Sunday, June 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሆርቲ ካልቸር ዘርፍ የልማት እንቅስቃሴ በዝዋይ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ በአበባ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ኢንቨስትመንት ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ ከ90 በላይ ኩባንያዎች ውስጥ ከ80 በመቶው በላይ የሚሆኑት የውጭ ኩባንያዎች ናቸው፡፡ በዘርፉ የሚሳተፍ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በአሁኑ ወቅት ቁጥራቸው እየቀነሰ ነው፡፡

ነገር ግን በኢትዮጵያዊያን ተይዘው የነበሩ የአበባ እርሻዎችን የውጭ ኩባንያዎች እየገዙዋቸው የአበባ ልማቱ እየቀጠለ ነው፡፡ ባለፉት አራትና አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ ከተከሰቱ የፀጥታ ችግሮች ጋር ተያይዞ አንዳንድ የአበባ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች፣ የአበባ እርሻቸውን ተመሳሳይ ሥራ ለተሰማሩ ኩባንያዎች በሽያጭ ቢያስተላልፉም የአበባ ምርቱ እየተመረተና ለውጭ ገበያ የቀረበ ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ የኢትዮጵያ ሦስተኛው የውጭ ምንዛሪ የገቢ ምንጭ ለመሆን በቅቷል፡፡

ሥራ ላይ የነበሩ አበባ እርሻዎችን ገዝተው ሥራውን የቀጠሉ ኩባንያዎች የአበባ ምርት መጠናቸውን ለማሳደግ አሁንም እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል በመቂ የሚገኘው ዝቋላ ሆርቲ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርና በዝዋይ በሼር ኩባንያ ሥር የሚገኙ አራት የአበባ እርሻዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ መቂ ከተማ የስትሮበሪ አምራችነቱ የሚታወቀው ኤሌምቶት ኩባንያን በመግዛት እርሻውን በማስፋትና የምርት መጠኑን ለመጨመር እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው ዝቋላ ሆርቲ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሰሞኑን ባዘጋጀው የመስክ ጉብኝት ወቅታዊ እንቅስቃሴውን አስተዋውቋል፡፡ ኩባንያው ኤሌምቶትን ለመግዛት ወጪ ካደረገው ገንዘብ ባሻገር፣ ከ7 ሚሊዮን ዩሮ በላይ (ወደ 400 ሚሊዮን ብር) የሚጠጋ ገንዘብ በመመደብ የማስፋፊያ ሥራ እያከናወነ ስለመሆኑ በጉብኝቱ ወቅት አስታውቋል፡፡

ዝቋላ ሆርቲ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በአሁኑ ወቅት የማያመርታቸውን  ቅንጥብ አበባ ምርቶች ለማሳደግ የሚያስፈልገውን የኮንትራክሽን ግንባታ በማጠናቀቅ ላይ እንዲሆንና ግንባታው ሲጠናቀቅም 1.1 ሔክታር መጠን ያላቸው አምስት የአበባ ማምረቻ ሼዶች ላይ በዓመት ከ40 ሚሊዮን ዘንግ በላይ ማምረት እንደሚያስችል አመልክቷል፡፡

በተለይ ዝቋላ ሆርቲ የተረከበው የእርሻ ቦታ ቀደም ብሎ የሚታወቀው ለወጪ ንግድ የሚቀርቡ ስትሮቨሪ ምርቶችን በማምረት በመሆኑ፣ ይህን ምርት ለማሳደግ ከቀደመው የአመራረት ሥልት በተለየ መንገድ ለማምረት የሚያስችለው ሼድ በመገንባት የምርት መጠኑን ለማሳደግ እየሠራ ነው፡፡ በመጀመርያው ዓመት ዕቅዱ ከ40 እስከ 50 ሚሊዮን የሚሆኑ የአበባ ዘንጎችን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚችል መሆኑ ነው፡፡

በኩባንያው የሥራ ኃላፊዎች ገለጻ መሠረት ከዚህ እርሻ የሚላከው የምርት መጠን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጨምር ተስፋ ተይዟል፡፡ ኩባንያው የሚያመርተውን ምርት ለመጨመር ያካሄደው የማስፋፊያ ሥራ ደግሞ በኩባንያው ሥር እስካሁን በ300 ተወስኖ የቆየውን የሠራተኞች ቁጥር ከ1200 እስከ 1500 የሚያደርስ መሆኑም ታውቋል፡፡

እንዲህ ያሉ የማስፋፊያ ሥራዎች ከአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ከፍ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከዝቋላ ሆርቲ በተጨማሪ ሌሎች ዝዋይ ከተማ የሚገኙ አራት የአበባ አልሚዎቸም በተመሳሳይ የምርት መጠናቸውን ለመጨመር በሚያስችላቸው እንቅስቀሴ ውስጥ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ ከዚህም ሌላ አካባቢን ከሚበክል አሠራር እየተገበሩ መሆኑንም አሳውቀዋል፡፡

ከሼር ኢትዮጵያ ባገኙት የማልሚያ ቦታ የአበባ ልማታቸውን እያከናወኑ የሚገኙት እነዚህ አራት አበባ አልሚዎች ኤኪው ሮዝ፣ ብራም ፍላወር፣ ኸርበርግ ሮዝና ዝዋይ ሮዝ የተባሉ የጀርመንና የሆላንድ ኩባንያዎች ሲሆኑ በየዓመቱ ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡትን የምርት መጠን በማሳደግ ላይ ናቸው፡፡ የአራቱ ኩባንያዎችን በመወከል በዕለቱ በአራቱ የአበባ አምራቾች እንቅስቃሴ ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡት አቶ ኤርሚያስ እንዳመለከቱት፣ ባለፉት አራት ዓመታት 141.7 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ያስገኘ አበባ ለውጭ ገበያ አቅርበዋል፡፡

እንደ አቶ ኤርሚያስ ገለጻ፣ በአራቱ ኩባንያዎች እየተላከ ያለውን የአበባ መጠን ለማሳደግ የኩባንያዎቹ ፍላጎት መሆኑን ገልጸው፣ ለዚህም በተለይ ዝዋይ ሮዝ ምርቱን ለማስፋት በባህር ዳር ተጨማሪ ማልሚያ ቦታ እንደወሰደና  በቀጣይም ምቹ ሁኔታዎች ከተፈጠሩ አሁንም በዓለም አቀፍ ደረጃ ገበያው ስላለ ምርቱን ለማሳደግ ተጨማሪ ማስፋፊያ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡ የዝዋይ ከንቲባ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት በዝዋይ የሚገኙ የአበባ አልሚዎች ለከተማዋ እየሰጡ ያሉ ኢኮኖሚዊ ጠቀሜታዎች ጎልቶ የሚታዩ በመሆናቸው ለማስፋፊያ ሥራቸው የሚፈልጉት መሬት ካለ ጥያቄያቸውን ለማስተናገድ ዝግጁ መሆናቸውን፣ ነገር ግን እስካሁን የቀረበላቸው ጥያቄ እንደሌለ ገልጸዋል፡፡  

በቆቃ በዝቋላ ሆርቲም ሆነ በዝዋይ በአራቱ የአበባ እርሻዎች እንቅስቃሴዎች ዙሪያ በተደረገው የመስክ ጉብኝት ኩባንያዎቹ የአበባ ልማታቸው በአካባቢው ላይ ብክለት እንዳያደርስ ከፍተኛ ጥንቃቄ እያደረጉ መሆኑን ለማስተዋል ተችሏል፡፡ በተለይ ከዚህ አንፃር የዝዋይ የአራቱ የእርሻዎችን እንቅስቃሴ በተመለከተ መረዳት እንደተቻለው፣ አበባ እርሻዎቹ የሚጠቀሙበትን ውኃ ከእርሻው ውጪ እንዳይወጣ ዘመናዊ አሠራር መተግበራቸውን ነው፡፡ ከአካባቢው ኅብረተሰብ ከዚህ ቀደም ሲቀርቡ ከነበሩ አቤቱታዎች ውስጥ ከዝዋይ ሐይቅ የሚወሰዱትን ውኃ ከተጠቀሙ በኋላ ፍሳሹን መልሰው ወደ ሐይቁ ይለቃሉ የሚል እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በሰሞኑ የመስክ ጉብኝት ወቅት ግን ውኃው በምንም ሁኔታ ወደ ሐይቁ የማይፈስ መሆኑንና ከሐይቁ የሚወስዱትን ውኃ እዚያው እንዲዘዋወርና ከእርሻው እንዳይወጣ የሚያደርግ ዘመናዊ አሠራር ተከታትለው እየሠሩ መሆኑን ነው፡፡

አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ምርት በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ከሚጠቀሱት ቡናና የማዕድን ዘርፍ ቀጥሎ በሦስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ሲሆን፣ በ2013 በጀት ዓመት ከዘርፉ 513 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል፡፡ ይህንን በቀጣይ  ዓመት ለማሳደግም ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑ ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች