Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየአሜሪካ ሴኔት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ሰብሳቢ ለተመድ የጻፉትን ደብዳቤ መንግሥት አወገዘ

የአሜሪካ ሴኔት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ሰብሳቢ ለተመድ የጻፉትን ደብዳቤ መንግሥት አወገዘ

ቀን:

የአሜሪካ ሴኔት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሴናተር ቦብ ሜንዴዝ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጦርን በተመለከተ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የላኩትን ደብዳቤ፣ ኢትዮጵያ እንደምታወግዘው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን አስታወቁ፡፡

አቶ ደመቀ ሰኞ ጳጉሜን 1 ቀን 2013 ዓ.ም. የተመድ የሰላም ማስከበር ጉዳዮች ረዳት ጸሐፊ ጃንፒዬር ላክሮይዝን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት፣ የአሜሪካ ሴኔት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ሰብሳቢ ከአንድ ወር በፊት ለተመድ ዋና ጸሐፊ የላኩት ደብዳቤ ኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጦሯን በተለያዩ አገሮች በመላክ ለሰላም ያበረከተችውን አስተዋጽኦ የዘነጋ ነው ሲሉ ገልጸውታል፡፡ ሴናተር ቦብ ሜንዴዝ ከአንድ ወር በፊት ለተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ በላኩት ደብዳቤ፣ በትግራይ ክልል ጦርነት ውስጥ የተሳተፉ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት ከዚህ በኋላ ለሰላም አስከባሪነት እንዳይሰማሩ የሚጠይቅ ነው፡፡

በትግራይ ክልል ጦርነት በርካታ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በወታደሮች መፈጸማቸውን የሚጠቁሙ መረጃዎች የወጡ በመሆናቸው፣ በዚህ ክልል የተሰማራው ጦር በተመድ ሥር ሆኖ በሰላም አስከባሪነት ቢሰማራ ተመሳሳይ ጥሰት በተሰማራበት አካባቢ አለመፈጸሙን እርግጠኛ መሆን እንደማይቻል በላኩት ደብዳቤ ገልጸዋል፡፡

ምንም እንኳ ኢትዮጵያ በሰላም አስከባሪነት በግንባር ቀደምትነት በተመድ ሥር እየተሳተፈች ቢሆንም፣ ከዚህ በኋላ ግን ኢትዮጵያ የምትልከው የሰላም አስከባሪ ኃይል በትግራይ ጦርነት ውስጥ የተሳተፈ መሆን አለመሆኑ ሳይጣራ ተመድ እንዳይቀበል ጠይቀዋል፡፡

በዚህም መሠረት አሁን የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይሎች በሚገኙባቸው አካባቢዎች ላይ የሚደረግ የወታደሮች መተካካት ሒደትም ጥብቅ ምርመራ ተደርጎ፣ በትግራይ ግጭት ውስጥ ላልተሳተፉ ኃይሎች ብቻ እንዲፈቀድ ለተመድ አሳስበዋል፡፡

አቶ ደመቀ መኮንን ይህ የሴናተሩ ደብዳቤ መንግሥታቸውን እንዳሳዘነ ለተመድ የሰላም አስከባሪ ጉዳዮች ረዳት ጸሐፊ እንደገለጹላቸው፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡

የተመድ ረዳት ጸሐፊ ጉዳዩን በተመለከተ ስለተናገሩት የተጠቀሰ ባይኖርም፣ የተመድ የፀጥታ ምክር ቤት በሱዳን የተሰማራው የተመድ የሰላም አስከባሪ ኃይል ቆይታን አስመልክቶ ባለፈው ግንቦት 2013 ዓ.ም. በተወያየበት ወቅት አሜሪካን ጨምሮ የፀጥታ ምክር ቤቱ ሁሉም አባል አገሮች፣ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል ሚናን በማድነቅ የኢትዮጵያ መንግሥትን በይፋ እንዳመሠገኑ የድርጅቱ መረጃ ያመለክታል፡፡

የሱዳን መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን የድንበር ውዝግብ በመጥቀስ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል ከሱዳን ላይ እንዲወጣና በሌላ አገር ጦር እንዲተካ ጠይቆ የነበረ ቢሆንም፣ የፀጥታው ምክር ቤት ግን ጥያቄውን በይደር አቆይቶ የሱዳን አብዬ ሰላም አስከባሪ ኃይል ቆይታ እስከ መጪው ኅዳር ወር 2014 ድረስ እንዲራዘም ወስኗል፡፡

የተመድ የሰላም አስከባሪ ጉዳዮች ረዳት ጸሐፊ ከሰሞኑ በኢትዮጵያ የተገኙት ይህንኑ ሰላም አስከባሪ ኃይል ቆይታ በተመለከተ ለመነጋገር ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ቆይታቸውን አጠናቀውም ወደ ሱዳን አምርተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...