Wednesday, June 12, 2024

ሥጋታቸው ወደ አዲሱ ዓመት የሚሻገረው የ2013 ዓ.ም. የፀጥታ ችግሮች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

Keywords፡- ፣  ፣ ፣ ፣ ፣ ፣ ፣

መስከረም 24 ቀን 2013 ዓ.ም. የወሩ የመጨረሻው ሰኞ አዲስ መንግሥት ይመሠረታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ በተደረገው የመጀመርያው ምርጫ መሠረት የሚመሠረተው ይኼ አዲስ መንግሥት፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደር አዲስ የፓርላማ አባላትን የሚያመጣ ሲሆን፣ ይኼ አዲስ ፓርላማ ግን አዳዲስ ችግሮች ብቻ ሳይሆን የተንከባለሉ ነባር ችግሮችንም የሚጋፈጥ ነው የሚሆነው፡፡

የዓለምና የአገሪቱ ትኩረት በዋናነት በትግራይ ክልል በተፈጠረው ጦርነት ላይ ቢሆንም ቅሉ፣ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ላለፉት ዓመታት ሲከሰቱና ሲንከባለሉ የመጡ ግጭቶች ለአዲሱ የ2014 ዓ.ም. ሥጋትነታቸው አልረገበም፡፡

ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ እንዲራዘም ካደረጉ ግጭቶች መካከል የቤኒሻንጉል ጉምዝ ከማሽና መተከል ዞኖች ግጭቶች፣ የአማራ ክልል የአጣዬና አካባቢው ግጭቶች፣ የኦሮሚያ ክልል የአራቱ ወለጋ ዞኖች ጥቃቶችና ተደጋጋሚ ግጭቶች ተጠቃሽ ሲሆኑ፣ በደቡብ ክልል የኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች የሚታዩ የታጠቁ አካላት ጥቃቶች፣ የቤንች ሸኮ ዞን ጉራፈርዳ ጥቃቶች፣ እንዲሁም የምዕራብ ኦሞ የፀጥታ ችግሮች ወደ 2014 ዓ.ም. በመሻገር ላይ የሚገኙ ሥጋቶች ናቸው፡፡ ከዚህ ባለፈም የሶማሊና ኦሮሚያ፣ እንዲሁም የሶማሊና የአፋር ክልሎች ድንበር አካባቢ ግጭቶች ማባሪያ አላገኙም፡፡

ካሁን ቀደም እነዚህ ግጭቶች እንደ ምርጫና የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ዓይነት አገራዊ ሁነቶች እንዲስተጓጎል ያደረጉ ሲሆን፣ በቀጣይም አገራዊ ተግባራትና የኢኮኖሚ እቅስቃሴዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደራቸው አሌ እንደማይባል የብዙዎች እምነት ነው፡፡

የትጥቅ ግጭቶች ጥቆማና የሁነቶች መረጃ ፕሮጀክት (The Armed Conflict Location & Event Data Project/ACLED) በየወቅቱ በሚያወጣው የግጭቶች የቁጥር መረጃ መሠረት፣ ከመጋቢት እስከ ሚያዚያ 2013 ዓ.ም. ባሉ 30 ቀናት 134 ክስተቶች ተመዝግበው የ556 ሰዎችን ሕይወት ቀጥፈዋል፡፡ የእነዚህ ሞቶች ምክንያት የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች እንደሆኑ የሚጠቁመው መረጃው፣ ከእነዚህ ሟቾች መካከል 172 ከአማራ ክልል፣ 159 ከኦሮሚያ ክልል፣ እንዲሁም 102 ደግሞ ከአፋር ክልል እንደሆኑ መረጃው ይጠቁማል፡፡

በተመሳሳይ ከሚያዚያ 23 ቀን 2013 ዓ.ም. እስከ ግንት 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ 48 ግጭቶች የተመዘገቡ ሲሆን፣ እነዚህ የግጭት ሁነቶች ለ429 ሰዎች ሞት ምክንያት ሆነዋል፡፡ ከግንቦት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ባሉት ቀናት ደግሞ 60 የተደራጁ የፖለቲካ ግጭት ሁነቶችን ፕሮጀክቱ የመዘገበ ሲሆን፣ እነዚህ ግጭቶች ደግሞ የ624 ዜጎችን ሕይወት ቀጥፈዋል፡፡ ከሰኔ 24 ቀን 2013 ዓ.ም. እስከ ሐምሌ 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ባለው ወቅት፣ 100 የተደራጁ የፖለቲካ ግጭቶች ሲታዩ በዚህ ምክንያት ደግሞ 758 ሟቾች ተመዝግበዋል።

እነዚህ የግጭት ሪፖርቶች በትግራይ ክልል ባለው ጦርነት ሳቢያ የታዩ ግጭቶችን ያካተቱ ሲሆን፣ በርካቶቹ ግጭቶችና ጥቃቶች ግን በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የታዩ ነበሩ፡፡

ልክ የዛሬ ዓመት ገደማ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ጉባና ቡለን ወረዳዎችእንዲሁም ዳንጉር ወረዳ በንገዝ ቀበሌ በታጠቁ ቡድኖች ብሔርን መሠረት ባደረጉ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ዜጎች እንደተገደሉና እንደቆሰሉ፣ እንዲሁም ንብረታቸው እንዲወድምባቸው ተደርጓል፡፡ ገሚሶቹም አካባባቢውን ለቀው ለመሰደድ ምክንያት መሆናቸው የሚታወስ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) ይኼንኑ አስመልክቶ፣ መንግሥት የሰዎችን በሕይወት የመኖር መብት ያስከብር ዘንድ ጥሪ ማቅረቡ የሚታወስ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሰበብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በተመሳሳይ በጥቅምት ወር 2013 በኮንሶ ዞን አካባቢ የሚገኘው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አካባቢውን ለቅቆ መውጣቱን ተከትሎ፣ ከኅዳር 1 እስከ ኅዳር 11 ቀን 2013 .. ድረስ በአሌ፣ በኮንሶ ዞን በሰገን ዙሪያ ወረዳ ውስጥ በሚገኙ ቀበሌዎች፣ በአማሮ ወረዳ ቡኒቲ ቀበሌ፣ እንዲሁም ከኅዳር 6 እስከ ኅዳር 8 ቀን 2013 .. በደራሼ ወረዳ ጋቶ ቀበሌ ተከታታይ ግጭቶች ዳግም ተከስተው 66 ሰዎች መገደላቸውን፣ 39 ሰዎች መቁሰላቸውን፣ እንዲሁም 132,142 ሰዎች መፈናቀላቸውን ጠቁሞ፣ ‹‹የችግሩ መሠረታዊ ምክንያት ወይም የሥር መንስዔ ገና ዕልባት ያላገኘና ግጭቱ መልሶ ሊያገረሽ የሚችል በመሆኑ ዘላቂ መፍትሔ የመፈለጉ አስፈላጊነት እንደተጠበቀ ነው፤›› ብሏል፡፡ በተጨማሪም የአስተዳደርና የማንነት ጥያቄዎች መፍትሔ እንደሚሹ፣ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ሆነው ግጭቱን የሚያባብሱ አመራሮች እንደሚገኙም አመላክቷል፡፡

እነዚህ ግጭቶች የሚከሰቱባቸው ጊዜያት እንዲሁ እየተደጋገሙና የንፁኃንን ሕይወት እየቀጠፉ መቀጠላቸው የ2013 ዓ.ም. እውነታ ሆኖ የቆየ ሲሆን፣ በቅርቡም በምሥራቅ ወለጋና በቤኒሻንጉል ጉምዝ የተከሰቱ ግጭቶች እነዚህ ችግሮች ማባሪያ ይኖራቸው ይሆን ወይ? የሚል ጥያቄ እንዲነሳ አድርገዋል፡፡ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በምሥራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ ኪራሙ ወረዳ በአካባቢው ተሰማርተው የነበሩ የፀጥታ ኃይሎች ወደ ሌላ አካባቢ መንቀሳቀሳቸውን ተከትሎ፣ በነጋታው ታጣቂዎች በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ብሔርን መሠረት ያደረገ ጥቃትማድረሳቸው 150 በላይ ነዋሪዎች መገደላቸውን አስታውቆ ነበር።

እነዚህ ችግሮች መንግሥት በተለይም አሸባሪ ብሎ በፈረጃቸው ሕወሓትና የኦነግ ሸኔ ቡድኖች የሚፈጠሩ እንደሆነ ሲናገር ከርሟል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይቀሩ ሕወሓት ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ለቅሶና ሞት እየደገሰ እንደሚገኝ በፓርላማ በአንድ ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹በእያንዳንዱ ሳምንት የጦርነት ድግስ ነበር። የመንግሥት ሥራ እዚህ ማልቀስ መቅበር እዚህ ማልቀስ መቅበርከአንደኛው ለቅሶ ሳይነሳ ወደ ሌላው ለቅሶ መሄድ ነበር፤›› ብለው ነበር፡፡

በተለይ በአጣዬ ከተማና አካባቢው ኦነግ ሸኔ ፈጽሞታል ተብሎ በነበረው ግጭት ሳቢያ በርካቶች ለሞት መዳረጉንና ከቤት ንብረት ማፈናቀሉን፣ እንዲሁም ንብረት ማውደሙን ተከትሎ የፓርላማ አባላት አማራው ላይ የታለመ ጥቃት እየተፈጸመ ሳለ መንግሥት እንዴት ዝም ይላል ሲሉ አምርረው ላቀረቡት ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ትልቁ የኢትዮጵያ ካንሰር፣ ነቀርሳ፣ እንዳናድግ፣ እንዳንለወጥ፣ እንዳንሻሻል እያደረገን ያለው ከሠፈራችን የዘለለ ነገር ማሰብ አለመቻል ነው። በሠፈር ሐሳብ ኢትዮጵያን ማሳነስ እንጂ ማሳደግ አይቻልም። እባካችሁን ቢያንስ የፓርላማ አባላት ከዚህ ውጡ፤›› ሲሉ ግጭቶችንና ሞቶችን ከብሔር ጋር ማያያዝ እንደማያስፈልግ አሳስበው ነበር፡፡

በተደጋጋሚ እነዚህ ግጭቶች የመንግሥትን ትኩረት ከልማት ወደ ግጭት መፍታት ለማዞር ታልመው የሚከናወኑ ናቸው በማለት፣ በተለይ የውጭ አካላትን የሚከሰው መንግሥት፣ ግጭቶቹ የሚቆሙበትን መንገድ ግን ሲገልጽና ይኼንን አድርገን የዜጎችን በሰላምና በሕይወት የመኖር መብት እናስከብራለን ሲል ተደምጦ አያውቅም፡፡ ሕወሓት አንደኛው የግጭቶች መንስዔ እንደሆነ ሲነገር የቆየ ቢሆንም፣ መንግሥት ሕወሓት ለኢትዮጵያ ሰላም ሥጋት መሆኑ አብቅቷል ካለባቸው ጊዜያት ወዲህ እንኳን ግጭቶች መከሰታቸውን ያላቆሙ ሲሆን፣ ይኼም የመንግሥት የችግር ትንተናና ልየታ ላይ ክፍተት እንዳለ የሚያመላክት መሆኑን ይጠቁማል፡፡ ከዚህ ባለፈም በመንግሥት የሚጠሩ የችግር ፈጣሪዎች በስም ከሚጠቀሱ ይልቅ ማንነታቸው ያልታወቁ የሚል መገለጫም ይለጠፍላቸዋል፡፡

በርካታ ችግሮች የፖለቲካ መንስዔ እንዳላቸው በአክሌድ የወጡ ሪፖርቶች በግጭቶቹ ሳቢያም ጣት የሚቀሰርባቸው ተዋናዮች ማንነት የሚያመላክቱ ቢሆንም፣ መንግሥት ግን የሥልጣን ጥም አለው ከሚለው ሕወሓትና ተባባሪው ነው ከሚለው ኦነግ ሸኔ በስተቀር የፖለቲካ ፍላጎት ኖሯቸው እነዚህን ግጭቶች እያስከተሉ ነው የሚባሉ አካላትን በመለየትም ይሁን፣ ዓላማቸውን በመግለጽ ረገድ ያደረገው ጥረት እምብዛም ነው፡፡

ለአብነትም ተመሳሳይ ዓላማ ያላቸው የጋምቤላ ነፃነት ግንባርና የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የሚሰነዘሩ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን የሚመራው የጉምዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ እንዲህ ዓይነት ዓላማ እንዳላቸው የሚነገር ቢሆንም፣ መንግሥት ግን በዚህ መንገድ ሳይሆን የሚገልጻቸው ሽፍታና አሸባሪ አድርጎ ስለሆነ ችግሩን ከዓላማው ጋር ለማጣጣም ያስቸግረዋል የሚሉ አልታጡም፡፡ በቅርቡም በጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ታጣቂ ቡድን አባላት በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ካማሺ ዞን በሎ ጅጋንፎይ ወረዳ 50 በላይ ንፁኃን ዜጎች ለሞት ተዳርገዋል፡፡

ለእነዚህ ግጭቶች መባባስ አንዱ ምክንያትም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እየተስፋፋ የመጣው ሕገወጥ የመሣሪያ ዝውውር ሚና ያለው ሲሆን፣ በነሐሴ ወር ብቻ በጋምቤላ፣ በጎንደር፣ በባህር ዳር፣ በአዲስ አበባ፣ በሐመር ወረዳ፣ በከሚሴ፣ በገንዳ ውኃ ከተማ፣ በካፋ ዞን ጊምቦ ወረዳና በተለያዩ አካባቢዎች ሕገወጥ የመሣሪያ ዝውውሮች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን መንግሥት አስታውቋል፡፡ ይኼ በመንግሥት ይፋ የተደረገ ቁጥር ቢሆንም፣ አገራዊ የሕገወጥ መሣሪያ ዝውውር መመዝገቢያ የመረጃ ቋት ካለመኖሩም በላይ በመንግሥት ሳይያዝ የሚያመልጥ በርካታ መሣሪያ ሊኖር እንደሚችል ያምናል፡፡

እነዚህ ግጭቶችና የፀጥታ ችግሮች ከሁነትነታቸው ባለፈ በቤተሰብ ደረጃም ሆነ በአገር ደረጃ ዘላቂ የሆነ ችግር እንደሚያስከትሉ ዕሙን ሲሆን፣ የኢኮኖሚ መጓተትና መስተጓጎልም አንዱ የዚህ አካል ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በተለያዩ አካባቢዎች ባጋጠሙ የፀጥታ መደፍረስ ችግሮችና የወሰን ማስከበር ማነቆ ሳቢያ፣ ግንባታቸው በተለያየ ደረጃ ላይ ያሉ 61 የመንገድ ፕሮጀክቶች መስተጓጎላቸውን ሚያዚያ 20 ቀን 2013 .. ዋና ዳይሬክተሩ ሀብታሙ ተገኝ (ኢንጂነር) ለፓርላማ ተናግረው ነበር፡፡

የአገሪቱ የፖለቲካ ችግር ሥር የሰደደ እንደሆነ የሚያምኑ የተለያዩ አካላት ለእነዚህ ችግሮች መፍትሔ መስጠት የሚቻለው ብሔራዊ ውይይቶችን በማድረግ እንደሆነ፣ ይኼም ውይይት አካታችና በተቻለ መጠን በርካታ ጉዳዮችን የሚዳስስ እንዲሆን ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡

ይኼንን ወደ ብሔራዊ መግባባት ያደርሳል ተብሎ የታመለትን ብሔራዊ ውይይት መንግሥት የተቀበለው በሚመስል ሁኔታ በአዲሱ ዓመት የብሔራዊ ውይይት እንደሚጀመር፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት የውጭ ቋንቋዎችና የዲጂታል ሚዲያ ኃላፊ ቢልለኔ ሥዩም ከሁለት ሳምንታት በፊት በሰጡት መግለጫ ተናግረው ነበር፡፡

እነዚህ ግጭቶች ቅጥልጥሎሻቸውን ጠብቀው ወደ 2014 ዓ.ም. የሚሸጋገሩ ከሆነ በኢኮኖሚው ላይ፣ በሰዎች ሕይወትና ኑሮ፣ እንዲሁም በምግብ ዋጋ ላይ የሚያስከትሉት ጉዳት እያየለ ሲመጣ የፖለቲካ ቀውስ የሚፈጥር ሊሆን እንደሚችል ዕሙን እንደሆነ በርካቶች የሚስማሙ ሲሆን፣ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ግጭቶቹ ሊረግቡ የሚችሉበትና ወደ ቀጣይ ዓመት ላይሸጋገሩ የሚችበት ምክንያት አነስተኛ እንደነበር አመላካች ሁነቶች በርካታ ናቸው፡፡

በአገሪቱ የሚከሰቱ ግጭቶችና ጥቃቶች አንድ ቀስቃሽ ሰበብ የሚፈልጉና መላ አገሪቱን ሊያናጉ እንደሚችሉ፣ እንደ ድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያና መሰል ሁነቶች ሲከሰቱ ለማቆም አዳጋች የሆኑ ብጥብጦችና አመፆች ማቆሚያ አልባ ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚያመላክቱ አልጠፉም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -