የኢትዮጵያ ባንኮች በሁሉም ረገድ ዕድገት እያሳዩ ቢመጡም ከፊታቸው ለሚጠብቃቸው ፈታኝ ውድድር መዘጋጀት እንደሚኖርባቸው፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) አሳሰቡ፡፡ አሁን ለደረሱበት ደረጃም የብሔራዊ ባንክ ጥብቅ ክትትል፣ ቁጥጥርና ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡
የብሔራዊ ባንክ ገዥው ይህንን የገለጹት፣ ቅዳሜ ነሐሴ 29 ቀን 2013 ዓ.ም. የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ባለ37 ወለል የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ የምረቃ ሥርዓት ላይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ባንኮች በየዓመቱ ዕድገት ለማሳየታቸው ከሚያደርጉት ጥረት ባሻገር፣ የብሔራዊ ባንክ ያልተቋረጠ ቁጥጥርና ክትትል የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ እንዳለው በመጥቀስ፣ ‹‹ብሔራዊ ባንክ ቁጥጥር ያበዛል›› መባሉ ተገቢ እንዳልሆነም ጠቁመዋል፡፡
ከተለያዩ አቅጣጫዎች ‹‹የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቁጥጥር ያበዛል›› የሚል አስተያየትን እንደሚሰሙ ያመለከቱት ይናገር (ዶ/ር)፣ የብሔራዊ ባንክ ቁጥጥር ይጠቅም ይሆናል እንጂ ጉዳት የለውም ብለዋል፡፡ አክለውም በቁጥጥሩ እንደሚቀጥልበትም ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ባንኮች አሁን ያሉበት የዕድገት ደረጃ ላይ የመድረሳቸውም ሆነ፣ በየዓመቱ ከፍተኛ ትርፍ በማግኘት የመቀጠላቸው ሚስጥር የብሔራዊ ባንክ ቁጥጥርና ክትትል ውጤት እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
‹‹በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ እንደ ሱቅ እየከሰሩ የሚዘጉ ባንኮች አሉ፤›› ያሉት ገዥው፣ ‹‹እንዲህ ያለው ታሪክ ኢትዮጵያ ውስጥ አለመታየቱ የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ያለበትን ደረጃ አመላካች ነው፤›› ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ የግል ባንኮች መሥራት እንዲችሉ ከተፈቀደበት ጊዜ አንስቶ በኪሳራ የተዘጋ ባንክ እንደሌለ፣ ወደፊትም በኪሳራ የሚዘጋ ባንክ እንደማይኖር ያላቸውን ተስፋም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ባንኮች አሁን ባሉበት ደረጃ አትራፊነታቸው የቀጠሉ ቢሆንም፣ አሁንም ራሳቸውን አጠናክረው በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሆነው ለመውጣት ጠንክረው መሥራት እንዳለባቸው ሳያስገነዝቡ አላለፉም፡፡
በተለይ እስካሁን ለውጭ ባንኮች ዝግ ሆኖ የቆየው የፋይናንስ ዘርፍ መከፈቱና የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸው እንደማይቀር ጠቁመው፣ ዘርፉ ለውጭ ባንኮች መቼ ክፍት ይሆናል ከሚለው ጥያቄ በስተቀር መምጣታቸው የማይቀር መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡ በመሆኑም ባንኮች ከፊታቸው ሊጠብቃቸው የሚችለውን ውድድር ታሳቢ በማድረግ መንቀሳቀስ እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል፡፡ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቀጠልም ሆነ ከኢትዮጵያ ውጪ በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ባንኮች ለመሆን ደግሞ፣ ባንኮች የዘመኑን ቴክኖሎጂ መታጠቅ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡
በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት ለመስጠትና መጪውን ውድድር ለመቋቋም የሁሉም ባንኮች የቦርድ አባላትና አመራሮች ለዚህ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ያሳሰቡት ገዥው፣ ‹‹የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ጠንከር ያለ ፉክክርና ውድድር፣ ስላማይቀር፣ ይህንኑ ታሳቢ ያደረገ ሥራ ማከናወን ያስፈልጋል፤›› በማለት ባንኮች ከወዲሁ ይዘጋጁ ዘንድ ይናገር (ዶ/ር) አሳስበዋል፡፡