Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ትዝብት ነው ትርፉ!

ክረምትና የታክሲ ተራ ግፊያ እንዴት ይዟችኋል? ወፈ ሰማይ ተቆጣጣሪዎችና ተራ አስከባሪዎች በሞሉባቸው የታክሲ ማሳፈሪያና ማውረጃ ቦታዎች ታክሲዎች እልም ብለው ሲጠፉ ምን ይባላል? ጧት ወደ ሥራ ለመሄድ ታክሲ መያዣው ሲደረስ፣ የተሠለፈው ሰው ታክሲ ፍለጋ ሳይሆን ሰላማዊ ሠልፍ ለመውጣት የተዘጋጀ አይመስልም? የመንገዱ ዳርቻና መሀል በሰው ተሞልቶ ሲታይ፣ ሕዝቡ የኑሮ ውድነቱን በተመለከተ ለመንግሥት ጥያቄ ለማቅረብ ወደ አደባባይ የሚነጉድ ይመስላል፡፡ በዚህ መሀል አንድ ታክሲ ከመጣ የሚቀጥለው ለበርካታ ደቂቃዎች አይከሰትም፡፡ አሁንማ ተቆጣጣሪዎች ባሉበት ሥፍራ ሳይቀር የታፔላ ሥምሪት የቀረ ይመስላል፡፡ “ቦሌ በአቋራጭ፣ ፒያሳ በአቋራጭ፣ ሜክሲኮ በአቋራጭ…” እየተባለ ሕዝባችን መቀለጃ ሆኗል፡፡ ተቆጣጣሪ የለማ፣ ቢኖርም ሸሪክ ነዋ፡፡ ምሽት ላይ የሚታየው ትዕይንት ደግሞ ለጉድ ነው፡፡ በካፊያ ወይም በኃይለኛ ዝናብ ውስጥ ታክሲ ለመሳፈር የሚደረገው ሙከራ ከጦርነት አይተናነስም፡፡ ዝናብና ግፊያ፣ ጭቃና እርግጫ፣ ጡጫና ዘረፋ የተቀላቀሉበት የታክሲ ጥበቃችንን ነገር ማን አንድ ይበልልን? ለጊዜው ማንም የለም!

ከመገናኛ ወደ አውቶቡስ ተራ አቅጣጫ የጉዞ መስመር የወጣለት ታክሲ ውስጥ ገብተናል፡፡ ወያላው የተለመደውን ጥሪ እያደረገ ነው፡፡ ‹‹የሞላ አንድ ሰው፣ የሞላ አንድ ሰው…›› እያለ ሲጣራ እኛ ግን መታዘባችንን ይዘናል፡፡ ሙሉ ተሳፋሪ ጭኖ ተጨማሪ አምስት ተሳፋሪዎች ለሚፈልግ ታክሲ፣ ‹‹አንድ ሰው የሞላ…›› ሲባል ወይ አንጮህ፣ ወይ አንስቅ፣ ወይ ተው አንል እንታዘባለን፡፡ ዘንድሮ እንኳን የወያላን ድርጊት ቀርቶ የሹማምንትን ነገር እየታዘብን አይደል? ደግሞ ለመታዘብ ማን ብሎን? ‹‹ትዝብት ዱሮ ቀረ…›› አለች አንዲት በወያላው ድርጊት ብግን ያለች ተሳፋሪ፡፡ ‹‹የድሮ ትዝብት ደግሞ ምን የሚሉት ነው?›› አለ ሾፌሩ የበለዙ ጥርሶቹን እያሳያት፡፡ ‹‹የድሮ ትዝብትማ መጥፎ ድርጊት ፈጻሚውን አንገት ያስደፋ ነበር፡፡ ዛሬ ግን እንኳን ትዝብት ሌላ ነገር ቢመጣም የሚገርመው የለም፣ ማፈር ዱሮ ቀረ ተወኝ እባክህ…›› ስትል የሁላችንንም አንገት አስነቀነቀችን፡፡ እውነት ነዋ!

ወያላው እየደጋገመ፣ ‹‹አንድ ሰው የቀረ…›› እያለ ለደቂቃዎች ያህል ካቆየን በኋላ ሚኒባሱ ከአፍ እስከ ገደፉ ሞልቶ ተቆጣጣሪዎች እያዩት፣ ጉዞውን በቀበና አቅጣጫ ወደ አውቶቡስ ተራ ተጀመረ፡፡ የታክሲ ሾፌራችን ለወያላው፣ ‹‹ትዝብት ስለሚባለው ነገር ታውቃለህ?›› አለው፡፡ ወያላው ለወሬ እየተስገበገበ፣ ‹‹ማን ታዘበህ? አንተን ነው ወይስ እኔን ትዝብቱ የሚመለከተው? ወይስ ዛሬ ከመኝታህ ስትነሳ ስለትዝብት ያነሳብህ ሰው ነበር ወይ?›› እያለ ይንጣጣ ጀመር፡፡ ሾፌሩ፣ ‹‹የለም አንድ ሰው እያልክ ስትጣራ ሰው በሙሉ ታዘበህ፡፡ መንግሥትም ዋጋ ተቆጣጠርኩ ብሎ ሽል ሲል አገሩ ታዘበው…›› አለው፡፡ ወያላው ከጣርያ በላይ ሳቀ፡፡ ሳቀ ከማለት እንደ ዶሮ አሽካካ ማለቱ ይቀል ነበር፡፡ ‹‹እኔን አንድ ምስኪን ደሃ ነው ታዘቡ የምትለኝ? ስንት ትዝብት ውስጥ የሚገባ በሞላበት አገር እኔ ብቻ ተገኘሁ? እኔም ከመንግሥት ጋር ተወዳደርኩ?›› እያለ ሳቁን ያስነካው ጀመር፡፡ ይሳቅ እንሂድ!

የወያላው አሳሳቅ ያልተመቻት ያቺ ተሳፋሪ፣ ‹‹እንዴት አንታዘብህ? ሙሉ ተሳፋሪ ጎልተህ ተጨማሪ ለማስገባት አንድ ሰው የቀረ ስትል እንዴት አንታዘብህ?›› አለችው፡፡ ወያላው አሁንም ሳቀ፡፡ አሁንማ ተንፈራፈረ ነው የሚባለው፡፡ ሳቁን ሲጨርስ፣ ‹‹ድንቄም ትዝብት፣ የምትታዘቡት ብታጡ እኔን ትታዘቡ? ስንትና ስንት ለትዝብት የሚበቃ እያለ እኔ የእናንተ ትዝብት ማሟሻ ልሁን? በጣም ያሳዝናል፣ በጣም ያበሳጫል…›› በማለት አኮረፈ፡፡ አኮረፈ ብቻ ሳይሆን ፊቱን ጭጋግ አስመሰለው፡፡ ሾፌሩ ጣልቃ ገብቶ፣ ‹‹አይዞህ አትናደድ፣ አሁን ይኼ ያናድድሃል? ስንትና ስንት የሚያናድድ ነገር እያለ በዚህ ተራ ነገር ትንጨረጨራለህ? እንኳን አንተ ምስኪኑ ሌላውም ደንታ አልሰጠው…›› አለው፡፡

ያቺው ሴት መልሳ፣ ‹‹ቅድም እንደዚያ ሲገለፍጥ እኮ እንዲህ የሚናደድ አይመስልም ነበር፡፡ እኛም በብዙ ነገር ውስጣችን የጨሰው እንደዚህ ነው…›› ብላ ሳቀችበት፡፡ ወያላው ፊቱን ፈታ እያደረገ፣ ‹‹ትገርማላችሁ፣ ሳቅና ብስጭት እንኳን አይገባችሁም፡፡ ቅድም የሳቅኩት ውስጤ በግኖ እኮ ነው…›› አላት፡፡ ሴትየዋ መልሳ፣ ‹‹ምን የሚያበግን ነገር አጋጠመህ እባክህ? የሰው ጨጓራ ስትልጥ እየዋልክ በገንኩ ስትል አታፍርም?›› ብላ አፈጠጠችበት፡፡ ወያላው፣ ‹‹ኑሮ እንደ ጋለ ምድጃ ይፋጃል፣ የሰው ነገር እንደ እሳት ያንገበግባል፣ የአንቺ ምላስ ደግሞ እንደ ሳማ ይለበልባል፣ ሥራው እንደ እሾክ ይዋጋል፣ የመንግሥት ተቆጣጣሪዎች ድርጊት ደግሞ ኡ…ኡ… ያሰኛል…›› እያለ ሒሳቡን መሰብሰብ ጀመረ፡፡ ተጀመረ ማለት ይቀላል!

አጠገቤ የተቀመጡ አዛውንት የሚባለው አልገባቸውም መሰል፣ ‹‹ልጄ ስለምንድነው የሚያወሩት?›› ሲሉ ጠየቁኝ፡፡ እኔም ነገሩ እንዳልገባኝና ነገር ግን ትንሽ ቅኔ ቢጤ እንዳለበት ጠቆም ሳደርጋቸው፣ ‹‹እንዲህ ነው ነገሩ? እንኳን ነገር የሴት ልጅ አካል ግልጥልጥ ተደርጎ በሚታይበት ዘመን የምን ቅኔ ነው? ልጅቷ ትዝብት ድሮ ቀረ ብላ ነገር ቆሰቆሰች፡፡ ወያላው ደግሞ የምን ትዝብት ነው? የምትታዘቡት አጣችሁ ወይ ይላል፡፡ ለመሆኑ ማን ማንን ነው የሚታዘበው? ትዝብቱስ ምንድነው?›› ሲሉ ለሁላችንም ጥያቄ አቀረቡ፡፡ የአዛውንቱ አጠያየቅ ነገር ለመቆስቆስ ወይም ውስጥ ለውስጥ የሚብላላውን ሐሜት አደባባይ ለማውጣት ይመስላል፡፡ እኔ ይኼንን ጠርጥሬያለሁ፡፡ ሌሎች ደግሞ የራሳቸው ጥርጣሬ ይኖራቸዋል፡፡ የታወቀ ነው!

ወያላውና ሾፌሩ የራሳቸውን አጀንዳ አመጡ፡፡ ሾፌሩ መሪውን በቡጢ እየጠለዘ፣ ‹‹የነዳጅ ዋጋ እንዲህ አልቀመስ ባለበት ጊዜ መከራችንን እያየን ሒሳብ እናሟላለን፡፡ ሰው ደግሞ ታዘብናችሁ ምናምን እያለ መከራችንን ያበላናል፡፡ ስንትና ስንት ትዝብት ውስጥ መግባት ያለባቸው ሰዎች እያሉ የታክሲ ሾፌርና ወያላ የማንም ብሶት ማስተንፈሻ፣ የማንም ጥጋብ ማስታገሻ መሆናችን ይቆጨኛል…›› እያለ ይብከነከን ያዘ፡፡ ታክሲዋን በቀበና ሰፊው መንገድ ላይ እንደ ውድድር መኪና እያከነፋት እርር ትክን ብሎ ሲሾፍር ‹‹እግዚኦ!›› ያሰኛል፡፡ አንዲት ተሳፋሪ  ጭንቅ  ጥብብ ብለው፣ ‹‹ሾፌር ቀስ ብለህ ንዳ እንጂ፣ እንዳትጨርሰን…›› አሉ፡፡ ወያላው፣ ‹‹ከዘንድሮ የተንቀረፈፈና አዝጋሚ ኑሮ እንደ አውሮፕላን ብንፈጥን አይሻልም?›› ሲላቸው፣ አጠገቤ የተቀመጡት አዛውንት በንዴት፣ ‹‹አፍህም፣ ጆሮህም ይደፈን…›› ሲሉ ተራገሙ፡፡ ታክሲው ውስጥ የተከፈተው ሬዲዮ ስለትራፊክ አደጋ እያወራ የሾፌሩ እንደዚያ ኃላፊነት የጎደለው አነዳድ ሁላችንንም በጣም እያሳሰበን ነው፡፡ ምን የማያሳስብ ነገር አለ ዘንድሮ!

የሚወርዱትን ለማውረድ የሚሳፈሩትን ደግሞ ለማሳፈር ታክሲው ሲቆም የሁላችንም ትንፋሽ መለስ አለ፡፡ የእኔ ልብማ ቀጥ ልትል ምንም አልቀራትም ነበር፡፡ የታክሲዋ ሾፌር ፍርኃታችን ታወቀው መሰል ፍጥነቱን ከቅድሙ ቀነስ አድርጎ፣ ‹‹ይኼውልህ ወዳጄ…›› አለና እንደገና ወያላውን ያናግረው ጀመር፡፡ ‹‹ይኸውልህ ሰው የሚደፍረው እኔንና አንተን ብቻ ነው፡፡ ታክሲዋ ትንሽ ፈጠን ስትል ይጮኻል፡፡ ዝግ ስትል ፍጠን ይልሃል፡፡ አንድ ነገር ብትናገር ታዘብኩህ እያለ ያላዝናል፡፡ ከዚህ ሁላ ጭቅጭቅ የዘይትና የስኳር ወረፋ መያዝ ይሻላል፡፡ በቃ ምን ማድረግ እንደሚቻል ግራ ግብት ብሎኛል…›› አለው፡፡ ወያላው፣ ‹‹ስለሰው፣ ስለሰው ቀድጄ ልልበሰው የሚለውን ዘፈን ማናት የዘፈነችው? ተወው እባክህ፣ ሰው እንደሆነ መብቱ ትዝ የሚለው እኛ ዘንድ ሲመጣ ነው፡፡ ሌላው አንዴ ወደ ታች አንዴ ወደ ላይ እያደረገ ሲያንገላታው ግን ጭጭ ነው…›› ብሎ ከሬዲዮኑ ሙዚቃ ጋር ማንጎራጎሩን ቀጠለ፡፡ ይሻላል!

አዛውንቱ አሁን የበለጠ ብልጭ ብሎባቸው፣ ‹‹እናንተ ጉዶች ምንድነው የምታወሩት? የምን ማጉረምረም ነው? ምን አድርጉ ነው የምትሉት?›› እያሉ በቁጣ ጠየቁ፡፡ ያቺ ሴት ፈገግ እያለች፣ ‹‹ብሶት ነው የሚያብሰለስላቸው፣ ሒሳቡ አልሞላ ሲላቸውና ሱሱ ሲነሳባቸው እንዲህ ነው የሚያደርጋቸው፡፡ የቅጠላ ቅጠሉ ሰዓት ሲደርስ ፖለቲካ ያምራቸዋል፣ ያነጫንጫቸዋል…›› ስትል፣ አዛውንቱ ሳቅ እያሉ፣ ‹‹ገባኝ የኑሮ ብሶት ሳይሆን የሱስ ብሶት ነው ለካ እንዲህ የሚያደርጋቸው?›› በማለት ወያላውን ገርመም አደረጉት፡፡ ነገረኛው ወያላ እንደ እሳቸው ፈገግ ብሎ፣ ‹‹የእርስዎ ሱስ ምንድነው? ወሬ፣ ጠጅ ወይስ አረቄ?›› አላቸው፡፡ አዛውንቱ አበዱ፡፡ ‹‹አንተ ርካሽ የሰው ልክ የማታው፣! እንዴት ብትደፍረኝ ነው ሱስህ ምንድነው የምትለኝ?›› እያሉ ሊያንቁት ሲንጠራሩ እንደ ምንም ብዬ ያዝኳቸው፡፡ በስንት መከራ አባብዬ አስቀመጥኳቸው፡፡ ወያላው ምንም እንዳልተፈጠረ እየሳቀ፣ ‹‹አላልኳችሁም? የኑሮ ጭንቀት የሰው ጭንቅላት ላይ እየፈላ ያሳብደው ጀምሯል፡፡ ትንሽ ፖለቲካ ሲጨመርበት ደግሞ ወፈፍ ያደርገዋል…›› እያለ ሲያላግጥ ሾፌሩ በዓይኑ ጠቅሶት አስቆመው፡፡ አዛውንቱ ግንባራቸው ላይ ያለው  ሥር ተግተርትሮ ትንፋሻቸው እየቃተተ፣ ‹‹ወራዳ ሁላ! ወራጅ!›› ብለው እየተራገሙ ወረዱ፡፡ ሰው እንዲህ ሲናደድ አይቼ አላውቅም፡፡ አለማየት ይሻላል!

ቢቸግረኝ ያቺን ሴት፣ ‹‹ይኼ ሁሉ አሽሙርና ሽሙጥ የበዛበት ወሬ መነሻው ምንድነው?›› በማለት ጥያቄ አቀረብኩላት፡፡ እሷ ከበፊቱ የበለጠ ድምጿን ጎላ አድርጋ፣ ‹‹መነሻውማ ትዝብት ነበር፡፡ ወያላውን በተመለከተ ትዝብት ድሮ ቀረ ብዬ የጀመርኩት ወሬ ይኼው ጠብ ቀሰቀሰ፡፡ ወያላና ሾፌር ደግሞ ስንትና ስንት ትዝብት ውስጥ መግባት ያለባቸው እያሉ እኛን ብቻ ለምን ትታዘባላችሁ ይላሉ፡፡ አዛውንቱ ተናደው ይኼ ሁሉ ሁካታ ምንድነው ግልጹን ተናገሩ አሉ፡፡ ግልጽ ግልጹን ልንነጋገር ስንል ድንገት አዛውንቱ ለዱላ ተነሱ፣ ይኼው ነው በቃ፡፡ መግባባት ድሮ ቀረ…›› አለችኝ፡፡ እኔም ይኼው በቃ የሚባለው ነገር ስላልተዋጠልኝና ስላልገባኝ ማብራሪያ ለመጠየቅ ፊቴን ወደ ወያላው አዞርኩ፡፡ ወያላው እያዛጋ፣ ‹‹ምነው ጌታው እሑድ ሰንበት ነው ካልተባለ አይገባህም እንዴ?›› ሲለኝ፣ ግራ እየተጋባሁ፣ ‹‹እንዴት?›› በማለት ጥያቄ አቀረብኩለት፡፡ ይኼኔ ሾፌሩ ጣልቃ ገብቶ፣ ‹‹ርዕሳችን ትዝብት ነበር፡፡ ትዝብትን በአንድ አቅጣጫ ሳይሆን በሁሉም አቅጣጫ ብናደርገው ይሻላል፡፡ ስለዚህ አንተ እኛን ስትታዘብ ራስህንም መታዘብ ያስፈልግሃል፡፡ ሱሰኞች ናችሁ ተብለን በትዝብት ተፈረጅን፡፡ እኛ ደግሞ ሌሎችን የእናንተስ ሱስ ምንድነው ብለን ስንጠይቅ ዱላ ይመዘዝብናል፣ አልተግባባንም ማለት ነው…›› አለኝ፡፡ ‹‹ይኼ ሁሉ ቅኔ ለምን አስፈለገ?›› ስል ጠየቅኩት፡፡ ‹‹‘ከገባህ ገባህ ካልገባህ ገደል ግባ’ የሚባል ምሳሌ ታውቃለህ?›› ሲለኝ፣ አገር ምድሩ በትዝብት ድር ተተብትቧል ወይ ብዬ እኔም ‹‹ካልገባኝስ?›› ብዬ ወራጅ አልኩ፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት