በአገራችን ታሪክ እጅግ በጣም ዘግናኝ ከሚባሉት ጊዜያት ውስጥ ተጠቃሽ የሆነው የ1977 ዓ.ም. ረሃብ መቼም አይዘነጋም፡፡ የረሃብ ነገር ሲነሳ በሕይወቴ የዚያ ዘመን አስደንጋጭ ምሥል አሁንም ውስጤ ቀርቷል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን በተከሰተው ጦርነት ምክንያት በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች በደረሰው መፈናቀል ምክንያት ወገኖቻችን ለረሃብ መጋለጣቸው ያሳስባል፡፡ በ1977 ዓ.ም. ከአንድ ሚሊዮን በላይ ወገኖቻችን ሕይወት እንደቀጠፈ የሚነገርለት ክፉ ጊዜ፣ በዚህ ዘመን እንዳይደገም ከልቤ እመኛለሁ፡፡ ያ አሰቃቂና አስጨናቂ ረሃብ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ሲተላለፍ፣ እኔም በራሴ ላይ የደረሰውንና ያን ክፉ አጋጣሚ ለአንባቢያን ማቅረብ ፈለግኩ፡፡
በዚያን ወቅት በአሁኗ ሩሲያ በዚያን ጊዜው የሶቪየት ኅብረት ሪፐብሊክ ዋና ከተማ ሞስኮ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተማሪ ነበርኩ፡፡ በኮሙየኒስቷ ሩሲያ የተለያዩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች አሰቃቂው ረሃብና የሚረግፈው ሕዝባችን ምሥል ሲቀርብ እውነት ሳይሆን ቅዥት ይመስለኝ ነበር፡፡ እነዚያ ጡታቸው የደረቀ እናቶችና አፅማቸው በደመነፍስ የሚላወስ ሕፃናት የሚልሱትና የሚቀምሱት አጥተው ከህቅታቸው ጋር ሲታገሉ ማየት ቅዥት እንጂ ሌላ ምን ይባላል?
በዚያ ላይ ከሩሲያና ከተለያዩ የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች፣ እንዲሁም ከአፍሪካና ከላቲን አሜሪካ አገሮች የተውጣጡ የክፍል ጓደኞቼ ይህንን አሰቃቂ ትዕይንት እያዩ፣ እኔ ከዚህ ጉድ ተርፌ ከእነሱ ጋር በመማሬ ዕድለኛ መሆኔን ያለ ምንም ኃፍረት በግልጽ ሲናገሩ ያንገበግበኝ ነበር፡፡ በተለይ ካርሎ አውጉስቶስ የሚባል በአንድ ወቅት አንጎላ ውስጥ ከፍተኛ የመንግሥት ሥልጣን የያዘ፣ በዚያን ጊዜ ግን እንደ እኔ ተማሪ የነበረ ጉረኛ፣ ‹‹እናንተ ኢትዮጵያውያን ቅኝ ገዥዎችን አንበረከክን ብላችሁ ጉራ ትነፋላችሁ፣ ድርቅና ረሃብ ግን ሲጫወትባችሁ ደግሞ ታሳዝናላችሁ፡፡ በል ዘመዶችህ ከመሞታቸው በፊት ይኼንን ላክላቸው፤›› ብሎ እጄ ላይ ያስቀመጠው የአሥር ዶላር ኖት አይረሳኝም፡፡
አውቶቡስ ውስጥ፣ ባቡር ውስጥ፣ ቴአትር ወይም ፊልም አዳራሽ ውስጥ የማገኛቸው በሙሉ ሲያዩኝ፣ የእኔ ከዚያ ጉድ ውስጥ አለመገኘት መነጋገሪያቸው ነበር፡፡ ለነገሩ በዘመኑ ሩሲያም ሆነ አሜሪካ፣ ጀርመንም ሆነ ፈረንሣይ፣ እንግሊዝም ሆነ ጣሊያን፣ ብቻ ከአገር ውጭ ይኖሩ የነበሩ ዜጎቻችን አንገታቸውን ደፍተዋል፡፡ ለዓመታት ሳያቋርጥ በሚካሄድ ጦርነት ላይ አሰቃቂው ረሃብ ተጨምሮበት፣ ኢትዮጵያ የልመናና የውርደት አኮፋዳዋን ይዛ በአደባባይ እርቃኗን የታየችበት ጊዜ በመሆኑ ሁላችንም አንገታችንን ደፍተናል፡፡ ከማንም በላይ ግን የሚላስና የሚቀመስ አጥተው እህልና ውኃ እንደ ናፈቃቸው ለዘለዓለም ያሸለቡት ሚሊዮኖችን ግን እስከ ዛሬ ድረስ ሳስባቸው እሸበራለሁ፡፡ ያ አሰቃቂ ረሃብ በሆነ አጋጣሚ ሲታወስም እንቅልፍ አጥቼ ነው የምሰነብተው፡፡
ዕድሜ በወቅቱ ለነበሩ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያንና ዓለም አቀፋውያን በተደረገ እጅግ ከባድ ርብርብ ረሃቡ ጋብ አለ፡፡ የተረፉት ወገኖቻችንም አገገሙ፡፡ ያ ረሃብ ግን አገሪቱን የረሃብና የውድቀት ተምሳሌት አድርጓት በየደረስንበት ሲያቃጭልብን ኖረ፡፡ በኦክስፎርድ የእንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት ኢትዮጵያ ‹‹ረሃብ›› ለሚለው ፍቺ ተጠቃሽ ሆነች፡፡ ወገኖቻችንን እንደ ወረርሽኝ በሽታ የጨፈጨፈው ረሃብ የዚችን ጥንታዊና ታሪካዊ አገር ገጽታ አጨለመው፡፡ ሁላችንንም አንገታችንን ደፋን፡፡ ጦርነቱም እየገፋ ሄዶ ደርግ ወደቀ፣ ኢሕአዴግ ተተካ፡፡
ሩሲያ ውስጥ የነበርን ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች የሚያናግረንም ሆነ የሚደግፈን አጣን፡፡ በሩሲያ የመንግሥትና የሥርዓት ለውጥ እየተካሄደ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ 17 ዓመታት ጫካ ቆይቶ በትጥቅ ትግል የመጣው ኃይል አያውቀንም፡፡ ሁሌም ፈጣን መሆን ጠቃሚ በመሆኑ በመጀመሪያው ዕርምጃዬ እንደ ምንም ብዬ ጀርመን ገባሁ፡፡ ዕድሜ ለዘመድ ጀርመን ውስጥ ወዲያ ወዲህ እያልኩ ትንሽ ከቆየሁ በኋላ ወደ አሜሪካ ተሻገርኩ፡፡ አሜሪካ ገብቼ እንደ ወገኖቼ የተገኘውን እየሠራሁ ትምህርቴን ቀጠልኩ፡፡ እንዲያም ሆኖ የዚያ አሰቃቂ ረሃብ ጉዳይ እንደ ጥላ ይከተለኛል፡፡ አንድ ጊዜ አብሮኝ ከሚሠራ ሜክሲኳዊ ጋር ተጋጭተን፣ ‹‹ከረሃብ ተላቀህ ጥጋብ ጀመረህ?›› እያለ ስፓኒሽኛ በሚጫነው እንግሊዝኛ ሲሰድበኝ አበድኩ፡፡ የመጣው ይምጣ ብዬ ከእሱ ጋር በመቧቀሴ ከሥራ ተባረርኩ፣ በዚያ ምክንያት ብዙ ተሰቃየሁ፡፡
የአሜሪካ ኑሮን ከእነ ውጣ ውረዱ ተላምጄ ትምህርቴን ከጨረስኩ በኋላ ደህና ቦታ መሥራት ብጀምርም፣ ከዕውቀቴ ይልቅ የረሃብ ታሪካችን ጥላውን እያጠላ አስቸገረኝ፡፡ አትሌቶቻችን በኦሊምፒክ ወይም በታላላቅ ውድድሮች አሸንፈው ሜዳሊያ ሲያጠልቁ፣ የሚዲያዎቹ ማሳረጊያ ያ ረሃብ ከእነ ፊልሙ መሆኑ አዕምሮ ያሳምም ነበር፡፡ አብረውኝ የሚሠሩ ከአትሌቲክሱ ድል ይልቅ ረሃቡን እያሟሟቁ እያወሩ ሞራሌን ይገድሉታል፡፡ ከዚህ ታሪክ ጋር እንደተቆራኘን ዓመታት እየነጎዱ ሲሄዱና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት አዎንታዊ ጎኖች ሲነሱ ተንፈስ ብለን መኖር የጀመርን ብዙ ነን፡፡ እንደ አቅማችን ዕውቀታችንንና ገንዘባችንን ይዘን አገር ቤት የገባንም አለን፡፡ ለወገኖቻችን የሥራ ዕድል ፈጥረን እየሠራን ነው፡፡ አስቸጋሪ ነገሮች ቢኖሩ እንኳ ተስፋ እያየን ነው፡፡ በዚህ ሁሉ መሀል ግን የዚያ ክፉ ረሃብ ዘመን አቻ የሆነ ጊዜ እንዳይመጣ እመኛለሁ፡፡ ስማችንን በክፉ ሲያስነሳ የነበረው ረሃብ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ በዚህ መከረኛ ጦርነት ሳቢያ በወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለው መከራ ያስፈራኛል፡፡ በአዲሱ ዓመት ፈጣሪ ከዚህ መከራ ይገላግለን ዘንድ እመኛለሁ፡፡
(ዘውዱ መስፍን፣ ከአዲስ አበባ)