በዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ዘመን በ1860 ዓ.ም. ከመቅደላ አምባ በእንግሊዝ ወታደሮች ተዘርፈው ከነበሩት ተንቀሳቃሽ ቅርሶች መካከል አሥራ ሦስቱ በለንደን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተረከበ፡፡
ኤምባሲው በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳስታወቀው፣ የተረከባቸው ቅርሶች ከወራት በፊት ለሽያጭ ቀርበው የነበሩ ናቸው፡፡
ቅርሶቹ የብራና መጽሐፍ ከነማህደሩ፣ ልዩ ልዩ መስቀሎች፣ በነሐስ የተለበጠ የንጉሠ ነገሥቱ የጦር ጋሻ፣ ጽዋ፣ የጳጳስ አክሊል፣ የቀንድ ዋንጫዎች ናቸው፡፡
ቅርሶቹን ጳጉሜን 3 ቀን 2013 ዓ.ም. ለኤምባሲው ያስረከበው ሻይራዛድ ፋውንዴሽን ቅርሶቹን በእንግሊዝ ከሚገኝ አንድ የጨረታ ድርጅትና ከነጋዴዎች መግዛቱን ገልጿል፡፡
በአቴናዩም ክለብ ውስጥ ቅርሶቹን ለመቀበል በነበረ ዝግጅት ላይ በእንግሊዝ የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈሪ መለሰ እንደተናገሩት እነዚህን ድንቅና ብርቅዬ ቅርሶች በመመለሳቸው ተቋሙን አመስግነዋል። አምባሳደሩ ከመቅደላ የተዘረፉ ቅርሶችን የያዙ ሙዚየሞች፣ የቅርስ ሰብሳቢዎችና ግለሰቦች በተመሳሳይ ንብረቶቹን እንዲመልሱ ጥሪ አድርገዋል።
የሻሃራዛድ ፋውንዴሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታሂር ሻህ በበኩላቸው የቅርሶቹ መመለስ ለኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ሥፍራ እንዳለው እንደሚያውቁና ድርጅታቸውንም በመጠቀም በሁለቱ አገሮች መካከል ድልድዮችን እንደሚገነቡ ተስፋ አድርገዋል።
የኢትዮጵያ የቅርስ ባለአደራ ማኅበር የቦርድ አባል አሉላ ፓንክረስት (ዶ/ር) በርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው እንደተናገሩት ‹‹ይህ ቀን ለኢትዮጵያ የአንድነት ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው፡፡ ጥንታዊ ታሪክ ያላትን አገር ቅርሶቿን በአግባቡ እንዲመለሱ ማድረግ መቻሉ የአገሮቹን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክር ነው፤›› ብለዋል፡፡
ገጣሚና የማንችስተር ዩኒቨርሲቲ ቻንስለር ለምን ሲሳይ በበኩሉ ‹‹በትውልድ ኢትዮጵያዊ መሆኔ ያኮራኝ ዕለት ቢኖር ዛሬ ነው፣ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን እንኳን ደስ አለን›› በማለት ታሪክ የአገር መሠረት በመሆኑ ሥነ ሥርዓቱ ለኢትዮጵያ ሌላ የታሪክ ምዕራፍ ነው በማለት ተናግሯል፡፡
የተመለሱት ቅርሶች በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ የገቡ ሲሆን፣ በቅርቡ ወደ አገር ቤት እንደሚላኩ ተገልጿል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት የአፄ ቴዎድሮስ ፀጉር ቁንዳላ ከለንደን ወደ አገሩ መመለሱን ይታወቃል፡፡
ኢትዮጵያን ዳጀስት እንደዘገበው፣ ከመቅደላ የተዘረፉ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ቅርሶች በብሪትሽ ሙዚየም፣ በቪክቶሪያና አልበርት ሙዚየም፣ በብሪትሽ ላይብረሪና በዊንድሰር ካስል የሚገኙ ሲሆን ከነዚህም መካከል 11 ቅዱስ ታቦታትን ጨምሮ የብራና መጻሕፍት፣ ዘውዶች፣ በወርቅና በብር ያጌጡ የቤተ ክርስቲያን መገልገያዎችና አልባሳት ይገኙበታል።