Tuesday, February 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መጪውን በዓል ታሳቢ በማድረግ የምግብ ዘይት ሥርጭት መጀመሩ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥት መጪውን አዲስ ዓመት ታሳቢ በማድረግ የዘይት አቅርቦት እጥረቱን ይቀንሳል ያለውን የምግብ ዘይት አቅርቦት፣ ከአገር ውስጥና ከውጭ የምግብ ዘይት አምራቾች በመግዛት በመላ አገሪቱ ማሠራጨት መጀመሩ ተገለጸ፡፡

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር / አበባ ታመነ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ መንግሥት የኑሮ ውድነትና የኢኮኖሚ አሻጥርን ለመቀነስ የምግብ ዘይት አቅርቦትና ሥርጭት ለማሳደግ ጥራቱን የጠበቀ 62 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት በማቅረብ በመላው አገሪቱ የማሠራጨት እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡

ወደ አገር ውስጥ የሚገባው ዘይት በቀጥታ ወደ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በተመደበላቸው ኮታ እንዲተላለፍ ቅንጅታዊ ሥራዎች መከናወናቸውን ያስታወቁት ወ/ሮ አበባ፣ ለሥርጭቱ የሚያገለግሉ ተሽከርካሪዎች ተሟልተው መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

የምግብ ዘይቱ ከጳጉሜን 1 ቀን 2013 ዓ.ም. አንስቶ ወደ አገር ውስጥ የምርት ማከማቻ መጋዘኖች እየገባ እንደሚገኝ ያስታወቁት የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊዋ፣ ከግብዓት አቅራቢ ድርጅት መጋዘኖች ወደ ተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ማጓጓዝ ከጳጉሜን 2 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡

ከአጠቃላዩ 62 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ውስጥ 36.5 ሚሊዮን ሊትር ያህሉ ከውጭ አገር እየገባ እንደሚገኝ ተጠቁሞ፣ ቀሪው 25.5 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት በአገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች መሸፈኑ ተገልጿል፡፡

የአገር ውስጥ ዘይት አምራቾች በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ የተለያዩ ድጋፎች እያደረገ እንደሚገኝ ያስታወቀው ሚኒስቴሩ፣ ይህ በመሆኑም 25.5 ሚሊዮን ሊትር የሚሆነውን ፍላጎት ያሟላሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል፡፡ ይህንን የአገር ውስጥ ፍላጎት ለማሟላት እየተንቀሳቀሱ ካሉ የአገር ውስጥ ዘይት አምራቾች ፊቤላ ዘይት ፋብሪካና ሸሙ ተጠቃሾቹ እንደሆኑ ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

ተጓጉዞ ለኅብረተሰቡ የሚዳረሰውን ዘይት የሚመለከታቸው የመንግሥት፣ የልማት ድርጅቶችና የክልል አከፋፋዮች በምን ያህል ዋጋ ማከፋፈል ይገባቸዋል የሚለው የዋጋ ታሪፍ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የማኔጅመንት አባላት ተወስኖ በቀጣዮቹ ቀናት ይፋ እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡

በኢንዱስትሪ ግብዓት አቅራቢ ድርጅትና በሌሎች የምርቱ አከፋፋዮች የገባው የምግብ ዘይት ባለሁለት፣ ሦስትና አምስት ሊትር መጠን ያለው እንደሆነ የገለጹት ወ/ሮ አበባ፣ ከዚህ ውስጥ ባለአምስት ሊትር መጠን ያለው የምግብ ዘይት 50 በመቶውን እንደሚሸፍን አስረድተዋል፡፡

እስካሁን የገባው ዘይት በቀጥታ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ በሸማች ማኅበራት በኩልማክሰኞ ጳጉሜን 2 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ መሠራጨት መጀመሩን፣ ተጠቃሎ ወደ አገር ውስጥ ያልገባው ዘይት ደግሞ በቀጣዮቹ ቀናት ውስጥ በባቡር የሚገባ ስለሆነ የአቅርቦት ችግር አይኖርም ሲል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አስታውቋል፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የራሱ የሆነ ከዋጋ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የሚቆጣጠር ሬጉላቶሪ ዘርፍ እንዳለ ያስታወቁት ወ/ሮ አበባ፣ ከሚገባው በላይ ዋጋ የሚጠይቁ ነጋዴዎች ካሉ ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ዕርምጃ እንደሚወሰድባቸው ተናግረዋል፡፡

የኢኮኖሚ አሻጥሩን ለመቀልበስ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ እንደሚገኙ የገለጹት ወ/ሮ አበባ፣ በፌዴራል ደረጃ ተቋቁሞ በርካታ ንዑሳን ኮሚቴዎች ያቀፈው ግብረ ኃይል አዲስ አበባ ብቻም ሳይሆን፣ በተለያዩ ክልሎች ያለውን ሁኔታ እየተከታተለ የተለያዩ ውጤቶች እያገኘ እንደሆነ አስታውሰዋል፡፡

ጉዳዩ ምርትን በመቀማትና ንግድ ቤቶችን በማሸግ ብቻ የሚፈታ ሳይሆን፣ አስተዳደራዊ ዕርምጃዎችን በሕጋዊ መንገድ መውሰድን ይጠይቃል ያሉት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተሯ፣ በተቋቋመው ግብረ ኃይል አማካይነት ሕገወጦችን የተመለከቱ ውሳኔዎች እንደሚወሰኑ አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች