በኢትዮጵያ ተመርቶ ለውጭ የቀረበው የአቮካዶ ምርት የሚቀርብበት ወቅት፣ የሌሎች አቮካዶ አምራቾች ምርታቸው የማይደርስበት በመሆኑ ኢትዮጵያ የተሻለ የኤክስፖርት ገቢ የምታገኝበት መልካም አጋጣሚ መፈጠሩ ተጠቆመ፡፡
በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ የግብርና ኮሜርሻላይዤሽን ክላስተር ዳይሬክተር አቶ ተጫነ አዱኛ ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ ኤጀንሲው ካለፉት ሦስት ዓመታት ጀምሮ በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይና ደቡብ ክልሎች የአቮካዶ ምርት በስፋት እንዲመረትና ለውጭ ገበያ እንዲቀርብ የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በዚህም ምርቱን ወደ ውጭ መላክ እንደተጀመረና በኢትዮጵያ የሚመረተው አቮካዶ በሐምሌ ወር የሚደርስ በመሆኑ፣ አቮካዶን ለውጭ ገበያ በማምረት የሚታወቁት አገሮች በዚህ ወቅት ስለማያቀርቡ፣ ምርቱን ወደ ውጭ በመላክ የተሻለ ገቢ የሚገኝበት መልካም አጋጣሚ እንደተፈጠረ አስታውቀዋል፡፡
ከዚህ በፊት በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ የነበረው አሠራር ምርት እንዲመረት ብቻ ግፊት የሚያደርግ እንደነበር ያስታወሱት ዳይሬክተሩ፣ በዚህም አርሶ አደሩን ከገበያ ጋር የሚያገናኝ አሠራር እስካልመጣ ድረስ ቀጣይነት ያለው ለውጥ ማምጣት እንዳልተቻለ ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ የገበያ ፍላጎትን መሠረት ያደረገ፣ ገበሬው እንዴት ተደግፎ የተሻለ ደረጃ ላይ ይደርሳል የሚል አሠራር ተዘርግቶ ወደ ሥራ መገባቱን አስታውሰዋል፡፡
በተለይ ኤጀንሲው የግብርና ኮሜርሻላይዜሽን ክላስተር በሚል ዘዴ የሚያመርቱትንና በዙሪያቸው ያሉ አካላትን የሚደግፍ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ አርሶ አደርን ብቻ በመደገፍ የሚመጣ ውጤት የለም ያሉት አቶ ተጫነ፣ ከአርሶ አደሩ ጋር ቢዝነስ የሚሠሩና በግብርናው ሰንሰለት ውስጥ ሚና ያለውና ግብዓት አቅራቢው፣ የአርሶ አደሩን ምርት የሚገዛውና ብድር የሚያቀርበው ሳይቀሩ ተደጋግፈውና ተማምነው አብረው መሥራት ስላለባቸው ክላስተሩ የተነደፈው በዚህ መንገድ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በክላስተር አተገባበሩ ወቅት ማንኛውም ምርት ሳይሆን እንዲመረጥ የሚደረገው ውጤታማ ሊያደርጉ የሚችሉ ምርቶች እንደሆኑ ተገልጾ፣ ምርቱም ሲመረጥ መመዘኛ መሥፈርት በማውጣት እንደሆነና ለአብነትም የተመረጠው ምርት ምን ያህል ገቢ የሚያስገኝ ነው? በውጭ አገርስ ተፈላጊ ነው ወይ? ለኢትዮጵያስ የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል ወይ? የአርሶ አደሩን ገቢ ያሻሽላል ወይ የሚሉና ሌሎች መሥፈርቶች ይታያሉ ብለዋል፡፡
በኤጀንሲው ከተመረጡ አሥር ምርቶች አቮካዶ አንዱ እንደሆነ ያስታወሱት አቶ ተጫነ፣ በአቮካዶ ላይ ሚደረገው ድጋፍ በሌሎች የሰብል ምርቶች ላይ እንደሚደረገው ዓይነት ድጋፍ እንዳልሆነ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ቶሎ ገበያ ካላገኙ የሚበላሹ በመሆናቸው፣ ገበያ ማፈላለግ፣ ችግኞች ማቅረብ፣ አርሶ አደሩን የማንቃትና የዝግጅት ሥራ ያካተተ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ከላይ የተጠቀሱት ጉዳዮች ሲታሰቡ በመጀመርያ የተደረገው ተመርቶ ሲጓጓዝም ሆነ ሲከማች የማይበላሸውን ሃስ የተባለውን የአቮካዶ ዝርያ ከእስራኤል በማስመጣት፣ በችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች ችግኞቹ እንዲፈሉ መደረጉን አቶ ተጫነ አስረድተዋል፡፡ ከዘጠኝ በላይ የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎችን በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብና በትግራይ ክልሎች በኤጀንሲው አማካይነት እንደተቋቋሙ እንዲሁ ተገልጿል፡፡
ችግኝ ስለፈላ ብቻ መከፋፈል ስለሌለበት አርሶ አደሩን መሬትን እንዴት መቆፈር አለበትና እንዴት በአግባቡ መትከል አለበት? በሚለው ጉዳይ ላይ ሰፊ ሥልጠናዎች እንደተሰጡ ያስታወሱት ዳይሬክተሩ፣ ገዥዎች ምርቱ በምን ዓይነት ሁኔታ እንደሚመረት በአካል ቀርበው እንዲረዱ የማድረግ ሥራ እንደተሠራ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
አቮካዶን በተመለከተ በኤጀንሲው የተደረገው ድጋፍ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ሲተገበር እንደቆየ የተገለጸ ሲሆን፣ ምርቱ ፍሬ አፍርቶ ለኔዘርላንድ፣ ለእንግሊዝና ለቤልጂየም ገበያዎች እንደቀረበ ተጠቁሟል፡፡
አንድ ገዥ ከእያንዳንዱ አርሶ አደር ሳይሆን እንዲገዛ የሚደረገው፣ ከዚያ ይልቅ የአርሶ አደሮች ምርት ቡድን ወይም ክላስተር የሚባል አደረጃጃት እንደተዋቀረና በዚህም ፈቃደኛ የሆኑ አርሶ አደሮች ወይም መሬታቸው በኩታ ገጠም የተያያዘ ምርቱን አንድ ላይ እንዲያመርቱና ምርቱም ከደረሰ በኋላ እንዲያቀርቡ መደረጉን አቶ ተጫነ ተናግረዋል፡፡ ይህ መሆኑ አርሶ አደሩን በከፍተኛ ሁኔታ የሚጠቅም ስለሆነ ገበያ ለመደራደር አመቺ መሆኑ፣ የገዥውን ፍላጎት የሚስብና ጥራት ያለው ምርት ለማምረት የሚረዳ እንደሆነ አቶ ተጫነ ገልጸዋል፡፡ አልፎ ተርፎም በሜካናይዜሽን ለመደገፍ አመቺ እንደሆነም ተነግሯል፡፡
የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ለአርሶ አደሩ የገበያ ጥናቶችን፣ ገዥዎችን የመለየት፣ ከመንግሥት ፖሊሲ ጋር የተጣጣሙ ሥራዎችን የሚያግዙ ሥራዎችን የሚሠራ እንደሆነ ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል፡፡
በኤምባሲዎች አማካይነት ምርቶቹን እንዲሸጡ የማመቻቸት፣ እንዲሁም ከገዥዎች ጋር በቀጥታ በመነጋጋር የገበያ መዳረሻን የማስፋት ሥራ እንዲሁ በኤጀንሲው እየተሠራ እንደሚገኝ አቶ ተጫነ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ከአንድ ዛፍ እስከ ሁለት ኩንታል የሚደርስ የአቮካዶ ምርት እየተገኘ መሆኑን ተከትሎ የአርሶ አደሩ ምርቱን የማምረት ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ እንደጨመረ የገለጹት አቶ ተጫነ፣ ይህንን ተነሳሽነት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር የገበያ ፍላጎቶችን የማመቻቸት ሥራ ይበልጥ ሊሠራበት ይገባል ብለዋል፡፡