Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉእያደገ ያለውን የዋጋ ንረት ለመግታት ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ማረጋጊያ ፕሮግራም ያስፈልጋል -...

እያደገ ያለውን የዋጋ ንረት ለመግታት ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ማረጋጊያ ፕሮግራም ያስፈልጋል – የእስራኤል ልምድ

ቀን:

በተስፋዬ ቦሩ (ዶ/ር)

የአንድ አገር የኢኮኖሚ መዋቅር በተለያዩ ገፊ ምክንያት በተረጋጋ መንገድ ሊጓዝ የማይችልበት ሁኔታዎች ይፈጠራሉ፡፡ ምንም እንኳ የአገር ኢኮኖሚ በየጊዜው የተሻለ የዕድገት መስመር እየተጓዘና ዜጎችን በተረጋጋ ዋጋና በቀጣሪነት ደረጃ በማሳተፍ ተጠቃሚ ማድረግ ቢጠበቅበትም፣ በውስጥና በውጫዊ ምክንያቶች ከሚጠበቀው መስመር ሊዛነፍ የሚችልበት ዕድል ከፍተኛ ነው፡፡ አንዳንድ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የአጭር ጊዜና ችግሩን ታሳቢ መፍትሔዎች ተችሮዋቸው ቢስተካከሉም፣ ሌሎች እንደ ተከታታይነት ያለው የዋጋ ንረትን የሥራ አጥነት ምልክቶች በማኅበረሰብ ላይ ካላቸው ተፅዕኖ አንፃር ዘርፈ ብዙ የኢኮኖሚ መዋቅር ለውጥ ያሻቸዋል፡፡

በብዙ አገሮች ላይ (ጀርመን 1923፣ አርጀንቲና 1985፣ ሜክሲኮ 1988፣ ቦሊቪያ 1984-85) እነዚህ የኢኮኖሚ መዛነፎች የተከሰቱና እየተከሰቱ ቢሆኑም፣ አገሮች እነዚህ ችግሮችን እንደ መማሪያና መልካም ዕድል በማድረግ የኢኮኖሚ ሥርዓታቸውን አስተካክለው በዕድገት ጎዳና እየተጓዙ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ አገሮች መሀል እስራኤል አንዷ ስትሆን፣ በተለይ አገር ሆና ከተመሠረተችበት እ.ኤ.አ. ከ1948 ጀምሮ በጦርነትና በዓለም ላይ በተከሰቱ የኢኮኖሚ ምክንያቶች (እንደ ነዳጅ ዋጋ መጨመር) የኢኮኖሚ ሁኔታዋ ሲዋዥቅና ብዙ ችግሮችን ሲያስተናግድ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን በጣም በባሰ ሁኔታ በ1980ዎቹ የተከሰተው የዋጋ ንረት በታሪኳ ታላቁ የኢኮኖሚ ችግር በመሆን የሚታወቅ ሲሆን፣ በዚህ ጊዜ የዋጋ ንረት መጠን ወደ ሦስት አኃዝ የተሻገረና ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ያስተናገደ ነበር፡፡

- Advertisement -

ለዚህ ችግር መነሻ ሆነው የሚጠቀሱት ብዙ ምክንያቶች ቢሆኑም፣ ዋነኞቹ ግን ሁለት ናቸው፡፡ አንደኛው የመንግሥት የበጀት ጉድለት መጠን የሰፋ መሆን ጋር ተያይዞ መንግሥት ከገበያው የሚበደረው ገንዘብ መጣን እየጨመረ መምጣቱ ነው፡፡ በተለይ ይኼ ችግር ጥልቅ በሆነበት ጊዜ የመንግሥት የአገር ውስጥ ብድር ከጠቅላላ አገራዊ ምርት ጋር ያለው ጥምረት ትልቅ ሲሆን፣ ይህም በመንግሥት ደረጃ አዲስ የአገር ውስጥ ብድርን መውሰድ ከማይቻልበት ደረጃ  ላይ የደረሰ  ነበር፡፡

በሁለተኛ ደረጃ ከውጭ ምንዛሪ ክምችት ጋር በተገናኘ የነበረው መዋዠቅ በክፍያ ሚዛን (Balance of Payment) ላይ የፈጠረው መዛባት እንደ ዋነኛ ምክንያት ይጠቀሳል፡፡ እስራኤል በብዙ ጠላት አገሮች እንደ መከበቧ ብዙ ወጪዎቿ ከወታደራዊ ጋር የተገናኙና የውጭ ምንዛሪን የሚጠይቁም ናቸው፡፡ ሁለቱ ምክንያቶች የተለያዩ ቢመስሉም በጥምረት ሲታዩ ግን የኢኮኖሚ ችግሩን ከማባባስ አንፃር ተመሳሳይ ውጤትም ያላቸው ናቸው፡፡ ለምሳሌ የበጀት ጉድለት ሳይስተካከል የውጭ ምንዛሪ ተመን መውረድን ለመከላከል ሲደረግ የነበረው ጥረት በተጓዳኝ የዋጋ ንረት ላይ ተፅዕኖ ከመፍጠሩም በላይ፣ ለውጭ ምንዛሪ ማሸሽ (Capital Flight)  አስተዋጽኦ በማድረግ የአገሪቱን የክፍያ ሚዛን ጭራሽ ያባባሰና አገሮቹ የውጭ ዕዳዎችን ለመክፈል  የሚያሠጋም ነበር፡፡

በእያንዳንዳቸው ምክንያቶች ውስጥ ብዙ የፖሊሲ ችግሮችንና ንዑስ መነሻ መንስዔዎችን ማንሳት ቢቻልም፣ የሁሉም ውጤት የሆነው ግን የዋጋ ንረትን ከቁጥጥር ውጪ በማድረግ ዜጎች በራሳቸው ገንዘብ (Shekel) ላይ እምነት የሚያጡበትን ሁኔታን የፈጠረ ነው፡፡ የአገራችን የዋጋ ንረት መጠን እንደ እስራኤል የሦስትና የአራት ዲጂት መጠን ላይ ባይደርስም፣ አሁን እያደገበት ያለው ደረጃ ወደፊት ከቀጠለ የእስራኤል ታሪክ መድገሙ የማይቀር ነው፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓላማም በዋጋ ንረት የሚሰቃዩ ኢኮኖሚዎች ምን ዓይነት የፖሊሲና የአመራር ዕርምጃዎች በመውሰድ ችግራቸውን ፈቱ የሚለውን በቁንፅሉ በማሳየት፣ በጉዳቱ ላይ ጥልቅ ጥናት ማድረግ የሚችሉ የፖሊሲ ሰዎች ይህን ልምድ በማየት ለአገራችን የኢኮኖሚ ችግር መፍትሔ እንዲጠቁሙ ለመቀስቀስ ነው፡፡

የእስራኤል የ1980ዎቹ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም

የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሙ ይዘት ሰፋ ያለ ቢሆንም፣ በሁለት ዓበይት ክፍሎች ለይቶ ማየቱ ጉዳዩን አሳጥሮ ለማቅረብ አመቺ ይሆናል፡፡ በአንድ ጎን መሠረታዊ የሆኑ የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ለመቆጣጠር የሚረዱ ቅድመ ሁኔታዎችን  መተንተን፣ ለሌላው ደግሞ ቀጥታ የኢኮኖሚ የፖሊሲ ለውጥ የተደረገባቸውን ጥቅል ሐሳቦች ማስቀመጥ ነው፡፡ መሠረታዊ የሚባሉ የኢኮኖሚ ማሻሻያ አውታሮች እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

የአመራር ቁርጠኝነት

በወቅቱ በእስራኤል የነበረው የዋጋ ንረት መጋለብ (Hyperinflation) ከቁጥጥር ውጪ መሆን ሕዝቡ በኢኮኖሚና በአገሪቱ ገንዘብ ላይ ያለውን እምነት ከመሸርሸሩም በላይ፣ የኑሮ ውድነት መባባሱ ዜጎችን ወደ አመፅና የመንግሥት ተቀባይነትን ከማሳጣት አንፃር የሚኖረውን ሚና በመገንዘብ በወቅቱ የአገሪቱ መሪ የነበሩት ሺሞን ፔሬስ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዕርምጃዎችን በመውሰድ ግንባር ቀደም ተሳታፊ ነበሩ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዘርፉ ዕውቀት ያለውን የኢኮኖሚስት ቦርድ በማዋቀር የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ከመንደፍ አልፎ ካቢኔያቸውን በፕሮግራሙ ላይ እንዲወስን እስከ ማሳመን፣ እንዲሁም ተፈጻሚነቱን በመከታተል ትልቅ ድርሻ እንደነበራቸው ይነሳል፡፡ እንዲሁም በሥልጣን ዘመናቸው ከሠሩት ትልቅ ተግባር ጎልቶ የሚጠቀሰው የኢኮኖሚ ስብራቱን በማስተካከል ረገድ የተጫወቱት ታላቅ ገድልም ነበር፡፡ ስለዚህ ከላይ የሚወርድ (Tone at the Top) ቁርጠኝነት የኢኮኖሚ ፕሮግራማችን ከመንደፍ ባለፈ በጥሩ እንዲተገበር ጭምር ጠቃሚ መሆኑም ማሳያ ነው፡፡

የማኅበረሰብ ቁርጠኝነትና ድጋፍ

ከኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሙ ቀረፃ በኋላ ትልቁ ዕርምጃ የነበረው ሕዝቡ ሊጋራው የሚችልና መስዋዕትነት ሊከፈልለት የሚገባው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መሆኑን ማሳመን ነው፡፡ እዚህ ላይ የኢኮኖሚ ዕርምጃዎችና የፖሊሲ ግብዓቶች ከሕዝቡ ጋር የሚያገናኙ የማኅበረሰብ ውሎች (Social Contracts) በማድረግ፣ ለአፈጻጸሙ ማኅበረሰቡ የራሱን ድርሻ እንዲወጣ የማሳመን ሥራዎች ስኬታማ ነበሩ፡፡ በመንግሥት የሚወሰዱ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች የማኅበረሰቡን የዛሬ ጥቅም የሚነኩ ቢሆኑም፣ ለተሻለ ነገ መሆኑን በማሰብ ከመንግሥት ጎን መቆም ለአንድ ኢኮኖሚ ለውጥ ሁነኛ ግብዓት እንደሆነ የእስራኤል ልምድ ያሳያል፡፡ በተለይ በመንግሥት ሲደገፉ የነበሩ የማኅበረሰብ ግልጋሎቶች (Subsidies) መነሳት፣ የዋጋ ትመናና ሌሎች የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች የማኅበረሰቡን ጥቅም ቢነኩም ለወደፊት ዕድገት ጠቃሚነታቸውን  በማመን የዛሬን ጥቅም መስዋዕት ማድረጉም የሚያስደንቅ ነው፡፡ አንድ ባለሥልጣን እንዳሉትም የእስራኤል ሕዝብ በጦርነት ጊዜ ጄኔራል እንደሆነው ሁሉ በኢኮኖሚያዊ ቀውስ ጊዜያት ሁሉ፣ ኢኮኖሚስት ሊሆን ይገባል፡፡ ይህም ተጎጂውም ተጠቃሚውም ሕዝቡ ስለሆነ ያለማቅማማት ከመንግሥት ጋር በመወገን ለኢኮኖሚ አብዮት በሩን  ሊከፍት ይገባል፡፡

ከተፅዕኖ ፈጣሪ ተቋማት ጋር መደራደር

አንዱ የኢኮኖሚ መዋቅሩ ትልቁ ስኬት የመሪዎች የድርድር ብቃት በስፋት የተስተለዋበት ሲሆን፣ ማኅበረሰቡ ውስጥ የሚገኙ ነገር ግን ተጠናክረው የተደራጁ ተቋማት አባሎቻቸውን ለማሳመንም ሆነ ከመንግሥት ጋር ድርድር ለማድረግ ዋነኛ የትኩረት ዒላማዎች መሆናቸውን ያሳያል፡፡ ትልቁ የእስራኤል የሠራተኞች ኅብረት (Histadrut) በውስጡ ዘርፈ ብዙ የኢኮኖሚ አውታሮች ላይ የሚሠሩ የሠራተኛ ማኅበራት ጥምር ውጤት በመሆኑ በተለይ ሠራተኛውን የተመለከቱ የደመወዝ ክፍያ፣ ጡረታና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች ጋር የሚገናኙ ውሳኔዎች ላይ ያለው ድምፅ ታላቅ ነበር፡፡ መንግሥትም ከእነዚህና ከመሰል ተቋማት ጋር ያደረገውን ድርድር ከማኅበረሰቡም ለየት ባለ መንገድ ሰጥቶ በመቀበል መርህ ላይ የተመሠረተ ሲሆን፣ ሁለቱም ተዋንያን ሊያተርፉበት የሚችልበትን አማራጭ የመለየት ሥራም ተሠርቷል፡፡ ለምሳሌ ያህል በኢኮኖሚ ማሻሻያ ጊዜ መንግሥት የሠራተኞችን ደመወዝና ክፍያ እንዳይጨምር ሲያደርግ፣ ለሠራተኛው በቀጣሪ ድርጅት የሚከፈለውን የጡረታ መዋጮ መጠን ዝቅ በማድረግ ነበር፡፡

ስለዚህም ተፅዕኖ ፈጣሪ በሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ ለየት ያለና ለሁሉም የሚጠቅም (Win-Win) ድርድር ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን የእስራኤል ልምድ ያሳየናል፡፡ የእዚህ ዓይነት አካሄድም ከመንግሥት የሚገኝን ጥቅም ለሠራተኞች ከማስከበርም በላይ፣ ሠራተኞች ሥራቸውን እንዳያጡ ወይም አገሪቱ ውስጥ የሥራ አጥ መጠን (Unemployment) እንዳይስፋፋም ጉልህ ድርሻ ነበረው፡፡

የኢኮኖሚ መዋቅር ሊነድፉና ሊመሩ የሚችሉ ባለሙያዎችን ማሰባሰብ

የኢኮኖሚ መዋቅሮች ለመቅረፅና ለመተግበር ግንባር ቀደም ከነበሩት ሥራዎች ውስጥ፣ በአገሪቱና በውጭ የሚኖሩ ዕውቅ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ቦርድ የማቋቋም ሒደት ነው፡፡ ከእነዚህ አማካሪ ቦርድ አባላት ውስጥ ታዋቂ የነበሩ ከፍተኛ ኢኮኖሚስቶች፣ በኋላም የማዕከላዊ ባንኩ ገዥን የኢኮኖሚ አማካሪ እስከ መሆን ደርሰዋል፡፡ በኢኮኖሚ ላይ የባለሙያዎች አስተዋጽኦ የአንድን አገር የኢኮኖሚ ችግር ሊቀርፍ (ያውም በዘላቂነት) እንደሚችል የነበረው ልምድ ያሳያል፡፡ አውሮፕላን ባልሠለጠነ አብራሪ ሊዘወር እንደማይችል ሁሉ፣ የአገር ኢኮኖሚም በሳልና ልምድ ጠገብ በሆኑ የባላሙያዎች ዕገዛ ሊቸረው እንደሚገባ የእስራኤል ታሪክ ማሳያ ሆኖ አልፏል፡፡

ነፃና የተጠናከረ ማዕከላዊ ባንክ

የብዙ አገሮች የኢኮኖሚ ጥንካሬ ምንጭ የሆነው ጠንካራና ነፃ የሆነ ማዕከላዊ ባንክን መገንባት መሆኑ ይታወቃል፡፡ እስራኤልም አገር ከሆነችበት ከአምስት ዓመት በኋላ እ.ኤ.አ. በ1953 የማዕከላዊ ባንክ ሥራን የጀመረች ሲሆን፣ የእዚህን ተቋም ነፃነት በማክበር በኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ላይ ብቻ በገለልተኝነት እየተወሰነ እንዲሠራ ዕድሉ ተመቻችቷል፡፡ በመስኩም ጥሩ ዕውቀት ያላቸው አመራሮችንና ባለሙያዎችን በማቀፍ ከኢኮኖሚ መሻሻያ ጊዜዎች አልፎ ለውጡ መስመር እስኪይዝ፣ እንዲሁም እስካሁን ድረስ በኢኮኖሚ እንቅስቃሴው ላይ በበላይነት እጁን እያሳረፈ ቆይቷል፡፡ በዋጋ ንረቱም ጊዜ የወሰደው ብዙ ወሳኝ ጉዳዮች ቢኖሩም፣ እንደ ዋነኛ የሚጠቀሰው የወለድ ምጣኔን ካለው የዋጋ ንረት አንፃር ተመጣጣኝ በማድረግ እንዲጓዝ ቆራጥ ዕርምጃዎችን ሲወስድ ቆይቷል፡፡ ከገንዘብ ሥርዓትም ጋር ሆነ የፋይናንስ ጤንነትን ከማረጋገጥ አኳያ በነፃነት እንዲሠራ የተደረገ ሲሆን፣ ተመሳሳይ የኢኮኖሚ ችግሮች እንዲያጋጥሙም ኃላፊነት በመውሰድ እየሠራ ነው፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ አቋም በኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ላይ መኖር

በወቅቱ የእስራኤል የመንግሥት ምርጫ ውጤት በአገሮች ውስጥ ጉልህ ድርሻ የነበራቸው ሁለት ፓርቲዎች ሲሆን (Labor and Right Wing)፣ አገሪቱን  በተራ (Rotation) የማስተዳደር ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ነበር፡፡ የሺሞን ፔሬዝ መንግሥት የተሰጠው የሁለት ዓመት ጊዜ (Term) ሲሆን፣ ቀጣዩን ሁለት ዓመት በሌላኛው ፓርቲ እንዲመራ ቢደረግም፣ በሺሞን ፔሬዝ የተጀመረውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዕርምጃዎች በማስቀጠል ለውጡ እንዲጎለብት አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ በተለይ ለችግሩ ትልቅ ምንጭ ነው ተብሎ በሚታሰበው የበጀት ጉድለት ከመመጠን አንፃር የመንግሥት ወጪን የመቀነስ አካሄድ ላይ ሁለቱም ፓርቲዎች ተመሳሳይ ጥብቅ አቋም በመያዝ፣ የለውጥ ሒደቱ ቀጣይነት ላይ እኩል አሻራ ማኖር ተችሏል፡፡ ስለዚህም ምንም እንኳ በፖለቲካና በሌሎች ጉዳዮች ላይ የተለያየ አቋም በአገሪቱ የፖለቲካ ተቋማት ውስጥ ቢኖርም፣ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ላይ የጋራ አቋም ይዞ መቀጠል ለውጥን ሊያሳልጥ እንደሚችል ጥሩ ማሳያ ነበር፡፡

የአገሪቱን አቅምና የወደፊት የኢኮኖሚ አውታር መለየት

የኢኮኖሚ ማሻሻያው በአጭር ጊዜ ውስጥ የዋጋ ንረትን የመቀነስ ዓላማ ይዞ ቢነሳም፣ በረጅም ጊዜ ግን የኢኮኖሚውን አውራ የለውጥ ምንጭ በግልጽ ያስቀመጠም ነበር፡፡ በተለይ እስራኤል እንደ ዋነኛ የኢኮኖሚ ለውጥ ግብዓት አድርገው የወሰዱት በጣም የሠለጠነ የሰው ኃይል አቅም በሁሉም ሊባል በሚችል ዘርፍ (በተለይ ደግሞ በእርሻና በቴክኖሎጂ) አስተዋጽኦ እንደሚያደርግና ለወደፊትም የዕድገት ምንጭ እንደሚሆን ራዕይ ያለው የኢኮኖሚ ማሻሻያም አስቀምጠዋል፡፡ ዛሬ በእስራኤል የሚታየው የቴክኖሎጂ ዕድገት ምንጭ በዚህ ለችግር ጊዜ ተለይቶ የተቀመጠው የአገሪቱ ዕምቅ ሀብት የሆነውን የሰው ኃይል የማብቃትና የማሠራት አቅምን የመገንባት ሥራ ማከናወን ነው፡፡ ይህ የዕድገት ምንጭ ታዲያ የተተለመው ዛሬ ሳይሆን፣ የኢኮኖሚ ችግሮች በስፋት በተስተዋሉበት በእዚያ የችግር ወቅት በመሆኑ፣ የአንድ አገር የኢኮኖሚ ማሻሻያ ጊዜያዊ ችግሮችን ከመፍታት ባሻገር የወደፊት የዕድገት ምንጭ ራዕይን የመተለም አቅም ሊኖረው እንደሚገባ በግልጽ ያሳየ ነው፡፡

የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ቅቡልነትን ማስፈን

እ.ኤ.አ. ከ1987 የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች በፊት በነበሩ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ችግር ምክንያት፣ አብዛኛው የእስራኤል ማኅበረሰብ አዲሱ የኢኮኖሚ ዕርምጃ የተለመደና የሚፈለገውን ለውጥ ላያመጣ ይችላል የሚል ጥርጣሬ ነበረው፡፡ ነገር ግን ማኅበረሰቡን ሲያሳትፍ፣ ከተፅዕኖ ፈጣሪ ተቋማት ጋር ድርድር ሲካሄድ፣ በመጀመርያው ዙር በተወሰዱ ቆራጥ የማስተካከያ ዕርምጃዎች ምክንያት የዚህ ወቅት የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሥር ነቀል እንደነበር ባለድርሻዎች እንዲገነዘቡት የተደረገበት ነው፡፡ ይህም ቅቡልነትን ከማሳደግ ባለፈ ባለድርሻዎቹ በሕጋዊ መስመር የሚጓዙበትና ለውጡን እንዲደግፉም ያስቻለ ነው፡፡ በተለይ እንደ ዋጋ ንረት ያሉ የማኅበረሰቡን የወደፊት ትንበያ ውጤት (Expectation) ላይ የተመረኮዙ የኢኮኖሚ ችግሮች ማሻሻያ ዕርምጃዎች፣ ያለ ቅቡልነት ግባቸው ላይ እንደማይደርሱ ግልጽ ያደረገም ነበር፡፡ በዚህ ላይ ትልቁ ሥራ የወደፊት ትንበያ ማኔጅመንት (Expectation Management) ላይ ሰዎች የዋጋ ንረቱን ሊገታ የሚችልበትን ጭላንጭል ተስፋ በመስጠት፣ የዋጋ ግሽበት ዕርምጃና አቅጣጫ ወደ ላይ ሳይሆን ወደ መቀነስ እንደሚጓዝ ማሳየት ትልቅ የማሻሻያው ግብዓት እንደሆነም ነው፡፡

ከአጋር አገሮች ጋር አብሮ መሥራት

እስራኤል እንደ አገር ከተመሠረተችበት እ.ኤ.አ. ከ1948 ዓ.ም. ጀምሮ የቅርብ አጋር የነበረችው አሜሪካ የእስራኤልን ኢኮኖሚ በመደገፍ ረገድ ትልቅ ሚና ነበራት፡፡ በተለይ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሙ በተቀረፀበት ጊዜም ለኢኮኖሚ ለውጡ የሚውል ድጋፍ በገንዘብም ሆነ በማማከር ደረጃ የነበራት አስተዋጽኦ ጉልህ ነው፡፡ ይኼም ድጋፍ ከለውጡ በፊት እንደነበረው ቀጥታ ዕርዳታ ሳይሆን፣ በግልጽ በተቀመጠ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ተሞርኩዞ መሆን እንደሚገባው የሁለቱ አገሮች ስምምነት ስለነበረ፣ የኢኮኖሚ ማሻሻያው ከተደረገ በኋላም ወሳኝ የሆነ የዕርዳታና የብድር አቅርቦት በመለገስ የችግር ጊዜ ጓደኛና (A Friend in Need is a Friend Indeed) የቁርጥ ቀን አጋር አስፈላጊነት ማሳያም ነበረች፡፡ ስለዚህም አገሮች በኢኮኖሚ ችግር ውስጥ በሚሆኑበት ጊዜ በራስ ተነሳሽነት የሚደረግ ለውጥ ወሳኝ ምዕራፍ ቢሆንም፣ የቅርብ አጋር አስፈላጊ እንደሆነ ትልቅ ማሳያ ነው፡፡

እንዚህ ከላይ የጠቀስኳቸው መሠረታዊና የኢኮኖሚ ማሻሻያን ለመቅረፅና መሬት ለማውረድ አስፈላጊ ግብዓቶች ሲሆኑ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ቀጥታ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዕርምጃዎች ጥራትና አተገባበር ለለውጡ መሳካት ሁነኛ መሣሪያዎች ናቸው፡፡ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዕርምጃዎችን በጥቅል ስናይ የሚከተሉትን ያካትታሉ፡፡

የበጀት ጉድለትን መቆጣጠር

ለእስራኤል የዋጋ ንረት አንዳንድ መነሻ ምክንያት ሲጠቀስ የነበረውን የመንግሥት የበጀት ጉድለት መስፋት ሲሆን፣ መንግሥት ይኼንን ጉድለት ለመሙላት ከአገርና ከውጭ ያለው የብድር ተጋላጭነት መጠን በጣም የጎላ ነበር፡፡ በተለይ በአገር ውስጥ ያለው የብድር ተጋላጭነት መጠን ከአገሪቱ ምርት አንፃር ሲታይ፣ ተጨማሪ ብድርን መውሰድ የማይቻልበት እንዲያውም ብድሩን ለመክፈል የውጭ ምንዛሪን ለመሸጥም የተገደደበት ነበር፡፡ ይህም የውጭ ምንዛሪ ክምችቱን ከመሸርሸሩም በላይ፣ ለዋጋ ንረትና ለካፒታል ሽሽት (Capital Flight) ያጋለጠ ነበር፡፡ ስለዚህ የእስራኤል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትልቅ ትኩረት የተስተካከለ የበጀት ሁኔታ (Balanced Budget) የመፍጠር ሲሆን፣ የበጀት ጉድለት መጠኑ ከ17 በመቶ ወደ ስምንት በመቶ የአገር ምርት አንፃር በመገደብ ለማስተካከል ተሞክሯል፡፡ እነዚህም በሁለቱም የበጀት ሥሌቶች ማለትም ከገቢና ከወጪ አንፃር ያለውን በማሻሻል ላይ የተመረኮዙ ናቸው፡፡ አብዛኛው የሚያተኩረው የመንግሥት የግብር ገቢ ከማሳደግ አንፃር ሲሆን፣ ሌላኛው የመንግሥት ወጪዎችን በመቀነስና ለሕዝብ ድጋፍ (Subsidy) የሚውሉትን በማንሳት ጭምርም ነው፡፡ ይኼም ማስተካከያ የሁለት ዕርምጃዎች ውጤት መሆኑና የመንግሥት በጀት ጉድለት የተስተካከለና ኢኮኖሚው ሊሸከመው በሚችለው መጠን መሆን እንደሚገባው ማረጋገጫ ነው፡፡ በተለይ ገቢ ከቀረጥ ከሚሰበሰብ ምንጭ የመሰብሰብ ሒደት በዋጋ ንረት ምክንያት የተቀነሰ ቢሆንም፣ በተመሳሳይ ቀረጥን የሚሰበስብበት ሥርዓትን ስኬታማና ወጪ ቆጣቢ በማድረግ የተጣራ ገቢ መጠንን ለማሳደግ መቻሉም አስደናቂ ነው፡፡ የመንግሥት ኢንቨስትመንትንም በመቆጣጠርና መጠኑን በመቀነስ የንግድ  ጉድለት (Import Surplus) ለማጥበብም ተችሏል፡፡ ይህም በኢኮኖሚው ዕድገት ላይ የራሱ አሉታዊ አስተዋጽኦ ቢኖረውም የበጀት ጉድለትን ከማስተካከል አንፃር ግን  አዎንታዊ ነበር፡፡

የጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ መተግበር

ሚልተን ፍሬድማን እንደሚለው “Inflation is always and everywhere a monetary phenomenon”፡፡ ስለዚህም የዋጋ ንረት መነሻዎች በኢኮኖሚው ውስጥ በስፋት ከገንዘብ ፍሰት መጨመር ጋር የተያያዙ በመሆናቸው የእስራኤል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዕርምጃዎች ጥብቅ የሆነ የገንዘብ ፖሊሲዎችንንም ሲተገብር ቆይቷል፡፡ የዚህም የፖሊሲ አካሄድ የገንዘብ ፍሰቱን በተለይ “M3” (M2+Large Time Deposit in Bank) በመቆጣጠርና የገንዘብ ዋጋን (Interest Rate) ከተለመደው የዋጋ መጠን ጋር እንዲሄድ በማድረግ የተከናወነ ሲሆን፣ የብድር ፍሰትን በብድር የዋጋ ተመንን ከፍ በማድረግ እንዲያድግ በመፍቀድ ሲካሄድም ነበር፡፡ ይኼም የዋጋ ንረትና የገንዘብን የዋጋ (Normal Interest) ጥምረት አብረው እንዲሄዱም ያደረገም ነበር (Fisherin Correlation)፡፡ በተጨማሪም የገንዘብ ፍልሰትን (Capital Flight) በመቆጣጠር የገንዘብ ክምችት መጠን ሳይዛባ ለማካሄድ ጥረት ተደርጓል፡፡

የውጭ ምንዛሪ ፖሊሲ

በዚህ ረገድ የውጭ ምንዛሪ ተመኑን ከአሜሪካን ዶላር ጋር በማጣመርና (Pegged) ቋሚ እንዲሆን በማድረግ የተከናወነ ሲሆን፣ በኢኮኖሚ ማሻሻያው መጀመርያም የዶላር የወደፊት መዳከምን በመተንበይ የአንድ ጊዜ የአገር ውስጥ ገንዘብ ከዶላር ጋር በ16 በመቶ እንዲዳከም ያደረገም ነው፡፡ ይኼም የዋጋ ንረቱን የጨመረ ቢሆንም፣ በቀጣይ ጊዜያት የውጭ ምንዛሪ ተመኑን እንብዛም ሳይለወጥ እንዲቀጥል ተደርጓል፡፡ ቀስ በቀስ የአገር ውስጥ ገንዘብን ከዶላር አንፃር የማውረድን ሒደት (Crawling Devaluation) ማሻሻያው ያልደገፈው ሲሆን፣ ይኼም በገንዘብ ግሽበት ምክንያት የሚመጣን የዋጋ ንረት ዕውቅናን ለማስቀረትም የታሰበ ነው፡፡

ደመወዝና የሸቀጥ አገልግሎት ዋጋን እንዳይለወጥ ማድረግ

ከሠራተኛ ማኅበራትና ከተፅዕኖ ፈጣሪ ድርጅቶች ጋር በተደረገው ድርድር ምክንያት፣ የደመወዝ ዋጋ (Wage) እና ወደ 90 በመቶ በሚሆኑት የሸማቾች ቅርጫት ላይ በሚገኙ ዕቃዎች ላይ ዋጋን የመተመንና እንዳይለወጥ (Freeze) የማድረግ ሒደትም ተፈጽሟል፡፡ ይኼም ትክክለኛውን የደመወዝ ክፍያ (Real Wage) ዝቅ ያደረገና እስራኤል ከኢኮኖሚ ማሻሻያው በፊት ትጠቀምበት የነበረውን ዋጋን ከዋጋ ንረቱ ጋር ማስተሳሰር (Indexation) በማስቀረት፣ የዋጋ ለውጡ አካሄድም በገበያው እንዳይወሰን በማድረግ የተተገበረ ነበር፡፡

የቀረጥ ማሻሻያ

መንግሥት በሁለት የቀረጥ ዓይነቶች ላይ የግል የገቢ ግብርና የድርጅቶች ዓመታዊ ግብር ላይ የማሻሻያ አዋጆችንም ተግባራዊ አድርጓል፡፡ በተለይ የግብር መጠንንና የዋጋ ንረት መጠንን ከግምት ውስጥ በማስገባት እንዲከናወን የተደረገ ሲሆን፣ ይኼም የመንግሥት ግብርን የመቀነስ ውጤት ቢኖረውም የድርጅትና የግል ምርታማነት ላይ ተፅዕኖ እንዳያመጣ ማሻሻያዎች እንዲቀጥሉ አዎንታዊ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

በመንግሥት የተያዙ ድርጅቶችን ወደ ግል የማዞርና የሞኖፖል ባህሪዎችን ማስተካከል

የግሉ ዘርፍ ለኢኮኖሚ ማሻሻያው የሚኖረውን ድርሻ ከማጠናከር አንፃር፣ በመንግሥት የተያዙ የንግድ ተቋማትን ወደ ግል የማዞር ሥራዎችንም በሒደት የመፈጸም አካሄድ ነበረ፡፡ በተጨማሪም የሞኖፖል ባህሪ ያላቸው የንግድ ዘርፎችን በመለየት በረዥም ጊዜ ዕቅድ ይኼ ባህሪ እንዲቀንስ፣ ወይም እንዲጠፋ የማድረግ ዕቅድም የማሻሻያው ዓበይት ጉዳይ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ የሞኖፖል ባህሪ የዋጋ ትመና ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ዕውቅና የሰጠ የፖሊሲ ማሻሻያ መሆኑም አስተማሪ የሚሆን ነው፡፡

የአገራችን የኢኮኖሚ ሁኔታ በጥቅሉ

የአራችን የዋጋ ንረት መጠን የሁለት አኃዝ (25 በመቶ) መጠን ያለው ሲሆን፣ ይህም በተከታታይ የዓመቱን ሙሉ ሳይወርድ የቀጠለ ነው፡፡ የገንዘብ ዋጋ መጠን በተቀማጭ ሒሳብና በብድር ረገድ ከዚያም በታች ሲሆን፣ የገንዘብ ፍሰት መለኪያዎችም (M1፣ M2፣ M3) ከአገር ውስጥ ምርት ዕድገት በላይ እየጨመሩ ይታያሉ፡፡ የመንግሥት የበጀት ጉድለት መጠን ከአገራዊ ምርት አንፃር እስራኤል ችግር ውስጥ ከነበረችበት ወቅት በላይ በመሆን፣ ጥንቃቄ የሚፈለግበት ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

እያደገ ያለውን የዋጋ ንረት ለመግታት ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ማረጋጊያ ፕሮግራም ያስፈልጋል - የእስራኤል ልምድ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተርእያደገ ያለውን የዋጋ ንረት ለመግታት ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ማረጋጊያ ፕሮግራም ያስፈልጋል - የእስራኤል ልምድ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

የውጭ ምንዛሪ ዋጋ መጠን ቀስ በቀስ (Crawling) እየጨመረ የብር ዋጋን እያወረደው ይገኛል፡፡ ይኼም እስራኤል ስትከተለው ከነበረው ፖሊሲ የተቃረነ አካሄድንም ያመለክታል፡፡ የንግድ ሚዛኑም ባጠቃላይ ወደ ኢምፖርት (Import Surplus) ያደላና መስተካከልን የሚጠይቅ ነው፡፡ የመንግሥት የዕዳ መጠንም ካለው የበጀት ጉድለት ምክንያት ጭማሪን ከዓመት ዓመት እያስተናገደ በመሄድ ላይ ነው፡፡

እያደገ ያለውን የዋጋ ንረት ለመግታት ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ማረጋጊያ ፕሮግራም ያስፈልጋል - የእስራኤል ልምድ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተርእያደገ ያለውን የዋጋ ንረት ለመግታት ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ማረጋጊያ ፕሮግራም ያስፈልጋል - የእስራኤል ልምድ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

በአጠቃላይ የዋጋ ንረትን ሊያባብሱ የሚችሉ የኢኮኖሚ መለኪያዎችን በኢኮኖሚያችን ውስጥ ታጭቀው ይታያሉ፡፡ ስለዚህም ለውጡ የአንድ ሰሞን ዕርምት ሳይሆን፣ እንደ እስራኤል ቀጣይና ዘርፈ ብዙ ሊሆን እንደሚገባ ሊሰመርበት ይገባል፡፡

ማጠቃለያ

የእስራኤል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም በዓለም ላይ ከሚነሱ በጣም ውጤታማ አካሄዶች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች የተለመዱ (Orthodox) የፖሊሲ ዕርምጃዎችንና ያልተለመዱ (Heterodox) ያካተተ ሲሆን፣ በውጤቱም በተለይ የዋጋ ንረትን ከነበረበት 400 በመቶ በላይ ወደ 20 በመቶ በመቀነስ፣ እንዲሁም ለረጅም ጊዜ ይኼ ሁኔታ እንዳይደገም ወደ አንድ ዲጂት በማውረድ ሥር ነቀል  አካሄድና ሥርዓትን ያሰፈነ ነው፡፡ ማሻሻያው የወሰዳቸው ዕርምጃዎች የዋጋ ንረትን ከመቀነስም በላይ፣ የሥራ አጥንት መጠንና (Unemployment Rate) በኢኮኖሚው ዕድገት ላይ የነበረው ጉዳት እምብዛም ያልነበረ በመሆኑም የተለየ እንደነበረም ይወሳል፡፡ ከቀጥታ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችም በላይ መሠረታዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያን ሊያመጡ የሚችሉ ግብዓቶችም በግልጽ የተቀመጡና ተመሳሳይ ችግር ያለባቸው አገሮች ዘላቂ መፍትሔን የሚፈልጉ ከሆነ፣ በአገራቸው የኢኮኖሚ መስክ ሊተገብሯቸው እንደሚገባም የሚያሳይ ነው፡፡

እነዚህም የመሪዎች ቁርጠኝነት፣ የማኅበረሰብ ድጋፍ፣ ከተፅዕኖ ፈጣሪ ተቋማት ጋር መደራደር፣ ኢኮኖሚን ባለሙያ መምራት፣ ነፃና ጠንካራ ማዕከላዊ ባንክ ማዋቀር፣ የኢኮኖሚ ማሻሻያን በፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ምክንያት አለመሸርሸር፣ የአገርን ዕምቅ አቅም የመፈተሽና የሚመጥን ራዕይ ማስቀመጥንና ቅቡልነትን ማስፈን በጣም ወሳኝ እንደሆኑ ያስተምራሉ፡፡

በሌላ በኩል ቀጥታ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ሲነደፉ የችግሮቹን መንስዔዎች በማገናዘብ ሥር ነቀል ለውጥ ማምጣት በሚያስችል አካሄድ መተግበሩም ጠቃሚ ነው፡፡ በተለይ ለኢኮኖሚ ስብራት መጠገኛዎች የመንግሥት ድርሻ ጉልህ እንደሚሆንና አንዳንዴም በገበያ መርህ ብቻ ከሚናገሩ የለውጥ ዕርምጃዎች ወጣ ብሎ ለችግሮቹ መፍትሔ በሚሆኑ፣ የዕርምት ዕርምጃዎች ላይ መንግሥትን ተሳታፊ ማድረግንም የሚጠይቅ ነው፡፡

በተመሳሳይ በአገራችን አሁን ያለው የዋጋ ንረት መጠን እስራኤል ከነበረችበት ሁኔታ አንፃር ሲታይ ገና ቢሆንም፣ ወደፊት በተመሳሳይ መንገድ እንዳይዘልቅ ከወዲሁ የዕርምት ዕርምጃዎችንና የመሠረታዊ የኢኮኖሚ ተቋማትን የመገንባት ሥራ ትልቅ ትኩረት ያሻዋል፡፡ በሌላ በኩል ችግር መኖር (ለምሳሌ ጦርነት) ለኢኮኖሚ ዝቅጠት ድርሻ ቢኖረውም፣ መፍትሔ አልባ እንዳልሆነ የእስራኤል ልምድ አስተማሪም ነው፡፡ ዋጋን የሚጨምሩ የኢኮኖሚ ኩነቶች ላይ ዕርምጃ የመወሰዱ አካሄድ በቁንፅል ሳይሆን፣ በስፋት መተግበሩም ጠቃሚ እንደሆነ የእስራኤል ልምድ በደንብ አሳይቷል፡፡ ለምሳሌ በቤት ኪራይ ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ ክልከላ በሌሎች የዋጋ ንረት ያለባቸው የኢኮኖሚ ቅንጣቶች ላይም መተግበሩን መታየት አለበት፡፡ የውጭ ምንዛሪ ዋጋን ቀስ በቀስ (Crawling) ሆነ በአንድ ጊዜ (Devaluation) የማውረድ አካሄድም፣ በዋጋ ንረት ላይ ቀጥታ ድርሻ እንደሚኖረው የበፊት የእስራኤል ልምዶችም ሆኑ የአሁኑ የአገራችን አካሄድ የሚያሳይ በመሆኑ፣ በጥንቃቄ ሊታይም ይገባዋል፡፡

የመንግሥት የበጀት ጉድለት መጠንም መቆጣጠርና በኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን የገንዘብ ፍሰት ከአገራዊ ምርት ዕድገት አንፃር የመቃኘት ጉዳይም ሊታሰብበት የሚገባ ነው፡፡ አሁን ያለው የበጀት ጉድለትም ሆነ የገንዘብ ፍሰት ከአገር ውስጥ ምርት አንፃር በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ መሆን የእስራኤልን ልምድ ለአገራችን ጠቃሚ ያደርገዋል፡፡

የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መጠንም ሆነ የብድር የዋጋ ተመን ከዜሮ በታች (Negative) ሆኖ ለብዙ ጊዜ የታየ፣ ነገር ግን ማሻሻያ ያልተቸረውና ከኢኮኖሚክስ ደንቡም የራቁ በመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የገንዘብ ፖሊሲ ጠንካራ ነው ለማለትም አያስደፍርም፡፡ ከቀረጥ ግብር ጋር የተገናኙ ማሻሻያዎችም የዋጋ ንረትን ከግምት ውስጥ ያስገቡ መሆናቸውም፣ ወደፊት ምርታማነትን በመጨመር የዋጋ ግሽበትን ለመከላከል የሚጠቅሙ ናቸው፡፡ የሞኖፖል ባህሪ ያላቸው የመንግሥትም ሆኑ የግል የንግድ (ኢንዱስትሪ) ዘርፎችን በመለየት ማሻሻያ ማድረግ፣ ዋጋን እንዳሻ የመጨመርና የኢኮኖሚ አሻጥር (Sabotage) መፍጠርን የሚከላከል በመሆኑ፣ ይኼን የማረም አካሄድ የረጅም ጊዜ ዕቅድ ሆኖ ሊያዝም ይገባል፡፡

ተጨማሪ ቻርቶች

እያደገ ያለውን የዋጋ ንረት ለመግታት ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ማረጋጊያ ፕሮግራም ያስፈልጋል - የእስራኤል ልምድ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተርእያደገ ያለውን የዋጋ ንረት ለመግታት ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ማረጋጊያ ፕሮግራም ያስፈልጋል - የእስራኤል ልምድ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

እያደገ ያለውን የዋጋ ንረት ለመግታት ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ማረጋጊያ ፕሮግራም ያስፈልጋል - የእስራኤል ልምድ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተርእያደገ ያለውን የዋጋ ንረት ለመግታት ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ማረጋጊያ ፕሮግራም ያስፈልጋል - የእስራኤል ልምድ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...