የሚዘዋወሩት ብርና ሳንቲሞችን ከገበያ ማስወጣትና ወደ ገበያ ማስገባት የገበያ ተሳትፎ (Opene Market Operations) ይገኙበታል፡፡

ብሔራዊ ባንክ ከሁለት ሳምንት በፊት ባወጣው መመርያ ከነሐሴ 26 ቀን ጀምሮ የገበያ ተሳትፎ እንደሚያደርግ የደነገገ ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት ደግሞ የተቀናሽ ወለድ መስኮት መጣኝን ተመን ከአሥራ ሦስት ወደ አሥራ ስድስት ሲያሳድግ፣ የመጠባበቂያ ተቀማጨ መጣኝን ከአምስት በመቶ ወደ አሥር በመቶ አሳድጓል፡፡ እነዚህ ውሳኔዎች በብዙ አገሮች የሚሠራባቸው የፖሊሲ መሣሪያዎች ሲሆኑ በኅብረተሰቡ ገቢ፣ በምርት አቅርቦት፣ በመዋዕለ ንዋይ፣ በሥራ አጥነትና በመንግሥት እንደ ዋና የገንዘብ ኢኮኖሚ አስተዳደር አቅጣጫ ተደርጎ ስለተደነገገው የገንዘብ ልቅነት (Financial Liberalization)፣ ከንግድ ሥራ ውጣ ውረድ መዋዠቅ ዑደት ጋር፣ ወዘተ. የሚኖራቸውን አንድምታ ባለሙያዎች ይተንትኑበት፣ እኔ ወደ እዚያ አልገባም፡፡

ከፍሕትዊነት አንፃር ግን ቆጣቢው በሃያ ስድስት በመቶ የዋጋ ንረት ሥሌት አሥራ ዘጠኝ በመቶ ከስሮ በባንክ በሰባት በመቶ የወለድ መጣኝ ለንግድ ባንኮች በማበደር የሚያስቀምጠው ቁጠባው በውኃ ሲበላ ዝም ብሎ ማየቱ፣ ለባለ አክሲዮኖች እስከ አርባ በመቶ ትርፍ ስለሚከፍሉት ንግድ ባንኮች የቁጠባና የብድር ወለድ መጣኞች መራራቅ ዝም ማለቱ፣ ቶሎ ከብረው ካፒታላቸውን አምስት ቢሊዮን እስከሚያደርሱ አስቦ እንደሆነ፣ አንዱን ጎድቶ ሌላውን ሲጠቅም፣ ጎጂዎችም ሆኑ ተጎጂዎች እውነቱን ማወቅ መብታቸው እንደሆነ የዘነጋ ይመስለኛል፡፡ የምርት ክፍለ ኢኮኖሚው ያትርፍ ይክሰር ሰምተን ሳናውቅ በመገናኛ ብዙኃን በየ ዕለቱ የምንሰማው ስለንግድ ባንኮች ቢሊዮኖችን ማትረፍ ነው፡፡ በተለይም የገጠር ቆጣቢዎች የእርሻ መሣሪያ መግዣ ጥሪታቸው ሳያውቁት በውኃ ሲወሰድ ዝም ማለት ያማል፡፡

ከላይ እንደገለጽኩት ብሔራዊ ባንኩ ያወጣቸው መመርያዎች በኢኮኖሚው ላይ የሚኖራቸው አንድምታ የምርት ኢኮኖሚውና የገንዘብ ኢኮኖሚው መስተጋበራዊ ሒደቶች በባለሙያ ተመርምረው የሚደረስበት ውጤት ሲሆን፣ እኔ ግን በዓይን ከሚታዩ ምንም ዓይነት ምርምር ከማያስፈልጋቸው ሁኔታዎች ተነስቼ የምለው ነገር አለኝ፡፡

ከላይ እንደገለጽኩት የብሔራዊ ባንኩን ዓመታዊ ሪፖርቶች እከታተላለሁ፡፡ በ2009 ዓ.ም. የያኔው ብሔራዊ ባንክ ገዥ ለሪፖርተር ጋዜጣ የሰጡትን ቃለ ምልልስም አስታውሰዋለሁ፡፡ ለምን የግል ንግድ ባንኮች በብሔራዊ ባንኩ አማካይነት ለልማት ባንክ ከብድራቸው ሃያ ሰባት በመቶውን እንዲሰጡ ይገደዳሉ ብሎ ጋዜጠኛው ለጠየቃቸው ጥያቄ የሰጡት መልስ፣ ንግድ ባንኮች ብሔራዊ ባንኩ ከሚፈልግባቸው መጠባበቂያ ተቀማጭ እጥፍ በብሔራዊ ባንክ ያስቀምጣሉ፡፡ ታዲያ ያለ ወለድ ከሚያስቀምጡ ወለዱ ቢያንስም የብሔራዊ ባንኩን ቦንድ ገዝተው ቢያተርፉ አይሻልም ወይ ነበር ያሉት፡፡

እኔም ያረጋገጥኩት ይህንኑ ነው፡፡ ለረጅም ዓመታት ንግድ ባንኮች በብሔራዊ ባንክ የሚያስቀምጡት ብር መጠን ከሚፈለግባቸው እጥፍ ነው፡፡ በዚህም ላይ እያንዳንዱ ባንክ የብር ችግር እንደሌለበት ባንክ ለባንክ አለመበዳደራቸው አስረጂ ነው፡፡ ለምሳሌ እ.ኤ.አ. የ2019 እና የ2020 መረጃን ብንወስድ ብሔራዊ ባንክ በአምስት በመቶ መጠባበቂያ ተቀማጭ የሚፈልግባቸው ብር መጠን ሃምሳ ሁለት ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ በዚህ ላይ የማይፈለግባቸውን ሃምሳ ሦስት ቢሊዮን ብር ጨምረው ያስቀመጡት መጠን አንድ መቶ አምስት ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ታዲያ የመጠባበቂያ ተቀማጩን ከአምስት በመቶ ወደ አሥር በመቶ ማሳደጉ ፋይዳው ምንድነው? ብሔራዊ ባንኩ ለንግድ ባንኮች የሚያበድርበትን የተቀናሽ መስኮት ወለድ መጣኝ ከ13 ወደ 16 በመቶ ማሳደጉስ ምን ፋይዳ አለው? የንግድ ባንኮችን በብሔራዊ ባንክ መጠባበቂያ ትርፍና ጠቅላላ ተቀማጭ መረጃዎች በሚከተለው ሠንጠረዥ እንመልከት፡፡

የንግድ ባንኮች በብሔራዊ ባንክ ተቀማጭ (በቢሊዮን ብር)

 

2016/17

017/18

018/19

2019/20

በአምስት በመቶ መጣኝ የግዴታ መጠባበቂያ ተቀማጭ

28

36

44

52

የውዴታ ትርፍ ተቀማጭ

26

27

44

53

ጠቅላላ ተቀማጭ

55

63

88

105

 

ተርፏቸው ብሔራዊ ባንክ የሚያስቀምጡ ንግድ ባንኮች ብር አጥሯቸው እርስ በርሳቸው የማይበዳደሩ ንግድ ባንኮች ወትሮውንስ በአሥራ ሦስት በመቶ ይበደሩ ነበርን? አስገድዶ የልማት ባንኩን ቦንድ እንዲገዙ ማድረጉስ ከገንዘብ ልቅነቱ፣ የመንግሥት የገንዘብ አስተዳደር አቅጣጫና ለዓለም ዓቀፍ የገንዘብ ድርጅቶች ከተገባው የገንዘብ ልቅነት ቃል ኪዳን አንፃር እንዴት ይታያል? ብሔራዊ ባንክ ብር በመግዛትና በመሸጥ የገበያ ተሳትፎው ዓላማውን ማሳካት አለማሳካቱም ቦንዱን እንደ የህዳሴ ግድብ ቦንድ ለሕዝብ በመሸጥና ለንግድ ባንኮች በመሸጥ መካከል የሚኖረውን ውጤትና ስኬት ባለሙያዎች ይተነትኑታል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ከዚህም በላይ የጥሬ ገንዘብ ፖሊሲ ከውጭ ምንዛሪ መጣኝ ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ስለሆነም፣ መንግሥት የብር ዋጋ እንዳይወድቅና እንዳይነሳ የውጭ ምንዛሪን በመግዛትና በመሸጥ ከሚያደርገው የውጭ ምንዛሪ አወሳሰን አስተዳደር ዘይቤ (Managed Float Exchange Rate Regime) ጋር እንዴት ይጣጣማል?

በርካታ የውጭ አገርም ሆኑ የአገር ውስጥ ኢኮኖሚስቶች በታዳጊ አገሮች ውስጥ ያለው መዋቅራዊ ችግር እንጂ ጎልቶ የወጣ፣ የንግድ ሥራ ውጣ ውረድ መዋዠቅ ዑደት  (Business Cycle Flactuation) ስለማይታይ የዑደት ተቃራኒ የጥሬ ገንዘብ ፖሊሲ ውጤት አያመጣም ቢሉም፣ ከዚህ በተፃራሪ አመለካከት ደግሞ ታዳጊ አገሮችም የአጭር ጊዜ የማክሮ ኢኮኖሚ ማረጋጋት ሥራ መሥራት እንዳለባቸው በዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ጭምር ይመከራሉ፡፡ ዕውን ታዳጊ አገሮች ያለባቸው የረጅም ጊዜ ልማት ኢኮኖሚ መዋቅር ማስተካከያ ችግር ብቻ ነውን? ወይስ የአጭር ጊዜ የንግድ ሥራ ውጣ ውረድ መዋዠቅ ዑደት ችግርም አለባቸው መዋዠቁ የድግግሞሽ ወጥነት መልክ (Pattern) አለው ወይ? በምን ያህል ጊዜስ ይደጋገማል? መዋዠቁን የሚፈጥሩ ንዝረቶች (Shocks) ምንና ምን ናቸው? የፖሊሲ መፍትሔውስ ምንድነው? ከሌለባቸው ለምን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ውስጥ የማክሮ ኢኮኖሚ ማረጋጊያ ቡድን ተቋቋመ? እስካሁንስ ምን ሠራ? በዋጋ ንረት ስንሰቃይስ የት ነበር? ኢኮኖሚስቶች በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ብርቱ ክርክር የሚያደርጉበት መድረክ መከፈት አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡

ብዙ አገሮች ከኢኮኖሚ ዕድገትም ከሌሎች የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ግቦችም በላይ ለዋጋ ንረት ቅነሳ (Inflation Targeting) ትኩረት በሰጡበት ዘመን የብሔራዊ ባንኩ፣ ‹‹ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ›› እንዲሉ በዋዛ ፈዛዛ ግብታዊ የመመርያ ዕርምጃዎች ብቻ የየአንዳንዳችንን ኑሮ ሁኔታ እያመሰቃቀለ ያለውን የዋጋ ንረት ችግር ይቀርፋል ብዬ አላምንም፡፡ ሕዝቡም ቢጠየቅም ‹‹የአህያ ባል ከጅብ አያስጥልም›› ሆኖብናል ነው የሚለው፡፡ ቢሆንም በዛሬው ጽሑፌ የሰጠሁት አስተያየት መመርያዎቹ በኢኮኖሚው ላይ ስላላቸው እንድምታ ሙያዊ አስተያየት ሳይሆን፣ እንደ ታዛቢ ኑሯችንን ባናጋው ጉዳይ ላይ ኢኮኖሚስቶች ሙያዊ ሙግት እንዲያደርጉ መድረክ እንዲዘጋጅላቸው መልዕክት ለማስተላለፍ ነው፡፡20 208/2019 2019/2020

ከአዘጋጁጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡In Millions of Birr)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...