Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና​​​​​​​‹‹የትግራይ ሕዝብ የእኛ ሕዝብ ነው ብለን በፅኑ እናምናለን›› ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል፣...

​​​​​​​‹‹የትግራይ ሕዝብ የእኛ ሕዝብ ነው ብለን በፅኑ እናምናለን›› ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል፣ የሰላም ሚኒስትር

ቀን:

የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ክልል እየተከናወነ ያለውን ጉዳይ ማወቅ ባይቻልም፣ ‹‹የትግራይ ሕዝብ የእኛ ሕዝብ ነው ብለን እናምናለን›› ሲሉ የሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል አስታወቁ፡፡

ሚኒስትሯ ሰኞ ጳጉሜን 1 ቀን 2013 ዓ.ም. የሰሜኑን የኢትዮጵያ ክፍል ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክተው በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች እየተከናወነ ስላለው የሰብዓዊ ዕርዳታ ድጋፍ አቅርቦት ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በትግራይ ክልል ምንም ዓይነት የፌዴራል መንግሥት መዋቅር ባለመኖሩ ፈቃድ የተሰጣቸው ዕርዳታ የሚያቀርቡ መንግሥታዊ ያልሆኑ አገር በቀልና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ለምን ያህሉ ሕዝብ፣ ምን ያህል ዕርዳታ፣ በምን አግባብ እንዳስተላለፉ ሪፖርት እየጠበቅን ነው ብለዋል፡፡

 የፌዴራል መንግሥቱ የተናጠል ተኩስ ማቆም አድርጎ ከትግራይ ክልል ሲወጣ ለአንድ ወር የሚሆን የዕለት ደራሽ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ አቅርቦቶችን፣ በተመሳሳይ የዕርዳታ ድርጅቶችም ለአንድ ወር የሚሆን ተመሳሳይ አቅርቦቶችን ጥለው መውጣታቸውን ሚንስትሯ አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም ከመንግሥት የተናጠል ተኩስ ማቆም በኋላም እሑድ ነሐሴ 30 ቀን 2013 ዓ.ም. የተንቀሳቀሱ 152 የጭነት ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ 500 ያህል ተሽከርካሪዎች ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ፣ እንዲሁም የዕርዳታ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን ጭነው ወደ ትግራይ ክልል መግባታቸውን ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ በሕወሓት ኃይሎች በተደጋጋሚ በአፋርና በአማራ ክልሎች ላይ ባደረጉት ወረራና በንፁኃን ዜጎች ላይ እያደረሱ ባለው ጥቃት ምክንያት፣ እንዲሁም በዕርዳታ መተላለፊያ መስመሮች ላይ በተደጋጋሚ በሚፈጸሙ ጥቃቶች ተጨማሪ ዕርዳታ የማድረስ ሒደቱን ውስብስብ እንዳደረገው ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የዕለት ደራሽ የዕርዳታ ምግብ ጭነው ወደ ትግራይ ክልል የገቡ ተሽከርካሪዎች መመለስ ሲኖርባቸው፣ 72 በመቶ የሚሆኑት አለመመለሳቸውን ወ/ሮ ሙፈሪያት አስታውቀዋል፡፡

‹‹ተሽከርካሪዎች ለተፈቀደላቸው ሥራ ብቻ መዋላቸውን ማረጋገጥ እንፈልጋለን፤›› ብለዋል፡፡

የፌዴራል መንግሥት ከትግራይ ክልል የተናጠል ተኩስ ማቆም አድርጎ ከወጣ በኋላ የክልሉ ሕዝቡ በመጪዎቹ ዓመታት በተመሳሳይ ችግር ውስጥ እንዳይገባ በማሰብ፣ የግብርና ግብዓት ሲያደርስ መቆየቱን በመጥቀስ የመንግሥት ፍላጎትና ጥረት ሕዝቡ እንዳይጎዳ ነው ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

‹‹በመሆኑም አምርቶ የሚመገብ ማኅበረሰብ መኖር እንዳለበት ስለምናምንና ሥራችን እሱን መሠረት ካላደረገ፣ ችግሩ በዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡

ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊትም በክልሉ ከ1.8 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የምግብ ዋስትና ችግር እንደነበረበት በመጥቀስ፣ ‹‹ከአንበጣ ወረርሽኝ ጋር ተዳምሮ ሕወሓት በራሱ ጊዜ ፈልጎ በከፈተው ጦርነት ለሕዝቡ ያተረፈው ቀውስ እንዳይቀጥል ስለምንፈልግ፣ የተለያዩ ዕርምጃዎችን እየወሰድን ነው፤›› ብለዋል፡፡

የፌዴራል መንግሥት ከክልሉ ሲወጣ በመጋዘኖች ያከማቻቸውን ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችና አሁን እየተላከ ያለውን አቅርቦት በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ፣ አሁን በአንዳንዶች የሚውሳው ረሃብና ሞት የማስከተል ዕድሉ ትንሽ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡

ነገር ግን በትግራይ ክልል ረሃብ ወይም ሞት ተከሰተ ቢባል እንኳ በክልሉ ቴሌቪዥን ጣቢያ ከሰሞኑ እየተሰማ ያለው ሰፊ የሆነ ለጦርነት የሚሆን የስንቅ ዝግጅት፣ ከሚባለው እውነት ጋር የተራራቀ ነው ሲሉ ወ/ሮ ሙፈሪያት አስረድተዋል፡፡

በሕወሓት ወረራ ምክንያት በአማራና በአፋር ክልሎች የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር 500 ሺሕ የደረሰ መሆኑን፣ በአማራ ክልል ለ150 ሺሕ ወገኖች ሰብዓዊ ዕርዳታ ማድረስ  መቻሉን ሚኒስትሯ አክለው ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም በአፋርና በአማራ ክልሎች ሕወሓት በፈጸመው ጥቃት 4.5 ሚሊዮን ዜጎች ለጉዳት መዳረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኩባንያ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ባንኮች ውጤታማነት

የጠቅላላ ጉባኤ፣ የጥቆማና ምርጫ ኮሚቴ፣ የተቆጣጣሪ ቦርድ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...