- ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ዋና መሥሪያ ቤቱን አስመርቋል
- ሠንጋ ተራ የፋይናንስ ተቋማት ዲስትሪክት እንዲሆን መንግሥት ወስኗል
የኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት በተለይም ባንኮች በአዲስ አበባ ሠንጋ ተራ አካባቢ የዋና መሥሪያ ቤታቸውን ሕንፃ በመገንባት ላይ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅትም ግንባታቸውን አጠናቀው ሥራ የጀመሩ ባንኮች ሲኖሩ፣ በቀጣይ ወራትም ተመርቀው ለአገልግሎት የሚበቁ አሉ፡፡
በባንኮቹ እየተገነቡ ያሉ ሕንፃዎች የአዲስ አበባን ገጽታ እየቀየሩም ነው፡፡ የተገነቡትና በመገንባት ላይ ያሉት የባንኮች ሕንፃዎች ከ30 ወለሎች በላይ ያላቸው ናቸው፡፡
ቅዳሜ ነሐሴ 29 ቀን 2013 ዓ.ም. ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በሥፍራው የገነባውን ዋና መሥሪያ ቤት አስመርቋል፡፡ በምርቃቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር)፣ ባንኮች ኢኮኖሚውን ከመደገፍ ባሻገር የሕንፃ ጥበብንም ለኢትዮጵያ በማስተዋወቅ ላይ መሆናቸውንና ንብ ኢንተርናሽናል ባንክም የዚህ አካል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በግንባታ ሒደቱ በርካታ አካላት እየተሳተፉ ቢሆንም፣ ባንኮች ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ የሕንፃ ግንባታ ቴክኖሎጂ የታገዙና ዘመናዊ ሕንፃዎችን በመገንባት ረገድ ግንባር ቀደም ኃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆኑንም ማሳያ እንደሚሆንም አመልክተዋል፡፡
እንደ ዶ/ር ይናገር፣ ሠንጋ ተራ አካባቢ በመንግሥት ደረጃ የፋይናንስ ተቋማት ዲስትሪክት እንዲሆን በመወሰኑ፣ በልዩ ትኩረት የሚታይ ሠፈር ነው፡፡ አካባቢው ባንኮች፣ ኢንሹራንሶችና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ማዕከልና መገኛ እንዲሆን ታስቦ እየተሠራም ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት ዋና መሥሪያ ቤቶቻቸውን እያስገነቡ ያሉ ወይም ለማስገንባት ሐሳብ ያላቸው ባንኮች ግንባታቸውን ሲያጠናቅቁ ደግሞ የከተማዋን ውበት በእጅጉ እንደሚያሳድግ እምነት እንዳላቸው ገልጸው በዕለቱ፣ ‹‹የተመረቀው የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ደስታ ፈጥሮብኛል፤›› ብለዋል፡፡
ባንኮች ግዙፍ ሕንፃዎችን ገንብተው ሲያስመርቁ ማየት ትርጉሙ ከሕንፃ ግንባታ በላይ እንደሆነ የተናገሩት ገዥው የባንኮቹ እንቅስቃሴ አጠቃላይ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ያላቸው አስተዋጽኦ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ የሚያመላክት እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡
ገዥው ባንኮች ከግንባታ ጋር ተያይዞ ካላቸው አስተዋጽኦ ባሻገር ለንብ ባንክና በአጠቃላይ የአገሪቱን የፋይናንስ ኢንዱስትሪ በሚመለከት ማሳሰቢያ የሰጡበትም ነበር፡፡ በተለይ በሚደረጉ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የንግድ ስምምነቶች የውጭ አገር ባንኮች ወደፊት መግባታቸው ስለማይቀር የባንኮችን ተወዳዳሪነት አቅም በማሳደግ ረገድ መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ባንኮችም እርስ በርስ መወዳደርና መፎካከር አለባቸው ብለዋል፡፡
‹‹ንብ ባንክ አሁን ያለው የባለአክሲዮኖች ድርሻ በጣም ከፍተኛ ስለሆነ፣ ውድድሮችን በብቃት ለመወጣት በሚቀጥሉት ሦስትና አራት ዓመታት በኢትዮጵያ ካሉት ግንባር ቀደም ባንኮች ከአንድ እስከ አራት እንዲሆን የባንኩ አመራሮች የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት አለባቸው፤›› ሲሉ መክረዋል፡፡
‹‹አሁን በያዛችሁት አያያዝ ሲታይም ይህንን እንደምትወጡ እምነቴ የፀና ነው፡፡ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ አመራሮች የተቀናጀና የተናበበ የማኔጅመንትና የሠራተኛ ትብብር ስላላችሁና ታታሪነትንም መለያ አድርጋችሁ ስለያዛችሁ የመጀመርያ ረድፍ ላይ ለመቀመጥ ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ ይጠበቅባችኋል፤›› ሲሉ ለባንኩ አመራሮች ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የገዥው መልዕክት የሕንፃ ግንባታ ላይ ብቻ የተወሰነ አልነበረም፡፡ በአብዛኛው መልዕክታቸው ‹‹ሁሉም ባንኮች ነገን አስቡ›› የሚል እና በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ማሳሰቢያ የሰጡበትም ነበር፡፡ ከዚህ ውስጥ ባንኮች የያዙትን ሀብት የተመለከተው ይገኝበታል፡፡
ባንኮች የያዙት ሀብት የሕዝብ በመሆኑ ይህንን ሀብት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በአግባቡ ቁጥጥር እንደሚያደርግበትና በዚህ ረገድ ባንኮች ችግር ቢገኝባቸው ጠንከር ያለ ቅጣት እንደሚጣልባቸው ገልጸዋል፡፡
‹‹በውድድርም ይሁን በሌላ ሁኔታ ባንኮች ውስጥ ያለው የዜጎች ሀብት ነውና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዜጎችን ሀብት በየባንኩ የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ የትኛውም ባንክ ላይ አንዳች ጉዳት እንዲደርስበት አንፈልግም፡፡ እንዳይደርስም የመከላከል ሥራ እንሠራለን፤›› በማለት አስረግጠው ተናግረዋል፡፡
ገለጻቸውን ሲያብራሩም፣ ባንኮች በአሁኑ ወቅት ካላቸው ጠቅላላ ሀብት ውስጥ የባለአክሲዮኖች ድርሻ ከባንኮች አጠቃላይ ሀብት ሲነፃፀር ከአሥር በመቶ የማይበልጥ በመሆኑ አብዛኛ የሆነውን የዜጎች ሀብት ለማስጠበቅ ብሔራዊ ባንክ ይሠራል ብለዋል፡፡
በአጠቃላይ በባንኮች ውስጥ አንዳንድ ሕገወጥ አሠራሮች ካሉ ከዚህ መራቅ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ አያዘውም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያዎች በጣም ጥብቅና ሕጎችን የጣሰ ባንክ ላይ ያለማቅማማት ዕርምጃ የሚወስድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ‹‹ቁጥጥር ያበዛል›› በሚል የሚሰጠውን አስተያየት በተመለከተም፣ ‹‹ብሔራዊ ባንክ ቁጥጥር ማብዛቱ ይጠቅም ይሆናል እንጂ፣ የሚጎዳ ነገር የለውም፡፡ ይህ ቁጥጥር በመብዛቱም በአብዛኛው ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ባንኮች በየጊዜው ዕድገት አሳይተዋል፣ ትርፋማ እየሆኑና በሁሉም ረገድ እያደጉ እዚህ ደረጃ የደረሱት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጥብቅ ክትትል፣ ቁጥጥርና ድጋፍም ጭምር ስለታከለበት ነው፤›› ብለዋል፡፡
በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ውስጥ በየጊዜው እንደ ሱቅ እየከሰሩ የሚዘጉ ባንኮች እንዳሉ በማስታወስም፣ ይህ በኢትዮጵያ ውስጥ እንደሌለና የግል ባንክ በኢትዮጵያ ውስጥ ከተፈቀደ ጀምሮ ይህ ሁኔታ እንዳልታየና ወደፊትም እንደማናይ ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ያሉት የአገሪቱ ባንኮች በአትራፊነት የዘለቁ ቢሆንም፣ ወደፊት ለሚጠብቃቸው ውድድር ዝግጁ መሆን እንደሚገባ በዚሁ ንግግራቸው የጠቀሱት ዶ/ር ይናገር፣ ከኢትዮጵያ ውጭ በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጠንካራ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመውጣት ሊሠሩበት ይገባል ብለው ከጠቆሙት ውስጥ ራስን በቴክኖሎጂ ማደርጀት ይገኝበታል፡፡ ስለዚህም ቦርዶችና አመራሮች ለዚህ ወሳኝ ተግባር ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ማድረግ እንደሚኖርባቸውና ይህንን ካላደረጉ በቀጣይ የሚጠብቃቸው ውድድር ቀላል እንደማይሆን ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ ባሻገር ባንኮች በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ስላላቸው ሚናና አበርክቷቸው ተናግረዋል፡፡ በዚሁ ዙሪያ ያመለከቱትም በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ የባንኮች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ነው፡፡ በባንኮች በኩል በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ኮቪድ-19ን ተቋቁመውና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ጠንካራ ክንድ ሆነው መዝለቃቸውን አመሥግነዋል፡፡
አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የመንግሥትም ሆነ የግልም ባንኮች ኢኮኖሚውን በከፍተኛ ሁኔታ እየደገፉ መሆኑን በመጥቀስም በተለይ በኮቪድ-19 እና በሌሎች ሁኔታዎች ይመጣ የነበረን የከፋ ጉዳት ከመቀነስ አኳያ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጋር በመሆን ከፍተኛ ርብርብ ስለመደረጉ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡
በንግግራቸው ማጠቃለያ ላይም የተለያዩ በርካታ ችግሮች ባሉበት የኢትዮጵያ ባንኮች በየዓመቱ ከፍተኛ የትርፍ መጠን እያገኙና እያተረፉ መሄድ ዋና ዓላማቸው ቢሆንም፣ ኢኮኖሚው ውስጥም አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅባቸዋልና በቅርቡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያወጣቸው መመርያ ላይ ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ሰሞኑን የወጡት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያዎች በባንኮች ላይ ጫና የሚያስከትሉ ስለመሆኑ እየተነገረ ነው፡፡
በተለይ በብዙ ሙግትና ውትወታ ተቋርጦ የነበረው የቦንድ ግዥ ዳግም መመለሱ የባንክ የሥራ መሪዎችን በእጅጉ ማሳሰቡ አልቀረም፡፡ ከውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ ባንኮች ለብሔራዊ ባንክ ያስገቡ የነበረው የ30 በመቶ መጠን ወደ 50 በመቶ ማደጉም ባንኮችን እንደሚጎዳ እየተገለጸ ነው፡፡
አሁን ወደ 50 በመቶ ከማደጉ ቀደም ብሎ ባንኮች ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ 30 በመቶውን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንዲያስገቡ መደረጉ ከውጭ ምንዛሪ ግኝት ጋር ሊያገኙ የሚችሉትን ጥቅም እያሳየ መሆኑን በመግለጽ ይህ አሠራር እንዲነሳላቸው በባንኮች ማኅበር በኩል በተደጋጋሚ ሲጠይቁ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ከዚህ አንፃር አዳዲሶቹ የብሔራዊ ባንክ መመርያዎች ባንኮች ላይ ተፅዕኖ ከማሳደራቸውም በላይ ሊፈትናቸው የሚችል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡