Sunday, June 16, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የቅል-ጡሌ እና ሥነጽሑፍ

በተሾመ ብርሃኑ ከማል

የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ በሚያዝያ ወር 1979 በታተመው የካቲት መጽሔት ላይ ‹‹ዱባና ቅል አበቃቀሉ ለየቅል›› በሚል ርዕስ፣ አንድ ሳይንሳዊ የጥናት ይዘት ያለውን ጽሑፍ አቅርቦ ነበር፡፡ እነሆ ከ32 ዓመታት በኋላ ደግሞ ሳይንሳዊና ኪነጥበባዊ ይዘት ያለው እንዲሆን አድርጎ ማቅረቡን አስቀድሞ ለመግለጽ ይወዳል፡፡ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ሁለት ዓበይት ጉዳዮች የሚነሱ ሲሆን አንደኛው የቅል ምንነት የሚያወሳ ሳይንሳዊ ትንታኔ ሲሆን ሁለተኛው የቅል በተለይም የጡሌን ትውፊት የሚመለከት ነው፡፡

ስለዱባና ቅል አጠቃላይ መግለጫ

አበው ሁለት የማይጣጣሙ ወይም የማይመሳሰሉ ወይም ተመሳሳይነት ኖሯቸው የየራሳቸው ጠባይ ያላቸው ተፈጥሮዎች፣ ድርጊቶችና ሁኔታዎች  ሲገጥማቸው ‹‹ዱባና ቅል አበቃቀሉ ለየቅል›› በማለት አስተያየታቸውን ይደመድማሉ፡፡ ሆኖም ዱባና ቅል አበቃቀሉ ለየቅል ለምን ተባለ ተብሎ ሲጠየቅ  ምንም እንኳ በተራ ተመልካች ዓይን የቅል አበቃቀል የዱባን፣ የዱባ አበቃቀል የቅልን ቢመስልም የየራሳቸው የአበቃቀል ባህርይ ስላላቸው ነው ማለት ይቻል ይሆናል፡፡

የሚገርመው ግን ዱባና ቅል አበቃቀላቸው ለየቅል ሳይሆን ተመሳሳይ መሆኑ ነው፡፡ የዱባ፣ የቅል ዝርያዎቻቸው ስሞች በተለያዩ አገሮች አንዳቸው የሌላውን ስም የሚይዙ ሆነው መገኘታቸው ብዙ የጥናት ጽሑፎች ያስረዳሉ፡፡ ይህም የአበቃቀል ዓይነታቸውን ተመሳሳይነት እንጂ ልዩነታቸውን ወየም ለየቅል መሆናቸውን አያሳይም፡፡

ሩቅ ሳንሄድ አምሳሉ አክሊሉና ሞስባክ ባዘጋጁት ‹‹እንግሊዝኛ-አማርኛ መዝገበ ቃላት›› ፐምፒኪንና ማረው የተሰኙትን ቃላትን ዱባ ሲሏቸው ስኳሽን ደግሞ ትንሹ ዱባ፣ ዝኩኒ፣ ሜለንን ከርቡሽ ወይም በጢሕ›› ይሏቸዋል፡፡ አቶ ወልደሚካኤል ከለቻ ‹‹የኢትዮጵያ አትክልት ስሞች መፍቻ›. በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፍ ዱባ፣ ሐብሐብ፣ ኪያርኪያር ወይም በጢሕ፣ ዝኩኒ፣ የሰይጣን ዱባ፣ ያሞራ ምሳ፣ የምድር እምቧይ፣ የቋራ ሐረግ፣ ውሽውሽ ወይም ሐምሐም (ትግርኛ) በአጠቃላይ የቅልና የዱባ ዘር መሆናቸውን ጠቅሰው በአገራችን ልዩ ልዩ ቋንቋዎች የተሰጣቸውን ስሞች አስፍረዋል፡፡

ሆኖም አቶ ወልደሚካኤል ከለቻና አቶ ጌታሁን አማረ ‹‹የኢትዮጵያ አትክልት ስሞች››  በሚል ርዕስ ባዘጋጁት አነስተኛ መዝገበ ቃላት (የቃላት መፍቻ) ለእያንዳንዱ የቅልና ዱባ ዝርያ ሳይንሳዊ ስም ላይ ልዩነት እንዳለ እንመለከታለን፡፡ ለምሳሌ አቶ ወልደሚካኤል የምድር እምቧይን ‹‹ኩኩሚሶ ሲፎሊየሲስ›› ሲሉት አቶ ጌታሁን አማረ ደግሞ ‹‹ኩኩምቢታ ፕሮፌላነም›› ይሉታል፡፡ በመንግሥት እርሻ ልማት ሚኒስቴር የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት መምሪያ መጋቢት 1973 ‹‹ዘመናዊ አትክልትና ፍራፍሬ አመራረት ዘዴ አንደኛ እትም ረቂቅ ላይ ባሰፈፈሩት ጽሑፍ ‹‹ዝኩኒ›› የተባለው የዱባና ቅል ዝርያ በእንግሊዘኛው ‹‹ዝኩኒ፣ ስኳሽ፣ ማረው›› እንደሚባልና ዱባ ደግሞ ‹‹ሳመር ስኳሽ ፐምፒኪን እና ዊንተር ስኳሽ ምኪንግ›. እንደሚባል ተጠቁሟል፡፡

እንግዲህ ከመዝገበ ቃላቱና ከሌሎችም የመረጃ ምንጮች የተገነዘብነው ዱባና ቅል በአባባል ካልሆነ በስተቀር ‹‹ለየቅል›› አለመሆናቸውን ነው፡፡ ይሁን እንጂ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የዱባን እንጅ የቅልን ጥብስና ወጥ መመገብ አልለመደምና ዱባና ቅል አበቃቀላቸውም፣ አገልግሎታቸውም ለየቅል ሆኖ ቢታየውም ሆነ ሌላ ጣፋጭ ምግብ ሳይቸገር መመገብ ሲችል እንደ ቅል ያለውን መራራ ተክል አጣፍጦ ለመመገብ የተገደደ አይመስልም፡፡

በዚህም ምክንያት ይመስላል፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም ከዱባና ቅል ዘሮች ለኪያር፣ ለዝኩኒ፣ ለከርቡሽ፣ (በጢሕና ሐብሐብ) ካልሆነ በስተቀር የተለያየ ዓይነት ስላለውና አገልግሎቱ ከፍተኛ ስለሆነው ስለቅል የተደረገ ዝርዝር ጥናት በጉልህ አይገኝም፡፡

ቅል-ጡሌ

‹‹ቅል›› ጠንካራ ሽፋን ላላቸውና በአብዛኛው ለጌጣጌጥነት የሚውል የኩኩርቢታ (Cucurbita) ዝርያ (ወገን) ነው፡፡ ጂ-ኤ-ሲ ሄሬክሊተስ፣ ቀደም ሲል በተጠቀሰው መጽሐፋቸው የቅልን ዘር ‹‹ወስከምቢያ›› (dishcloth) ተስለክላኪ-እባብ መሰል(snack gourd)፣ ሰም መሰል (waxgourd) የበጋ ቅል (summer gourd) በማለት ይለዩታል፡፡

የኢትዮጵያ ቋንቋዎች የምርምር ማዕከል ‹‹ኣማርኛ መዝገበ ቃላት›› (1993)  የቅልን ትርጉም ለተክሉና ለፍሬው የሚሰጥ ሲሆን አገልግሎቱንም ይገልጻል፡፡ በዚህም መሠረት 1) በውስጡ ትናንሽ ዘሮችን የያዘ፣ ክባና ውስጠ ክፍተት የሆነ፣ትልቅ ፍሬ የሚጥል ወይም የሚያፈራ፣ መሬት ላይ ተንሰራፍቶ ወይም በአጥርና በዛፍ ላይ እየተንጠለጠለ የሚያድግ የሐረግ ተክል ዓይነት፣ ፍሬውም ቅል ይባላል፡፡ 2) ከዚሁ ፍሬ ለውኃ መቅጃና መያ ወይም ለጥራጥሬ፣ ለሽሮ፣ ለድልህ፣ ለቅቤ ማኖሪያ የሚዘጋጅ ዕቃ፣ ቅምጫና፣ ሞራ ይለዋል፤፤ መዝገበ ቃላቱ በተጨማሪ ‹‹ቅሌን ጨርቄን አለ›› ማለትም ሰበብ፣ ምክንያት አበዛ፣ ‹‹ቅል ራስ›› የማያመዛዝን፣ ባዶ የሆነ፣ ዕውቀት የሌለው፣ ‹‹ቅል አንገት›› መንጠቂያ፣ በማለት ያብራራል፡፡ ከነዚህ ፍችዎች መካከል ‹‹መንጠቂያ›› የሚለው አንደኛው ጥጥ በደጋን ሲነደፍ የጅማቱ መንጠቂያ ወይም ጡንቻው ሲታመም እንደዋገምት በመሳብ ስለሚነጠቅበት (ምንጭቅ ስለሚደረግበት) ነው፡፡ የቅል አንገት ቅርጽ የዘይት፣ የጋዝ፣ ወይም የሌላ ፈሳሽ ማንቆርያ ቅርጽ ያለው የቅል አንገትና ከአንገቱ ትንሽ ወረድ ብሎ የሚገኘውን አካል ያጠቃልላል፡፡ ይህ ቃል የእንግሊዘኛውን ፋነል (funnel) የሚለውን ይወክላል፡፡

ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ ደግሞ ‹‹ለጌጣጌጥነት የሚውሉት የወፍ ጎጆ የሚመስሉት በአጠቃላይ የብጫ አበባ ቅል ዛፍ ዘሮች ኩኩርቢታ ፔፓ (Cucurbita pepo)፣ ለማቡኪያ፣ ለውኃ መጠጫ ወዘተ አገልግሎት የሚሉውሉት ደግሞ ላጀናሪያ ሲሴናሪያ (Lagenaria cecenaria) ተብለው በወል እንደሚጠሩ ገልጿል፡፡

ሁለቱም የቅል ዘሮ የሰው ልጅ ለረዥም ዘመን ሲጠቀምባቸው የኖረ ሲሆን ላጀናሪያ ሲሴናሪያ የተባለው የቅል ዘር መጀመሪያ በሐሩራዊው ክልል መገኘቱን ገልጸዋል፡፡ ለዚህም ግምት የበቁት ከ3300-2300 ቅድመ ልደት ከተሠሩት የግብፅ መካነ መቃብሮች በመገኘቱ ነው፡፡

ቅል ብረት ከመገኘቱ በፊት ለጥንታውያን ሰዎች በቁሳቁስነት ከፍተኛ አገልግሎት የሰጠ ተክል ሲሆን እንደሹካና ማንኪያ፣ ልዩ ልዩ ዕቃዎች ለጥራጥሬ ማስቀመጫ፣ ለአሳ ማጥመጃ (መረቦችን ለማንሳፈፍ)፣ ለጥሩምባ፣ እንደከበሮና ነጋሪት፣ ለጥራጥሬ መስፈሪያ ይጠቀሙበት ነበር፡፡   በዘመናችንም ለጋ ቅል የሚበላ ሲሆን በአብዛኛው ግን ልዩ ቀለማት እየተቀባና ልዩ ልዩ ሥዕል የተሳለበት ለጌጣ ጌጥነት ይውላል፡፡  ሆኖም ከትንንሾቹ ይልቅ ትልልቆቹ ለጌጥነት ተመራጭ እንደሆኑ ኢንሳይክሎፒዲያ ያስረዳል፡፡

ኤችጂ ፈለር የተባለ ሊቅ ከቅል ዘሮች ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚሰጠው  በውስጡ ሰፍነግ (ስፖንጅ) ሥጋ ያለው ሲሆን ይህም ዕውነተኘውን ሰፍነግ የሚተካ በጃፓንም ባርኔጣ መሥሪያ የሚያገለግል ነው ይላሉ፡፡

ህንዳዊው የግብርና ተመራማሪ አር ቺ ፕራዳህ (R. C. Pradhan P. P. Said, S. Singh) ቅል ርጥበት (2.47%)፣ ፕሮቲን (30.72%)፣ ቅባት ማለትም ዘይት(52.54%)፣ ካርቦ ሐይድሬት (8.3%)፣ ጭረት (1.58%) እና አመድ (4.43%) ነው፡፡ ከቅል የሚገኘው ዘይት ንጹህና ብጫ ቀለም ያለው ሲሆን ለምግብና ለጸጉር ቅባት አገልግሎት ሊውል ይችላል፡፡ ከቅል የሚገኘው ዘይት ከሁሉም የላቀ የምግብነት ደረጃ ሲኖረው ይህም የሆነው ኦሜጋ 3 የኋልን መጠን የሚጨምር፣ አእምሮን እንዲሠራ የሚያደርግና ለአካል እንቅስቃሴ ሁለንተናዊ ጠቀሜታ ስላላው ነው፡፡

ቅል ቢመርም በቻይና ብቻውን በለጋነቱ፣ በማሌዥያ ከሥጋ፣ ከእንቁላልና ከዓሣ ጋር ይበላል፡፡ በሆንግ ኮንግ ደግሞ ሁለት የቅል ዓይነቶች ሲኖሩ አንደኛው በለጋነቱ አመዳማ አረንጓዴ ሆኖ ጎበጥ ያና የጎሽ ጸጉር ያለው ነው፡፡ ይህም ከ1.8 ኢንች ከፍ ሲል ተቆርጦ ይበላል፡፡ ሁለተኛው ዓይነት ሲጎመራ ፍሬው ይወጣና ለውኃ መቅጃም ወዘተ አገልግሎት ይውላል፡፡ ለቁሳቁስነት ከተፈለገ ሌሎች ፍሬዎቹ ሁሉ ተቆርጠው አንድ ወይም ሁለቱ ብቻ እንዲስፋፉ ቢደረግ ይመረጣል፡፡

ቅል ለምግብነት አገልግሎት መዋሉ በብዙዎች ዘንድ አይታወቅም እንጅ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች በተለይም በሐረርጌና በሌሎችም የሸክላ ሥራ ባልተስፋፋባቸው ክፍላተ ሀገር በቁሳቁስ አገለግሎቱ የታወቀ ነው፡፡ ትልልቅ ቅል ለቡሃቃ፣ ለጥራጥሬ፣ ለልብስ ማስቀመጫ፣ ለማርና ቅቤ መያዣ፣ ወተት መግፊያ ወዘተ፤ ትንንሽ ቅልም  ለመስቲ (ሊጥ ማዞሪያ)፣ አንገተ ረጃጅም የሆኑት ለመታጠቢያ፣ ለውኃ መያዣ፣ ለውኃ መቅጃ፣ ለውኃ ወይም ለወተት ወይም ለሌላ መጠጫ (ቅምጫና፣ ሽክና)፣ ለዘይት ወይም ለቅባ ኑግ፣ ለማለቢያ፣ ለጭልፋ፣ ለማንቆርቆሪያ፣ (ፋነል) ወዘተ ያገለግላል፡፡ ትልልቅ ድፍን ቅልም በጎርፍ የሞላ ወንዝና ሰው ወይም ጎርፍ ሠራሽ ሐይቅ ለመሻገሪያ (መንሳፈፊያነት) ያገለግላል፡፡

የቅል አገልግሎት ጎልቶ የሚታየው በገጠሩ ኅብረተሰብ መሆኑ ባያጠያይቅም ዛሬ በከተሞችም ቀለም እየተቀባ፣ ሥዕል እየተሳለበትና እየተለጎመ የቤት በመሆን አገልግሎት በመስጠት ላይ ነው፡፡ ቅል የፈጠራ ሥራ ከተጨመረበትና ቅርጹን መለዋወጥ ከተቻለ እንደ አትክልትና ፍራፍሬ ማቅረቢያ ሆኖ ሊጠቅም ይችላል፡፡ ይልቁንም በስለት በቀላሉ የሚቆረጥና የሚበሳ ስለሆነ በተፈለገው መልክ እየተሸነሸነና እየተሰፋ ለሚፈለገው አገልግሎት ሊውል ይችላል፡፡ የቅል ውስጣዊ አካል ማለትም ሰፍነግነት ስለሰው ዕንቁላል እንዳይሰበር ደርድረን የምንይዝበትን ሰፍነግ መሰል ዕቃ ከቅል ውስጣዊ ክፍል መሥራት ይቻላል፡፡ በአነስተኛ ኢንደስትሪዎችም ወደ ውጤት በመለወጥ ልንጠቀምበት እንችላለን፡፡

ዱባና ቅል ፍሬው ብቻ ሳይሆን ቅጠሉ፣ ግንዱ አበባው የሚበላ ከመሆኑም በላይ የውጭ ምንዛሪን ሊያስገኝ፣ ለልዩ ልዩ ሕክምና አገልግሎት የሚውል፣ ያለክፍያ ሊሰጥ የሚችል መሆኑ ታውቆ በብዛት እንዲመረት ቢደረግ ለተያያዝነው የግብርና ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ በተለይም ደግሞ የአገራችን የግብርና ባለሙያዎች ያሉንን የዱባና ቅል ዝርዮች በስፋትና በጥልቀት ቢያጠኗቸው አጥንተዋቸውም ከሆነ የትኛው በየት አካባቢ እንደሚገኝ፣ ከጥቅሙ ጋር ቢገልጹልን ግንዛቤያችንን ያሳድገዋል፡፡

ጡሌ ከቅል ተክል የሚገኝ በእንግሊዘኛውና በሳይንሳዊ መጠሪያው bottle gourd, Calabash (Lagenaria siceraria) ተብሎ ይጠራል፡፡ እንደ ዱባ፣ ሐብሐብ፣ ከርቡሽ፣ በጢሕ፣ ኩከበር፣ የምድር እምቧይ የመሳሰሉት ሁሉ የቅርብ ዝርያዎቹ ናቸው፡፡

የጡሌ አዘገጃጀት

ጡሌን ጨምሮ ማንኛውም ከቅል የሚገኝ መገልገያ ዕቃ በጥቅም ላይ ከመዋሉ በፊት ‹‹ኳ›› ብሎ የደረቀ መሆን አለበት፡፡ ከዚያም ከላይ በኩል በተፈለገው መጠን ስፋት እንዲኖረው ተደርጎ ይቀደዳል፡፡ ጸሐፊው በተወለደበት ሰቆጣ አካባቢ በመጀመርያ ቅሉ በወስፌ ተቀራራቢ በሆነ ክፍተት በወስፌ ይበሳል፡፡ ከዚያም ብሶቹ ቀስ በቀስ በሳለ ቢላ በጥንቃቄ እንዲገናኙ ይደረጋል፡፡ በመጨረሻም ይከፈትና የደረቀው ቡጥ እንዲወጣ የተለያዩ ተክሎች ቅጠሎች ተቀጥጠው ቅሉ ውስጥ ይከተታሉ፡፡ ቀጥሎም ውኃ ይሞላና ተዘፍዝፎ ይሰነብታል፡፡ ራሱ ውልቅ ብሎ ሲሄድ ምሬቱ እንዲወጣ በተደጋጋሚ በውኃና በአመድ፣ በመዘፍዘፊያ እየተሞላ በመቆየት ለልዩ ልዩ አገልግሎት ይዘጋጃል፡፡

የጡሌ አዘገጃጀት ተመሳሳይ ቢሆንም አፏ ከአንድ የቅል ፍሬ ጋር ተመጣጣኝ ስለሚሆን ቡጡን የሚያሟሟው ተክል ተመርጦ ነው፡፡ ለምሳሌ የቁን ቁራ (ጋባ)፣ የምሬንዝ በሳይንስ «አኮካንተር ሺምፔሪ» (Acokanthera schimperi)፣ ወይም በቀረጥ (quadrrpartita, santalaceae, East African sandalwood)፣ ወይም በሌላ እንደ አካባቢው ተሞክሮ ይዘፈዘፍና ይሰነብታል፡፡ ቡጡ ወደ ሙልጭልጭ ሾርባነት ሲለወጥ ፍሬውም ቀረላሉ የሚታጠፍ ሆኖ ይወጣል፡፡ ከዚያም እንደማንኛውም ቅል  ፍሬውና ቡጡ ውልቅ ብሎ ሲሄድ ምሬቱ እንዲወጣ በተደጋጋሚ በውኃ፣ በአመድና በመዘፍዘፊያ እየተሞላ ከቆየ በኋላ ለመጨጫነት አገልግሎት ይዘጋጃል፡፡

መስሎ ፋል፡፡  ምሬንዝ እስከ 35 ጫማ ርዝመት ሊኖረው ይችላል፡፡ አበባው እንደመቅላት ሲል ወይም ሐምራዊ ሲሆን ፍሬው የዕንቁላል ቅርጽ ያለው ደማቅ ቀይ ነው፡፡ ይህ ዕፅ በስሜን ምሥራቅ የአፍሪካ ቀንድ ይገኛል፡፡ ቅጠሉን በሰቆጣና በትግራይ አዲስ ቅል ለጥቅም ከመዋሉ በፊት መራራውን ለማስለቀቅ ውስጡ በመዘፍዘፍ ሲጠቀሙበት የታመሙ አህዮችን በደረቀው ቅጠል ጭስ ያጥኗቸዋል፡፡

የቅል እና ጡሌ ትውፊት

ጫት ቁሉእ፣ መቀንታ ጫት፣ ጫት ቁሉ፣ ቆሙት (ጉራግኛ)፣ ቅምጫና (ጎንደር፣ ጎጃም፣ ሰቆጣ)፣ ወይሳ (በሱማሊኛ)፣ ፎሌ፣ ዱሌ (ራያ አካባቢ)፣ አንኮላ (ስልጤ)፣ ማስቁላ፣ ጡሌ ትባላለች፡፡ በቆራሱማ ታጥና ውኃ ይደረግባታል ውኃው የእርጎ ቃና ይኖረዋል፤ በተጨማሪም ረጃጅም ሴቶች አንገታቸው ረጅም ‹‹ጡሌ አንገት›› ተብለው ይጠራሉ፡፡ የቄስ  ተማሪ የሚጠቀምበት ከሆነ ቅምጫና የሙስሊም ተማሪ/ ደረሳ/ የሚጠቀምባት ከሆነ ደግሞ ጡሌ ይባላል፡

ጡሌ በአጠቃላይም ቅል ለሰው ልጅ እጅግ ከፍተኛ አገልግለት ከሰጡት የፈጣሪ ጸጋዎች አንዱ ነው፡፡ ይኸው ለብዙ ሺህ ዓመታት የሰውን ልጅ ሲያገለግል የኖረ የተፈጥሮ ጸጋ በሚመለከት የሚነገር ትውፊት ይኖር እንደሆን መጠናትና መቅረብ ያለበት ሲሆን፣ ለጊዜው ግን ያልተማረ እርባና ቢስ ነው ለማለት ‹‹ያልተማረና ጡሌ አንድ ነው›› ወይም ‹‹ቁርአን ያልቀራ፣ ከዚያ ላይ ተፍሲር ያልጨመረ የጡሊ ቅል ነው›› መባሉን፣ ‹‹ደረሳ ጡሊውን አይረሳ›› ወይም ‹‹ሁሉም ደረሳ በየራሱን ጡሌ ይጠቀም›› ወይም ‹‹ሁሉም ደረሳ በየራሱን ጡሌ ያንሳ›› እንደሚባል ይነገራል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ‹‹ተፍሲር ያልቀራ በኢልም ያልተስማራ ልክ እንደ ጡሌ ነው›› ይባላል::

ስለ ዱባና ቅል ብዙ የሚነገሩ ምሳሌያዊ ንግግሮች ሲኖሩ ከነሱ ሁለቱ የሚከተሉት ናቸው፡፡

‹‹ትመር እንደሆነ ምረር እንደ ቅል 

አልመርም ብሎ ነው ዱባ ሚቀቀል፡፡

ከዱባዎች መሃል፣ ዱባን የመሰለ፣

‹‹ተከትፎ፣ ተጥዶ አብሮ የበሰለ፣

ቀረበ ከማዕድ ሊበላ በንጀራ፣

ለካስ እሱስ ነበር፣ አያቅል መራራ፡፡

የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ከ60 ዓመታት በፊት ጀምሮ እንደሚያስታውሰው፡-

‹‹ያምስት ሳንቲም ቆሎ ይቆረጥምና፣

አንድ አንኮላ (ቅል፤ ሽክና፣ ጡሌ) ውኃ ግጥም ያደርግና፣

ተመስገን ይለዋል፣ አምላኩን ያይና፡፡

ጡሌ ከብዙ ሺህ ዓመታት ጀምሮ የሰው ልጅ ለውኃ፣ ለወተትና ለሌላም ፈሳሽ ነገር መያዣነት ሲጠቀምበት እንደኖረ ቢታወቅም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሲጠቀምበት የነበረው ደረሳ ነው፡፡ ቀደም ሲል በነበሩት ዓመታትም የቆሎ ተማሪ ይጠቀምበት ነበር፡፡ ሆኖም የቆሎ ተማሪው ወደ ሸክላ (ምንቸት) ፊቱን ሲያዞር ደረሳው በቆርቆሮ ወይም በፕላስቲክ መንቆርቆሪያዎች እስኪተካ ድረስ በጤሌ መገልገሉን ቀጥሎ ነበር፡፡ ስለዚህም፣

በረሃ ባቋርጥ፣ በጨለማ ብሄድ ፣

ዳገቱን ብወጣ፣ ቁልቁለቱን ብወርድ፣

ደጋ ብሄድ ቆላ፣ አግድመት ብራመድ፣

አንቺ ነሽ ጡሌዬ የእውነተኛ ዘመድ፡፡

ስቀመጥ ተቀምጠሸ፣ ብጓዝም ታዝለሽ፣

ውኃም ሆነ ወተት፣ ጥሬ ብየዝብሽ፣

የምትቀበይኝ እንዳመሌ አድርገሽ፣

ንብረቴ አገልጋዬ ጡሊዬ አንቺ ነሽ፡፡

ይላት ነበር፡፡ በእርግጥም የአንድ ደረሳ ጡሌ ከማንኛውም የበለጠ አጋር ናት፡፡ እርሷ የምትሰጠውን አገልግሎት ማንም አይሰጠውም፡፡ አንድ ሁለት ሊትር ውኃ የምትይዝ ጡሌ ያለው ደረሳ በረሃ ቢያቋርጥ በአንድ ጉንጭ ውኃ ጉሮሮን እያራሰ ይጓዛል፡፡ በጥቂት የውኃ ጠብታዎች ታጥቦ ለሰላት ራሱን ያዘጋጅባታል፡፡ የወንዝ ውኃ ካገኘ ከለል ብሎ ገላውን ይታጠብባታል፡፡ ከሀብታም በረት እግር ከጣለው ወተትም፣ እርጎም፣ ቅቤም ይይዝባታል፡፡  ጠብታ ውኃ አተር ቢያገኝ ነክሮና አርሶ ይበላባታል፡፡

ጡሌና ደረሳ

በመሠረቱ ደረሳ ማለት በዚህ ጽሑፍ ዓውድ ትርጉሙ በባህላዊ ኢስላማዊ ትምህርት ቤት የሚማር እንደማለት ነው፡፡

ጡሌና ደረሳ፣ ደረሳና ሰብእና አንዳቸው በሌላቸው እየተሳበቡ በመምጣት ባህልን፣ ማኅበራዊ ሕይወትን፣ ኪነጥበብን ሲገልጹ የሚከሰቱበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ በተለይ ወጣቶች በአፍላ ዕድሜያቸው በግጥምና በዜማ ስሜታቸውን ይገልጡበት ነበር፡፡ በተለይ ወጣቶች በአፍላ ዕድሜያቸው በግጥምና በዜማ ስሜታቸውን ይገልጡበት ነበር፡፡ ደረሳ አፍቃሪዋን የሚያሽሟጥጡ፣

‹‹አንቺ ደረሳ ወዳጅ፣ አንቺ ደረሳ ብርቁ፣

ባለጡሌሽ መጣ ይታያል በሩቁ፡፡›› በማለት ሲነግሯት እርሷ ደግሞ፡-

‹‹እስይ እንኳን መጣ፣ አጫውተዋለሁ፣

አሚተኛው ሁላ ጣት አስነክሳለሁ›› በማለት ትመልሳለች፡፡ ከዚህ ቀጥሎ የሚቀርበው በባለ ጡሌው ደረሳና በአፍቃሪው መካከል የሚደረግ ምልልስ ነው፡፡

ከጀርባህ እዘለኝ ከትከሻህ ላይ፣

ከኪታብ ከጡሊ እከብዳለሁ ወይ፡፡

ከኪታብ ከጡሌው ምን ትከብጅኛለሽ፣

መድረሻዬ ሩቅ ነው ትደክሚብኛለሽ፡፡

ምንስ ያደክመኛል ከጀርባህ ላይ ሆኘ፣

ተከትየህ ብሄድ ካንተ ጋር መንኘ፡፡

ምን ያደርግልሻል ብትሄጂ ኮብልለሽ፣

አላዋጣሽ እኔ ለምንም አልበጅሽ፡፡

እኔ መች አጣሁት የሚበጀኝ ለኔ፣

ባንተ አይደለም እንዴ እንደዚህ መሆኔ፡፡

አባትሽ አልሰሙ፣ እናትሽ አልሰሙ፣

የት ሄዳለች ቢባል ለማነው ሕመሙ፡፡

እኔን እምም ያርገኝ፣ ምንህን ተነክተህ፣

ልብ ያጣህ ይመስል ልቤን ነቅለህ ወስደህ፡፡

መቼም ስግብግብ ነህ ከንፈርክን አትሰጠኝ፣

ፍቅርህ ጠንቶብኛል  ምንያህ ብትጠይቀኝ፡፡

ባታውቂው ነው እንጂ ጡሌው የተሞላው፤

በፍቅር ወለላ በፍቅር ወይን ነው፡፡

ሲከፈት ሲዘጋ፣ ሲቀዳ ሲሞላ፣

በፍቅር ስም እንጅ መች ሆነ በሌላ፡፡

ላንድ ቀን አውሰኝ ጡሌህን ልዘላት፣

እሽሩሩ ብየ አቅፌ ልሳማት ፡፡

ማዘልስ እዘያት፣ እሽሩሩም በያት፣

ለምዳ ብትቀርብኝ በምኔ ልተካት፡፡

መተካቱን እንኳን አትጨነቅ አሁን፣

ከደረቴ ወስደህ ሁለት ጡሌዎቸን፤

ያለ አንዳች ተጋሪ ተወጣ ሐጃህን፡፡

ዋዘኛ ነሽና ልጅቱ ሳይሽ፣

አንድ ጡሌ ከብዶኝ ሁለት ማለትሽ፡፡

የኔማ ጡሌዎች ምን ይከብዱህና፣

ተሸክመው ወስደው ይመልሳሉና፡፡

እባክሽ አትያዥኝ ቃሪአየን ላድርግ፣

ሦስት ቤት አራት ቤት ራት ልፈልግ፡፡

ያምስት ቤት፣ ያሥር ቤት እሶድቅሃለሁ፤

አረፍ ብለህ አውጋኝ፣ ዓይንህን እያየሁ፡፡

አንቺ ምን ሆነሻል አደብም አታውቂ፣

ሴት ማየት ሐራም ነው መስመር አትልቀቂ፡፡

እንግዲያው አቀርቅር፣ አትየኝ ቀንተህ፣

እኔው አይሃለሁ ከራስ እስከግርህ፡፡

መስጠቱንስ ስጪኝ ያምስት ስድስት ቤት፣

ጓደኞቼ ሲያዩ የወጥ እንጀራ ዓይነት፡፡

ኧረግ ያንተ ነገር፣ ከቃሪአው እንጀራ፣ ከትርፍራፊው፣

የእኔ ይሻልሃል ማንም ያልነካው?

ደጋግመህ ብትመጣ ቃሪአ አምጭ ልትል፣

እኔ እሰጥሃለሁ፣ በፍቅር አገልግል፡፡

እንዲያማ ከሆነ  ይቅርብኝ ከእንግዲህ

ቃሪአም አደርጋለሁ አልመጣም ወደዚህ፡፡

አንተ ባትመጣ በሩቁ ብትሄድ፣ ላለማየት ፊቴን፣

መስጊዱ መድረሻው  እዚህ ጎረቤቴ ምን ታደርገው ይሆን?

በነቢ ብያለሁ፣ በረሱል ብያለሁ፣

ብቅ ብለሽ ብታይኝ አፍሬ እሞታለሁ፡፡

አፍረህማ ከሞትክ ከቶ ምን እላለሁ፣

ጡሌህን ወስጄ ለእኔ አደርጋታለሁ፡፡

እንደዚህ ከሆነ አልመጣም ቅሪብኝ፣

እኔም አልደርስብሽ አንቺም አታግኝኝ፡፡

እየተባባሉ ያሳልፉና እሱም ወደ ቃሪአው፣ ከዚያም ወደ መድረሳው ይሄዳል፡፡ በእርሷ ምክንያት አገር ለቆ ከሄደና እስከ መጨረሻው ካልተመለሰ፣ እርሷ፡-

ያ መልከ መልካም  ልጅ  ከነጓዙ  መጥቶ፣

ልቤን ይዞት ሄደ በጡሌው ውስጥ  ከትቶ፡፡

ምን ዓይነት ጡሌ ናት የተንጦለጦለች፣

እርሷ  ተንጦልጡላ  ሰው ጦልጧላ አረገች፡፡

ስትልፍቅሩ መናወዟን ያወቁ የሰፈር ሰዎች  ደግሞ፡-

አበደች  ይሏታል  ጨርቋን ጥላ  ሮጠች፣

ባለ  ጡሌ  ወድዳ አቅል ልቧን ጣለች፡፡

መቸም አንድ ነገር ተጀምሮ በተፈለገው መልኩ ሲያልቅ ደስ ይላልና  

ትላንትና ጡሌ አንጠልጣይ፣ ደረሳ ነበረ፣

ትላንት ለቃሪአ፣ ዘዋሪ ነበረ፣

ትላንት ሐርፍ አንባቢ ቆጣሪ ነበረ፣

ዛሬ ዓሊም ሆኖ ያቀራ ጀመረ፡፡

የደረሴው እናት ተነሽ እልል በይ፣

የደረሴው እናት፣ ዝለቂ አደባባይ፣

ተምሮ መምጣቱን አልሰማሽም ወይ፡፡

ደረሳው በትምህርት ቤት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገዶች የሚማራቸው ብዙ ናቸው፡፡ በተለይም ስለ ታላላቅ ሊቃውንትና በኅብረተሰቡ ያላቸው ቦታ ሲሰማ ልቡ እንደነሱ ለመሆን ይመኛል፡፡ ሆኖም በታሪክ የሰማውና በሕይወቱ የሚያጋጥመው አንድ ላይሆን ይችላል፡፡ ስለሆነም፡

የጨዋ ልጅና ቅል ተሰባሪ ነው፡፡

የሚሉትን ተረት የሰማ ደረሴው፣

በልቡ ይል ነበር፣ እውነት ነው፣ እርግጥ ነው፣

ስንቱ ተሰበረ፣ ስንቱ ጠፋ ከቶ፣

አጥብቆ ሚይዘው ጥንቃቄ ጠፍቶ፡፡

እያለ ሲሰብክ፣ እያለ ሲያስተምር፣

በቀየው ላይ ሆኖ የሚሰማው ነበር፡፡

እሰው አገር ሄዶ ደረሴው በድንገት

ቀኝ ሲላቸው ግራ፣ ኋላ ሲላቸው ፊት፣

ሆነበት ነገሩ ተገላበጠበት፡፡

እነሱ አዋቂ፣ እሱ ግን ደንቆሮ፣

ሆነና ነገሩ መልኩ ተቀይሮ፣

‹‹አያ ቅል ባገሩ ይሰብራል ድንጋይ፣

አሁን ተረዳሁ ይህ አይደለም ወይ?››

ጊዜ የሰጠው ቅል ዲንጋ እንደሚሰብር፣

ከዚህ ወዲያ የለም የሚሆን ምስክር፡፡

ማጠቃለያ

ስለዱባና ቅል ጥቅም መገለጥ ያለበት በጣም ብዙ ነው፡፡ በተለይም በዚህ ጽሐፍ በ1979 እና ከዚያ ወዲህ ስለዱባ ያጠናሁትን የገጽ መጣበብን ለማስቀረት ብዬ አላካተትኩትም፡፡ እንዳስፈላጊነቱ ወደፊት እልከዋለሁ፡፡ መሠረታዊው ቁምነገር ግነ እኔ የማውቀውን የደረሳውንና የጡሌን ግንኙነት በመጠኑም ቢሆን ጨለፍ አድርጌ አቅርቤያለሁ፡፡ ሌሎች ደግሞ የቆሎ ተማሪዎችንና የቅምጫናን ግንኙነት በሚመለከት በወል ግጥምም ሆነ በቅኔም ቢጽፉ ለአገሪቱ የተሟላ ቅርስ መግለጫ ይሆናል የሚል ጽኑ እምነት አለኝ፡፡

ከአዘጋጁጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛና ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ናቸው፡፡ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles