- ክቡር ሚኒስትር አዲሱን ዓመት ለመቀበል በአምስቱም የጳጉሜን ወር ቀናት ዝክሮች አዘጋጅተን ለሕዝብ ይፋ ተደርገዋል፣ ሚዲያዎችም እያስተዋወቁ ናቸው።
- እኔም የደወልኩት የክብረ በዓላቱን ዝርዝር ተመልክቼ ነው፡፡
- በአምስቱም ዝክረ ቀናት የተዘጋጁትን ፕሮግራሞች እንዴት አገኟቸው ታዲያ ክቡር ሚኒስትር?
- የምን ዝክር ነው የምታወራው? ጥሩ አገላለጽ አይደለም።
- እሺ፣ ይስተካከላል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- መስተካከል አለበት፣ ዝክር ምናምን ማለቱን ተውና አዲሱን ዓመት ለመቀበል የተዘጋጁ ቀናት ይባሉ፡፡
- ቀናት?
- ታዲያ ምን ይሻላል? በዓላት ይባሉ እንዴ?
- በዓል አላዘጋጀንማ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ታዲያ ምን ይሻላል?
- ክቡር ሚኒስትር ፕሮግራሞቹ ኢትዮጵያዊነትን፣ አገልጋይነትን ለመቀስቀስ በመሆናቸው ዝክረ ቀናት ቢባሉ ይሻላል፣ ኢትዮጵያን መዘከር እንደ ማለት ነው።
- ብቻ ቃሉን አልወደድኩትም፣ ሌላ የሚመጥን ከሌለ ምን ይደረጋል? ግን ጥንቃቄ አድርጉ፡፡
- የምን ጥንቃቄ?
- እንዘክራለን ብላችሁ መድረኩ ሌላ የፖለቲካ አታካራ መቀስቀሻ እንዳይሆን፡፡
- ተሳታፊዎችን በጥንቃቄ ነው የመረጥነው፣ አያስቡ ክቡር ሚኒስትር።
- ሌላም መስተካከል ያለበት ነገር አለ፣ መስተካከል ብቻ ሳይሆን ማብራሪያም እፈልጋለሁ።
- ምንድነው ጉዳዩ? ይንገሩኝ ማብራሪያ እሰጥበታለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አዎ ማብራሪያ ያስፈልገዋል፣ አልያም መሰረዝ አለበት።
- ምኑ?
- የመጨረሻው ቀን ላይ ይከናወናል ያላችሁት ነገር።
- እ… በመጨረሻው ቀን ያሰብነው የድል …
- እንዴት ነው በዚህ ተለዋዋጭ ሁኔታ ውስጥ ድል ይበሰራል የምትሉት? እንዴት ነው እርግጠኛ የሆናችሁት?
- ሥጋትዎ ገብቶኛል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ቢገባህ ነው እንዲህ ዓይነት መንግሥትን አጣብቂኝ ውስጥ የሚከት ዝግጅት የምታሰናዳው?
- በጥንቃቄ ነው እኮ ፕሮግራሙን ያሰናዳነው ክቡር ሚኒስትር።
- እኮ አብራራልኛ? እንዴት ተደርጎ በአንድ ሳምንት ሁሉ ነገር እንደሚያልቅና ድል እንደሚበሰር አብራራልኝ፡፡
- በዕለቱ የሚበሰር ድል የሚኖር ከሆነ ብቻ ነው ድሉ የሚበሰረው።
- ምን ማለት ነው? ድል የሚበሰርበት ቀን ብለህ ድሉ አልደረሰም ብለህ ልታበስር ነው?
- ክቡር ሚኒስትር እንደዚያ አይደለም።
- እና እንዴት ነው?
- ቃሉን በጥንቃቄ ነው የቀረፅነው ያልኩት ለዚህ ነበር።
- ምንድነው በጥንቃቄ ማለት?
- ለዕለቱ ዝግጅት የመረጥነው ቃል ድል የሚል ቃል ይኑረው እንጂ በዕለቱ ድል ይኖራል ማለት አይደለም፣ በጥንቃቄ ነው የሰየምነው ያልኩት ለዚያ ነው።
- ምንድነው ስያሜው? የድል ብሥራት ቀን አይደለም እንዴ የሚለው?
- አይለም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምንድን ነው ያላችሁት ታዲያ?
- የድል ቃል ኪዳን ብሥራት ቀን ነው ያልነው።
- ምን ማለት ነው ደግሞ እሱ?
- ድል ከተገኘ ድሉ ይበሰራል።
- ድል ከሌለ ምን ልታደርጉ ነው?
- ከሌለ ደግሞ ድል ለማድረግ ቃል ኪዳን የምንገባበት ይሆናል።
- ጥሩ ዘዴ ነው የቀየሳችሁት።
- በጥንቃቄ ነው የመረጥነው ያልኩት ለዚህ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ግልጽ ሆኖልኛል አሁን፣ ለማንኛውም ጥንቃቄ ይደረግ።
[የክቡር ሚኒስትሩ የእጅ ስልክ ጠራ፣ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው የተመደቡት አምባሳደር ናቸው የደወሉት]
- እንደምን አሉ አምባሳደር?
- የተጣበበ ሁኔታ ውስጥ ሆነው እኔን ለማነጋገር ስለፈቀዱ አመሰግናለሁ ክቡር ሚኒስትር።
- ምንም አይደል፣ አመሠግናለሁ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ድርድር እንዲመቻች በመጠየቅ ለዓለም መንግሥታት የተሠራጨውን ደብዳቤ በተመለከተ በእናንተ በኩል የተያዘውን አቋም ለመረዳት ነው የደወልኩት።
- በእኛ በኩል ሰላም ነው የምንፈልገው፣ ሌላ አቋም የለንም።
- እኮ ወደዚያ ለመምጣት በእነሱ በኩል ድርድር እንዲካሄድ ነው የጠየቁት፣ በእናንተ በኩል ለድርድር ዝግጁነት አለ?
- እኛ ወደ ውጊያ ከመግባታችን በፊት ጀምሮ ችግሩ በሰላም እንዲፈታ ከመጠየቅ አልፈን ለምነናል።
- እሱን አውቃለው፣ አሁን ዝግጁ መሆናችሁን ነው ለመረዳት የፈለግኩት?
- አሁንም ነገም ዝግጁ ነን በእኛ በኩል፣ ነገር ግን ያልተረዳነው ነገር አለ።
- ምንድነው ያልተረዳችሁት?
- ከማን ጋር እንደምንደራደር፡፡
- እንዴት? በእነሱ በኩል እኮ ጥያቄው ቀርቧል፡፡
- ገባኝ፣ ግን ከማን ጋር እንደምንደራደር ማወቅ እንፈልጋለን፡፡
- አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
- የሚደራደረው የትኛው አካል ነው?
- አመራሩ ነዋ ክቡር ሚኒስትር?
- የተፈረጀው ነው ወይስ ያልተፈረጀው?
- እሱን አልገለጹም።
- ሲገልጹ ብንወያይ አይሻልም?