Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ተሟገትየዴሞክራሲያዊነት ልምላሜ ለፖለቲካችን ሥልጡንነት

የዴሞክራሲያዊነት ልምላሜ ለፖለቲካችን ሥልጡንነት

ቀን:

በበቀለ ሹሜ

  1. መግቢያ

ከቅርብ ጊዜ በፊት የሲቪል ማኅበራት/ማኅበረሰብ ለዴሞክራሲ ስላላቸው ፋይዳ በ‹‹ሀበጋር›› ክርክር ሲደረግ ተከታትዬ ነበር፡፡ ከተከራካሪዎቹ አንዱ ትናንትንም፣ ዛሬም በአገራችን ውስጥ የጌታና የሎሌ ግንኙነት ነው ያለው… ዴሞክራሲ የለም … ሲቪል ማኅበረሰብ  የሚባለውም የጌታና የሎሌ ግንኙነት ነው… ዜጋም የለም… ቆንጆዎቹ ገና አልተወለዱም ሲል ስሰማ ሰውዬው የተናገረው ብዙው ነገር እውነት መሆኑን እያወቅሁ ሰውዬው ምን ነክቶታል የሚል ስሜት ነበር የደወለብኝ፡፡ በሰውዬው የሐሳብ መንገድ ከተሄደ ሙግታችን ማቆሚያ የለውም፡፡ ‹‹ቆንጆዎቹ ገና አልተወለዱም›› ያለው ሰውዬም ሆነ፣ ብዙ ጊዜ ስለሰው ሐርነት (ኢማኒሲፔሽን) የምናወራ ሰዎች በአኗኗርም፣ በአስተሳሰብም በጌታና በሎሌ ድሮች የተተበተብን እንደሆንን ተንትኖ ማሳየት ይቻላል፡፡ ነፃ ሰው አለ ወይ የሚለውን ጥያቄ ከቤታችን አልፈን በዓለም ደረጃም ልናነሳ እንችላለን፡፡

ከምዕራባዊ ትርዒቶች እጅግ ከምወዳቸው ትርዒቶች ውስጥ ሁለቱ ‹‹የማስተር ሼፍ›› ውድድሮችና ‹‹ኢምፕራክቲካል ጆከርስ›› የተሰኙት ናቸው፡፡ እነዚህና እነዚህን መሰል ትርዒቶች የሚጥሙኝ ምዕራብ አገር/አሜሪካ ሳልሄድ የምዕራባውያንን ሥነ ልቦና ቅርድድ፣ ጉልጉል አድርጎ ለማየት የሚያስችሉኝ በምሥል የሚነበቡ መጻሕፍት ስለሆኑ ነው፡፡ ‹‹ኢምፕራክቲካል ጆከርስ›› ውስጥ በአሜሪካ ኅብረተሰብ ውስጥ እስያ-መጥ ሰዎች፣ ጥቁሮች፣ ልዩ ልዩ የትውልድ አመጣጥ ያላቸው ነጮች እንዴት ያለ የሥነ ልቦና ጓዳ እንዳላቸው፣ የምር መሳዮቹ የቀልደኞቹ ትንኮሳዎች የሚሰጧቸው ምላሾች በግለሰባዊ ልዩነት ብቻ የማይገለጹ ስለመሆናቸውና ቀልደኞቹ ራሳቸው የተለያየ ማኅበራዊ ዳራ ስላላቸው፣ ሰዎች እንዴት ያሉ ግምቶች እንዳሏቸው ሁሉ እያነበቡ ዕውቀት መኮምኮም ይቻላል፡፡ ‹‹የማስተር ሼፍ›› ዓይነት ውድድሮችን (በልጆችና በአዋቂ ደረጃ የሚካሄዱትን) እያየ የሚያነብ ሰው፣ በእኛና በእነሱ መሀል ያለው የሥነ ምግባር ልዩነት ምን ያህል እንደሆነ፣ በየኑሮ ትግላቸው ውስጥ ምን ያህል መተሳሰብ፣ ርኅራኄና  ሻርካዊ ጥርስ እንዳለ፣ ‹‹ሥልጡኑ›› መጠላለፍ ከቶ እንደማያሳፍር፣ ልጆች በዚህ ዓይነት የግብግብ ኑሮ አሸናፊ ሆነው እንዲወጡ በምን ዓይነት የጩልፋትነት ሥልቶች እንደሚቀረፁ ወለል አድርገው ያሳያሉ፡፡ እነዚህን መሰል የትንቅንቅ አስተሳሰቦች ይዘን የሰው ልጅ በዓለም የብልፅግና ግስጋሴ ጉዞ ውስጥ ምን ያህል ሥልጡንነትንና ነፃነትን ተቋድሷል ብለን መጠየቅ እንችላለን፡፡ ሀብት ተከመረም አልተከመረም ሰው ገና ነፃ አልሆነም እስከ ማለት መሽቀንጠርም ይቻላል፡፡ በዛሬው ዓለም ውስጥ ዴሞክራሲ የለም ካላልን በቀር፣ ዛሬ በሚታየው የዴሞክራሲ (የባለመብትነት) ቅርፊት ውስጥ የጌታና የሎሌ መስተጋብር እንዳለ ማየትም አይከብድም፡፡ በአጭሩ አንዱ ባለበት ሌላው አይገኝም በማለት ዴሞክራሲን፣ ጌታና ሎሌነትንም ሆነ ጩልፋትንነትና ለሰው መራራትን አይደራረሴ ማድረግ አይቻለንም፡፡ እዚያ ውስጥ ገብቶ መብከንከን ወይም ሰው በአጠቃላይ እንደምን ሙሉ ነፃነቱን ይቀዳጃል ብሎ በሐሳብ መማሰን ወይም የሰውን ሥልጣኔ በመናኝ ዘይቤ መናቅ ለእኔና ለኢትዮጵያውያን ተንሳፍፎ መሞላቀቅ ነው፡፡

- Advertisement -

የኢትዮጵያ ወገኖቼን ኑሮ በሚያነሳ ተግባር ውስጥ ጠጠር ላዋጣ የሚል ኢትዮጵያዊ መብሰልሰልና መተለም ያለበት፣ በኢትዮጵያ እውነታ ውስጥ ሆኖ፣ ኢትዮጵያ ባላት ዕውናዊ የመንደርደርና የመስፈንጠር ቁመት ልክ ተመጥኖ እየመጠነ ነው፡፡ 2014 ዓ.ም. መስከረምን ይዞ በአሸናፊው ፓርቲና በተፎካካሪዎቹ የተባበረ ትግል የኢትዮጵያን ኅብረተሰብ የማንሳት ርብርብ እንደሚሞቅ እንጠብቃለን፡፡ ርብርቡ እንደምንጠብቀው የኢትዮጵያን ትኩስና ብስል የአዕምሮ፣ የፈጠራና የትጋት አቅሞችን አነቃንቆ መላ ኅብረተሰቡን የሚያስስ ይሆናል? ወይስ እንደተለመደው ሞቅ ሞቁ ወረቱን ጨርሶ ከላይ እስከ ታች ባለ የሥልጣን አውታር ውስጥ ስናየው የኖርነው ማግሳት፣ መቅለጥለጥና መንዘራጠጥ ይሰተር ይሆን? አንገብጋቢ ከሆኑ የኑሮ ጉዳዮቻችን ውስጥ፣ ነባራዊና ህሊናዊ አፈርና ውኃ የለማላቸውን ለይቶ ተግባራዊ ሕይወት የመስጠት፣ ሁኔታዎች ገና ኮረኮንች የሆኑባቸውን አዘግይቶ የማልማት፣ ገና ትክክለኛና የጠራ ግንዛቤ ያላገኙ ጉዳዮችን በምርምርና በውይይት የማብሰልና የማሰናዳት ዕውናዊ አቃጅነት ምን ያህል እየተዋጣልን ነው? እነዚህ ሁሉ በአገራችን እውነታ ወርድና ቁመት ልክ የሚያሳስቡ ፈታኝ ጥያቄዎች ናቸው፡፡

በፖለቲካ መልክዓ ምድራችን ውስጥ የኅብረተሰብ ማኅፀናችን፣ ምን ያህል በዕድገት ደረጃችን ልክ ሕይወት ልንሰጣቸውና የግስጋሴ ዒላማ ልናደርጋቸው የምንችላቸውን ነገሮች ማሳየትና መቀመር የሚችሉ የፖለቲካ አዕምሮዎችን አፍርቷል? ከዚህ አኳያ ፖለቲከኞቻችን ምን ያህል ሕዝብ-ገብ ዕትብት አዳብረዋል? የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ብዙ አነጋጋሪ ነው፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሕዝብ ያለው የፖለቲካ ኑሮ ከገዥ (መንግሥታዊ) ፖለቲካ ጋር የተያየዘ ሆኖ ቆይቷል፡፡ የአፄው ዘመን ገዥነትም ሆነ የደርግና የሕወሓት/ኢሕአዴግ አገዛዞች በጥቅል ባህርያቸው አፋኝና አስደግዳጊ እንደ መሆናቸው፣ ሕዝቡ ኑሮን ለማቅለልና ጉዳዩን ለመተኮስ ሲሠራበት የቆየው ‹‹ፖለቲካ›› እንደ ሥርዓቱ ሰበዝና አለላ ለወጥ ይበል እንጂ ስፌቱ ያው ነበር፣ ‹‹እሾህን በእሾህ›› የሚባል፡፡ እነ ዳጃዝማችና ባላንባራስን፣ የኢሠፓ ጓዶችን፣ የሕወሓት/ኢሕአዴግ ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራቶችን›› ደጅ ሲጠና ውጤታማ የሚሆንበትን የየሥርዓቱን ስብከት አስተውሎ ነው፡፡ የ‹እሾህን በእሾህ› ዘዴው ባለብዙ ጅማት ነው፣ የወንዝ ልጅነት ቅርበትን፣ የሥልጣን ቅርበትን፣ የፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ቅርበትን፣ የሥጋና የጋብቻ ዝምድና መንገዶችን ሁሉ የሚጠቀም ነው፡፡ በዚያ ውስጥ እጅ መንሻና የገንዘብ ጉርሻ አለ፡፡ ሥርዓቱ ሕዝብን የሚሸነግልበት ስብከትም ተመልሶ ለ‹እሾህን በእሾህ› ትግል ይሠራበታል፡፡ የቅርብ ምሳሌ ለማስታወስ የሕወሓት/ኢሕአዴግ አገዛዝ ‹‹ሕዝባዊ/የሕዝብ ወገንተኛ ነኝ››፣ ‹‹ልማታዊ ነኝ›› የሚል ፕሮፓጋንዳ ያለው መሆኑን በመመርኮዝ ባለአቤቱታዎች፣ ‹‹መንግሥታችን ለሕዝብ እንደቆመ ለሕዝብ እንደሚሠራ እናውቃለን፡፡ መንግሥታችንን እንድናማርር የሚያደርጉን…›› እያሉ የሽንገላ ጉቦም ሲሰጡ እንደኖሩ ይታወቃል፡፡ በዘመነ አፄና በደርግ ጊዜም እንዴት ያለ የውዳሴ ጉቦ ይሰጥ እንደነበር በጊዜው ከነበሩ ልብ ወለዶች ብዙ መቅሰም ይቻላል፡፡ ዛሬስ የዚህ ዓይነት ግንኙነት ምን ያህል ተለውጧል? ሕዝብ ምን ያህል ለፖለቲከኞች ልቡን ሰጥቷል? ይህ ጥያቄ በሌላ ፊቱ ሲታይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምን ያህል የሕዝብ ልብ ውስጥ ገብተዋል የሚል ፈርጅ አለው፡፡ በዚህ በኩል የአሁኑ የ2013 ምርጫ ብዙ ይናገራል፡፡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በአጠቃላይ የምርጫ ዘመቻ ቅስቀሳና ክርክራቸው፣ የኢትዮጵያን እውነታ እያፍረጠረጡ የማይታለፉና መደብዘዝ የማይገባቸውን ተግባሮች ወለል አድርጎ በሚያሳይ ትንታኔ ሕዝብን አገልግለዋል? ዛሬ የሚብስበትን ከማይብስበት/ ተቀዳሚውን ከተከታዩ ሕዝብ እንዲለይ ለፍተዋል? የሕዝብ ድምፅ ለማግኘት ሲፎካከሩ የነበሩት በጥያቄ መልክ የቀረቡትን ኃላፊነቶች በመወጣት ተግባር ላይ ነበር ብሎ በሙሉ አፍ መናገር አይቻልም፡፡

ብዙ የፖለቲካ ቡድኖች ይህንን ተግባር ዳሰስ ከማድረግና ሲባሉ የቆዩ ዕቅዶችን ከመደርደር ባሻገር፣ የሕዝብን አንጀት ሊበሉ የሞከሩባቸው ሰበዞች ሌሎች ናቸው፡፡ ደርግ ጭቁንነትን እያባዘተ ነግዷል፡፡ ራሱን የጭቁኖች ጠበቃ አድርጓል፡፡ ሕወሓት/ኢሕአዴግም በብሔረሰቦች እኩልነትና ነፃነት ነግዷል፡፡ የአሁኖቹ ፖለቲከኞች በብሶት፣ በቁስል፣ በኩራት፣ በምኞትና በአፍቅሮት በኩል ገብተው ድምፅ በድምፅ ለመሆን ሲሠሩ ዓይተናል፡፡ ሕዝብን ለመሳብ የጣሩት በምርጫ የተሳተፉት ብቻ አልነበሩም፡፡ ምርጫውን ያኮረፉም የእነሱን አባላት እስራት ‹‹የብሔር ጉስቁልና›› አድርጎ በማቅረብ ኩርፊያቸው የሕዝብ እንዲሆን ጥረዋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁኔታዎችን በደንብ እያበራዩ ተግባሮችን ፈትገው በማውጣት ፉክክር፣ ሕዝብ ‹‹ትክክለኛ›› ምርጫ እንዲያደርግ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ባይወጡም፣ ሕዝብ ከሞላ ጎደል በኩራቱ፣ በአገር ወዳድነት ቅርሱና በእናት ፍቅሩ ስለመጡበት አልቄለም፡፡ ብሶትና ጉጉት ስለታሰሰ በስሜት አልሰገረም፡፡ ምርጫውን አኩርፍ ብለው ውስጥ ለውስጥ ስለቀሰቀሱትና ስላስፈራሩትም አልተረታላቸውም፡፡ ሁላችንንም በፖለቲካ ትርዒታችን ሕዝብ ይመዝነናል፣ በአንዳንዱ ይታዘበናል፣ በአንዳንዱም በልቡ ይጽፈናል፡፡ ይህንን እያደረገም ልምዱንና መሠረታዊ የህልውና ጥቅሞቹን ዋና መሥፈርት አድርጎ፣ አሁን ስላለበት አደገኛ ሁኔታ ድምፅ የለሽ የፖለቲካ ትንታኔና የፖለቲካ ሒሳብ ሠራ፡፡ አጠቃላይ የድምፅ ውጤቱ ይህንን የሚናገር ነው ቢባል ስህተት አይሆንም፡፡

ወደፊትስ የፖለቲካ ልሂቃኑና የሕዝብ ግንኙነት እንደተፈናከረ ቀጥሎ ‹‹የኢትዮጵያ ፖለቲካ በሁለት ይከፈላል፣ የልሂቃን ፖለቲካና የተሬ ሕዝብ የዝምታ ፖለቲካ›› እያልን ልናወራ ነው? ይህንን በማለቴ ሦስተኛ የፖለቲካ ረድፍ (የማኅበራዊ ሚዲያ ረድፍ) መኖሩን እንደሳትኩ የሚሰማቸው ይኖሩ ይሆናል፡፡ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ ከፍተውና በማኅበራዊ ሚዲያ የሚደፋላቸውን ግሳንግስ እያሻመዱ ያልገባቸውንና ያልመረመሩትን የሚፈተፍቱ እንደ ጠንቋይም፣ እንደ ነብይም፣ እንደ መንግሥት መሪም፣ እንደ ፖለቲካ መሪም፣ እንደ ወታደራዊ ዕቅድ አውጪ፣ እንደ አዋጊና ተዋጊ ሁሉ መሆን ‹‹የሚቻላቸው›› (አላውቅም ማለት ሞታቸው የሆነ) የፖለቲካ መኃይማን አዎ በገፍ አሉ፡፡ የእነዚህ መኃይማን የስብጥር ስፋትም አስደንጋጭ ነው፡፡ ሁለተኛ ደረጃን ማጋመስ እንኳ ካቃታቸው አንስቶ ጋሻ የሚያካክሉ ዲግሪዎች እስከተሸከሙ ሰዎች ድረስ ያሉበት ነው፡፡ የደረጃ መበላለጥ ካልሆነ በቀር የሚጋሯቸው ባህርያትም የሚያስገርሙ ናቸው፡፡ ‹‹በኢትዮጵያዊነታችን የምንኮራ ኢትዮጵያዊ ነን›› እያሉ ለኢትዮጵያ መሥራትና ኢትዮጵያን መውጋት ምንና ምን እንደሆነ የማውያቁ፣ እንከንን በማሳየትና ሐሳብ በማዋጣት አገርን መጥቀምና ለጠላት ወሬ አቀባይ/የፕሮፓጋንዳና የከፋፋይነት ሥራ አካሂያጅ መሆን ምንና ምን እንደሆኑ የማያውቁና ማወቅም የማይፈልጉ፣ የተረጋጋ የኑሮ ጊዜን ከቀውጢ/የርብርብ ጊዜ ለይተው አድራጎታቸውን የማይገሩ፣ እንዲገሩም የሚመራቸው የኃላፊነት ስሜትና ዓላማ የሌላቸው፣ መቼውንም ጥርጣሬ፣ ሐሜት፣ ነቀፋ፣ ማመስኳትና መፈትፈት የአዋቂነት ማሳያቸው፣ የሱስ እርካታቸው የሆነ ሰዎች ናቸው፡፡ እነዚህ የማኅበራዊ ሚዲያ አንቃራሪዎች አገር ላይ ጉዳት የሚያደርሱ የሱስ ጉዳተኞች እንጂ ፖለቲከኞች አይደሉም፡፡

የእነዚህ ጉዳተኞች ፈውስ ከፖለቲካችን ፈውስ ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ በአግባቡ ከለፉ የማይቃና ነገር የለም፡፡ ፖለቲካችን የሕዝብ ዕውናዊ ፍላጎቶችን ከብዥታዎች አጥልሎና ቅደም ተከተል አስይዞ የማቅረቢያ ባለ ብዙ ፓርቲ ማዕከል የመሆን ታሪክ መጀመር ይችላል፡፡ ‹‹ቆንጆዎቹ›› ከሰማይ አይወርዱም፣ የሚወለዱት ከእኛ ‹‹ከድፍንድፎቹ›› ማኅፀን ነው፡፡ ማኅፀናችን ለምልሞ ቆንጆ ፍሬ እንዲሰጠን ምን እናድርግ? ይህ ጥያቄ በምርጫ 2013 ያሸነፉትንም ያላሸነፉትም የሚመለከት ነው፡፡

  1. የፖለቲካ ቡድኖች ጉልምስና

በዴሞክራሲ ግንባታ ውስጥ የተቋማት ግንባታ የዴሞክራሲን መሠረት የመጣል ዝቅተኛው ነገር ነው፡፡ ዋናው በተቋማቱ አማካይነት ሰዎች መብቶችን መተናፈስ መቻላቸው ነው፡፡ ይህ እንዲሳካ አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች አንዱ የፖለቲካ ቡድኖች/ፓርቲዎች አቅምና ባህርይ ማደግ ነው፡፡ የዚህ ዕድገት ዋና ማዕዘንም ከመጽሐፍ መጠጣ ይልቅ ለእውነታና ለሕዝብ ቅርብ መሆን ነው፡፡ እልህ ስለተጋቡበት፣ ስለሚመኙትና መሆን ስላለበት ከማውሳት ይልቅ፣ ወደ እውነታ ምድር አጎንብሶ ከጨቀየ እውነታችንና ከሕዝብ እየተማሩ በአለንበት ተጨባጭ ሁኔታ ውስጥ ልናደርግ የምንችለውን ለማወቅና ስለዚያ ለማውራት ስንጣጣር ነው፡፡ መጣጣር ስንል ምን ማለታችን እንደሆነ ለማጤን እንድንችል በምሳሌዎች እንነጋገር፡፡

ሀ) የቀበሌ (የክፍለ ወረዳ) ማኅበረሰብ የማቀናበር ነገር ከዚህ እስከዚህ ድረስ እያሉ የማካለል ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ የከተሞች አሸናሸን ለማኅበረሰባዊ ዴሞክራሲም ትርጉም የሚኖረው ‹‹ሽንሸናው›› ሜካኒካዊ ሳይሆን፣ እያንዳንዱ ተቀናጅ ክፍል በማኅበራዊ ግንኙነቶች የተሸመነ ማኅበረሰባዊ ቀዬ ሆኖ ሲላወስ ነው፡፡ ማኅበረሰብ አቀፍ ዕድር፣ የሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበር፣ ማኅበረሰቡ የሚጠቀምባቸውና የሚንከባከባቸው የወል ሥፍራዎች (ንዑስ መዝናኛዎች፣ የባህል ማዕከሎች፣ ንዑስ የጨዋታ ሜዳዎች)፣ በየጊዜው ስለ ልዩ ልዩ ጉዳዮች የሚመከርባቸው ሸንጎዎችና እነዚህን የመሳሰሉ ነገሮች ያያያዙት የጋራ ሕይወት ባለው የነዋሪዎች ማኅበረሰብ ውስጥ ዴሞክራሲን ለማለምለም ‹‹ቀላል›› ይሆናል፡፡ በደርግ አፍላ ጊዜ የዚህ ዓይነት የወል ልማቶች ተጀምረው የነበሩ ቢሆንም፣ ለቢሮክራሲያዊ ተባዮች የምጥመጣ ማሳ ሆነው መከኑ፡፡ ቀጥሎ የመጣውና እንደነገሩ ‹‹የወጣቶች ማዕከል›› የሞካከረው ሕወሓት/ኢሕአዴግም ቢሆን ምክንያቱን ከማስቀጠል፣ ሞታቸውን ከማሳመርና ለአዲስ ልማት ሊውሉ ይችሉ የነበሩ ክፍት (አረንጓዴ) ሥፍራዎችን እየቀረጠፉ ከማመናመን የተሻለ ነገር አላመጣም፡፡ የ‹ኮንዶሚኒየም› እና አፍርሶ የመገንባት መርሐ ግብርም የነበረ ማኅበረሰብን ከመበተን በቀር፣ ዘመናዊ የማኅበረሰብ ህዋሶችን አቅዶ የማልማት ትልም አልነበረውም፡፡ ተመናምነው የተረፉትም ክፍት ሥፍራዎች ዝም ብሎ ከመቀመጥ፣ የቴሌ ማማ ማቆሚያ ከመሆን ወይም የመኪና ማቆሚያ ኪራይ መነገጃ ከመሆን የበለጠ ጥቅም ሳይሰጡ ቆይተዋል፡፡

ከ2010 ዓ.ም. ለውጥ ወደዚህ በጣም ጥቂት የጨዋታ ሥፍራዎች በአዲስ አበባ ለምተው ከማየታችን በቀር የክፍት ቦታዎች መቀርጠፍ አልተገታም፡፡ ‹‹ክፍት ቦታዎች ይታረሱ/ፆም አይደሩ›› በተባለው መሠረት ታጥሮ ጎመን የተጀማመረበት ክፍት የጨዋታ ሜዳ፣ በስተኋላ በጎመን ፈንታ ቪላዎች ሲያበቅል ዓይቻለሁ፡፡ የቀጠለው የጋራ ቤቶች ግንባታም ማኅበረሰባዊ ህዋሶችን ከማዋቀር ዕቅድ የበቀለ እንዲሆን ሆኖ ለመታረም አልበቃም፡፡ የሕገወጥ ግንባታ አፈራረሱ፣ የጋራ ቤቶች ግንባታ አስተዳደርም ሆነ የቤት ዕደላው የቅሬታና የብሶት መፍለቂያ ከመሆን ሳይርቅ ቆይቷል፡፡ እነዚህን የመሳሰሉ ቅሬታዎች እልህና ፖለቲካዊ ሙሌት አግኝተው አዲስ አበባን ራስ ገዝ የማድረግ የፖለቲካ እንቅስቃሴን እንደወለዱም ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ‹‹ክልልነት/ራስ ገዝነት›› የበደል ቅሬታዎችን ማቃለያ እንደማይሆን በሌሎች ክልሎች የታየው የበደል መዓት ብቻውን ለምስክርነት በቂ ነው፡፡ የአዲስ አበባና የኦሮሚያ የተቆላለፈ ህልውናም ክልል ስለተሆነ የሚገላገሉት ነገር አይደለም፡፡ ዴሞክራሲን፣ ግልጽ አሠራርን፣ የሽፍንፍንና የበደል ሥራ ተጋላጭነትንና ተጠያቂነትን ነው አዲስ አበባም ሆነ ሌሎች አካባቢዎች በመፍትሔነት የሚሹት፡፡ እነዚህ መፍትሔዎችና ራስን በራስ የማስተደደር መብት በፌዴራል ከተማነት ውስጥ ተሆኖም ሊሟሉ ይችላሉ፡፡ የአዲስ አበባ የፌዴራል ከተማ ሆና መቀጠሏም በብዙ ነገር ለአዲስ አበባ ሕዝብም ለመላው ኢትዮጵያም የሚበጅ ነው፡፡ ራስ ገዝነት ኦሮሚያንና የአዲስ አበባን ሕዝብ ኑሮ ወደ ንቁሪያ የሚወስድ ነው፡፡ አዲስ አበባ የመላ ሕዝቦቻችን ፌዴራላዊ ማዕከል ሆና መልማቷ ግን፣ የኦሮሚያንና የአዲስ አበባን ሕይወት የሚያግባባ ከመሆኑ ባሻገር፣ ለኢትዮጵያ ማኅበረሰባዊ ትስስር ተምሳሌታዊ ጥቅም አለው፡፡ አዲስ አበባ የአገሪቱን ማኅበረሰቦች ገጽታዎች በባህል ማዕከላት ግንባታዎች ማንፀባረቅ መጀመሯ፣ እያንዳንዱ ‹‹ክልል›› እና ብሔረሰብ አዲስ አበባን የእኔ እንዲል የሚያስችል ነው፡፡ በአሁኑ ታሪካዊ ምርጫ፣ በሰኔ 14ቱ ምርጫ፣ በአዲስ አበባ በተገኘው አጠቃላይ የድምፅ ውጤት የ‹ራስ ገዝ› ባለመፈክሮች ያላሸነፉት፣ እነዚህን ነገሮች ሁሉ በግርድፉም ደረጃ ሆነ በተባ ደረጃ መራጩ አስተውሎ ይመስለኛል፡፡

በሕዝብ ዘንድ በተለያየ ደረጃ የተጤነውን ይህንን እውነታዊነት፣ ‹‹አዲስ አበባ ራስ ገዝ ትሁን›› ያሉ ሰዎችና ቡድኖች ማየት ከብዷቸው ነበር? ወይስ በብሶት የከተማውን ሕዝብ ቀዝፎ የመመረጥ ፍላጎት በልጦባቸው ነበር? ይህንን ጥያቄ እንተወውና ሌላ ጥያቄ እናንሳ፡፡ የመፈክሩ ባለቤቶች የአዲስ አበባ ምክር ቤትን ወንበሮች መቶ በመቶ ለሁለት ተከታታይ አምስት ዓመታት ቢያሸንፉ ኖሮስ አዲስ አበባን ራስ ገዝ ማድረግ ይችሉ ነበር? ባለው ሕገ መንግሥት መሠረት የምናገኘው የመሆን አለመሆን ዕድል የዚህን ጥያቄ ብቻ ሳይሆን የፊተኛውንም ጥያቄ መልስ ይነግረናል፡፡ የአዲስ አበባ የፌዴራል ከተማነት በሕገ መንግሥቱ ምዕራፍ አራት አንቀጽ 49 ውስጥ የተደነገገ ነው፡፡ የአዲስ አበባን የፌዴራል ከተማነት የሚያውጀውን አንቀጽ ያዘለው ምዕራፍ አራትና ሌሎች ብዙ ምዕራፎች የሚሻሻሉት በአንቀጽ 105 (2) አማካይነት ነው፡፡ የተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች በጋራ ስብሰባ በ2/3 ድምፅ የቀረበውን ማሻሻያ ሲያፀድቁና ከፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች ምክር ቤቶች ውስጥ የ2/3 የክልል ምክር ቤቶች በድምፅ ብልጫ ሲያፀድቁት ነው (የፓርላማው ምክር ቤቶች በጋራ ስብሰባ ከሚሰጡት የ2/3 ስምምነት ባሻገር፣ ሌሎች 6.6 ክልሎች በድምፅ ብልጫ አወሳሰን ማሻሻያውን ሲቀበሉት ማለት ነው)፡፡ ይህ ምን ያህል ተጨባጭ ሊሆን እንደሚችል የመፍረዱን ነገር ለአንባቢያን እተወዋለሁ፡፡ ያም ሆነ ይህ እጅግም ተጨባጭነት የሌለውን ጥያቄ እንዲደግፍ የሕዝብን ብሶት መፈናጠጥ ትምህርት ሊወሰድበት የሚገባ ይመስለኛል፡፡

ለ) የኢትዮጵያ እናቶች እናትነት በድፍኑ እንደ ውሻ ፍቅር ታማኝ ነው ሊባል ይችላል፡፡ በአብዛኛው ሁኔታ እናት ጊዜ አይታ አትከዳም፣ ልጄ አስቀየመኝ ብላ ልጇን አታነቅርም፡፡ ልጇ ጥሪቷን በዝብዞ ቢያባክን እንኳ ገንዘብ ከልጄ አይበልጥብኝም ልትል የምትችል ነች፡፡ መቆራረጥ የማይሆንላት፣ ለልጇ ስስታምና አድሏዊ ነች፡፡ የመሳሳቷ ብዛት ቢበላ፣ ቢበላ የጠገበ የማይመስላት፣ ከጉንጯ አውጥታ ልታጎርስ የምትከጅል ነች፡፡ ለልጇ መሳሳቷ ከሚስቱ/ከበሏ እስከ መሻማት ድረስ ይሄዳል፡፡ ልጆቿ ካገቡና ከወለዱም በኋላ እንደ ልጅነታቸው ብታሻሻቸውና እዚያም እዚያም ብትስማቸው ትናፍቃለች፡፡ ልጆቿም በአብዛኛው ሁኔታ ለእናታቸው ያላቸው ፍቅር ከአባት ፍቅር ጋር የማይወዳዳር ጭፍን ነው፡፡ እናቴ እንዲህ ያለ ድክመት አላት ብሎ መተቸት እንደ በደልና የእናትን ውለታ እንደ መርገጥ የሚቆጠር (መጥፎ ሰው/ነውረኛ) ሊያስብል የሚችል ነው፡፡ በኦርቶዶክስና በካቶሊክ ክርስትና እምነት ውስጥ የኢየሱስ ክርስቶስ እናት ድንግል ማሪያም በሩኅሩኅነቷና በአማላጅነቷ ልዩ ቦታ አላት፡፡ ኢትዮጵያም በእናት/በእምዬ ነው የምትመሰለው፡፡ ባይመቸንም የማንተዋት ‹‹መከበሪያዬ›› የምንላት ነች፡፡ በኢትዮጵያ እምዬያዊ ፍቅራችን ውስጥ በዕድገታችንና በኑሯችን ውስጥ የተቋደስነው መንፈሳዊና ቁሳዊ ባህል፣ ማኅበራዊና መልክዓ ምድራዊ አካባቢያችን ሁሉ አለ፡፡ የተወሰነ የፖለቲካ ቡድን ‹‹እናትን›› የፓርቲው መጠሪያ ሲያደርግ ለእናት ያለንን የተጋነነ (ወቀሳና ማብጠልጠል የሌለበትን) ፍቅር ለፖለቲካ ድጋፍና ለምርጫ ውጤት ለመከራየት መፈለጉ ነው፡፡ እንዲህ ያለ ፍላጎት ከሙስና ያንስ ይሆን?

ሐ) በአንጓላይ የብሔር ፓርቲዎች አገዛዝ ውስጥ መናቆር እንጂ፣ ተግባብቶ ጠንካራ ፌዴራላዊ አገር መገንባት እንደማይቻል፣ የእስካሁኑ የብሔር ፖለቲካ ልምዳችን ያስከፈለንን አስከፍሎ ከበቂ በላይ አስተምሮናል፡፡ በትግራይና በኦሮሚያ ምዕራባዊ (አንዳንዴም በስተደቡብ) ስናይ የቆየነው የሕወሓትና የሸኔ ጨካኝ አብጤነት፣ ‹‹ቃሬዛውን ያየ ውርጭት›› ነው ማለት ይቻላል፡፡ የኦፌኮና የዳውድ ኢብሳ ሰዎች አውጀው ነበር የሚባለው የሽግግር መንግሥት ደግሞ በእውነታና በቀን ቅዠት መካከል ያለው ልዩነት ተቀላቅሎበት፣ መንገድ ለመንገድ መለፍለፍ ውስጥ የገባ ብሔርተኝነትን የሚያንፀባርቅ መሳይ ነው፡፡ አንዴ የኬንያው ራይላ ኦዲንጋ እንዲህ ‹‹ቀውሶ›› አየር ላይ በዓለ-ሹመት ፈጽሞ ነበር፡፡ ደግነቱ እሱ በቶሎ ወደ ልቦናው ተመለሰ፣ የእኛዎቹም እግዜር ረድቷቸው ወደ ጤናቸው እንደሚመለሱ ተስፋ እናደርጋለን፡፡

እንዲህ ያለው የብሔርተኛ ፖለቲካ አወዳደቅ፣ የብሔረሰቦች መብቶችን የሚንከባከብ ሥርዓት ከማበጀት ጋር ወደ ኅብረ ብሔራዊ የአዕምሮ ሙሽትና የፓርቲ አደረጃጀት ተሸጋገሩ የሚል መልዕክት የሚረጭም ነው፡፡ የብሔረሰቦች፣ የቋንቋዎችና የባህሎች እኩል እንክብካቤ ሕይወት የሚያገኘው በየብሔር የተሰባሰቡ ቡድኖች የብሔር ‹‹ወገንን›› በቋንቋ እየለኩና በመብራት እየፈለጉ ይህ፣ ያ ጎደለ የሚል ፖለቲካ ስላቦኩ ሳይሆን፣ የሥርዓተ ማኅበሩ አገረ መንግሥት ብሔረሰቦችንና ቋንቋዎችን ያለ አድላዊነት የሚንከባከብ ሆኖ ለመደራጀት መቻል ነው፡፡ በዚህ ረገድ የአብላጫ ድምፅ ሥርዓት ለመወከል ዕድል የማይሰጣቸው ብሔረሰቦች ድምፃቸው የሚሰማበትንና የሚወከልበትን ዘዴ ማቀናበር አግባብ ነው፡፡ ቋንቋን ዋና የብሔረሰብ ዝምድና መለኪያ ማድረግ ግን እጅግ አሳሳች መሆኑ ከወዲሁ በደንብ ሊጤን ይገባል፡፡ በደም፣ በሥነ ልቦናና በባህል ተወራርሰው ለሚገኙ የወሊሶ ግድም የጉራጌና የኦሮሞ ማኅበረሰቦች የቋንቋ ልዩነት ግልብ ልዩነት ነው፡፡ ይህንን የቋንቋ ገጽታ ተመርኩዞ በዚያ አካባቢ ያለ ኦሮሚኛ ተናጋሪ ‹‹ዘመዱን›› ፍለጋ ወደ ባሌ ሐረርና ወለጋ ልቡን ቢያዞር አድራጎቱ ከዕይታ መቦዝ ያነሰ አይሆንም (የዚህ ዓይነት ብዙ ምሳሌ መደርደር ይቻላል)፡፡

በሌላ አኳያ ብሔረሰቦች እስካሉ ድረስ ብሔረሰባዊ ንቃት፣ ተቆርቋሪነትና ኩራት መኖሩ ተፈጥሯዊና ተፈላጊ ነው፡፡ የማኅበረሰቦች እንክብካቤ የተዛባ/አድህሏዊ ወደ መሆን ሲንሸራተት የብሔር ተቆርቋሪነት ከርሮ ወደ ብሔርተኝነት ሊቀየር ይችላል፡፡ እናም በብሔር (በየቋንቋ) የተቧደነ ፖለቲካ እየሳሳ ከመድረክ ቢጠፋ እንኳ ብሔርተኝነት አበቃለት ማለት አይደለም፡፡ ብሔርተኛነት የሚያበቃለት ለብሔረሰባዊ መብቶች የምናደርገው እንክብካቤ እስካልዛለና እኩል ነን የሚል እምነት እስካልቆሰለ ድረስ ነው፡፡ እናም  ብሔርተኝነትን ማሸነፍ ማለት፣ ሁሌም ኢአድሏዊነትን ማበልፀግ ማለት መሆኑ መቼም መዘንጋት የለበትም፡፡

በነፃነት (ፍሪደም) ተግባራዊ ትርጉም ውስጥ ሁልጊዜም ፍላጎት ከአስፈላጊነት ጋር ተገናዛቢ ነው፡፡ የመሬት ስበትን የማሸነፍ ነፃነት የመሬት ስበትን ባህርይ ከመረዳትና ስበትን ለማሸነፍ የሚያስችለውን ዕውቀትና ጥበብ ከመጨበጥ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በማኅበራዊ ኑሮ መስተጋብርም ውስጥ እንደዚያው ነው፡፡ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ቅንብር ውስጥ ባለ አካባቢያዊ አስተዳደር ውስጥ ቋሚ ነዋሪ ሆኖ፣ የአካባቢውን ይፋ የሥራ ቋንቋ አለማወቅ የገዛ ነፃነትን ማጓደል ነው፡፡ በኢትዮጵያ ደረጃ ከሰፊም ሰፊ ተነጋሪነት ያላቸውን አማርኛና ኦሮሚኛ ቋንቋዎች ማወቅ/ለማወቅ መጣጣር ነፃነትን ሙሉ ለማድረግ መጣጣርም ነው፡፡ ኑሮው ከሚሽከረከርበት ውስን ሥፍራ ወጣ ሲል በቋንቋ አለማወቅ ምክንያት ጆሮውን ቢቆርጡት የማይሰማና ዲዳ የሚሆን ሰው እንደምን ነፃነት አለው ይባላል! ብዙ ቋንቋ ተናጋሪነት ነፃነትን ማብዛት እንጂ ተጎጂነትን ማብዛት ፈጽሞ ሊሆን አይችልም፡፡

ይሁን እንጂ ይህንን ነፃነት በቅጡ ባላበለፀግንበትና ብሔርተኝነት ገና አግጦ ባለበት በዛሬው ሁኔታ፣ አንዳንድ የፖለቲካ ቡድኖች ያነሱት አማርኛ ቋንቋን ብሔራዊ (የአገር መታወቂያ) ቋንቋ የማድረግ ሐሳብ፣ ብሔርተኛ ሆኖ ተቀናቃኝ ብሔርተኛነትን ከማነሳሳት የራቀ አይደለም፡፡ አማርኛን ብሔራዊ ቋንቋ የማድረግ ግብ እንዳላቸው የለፈፉ ቡድኖች አማርኛ ተናጋሪዎችን ለመማረክ ይበጀናል ከሚል ሥነ ልቦናዊ ጨዋታ በላይ፣ ኢትዮጵያን በአሁኑ ደረጃ ይበጃል የሚል እምነት ይዘው ከሆነ፣ ዓይናቸውንና አዕምሯቸውን ከፍተው የኢትዮጵያን የፖለቲካ እውነታ በጥንቃቄ ቢመረምሩ ይሻላል፡፡ የብሔራዊ ቋንቋነት ማዕረግን ማግኘት (የአንድ አገር መለያ ምልክት መሆን) መሪዎች ከውጭ አገሮች ጋር ባላቸው ግንኙነት ኢትዮጵያን በይፋ የሚወክሉበት ቋንቋ መሆን ማለት ነው፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታ ይህን ማዕረግ ለአማርኛ ልስጥ ማለት አማርኛ ስለምን መለያችን ይሆናል የሚል ብሔርተኛ ጉምጉም ተነስቶ አገር እንዲያብጥ እሳት አቀጣጣይ ልሁን ከማለት ያነሰ አይደለም፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያውያን የሚያስፈልገን በአካባቢዎችና በፌዴራል ደረጃ ብዙ ቋንቋ ተናጋሪነትን ማበልፀግ ነው፡፡ የብሔራዊ ቋንቋ ማዕረገኝነት ዛሬ የሚያስጨንቀን አይደለም፡፡ ወደፊት የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ሊወስንበት የሚችል ጉዳይ ነው፡፡ ያኔም ቢሆን አማርኛ ብቻውን የብሔራዊ ቋንቋነትን የሚሾም አይመስለኝም፡፡

መ) በአሁኑ ጊዜ ያለው የለውጥ ጅምር የሴቶችን በአገራቸው ፖለቲካ ውስጥ የመሳተፍ ፍላጎት እየጨመረ እንደመሆኑ ሁሉ፣ የኢትዮጵያ ሙስሊም ማኅበረሰብና ከማኅበረሰቡ የበቀሉ ልሂቃኖቻችን በአገራቸው ፖለቲካ ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ በሚያስደንቅ አኳኋን እየጨመረ ነው፡፡ እየጨመረ ነው ከማለትም በበለጠ፣ አጠቃላይ መነሳሳት አለ፡፡ ትንንሽ ሴት ልጆቻችን ሁሉ ወደ ፖለቲካ ሳይንስ ትምህርት ሲያመሩ እያየን ነው፡፡ በ2013 ምርጫ የነፃነትና የእኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) ብቅ ማለት የዚህ መነሳሳት አንድ መገለጫ ነው፡፡ እሰየው!!

ነገር ግን መነሳሳታችንና የፖለቲካ ንቁ ተሳትፏችን ሊጠነቀቅባቸው የሚገቡ ድጦች አሉ፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከዚህ በፊት የማያውቀውን የአገር አቀፍ ፓርቲ ጥንቅር ነእፓ (ነፃነትና እኩልት ፓርቲ) ይዞ በ2013 የምርጫ ዘመቻ ላይ ሲታይ፣ ኃላፊነት የጎደላቸው ችኩል ፍረጃዎችና ነቀፋዎች እንደተሰነዘሩ እናስታውሳለን፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከጉልምስና ስክነት ይልቅ ጨቅላነት፣ ጎረምሳነትና ጃጃቲያምነት የሚያጠቃው እንደ መሆኑም እንዲህ ያለ የማይገነባ አቀባበል መከሰቱ አያስገርምም፡፡ ከ‹‹ነእፓ›› በኩልም ሆነ በሙስሊም ፖለቲካ ቀመሶች አካባቢ የተንፀባረቀው ለስላሳና ጨርጫራ ምላሽም እንደዚያው አያስገርምም፣ አያስገርምምና ዝም ብለን እንለፈው የሚባል ግን አይደለም (በነገራች ላይ እያወራሁ ያለሁት እንደ ታዛቢ ከመሆን በላይ በሙስሊምም በክርስቲያንም የሥጋ ዝምድና ውስጥ ሆኜ ነው)፡፡

ነእፓ ላይ ዓይን ሁሉ ማጉረጡ ምን የተለየ ነገር መጥቶ? ያለው ፖለቲካዊ አደረጃጀት በተዛነፍ የተሞላ አይደል!? ሙስሊም የተከማቸበት ፓርቲ ቢፈጠር ለምን ይደንቃል! … ይህ ካልተዋጠልንማ የሁለተኛ ዜጋ አስተሳሰብ… በጊዜው የሰማኋቸው ሙግቶች የዚህ ዓይነት ክሮች ያሏቸው ነበሩ፡፡ ቁምነገሩ ግን ክርክር ለክርክር ‹‹ድል›› ሲባል፣ እያደረጉ ‹‹መርካት›› ወይም በፖለቲካ እውነታችን ውስጥ እንዲህ ያለ የተዛነፈ ነገር አለና እኛም የተዛነፈ ነገር ይዞ መውጣት መብታችን ነው በሚል ዓይነት ተዛነፍን በተዛነፍ የመመለስ ፉክክር አይደለም፡፡ ለፉክክርና ለክርክር ሲባል የሚደረግ ነገር ወዴት ይወስደናል? ወደ ጥርጣሬ፣ ወደ ንቁሪያና ጥፋት ወይስ ተግባብቶና ተማምኖ አገራዊ ሕይወታችንን ወደ ማቃናት? መፈነካከርና መናቆር ሳይፈጠር፣ መተማመን ሳይበጠበጥ ተዛነፍን መቀየር የሚቻለው በየትኛው አካሄድ ነው? የሚል ኃላፊነትን ያልዘነጋ አሳቢነት ሁሌም ተግባራችንንና አንደበታችንን መምራት ያለበት ይመስለኛል፡፡ ይህ ሁላችንንም የሚበጅ ጠንቃቃነት ነው፡፡

ከዚህ ማዕዘን አኳያ ቆመን የተወሰኑ መሠረታዊ ነጥቦችን በቅድሚያ እናስቀምጥ፡፡

  • ‹‹የፉክክር ቤት ሳይዘጋ…›› እንደሚባለው፣ ሃይማኖታዊ አመጣጥን ምርኩዝ ያደረገ ፉክክር ወደ ብሽሽቅና ወደ አደገኛ ጥፋት ሊያንከባልል የሚችል መሆኑን ሁሉም ወገን ልብ ሊል ይገባል፡፡ ክርስቲያን-መጦች የበረከቱበት የዛሬ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ተሳትፎ ክርስትናን የመንከባከብና የማበልፀግ ተግባር ላይ ያለመ እንዳልሆነ ሁሉ፣ ሙስሊም-መጥ ኢትዮጵያውያን የሚያደርጉት የፖለቲካ ንቁ ተሳትፎም ዓላማ እስላማዊ አለመሆኑ፣ የሁለቱም የኢትዮጵያ ልጆች ዒላማ በአገራቸው ሶሲዮ ኢኮኖሚና ፖለቲካ ግንባታ ውስጥ ንቁ አስተዋፅኦ የማድረግ ጉዳይ መሆኑ፣ በሁሉም ወገን ጥርት ብሎ መታወቁ አስፈላጊ ነው፡፡
  • በኢትዮጵያ አገር አቀፍ ፖለቲካን የማካሄድ ተግባር የክርስቲያን ኢትዮጵያውያን ዋና ድርሻ፣ በንግዱ ዘርፍ ደግሞ ዋናውን ሚና የመጫወት ተግባር የሙስሊም ኢትዮጵያውያን ተግባር እንዲሆን/እንዲመሰል ያደረገው ተዛነፍ በረዥም ጊዜ የተፈጠረ የታሪክ ውጤት ነው፡፡ ይህ ተዛነፍም የጭቆና ቀላል ማብራሪያ የሚጠበው (ብዙ ሰበዞች ያሉበት) ነው፡፡
  • ይህ ተዛነፍ ፈጣን መቃለያም የለውም፡፡ ተዛነፍ ያለበት የፖለቲካ ተሳትፎም፣ የተዛነፈ ክምችት ያለው ፓርቲ በመፍጠር አይካካስም፡፡ እንዲያውም ሁለቱንም ወገኖች ሃይማኖታዊ ጥግ ወደ መያዝ ያንሸራትታል፡፡፡ የብሔር ፓርቲዎች ሕዝብን የብሔር ዘመዶቹን እየፈለገ ወደ መምረጥ እንደወሰዱት ሁሉ፣ ሙስሊሞች የተከማቹበት ፓርቲ፣ ክርስቲያኖች በተከማቹባቸው ፓርቲዎች አንፃር መቆምም ሕዝብን ሃይማኖታዊ ወገንን ወደ መፈለግ የሚወስድ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሴቶች በአገራቸው ፖለቲካ ውስጥ ያላቸውን አናሳ ተሳትፎ ለመቀየር ሌላ ተዛነፍ መፍጠር (የሴቶች ፓርቲ ወይም የሴቶች ቁጥር ያየለበት ቅንብር መፍጠር) አያስፈልጋቸውም፡፡ የሙስሊም ወገኖቻችንም ጉዳይ እንደዚያው ነው፡፡ በአካባቢ ፓርቲ ደረጃ የሃይማኖት ሥርጭት ተዛነፍ ሊኖር እንደመቻሉ በአካባቢ ፓርቲዎች ውስጥ የክምችት መሳሳትና መድመቅ ቢኖር ተፈጥሯዊ ይሆናል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ ግን የሚያሻው ሌላ ተዛነፍ መፍጠር ሳይሆን፣ በሃይማኖት አመጣጥም፣ በብሔርም ሆነ በፆታ ያለውን ያገጠጠ ተዛነፍ መቀየር ነው፡፡

ከእነዚህ ነጥቦች አኳያ ሆነን እናጠቃልል፡፡ ከመጋቢት 2010 ዓ.ም. ወደዚህ (በተለይም በ2113) የተነቃቃው የሴቶችና የሙስሊሞች የፖለቲካ ተሳትፎና የነእፓ መምጣት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አንድ የማይታለፍ መባነን ፈጥሯል፡፡  የኢትዮጵያ የፓርቲዎች ፖለቲካ ከእንግዲህ ከሁሉም ፆታዎች፣ ብሔረሰቦችና ሃይማኖቶች የሚመጡ ዜጎችን በአግባቡ ማካተትን ሆን ብሎ ሊሠራበት እንደሚገባ መልዕክት ሰጥቷል፡፡ ከዚህም ባሻገር ሙስሊም ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ሁለገብ ሕይወት ውስጥ ንቁ ተሳታፊ መሆን መብታቸውና ግዴታቸው መሆኑን ያለ ጎትጓች ልብ ማለታቸውንም መናገር ችለዋል፡፡ ሃይማኖትን መሥፈሪያ ሳያደርጉ ለወገን እያደረጉት ያለው የበጎ አድራጎት እንቅስቃሴም ከፖለቲካ ውጪ የታየ ሌላ አብነት ነው፡፡

ከዚህ የላቀና በእጅ የመዳሰስ ያህል ቅርብ የሆነ ተስፋም በኢትዮጵያ ምድር ፈንጥቋል፡፡ በብዙ ነገር የተሰናሰሉት የኢትዮጵያ ሙስሊምና ክርስቲያን ማኅበረሰቦች ሙስሊማዊና ክርስቲያናዊ ፖለቲካ ውስጥ ተንከባለው በቁርቁስና በአክራሪነት ሳይናጡ በተማመነና በተዘናነቀ ሁለገብ ተሳትፎ አገራቸውን የበለፀገች፣ የሠለጠነች፣ በማኅበራዊና በፖለቲካ ሰላም ምሳሌ ሆና የምትፈካ አድርጎ ለመገንባት ሥነ ልቦናዊ አቅም አሳይተዋል፡፡ በአጠቃላይ ሁሉም ዓይነት ማኅበረሰባዊ ብዝኃነት የተቀናበረበት የለውጥ መነሳሳት የኢትዮጵያን ትንሳዔ መደገስ ጀማምሯል ሊያስብል የሚያስችል የምሥራች እየተበሰረ ነው፡፡

ሠ) በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ‹‹ቀኝና ግራ››፣ ‹‹ወግ አጥባቂና ለውጥ ናፋቂ››፣ ‹‹አድሃሪና ተራማጅ›› የሚሉ ዕሳቤዎችን የመጠቀም ነገር የመጣው ከ1960ዎች የተማሪዎች እንቅስቃሴና ከ1966 ዓ.ም. አብዮት ጋር ነው ማለት ይቻላል፡፡ በዛሬውም የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ እነዚህና እነዚህን መሰል ቃላት ሲሠራባቸው እናያለን፡፡ የትናንትናና የዛሬ አጠቃቀማቸው ግን በአንድ ዓይን የሚታይ አይደለም፡፡ ዛሬ በመሰለኝ ትርጉም እያጠናገረ ‹‹ግራ/ቀኝ›› የሚለው ሳይበረክት አይቀርምና ጥቂት የግንዛቤ ነጥቦችን ማስቀመጥ ተገቢ ይመስለኛል፡፡

በዓለም ፖለቲካ ውስጥ የ‹ቀኝ ክንፍ› እና የ‹ግራ ክንፍ› አመጣጥ እ.ኤ.አ. በ1790 የፈረንሣይ አብዮት በአፍላ ሒደቱ በወለደው የሕገ መንግሥት ጉባዔ ውስጥ ከነበረ የሁለት የፖለቲካ ረድፎች አቀማመጥ የበቀለ ነው፡፡ ያኔ በሕገ መንግሥት ጉባዔው ውስጥ በስተቀኝ በኩል ይቀመጡ የነበሩት ዘውዳዊ ሥርዓትን ጠብቀው መሠረት የማያናጋ ቀላል ለውጥ ማድረግ የሚሹ ወገኖች ነበሩ፡፡ የግራውን የመቀመጫ ረድፍ ይዘው የነበሩት ደግሞ ዘውዳዊ ሥርዓት ተሽሮ ሁሉን አቀፍ ሪፐብሊክ የሚያቋቋም ሥር ነቀል ለውጥ ፈላጊዎች (አብዮተኞች) ነበሩ፡፡ ያኔ የነበራቸው አቀማመጥ ይዘዋቸው ለነበሩ የፖለቲካ አቋሞች ተለዋጭ መጠሪያም መሆን ችሎ ነበርና የግራና የቀኝ ክንፍ ፖለቲካ አጠቃቀም የጀመረው ያኔ ነበር፡፡ የቀኝና የግራ ፖለቲካ መሠረታዊ የትርጉም ፈለጉ ዛሬም ድረስ መሠረታዊ ለውጥ ከመፈለግና ካለመፈለግ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የለውጥ ሥር ነቀል መሆንና አለመሆን ከዘመንና ከአገራዊ እውነታ ጋር ይያያዛልና ይዘቱ ደርቆ የሚቆይ (ሁሉም ዘንድ አንድ ዓይነት) አይሆንም፡፡ በፈረንሣይ የ18ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ የመጣው አብዮት የከበርቴው አብዮት ነበር፡፡ ያኔ አንደኛና ክቡር መደብ የነበረው አሮጌው የመሳፍንት መኳንንት መደብ ሲሆን፣ ከበርቴው ሁለተኛ መደብ፣ ተሬው ደግሞ ሦስተኛ ነበር፡፡ በዚያ ጊዜው እውነታ በመሳፍንቱ የተናቀው ግን አዲስ የነበረው ከበርቴ መደብ፣ የመሳፍንት መኳንንቱን ዙፋናዊ አገዛዝ ሽሮ፣ በሪፐብሊክ ዘይቤ ራሱን ወደ ላይ ማውጣቱ ተራማጅና ሥር ነቀል ነበር፡፡ የከበርቴው ሥርዓት በአያሌው በምዕራብ አውሮፓ ከተዘረጋ በኋላ፣ በተለይ ከ19ኛው ሁለተኛ አጋማሽ ወደዚህ (ከበፊቱ ይበልጥ ረሃቡ የከፋ የካፒታሊስት የቅኝ ሽሚያና አንደኛው የዓለም ጦርነት የታየበት ዘመን) የከበርቴውን ሥርዓት በፀረ ዕድገትነት ፈርጆ፣ አዲስ ፍትሐዊ ሥርዓትን የሚያቀነቅነው ሶሻሊስት እንቅስቃሴ እየገነነ የመጣበት ጊዜ ነበር፡፡ ያኔ ደግሞ የ‹ቀኝ›ነት (የወግ አጥባቂነት) ትርጉም ካፒታሊስታዊ የከበርቴ ሥርዓትን ከማዳን ጋር፣ ‹ግራ›ነት (ሥር ነቀልነት) ደግሞ ከሶሻሊስት እንቅስቃሴ ጋር ተያይዟል፡፡ ዛሬም በዓለም ፖለቲካ ውስጥ ይኼው የትርጉም ክር ግልብ/ጉልድፍድፍ፣ እንዲያም ሲል ማስፈራሪያ በሚመስል መልክ የሚሠራበት ቢሆንም፣ ከአገር አገር ያለው የ‹ግራ› እና የ‹ቀኝ› አጠቃቀም ብዙ ቡራቡሬነት እንዳለው ማወቅ የፖለቲካ ሀሁ ነው፡፡

ከበርቴያዊ ገዥነትና ካፒታሊስታዊ ሥርዓተ ኑሮ ባዳበራቸውም ምዕራባዊ አገሮች ውስጥ ሥርዓተ ማኅበሩን የማያናጋ ጥገና እንኳ በቀኝና በግራ ፖለቲከኛነት ሊያስፈርጅ ይችላል፡፡ በአሜሪካ ውስጥ በጤና ደኅንነት ወይም ዋስትና መንግሥት ኅብረተሰብን የመንከባከብ ገጽታ እንዲኖረው በኦባማ ፕሬዚዳንትነት ጊዜ ሲሞከርና ሙከራው ያስገኘው ከአንጀት ጠብ ያላለ ውጤት፣ ዛሬም ድረስ በግራ (በኮሙዩኒስት) ናፋቂነት የሚወቀስ ሕዝብን ለማስፈራራት ሁሉ እየተሠራበት ያለ ነው፡፡ እንደ ዴንማርክ ባሉ የሶሻል ዴሞክራሲ አገሮች ደግሞ ኅብረተሰብን በብዙ ፈርጆች መንከባከብ የአገረ መንግሥቱ ባህርይና ኃላፊነት ሆኖ እናገኛዋለን፡፡ እዚያ ‹ግራ›ነት (ተራማጅነት) ከፍትሐዊ የዜጎች እንክብካቤ ጋር ተያይዟል፡፡ ‹‹መሬት ለአራሹ›› እንኳ ባረረባቸውና ከተፈጥሯዊ ኢኮኖሚ ፈቀቅ ባላሉ የዓለም ጥጎች ዘንድ ደግሞ ገና ከበርቴያዊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መስፋፋት ተራማጅ/ሥር ነቀል ተደርጎ ሊቆጠር የሚችል ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር የቡድኖች የፖለቲካ አቋም ደርቆ ሊቆይ እንደሚችል ሁሉ፣ በተለያየ ደረጃ ከቀኝነትም ሆነ ከግራነት ሊንፏቀቅ ይችላል፡፡ የለውጥ ዕንቢታም ሆነ የለውጥ ፈላጊነት የደረጃ ልዩነት ሊኖረውም ይችላልና ከቀኝም ቀኝ፣ ከግራም ግራ እያሉ አቋሞችን ማበላለጥ አለ፡፡

በኢትዮጵያ አፄያዊ ፍፁም ገዥነት በነበረበት ጊዜ ውስጥ በሕገ መንግሥት የተገደበ የዘውድ አስተዳደርን መጠየቅ ተራማጅ ነበር፡፡ የ1966 ዓ.ም. አብዮት ከፈነዳ በኋላ ከነበሩ የለውጥ ፍላጎቶች አኳያ ግን፣ ዘውዳዊውን አገዛዝ በትንሽ ማሻሻያ የማዳን ነገር የቀኝ ፖለቲካ ተደርጎ የሚታይ ነበር፡፡ ደርግ አፄ ኃይለ ሥላሴን ዘወር አድርጎ ሥልጣን ላይ በወጣበት ጊዜ፣ ጥንቅሩ ብዙ የፖለቲካ ፍላጎቶችን ያጎረ ነበር፡፡ የ‹‹ኢትዮጵያ ትቅደም!›› መፈክሩም በጊዜው የነበረውን ውል የለሽነት የሚያንፀባርቅ ነበር፡፡ ደርግ በለውጥ ግፊት እየተናጠና ከውስጡም የሚያራግፈውን እያራገፈ የተወሰነ ተራማጅ ዝንባሌ አሳይቷል፡፡ የከበርቴ ሥርዓትን በፍትሐዊነትና በሕዝብ ዴሞክራሲ ለመተካት የሞከረው የዓለም የሶሻሊስት እንቅስቃሴ፣ በጥቅሉ አብዮታዊ ለውጥን ሞክሮ ከመጨንገፉ የተገኘው ውርዴ ሥርዓት፣ ኅብረተሰቡንም ኢኮኖሚውንም የቀረቀበና በቆዳው የቀረ መንግሥታዊ ቢሮክራሲያዊ ሥርዓት ተብሎ ሊገለጽ ይችላል፡፡ የደርግ ‹‹ተራማጅነት›› ግን በወታደራዊ አምባገነንነት ግንባታ ውስጥ ሥር ነቀል የመሬት ሥሪት ለውጥ (የመደብ ገዥነት መገለባበጥ) ከማድረስና የኢኮኖሚ አውታሮችን በመንግሥት ይዞታነት ከመሰቀዝ በቀር የሕዝብ ዴሞክራሲ የምትባል ነገርን ጫፉንም ያልሞከረ በሒደት ‹ማርክሲዝም› እና ‹ሶሻሊዝም› የሚል ጥምጣምን የጠመጠመ፣ ከጅምሩ እስከ ጭርሱ ግን ባህርይው ወታደራዊ አምባገነንነት መሆኑ ልብ መባል አለበት፡፡

የደርግን ‹‹ተራማጅነት›› ይንቁና ተራማጅነት/ግራነት ‹‹ከእኛ በላይ ላሳር›› ይሉ የነበሩ የከተማ ተቃዋሚቹም ከተንኮታኮቱ በኋላ በማዝገምም ሆነ በፈጣን መፈናጠር ምዕራባዊ ከበርቴያዊነትን ማረን ብለዋል፡፡ ‹‹ማርክሲስትነት›› ወይም ‹‹ሶሻሊስትነት›› የሚባሉ አስተሳሰቦችና ስሞችን ባዘለው የደርግና የተቃዋሚዎቹ ‹‹አብዮተኝነት›› ውስጥ ‹‹በቀኝ አውለኝ›› ብሎ ማለት ከ‹‹አለመንቃት››ም ባለፈ በአድኃሪነት ሊያስጠረጥር ይችል ነበር፡፡ መፈክር በመፈከር ጊዜም ተሳስቶ የቀኝ እጅን ላለማውጣት ጥንቃቄ ይደረግ ነበር፡፡ የተጣመዱት ቡድኖች ግብግብ ‹‹ነጭ›› እና ‹‹ቀይ›› የሚል አሸባሪ መበላላት የነበረበት እንደመሆኑም፣ ያ ጊዜ ካለፈ በኋላ ስለ‹ግራ› ክንፍ ፖለቲካ ያለው ዕሳቤ እጅግ አሉታዊ (ፈጣሪን የካደ የውርጅብኝ/የኩነኔ) መስመር ተደርጎ የሚታይ ሆኗል፡፡ ከዚህ ስሜት ለመራቅ የዛሬ የፖለቲካ መስመሮችን ‹‹ተራማጅ››/‹‹ኢተራማጅ››፣ ‹‹ለውጥ ፈላጊ››፣ ‹‹ለውጥ ተቀናቃኝ›› እያሉ መግለጽ ሳይሻል አይቀርም፡፡

ወደዚያም ቢዞር ግን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የሚንፀባረቁትን የለውጥ ፈላጊና የለውጥ ተቀናቃኝ አዝማማያዎች በተፈላቀቀ ደረጃ ማሳየት ቀላል አይሆንም፡፡ ለዚህም ዋናው ምክንያት የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት የግንባታ አዝግሞት ይህ ነው በሚባል ስክነት ‹‹አለመገባደዱ›› እና የአገረ መንግሥት ግንባታው ጉዳይ ከፖለቲካ መድረኩ ገለል አለማለቱ (የፖለቲካችን ዋና መፋተጊያ ሆኖ መቀጠሉ) ነው፡፡ ረዥም ዘመናት የፈጀው ዘምቶ በማስገበር እየተገነባ የመጣው ‹‹የራስ ገዝ›› አካባቢዎችን አነሰም በዛ የያዘ አፄያዊ ቅንብር ከወዲህ ሲቀጠል፣ ከወዲያ እየተበጠሰ፣ እዚህ ሲጨመር፣ እዚያ እየተቀነሰ ዘምቶ የማስገበር መልክ የነበረው የአገረ መንግሥት ግንባታ እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን መጥባት ድረስ ያረፈደ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ ወደ ፍፁማዊና አሀዳዊ የአፄ አገዛዝ መጓዝ፣ ቀጥሎ ደግሞ ‹‹ሶሻሊስት ነኝ›› ወዳለ ወታደራዊ ቢሮክራሲያዊ ጥርነፋ ማለፍ፣ ከዚያ ደግሞ ‹‹ብሔርተኛ ፌዴራሊዝምን›› ደላጎው ወዳደረገ ጥርነፋ መዞር ተፈጽሟል፡፡ አሁን ደግሞ ከውጭ ጥቃት የተወዳጀ አፋጅቶ የመበተን የውስጥ አደጋን በማምከን፣ ፌዴራላዊነትንና ዴሞክራሲን እውነተኛ ያደረገ አገረ መንግሥት የመገንባት ጥረት ውስጥ እንገኛለን፡፡ ተፈላጊው የአገረ መንግሥት ግንባታ ጉዳይ ገና የፖለቲካ ትግል ጉዳይ እንደመሆኑም በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ቡድኖች፣ የኢትዮጵያ አንድነት ፓርቲ/የዚህ የዚያ ብሔር ፓርቲ ከሚል አደረጃጀት ወጥተው በፖለቲካና በኢኮኖሚ አስተሳሰብ ፈር እየለዩ መፈላቀቅ ገና ይቀራቸዋል፡፡

በብሔርተኛ ቡድን ውስጥ ከታሪክ የመጡ የመወራረስ ለውጦችን የሚቀበሉ፣ የትኛውንም አድልኦ፣ በደልና በቀል የሚቃወም አቋም ያላቸውን ሰዎች እንደምናገኝ ሁሉ፣ የብሔራቸው ቀደምት የባህል ገጽታዎችን የብሔራቸው ትክክለኛ የማንነት መለኪያ አድርገው ከዚያ ውጪ የመጡ ለውጦችን የሚፀናወቱ፣ በብሔራቸው ላይ ደረሰ የሚሉትን ጭቆናና ምዝበራ ተረኛ ጨቋኝና መዝባሪ ሆኖ ሒሳብ ከማወራረድ የበለጠ ነፃነትን የማይረዱ፣ ከዚህም አልፎ ጥላቻና በቀል እስከ ፋሺስታዊ ዝንባሌ ድረስ ገፍቶ የወሰዳቸውን ልናገኝ እንችላለን፡፡

በአንድነት ፓርቲነት ውስጥም በአያሌው ከነባር ገዥዎች ርዕዮተ ዓለም ገድልና ዝና ጋር የተጣበቁና ወደ አወዳሽነት ያደሉ፣ የይሁዳ አንበሳ ለኢትዮጵያ መታወቂያ ሆኖ አለመቀጠል የሚያሳዝናቸው፣ ለአመለካከት መሻሻል እጅግም ክፍት ያልሆኑ፣ የኢትዮጵያን አንድነት ከማምለክና ‹‹አንድነት›› ከሚል ድርቅና በቀር ለአንድነት ሲባል ከእኔ ይቅር የሚሉት (ተደራዳሪነት) የሚቸግራቸው፣ የባህል/የቋንቋና የብሔር ጭቆና በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ መካሄዱን መቀበል እንኳ የሚያቅራቸው ሰዎችን እናገኛለን፡፡ እዚህ መስመር ውስጥ ወደ ፋሺስታዊ አዘቅት ለመንከባለል ቅርብ የሆነ ጠርዝም አለ፡፡ ከዚህ ጠርዝ በተቃራኒ ተራማጅነት የሚያይልባቸው (በታሪክ ውስጥ የደረሱ በጎ ለውጦችን ብቻ ሳይሆን የጭቆናና የምዝበራ መራር ፈርጆችን የሚቀበሉ)፣ የኢትዮጵያ ዥንጉርጉር ኅብረተሰብ ተግባብቶ እንደ አገር መቀጠልና በግስጋሴ ጠንክሮ መውጣት የሚጠይቀውን የፍላጎቶች መቻቻል ሁሉ ለመቀበል ፈቃደኛ ልቦና ያላቸው ሰዎች እናገኛለን፡፡

ዛሬ በተያያዝነው ተቆራርሶ ከመጨራረስ የማምለጥ ግብግብ ውስጥ የቀኝ ቀኝ የሆነ ‹‹የብሔርተኛነት›› ፅንፍ የጥላቻና የጭፍጨፋ ጥርሱን አግጦ ባለ በሌለ አቅሙ እየተናነቀን ይገኛል፡፡ በዚህ ትንቅንቅ ውስጥ የፌዴራላዊ አንድነት መስመሩን የሚመሩት በፓርቲም በመንግሥት ደረጃም ለዘብተኛ ተራማጆች እንደ መሆናቸው፣ ከአንድነት አምላኪነት በኩል ሊከሰት ይችል የነበረው የቀኝ ቀኝ ዝንባሌ ተመርጎ እንዲቆይና በፖለቲካ ሜዳው ላይ እንዳይፈነጭ ለማድረግ አስችሏል፡፡ ይህ የግብግቡ አንድ በጎ ጥንካሬ ነው፡፡ በተረፈ አንድነትን ሙጥኝ ብሎ ከመበላላት የመትረፉ ትንቅንቅ በመላ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ድልነት እያበራ (ፌዴራዊ ዴሞክራሲያዊ የለማች አገር ግንባታችን የአንድ ልብ ተጋድሎነቱ ከአሁኑ የበለጠ እየወገገ) ሲመጣ፣ በአንድነትና በብሔር ፓርቲ ቀፎ ውስጥ የታጀሉና በቁርጥራጭ ቡድንነት ያሉ የሶሲዮ ኢኮኖሚ አስተሳሰቦች መስመራቸውን እየፈለጉ ሠልፍ የመያዛቸው ሒደት ይበልጥ እየተሟላ ይሄዳል፡፡

ረ) በዚህ የሐሳብ መስመር ውስጥ ሆኜ ስለ‹‹ነፃ አውጪነት›› ጥቂት ነጥቦችን ላክል፡፡ የሕወሓት የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር ነኝ ባይነት በኢትዮጵያ መንበረ ሥልጣን ላይ ከወጣ በኋላ እንኳ የአስተሳሰብ ለውጥ ለማድረግ ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ የብሔሮች ጥያቄ ተመልሷል ካለ በኋላ ‹‹ለምን ስምህን አትቀይርም?›› እየተባለ ቢነዘነዝ እንኳ መልሱ ጆሮ ዳባ ልበስ ነበር፡፡ ፌዴራላዊ ሥልጣን ሲሸሸውም ወዴት እንደሄደና በአገር ላይ ምን ዓይነት ደባዎች እየፈጸመ ዛሬ የደረሰበት እንደደረሰ ሁላችንም የምናውቀው ነው፡፡ ይህ ግፈኛ ቡድን ከኢትዮጵያ ከተቀነሰ ራሳችን ለራሳችን ጓጉንቸር እስካልሆንን ድረስና ዓላማችን ተሳስቦ መልማት እስከሆነ ድረስ የማይቻል ነገር የለም፡፡ ከሕወሓት የተላቀቀች ትግራይ ብቻዋን ራስ ገዝ በመሆን ላይ ብትፀናም ወይም የራስ አስተዳደር ባልተናጋበት ሁኔታ ከከፊል ተጎራባቾቿ ጋር በውዴታ የተጣመረችበት የላይ ሰሜን ራስ ገዝ ቢፈጠርም፣ ወይም ሌላ ዓይነት የልማት አቅም ማቻቻያ ቢደረግም አካባቢው የቱሪዝምና የሌሎች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች መፍለቅለቂያ መሆኑ አይቀርም፡፡

ከሕወሓት ጋር ያሳለፍነው የፖለቲካ ልምድ ወደ ኦነግም ይወስደናል፡፡ ኦነግ በፖለቲካ አስተሳሰብና በዓላማ እንዴት ያለ የግማሽ ምዕት ዓመት ጉዞ እንዳደረገ፣ እየተሸራረፈም ምን ያህልነት ላይ እንደደረሰ እዚህ ማተት አያስፈልገንም፡፡ በለውጡ ማግሥት በሰላማዊ መንገድ አቋሙን ለማራመድ አገር ውስጥ ከገባ በኋላ እንኳ የጠመንጃ ትግል ከመደገስ እንዳላመለጠ፣ ይህም ሥውር ሥራው ከመነጠል ዓላማ ጋር የተዛመደ እንደነበር ዛሬ ላይ ሆነን ሐሰት ለማለት የምንችል አይመስለኝም፡፡ የኦነግ መሪ የነበረው ዳውድ ኢብሳ በአንድ ወቅት የሚተኩስ ታጣቂ እንደሌለው ቢሸመጥጥም፣ ዓላማው መነጠል እንደሆነ አምልጦት መናገሩ ይታወሳል፡፡ ታጣቂው ክንፍ በፋሽስታዊ ጥላቻና ጭካኔ ተጠምዶ ስንት ግፍ ሲሠራ እንደቆየም ሁላችንም እናውቃለን፡፡ የእነ ቀጄላ መርዳሳ ቡድን ከዳውድ ቡድንም ሆነ ከ‹-ሸኔ› ጋር የዓላማም ሆነ የተግባር ዝምድና የለኝም ብሎ ራሱን ያገለለው ዘግይቶ የለውጡ ኃይል ከላይና ከወዲህ ‹‹ሰላማዊ››፣ ከሥርና ከወዲያ ነፍሰ ገዳይ ከሆነው ፅንፈኛነት ጋር የሚያደርገው ትንቅንቅ እየበረታ በመጣበት ጊዜ ነበር፡፡ እንደዚያም ሆኖ ኦነግ የሚለውን ስም ከራሱ ጋር ለማስቀረት ብዙ ለፍቷል፡፡

የኢትዮጵያነት መተሳሰሪያ አርማታ ብረት የሆነው የኦሮሞ ሕዝብ ከእነ ቋንቋው በነፃነት/በእኩልነትና በአገራዊ መተሳሰብ ኢትዮጵያነትን እያፋፋ ከመፋፋት ወደኋላ የሚመልሰው ምንም ኃይል የለም፡፡ ይህ ታሪካዊ እውነት የአሁኑ የኦሮሚያ ካርታ ቢነካካ እንኳ የማይቀለበስና የማይቋረጥ ነው፡፡ ምክንያቱም የኦሮሞነት ትልቁ ካርታ ኢትዮጵያ ስለሆነች፣ የኦሮሚኛ ተነጋሪነትም በመላዋ ኢትዮጵያ መናኘቱ አይቀሬ በመሆኑ ነው፡፡ የኦሮሚኛ በኢትዮጵያ መንተርከክም ኢትዮጵያን እንደ አርማታ ስለማጥበቁ ለመገንዘብ ጠንቋይ ዘንድ መሄድ አያስፈልገንም፡፡ ግርም የሚለኝ ግን ይህ እውነት ከሁለት በኩል የሚገባውን ያህል ግንዛቤ አለማግኘቱ ነው፡፡ የኢትዮጵያን አንድነት እስከ ዘለዓለም ድረስ እየወደዱ ኦሮሚኛን ለመማር አለመፍጠን አንድ ግርምት ነው፡፡ ኦሮሞ ግዙፍ የቋንቋና የመላላስ አቅም ያለው ሕዝብ ሆኖ ሳለ፣ የኦሮሞ ብሔርተኞች ኦሮሞ ከመሀልና ከዙሪያ ተጎራባቾቹ ማኅበረሰቦች ጋር እየተቀናጀ ብዙ ራስ ገዞች ቢፈጥር ቀረን እያሉ የሚቆጥሯቸው ሥፍራዎች ሁሉ ኦሮሟዊ እንደሚሆኑ ለማስተዋል አለመቻላቸውና የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሰላም መከታቸው አድርገው የዚህ ዓይነት አደረጃጀት አቀንቃኝ አለመሆናቸው ሌላ ግርምት ነው፡፡ ለማንኛውም ተቀንሶ ተቀንሶ አሁን የ‹አነግ›ን ስም ይዞ የቀረው ቡድን በኦሮሞና በኢትዮጵያ የተሳላ ጉዞ የሚስማማ ከሆነ፣ ‹‹ነፃ አውጪ ግንባር›› የሚል መጠሪያውንና ጊዜ ያለፈበትን  አቋሙን ከጊዜ ጋር ማስተካከል የሚገባው ይመስለኛል፡፡ አለዚያ በሕወሓት መጥፎ ልምድ ምክንያት፣ በጥርጣሬ መታየቱና ‹‹በኢትዮጵያ አንድነት ውስጥ ለኦሮሞ የምትሠራ ከሆነ ዛሬም ‹ነፃ አውጪ› የተሰኘ ስምህን ለምን ሙጥኝ አልክ?›› በሚል ጥያቄ መወትወት የሚቀርለት አይመስለኝም፡፡ ሌሎችም ‹‹ነፃ አውጪ››/‹‹ሊብሬሽን ፍሮንት›› የሚል ስም የያዙ ቡድኖች ለውጡን ለውጣችን እስካሉ ድረስ ፍሬያማና ዘላቂ ለማድረግ ከሌሎች ጋር ተጋግዞና ተሳስሮ መዋደቅ አይበዛባቸውም፡፡ የእነ ቀጀላ መርዳሳም ቡድን ሆነ ሌሎች መነጠል በሐሳባቸው የሌለና መነጠልን የጣሉ ‹‹ነፃ አውጪዎች››፣ የሰነዘርኩትን ሐሳብ በቀና ትርጉም እንደሚረዱልኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

  1. ማጠቃለያ

ከመስከረም 2014 ዓ.ም. በላ ከአዲሱ መንግሥት ጋር ብዙ ነገሮች እያማረባቸው እንደሚመጡ ተስፋ ይታየኛል፡፡ የሰኔ 14 ቀን 2013 ምርጫ ከአምስት ዓመት በኋላ ለሚመጣው ምርጫም ሆነ እዚያ ለሚደርሱ ፓርቲዎች የሰጠው ትምህርት ቀላል አይደለም፡፡ ይህ የአሁኑ ምርጫ የኢትዮጵያ ሕዝብ በልባምነት ልቆ የወጣበትም ምርጫ ነበር፡፡ በውስወሳና በቁስቆሳ ሳይሰክር ለህልውናው የሚበጅና ሊጨበጥ የሚችል ጥቅሙን የመረጠበት ምርጫ ነበር፡፡ በዚህም ውሳኔው ፓርቲ ነን ለሚሉ ሁሉ ታላቅ መልዕክት አስተላልፏል፡፡ በኩራቴ፣ በብሶቴና በሥነ ልቦናዬ ልትነግዱና ልትጋልቡኝ ከመሞከር ይልቅ ወደ ተግባር ሊቀየር የሚችል ሁነኛ ጥቅሜን ፈልቅቃችሁ ኑብኝ፣ ያን ጊዜ ጆሮ እሰስጣችኋለሁ ብሏል፡፡ የሆድ ቁርጠቴ የሆነውን ጥቅም ከማስተጋባት በላይ ሕዝብ አስተባብሮ ለመምራት የሚያስችል ብስለትና የድርጅት አቅም ሲኖራችሁ ደግሞ እከተላችኋለሁ የሚል መልዕክት አስተላልፏል፡፡ ከዚህ መልዕክት ያልተማረ ቡድን በመጪው የኢትዮጵያ ሕይወት ውስጥ ሥፍራ አይኖረውም፡፡ ወደፊት የአገረ መንግሥቱ አውታራት ከቡድን፣ ከብሔርና ከሃይማኖት ወገንተኛነት መራቅ ይበልጥ ይጎለብታል፡፡ አገረ መንግሥቱ እጅግ ወሳኝ ከሆነው ከዚህ ባህርይ እንዳያፈነግጥ፣ ማፈንገጥ ከተከሰተም ዴሞክራሲያዊነቱ የተሰለበ ሆኖ እንዳይከረክስ፣ የነፃ ብዙኃን ማኅበራት መጠናከር፣ የሕዝብ ንቁነትና የሚዲያ እውነት ፈላጊነት መስላት፣ የዴሞክራሲ መብቶች ሕይወታችን ውስጥ በሰፊው መግባት አስፈላጊ ነው፡፡ ሰዎች መብቶችን መኗኗሪያ ሲያደርጓቸው ማንም እንዳይሰርቃቸው መጠበቃቸው ነው፡፡ መብቶቻቸው እንዳይሰረቁ መጠበቅ ከቻሉ ደግሞ አገረ መንግሥታቸው እንዳይላሽቅ (ጥፋት/እንከን እያጋለጡና መጠየቅ ያለበት እንዲጠየቅ እየተጫኑ) መጠበቅ ይችላሉ፡፡

ውጤቱ አገረ መንግሥትን ከመዝቀጥ መንከበከብ ብቻ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያውያንን እንደ ሰውና እንደ ዜጋ መከበርንም ማበልፀግ ነው፡፡ ሰው በሰውነቱ ሊያገኝ የሚገባውን ክብር ለማሟላት እስከተጣጣርን ድረስ የዜግነታችንን ይዘትም ማዳበራችን አይቀሬ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ነኝ ከማለትና በኅብረ ብሔራዊ ባህልና ሕዝባዊ መተሳሰብ ውስጥ ማደግ ከሚሰጠን የአገር ፍቅርና ናፍቆት በቀር በመብት ይዘት ደሃ የሆነው ዜግነታችን፣ ሀብታም ወደ መሆን የሚጓዘው የሰብዕናን ይዘት ማጎልበትን ውሉ ማድረግ ከቻለ ነው፡፡ አዕምሯችን የፍለጠው ቁረጠውና የበደል አስተሳሰቦችን እየታገለ ከሄደ፣ ሰው አዋራጅና አጥቂ ድርጊቶችንና ልማዶችን (ማበሻቀጥን፣ ማንዘጥዘጥን፣ ደጅ ማስጠናትን፣ ጉቦኝነትን፣ ወዘተ) በየቤታችን፣ በየመንገዳችንና በየመሥሪያ ቤታችን መታገልና ማዳከም ከሰመረልን ያለ ጥርጥር መንግሥትነት በሕዝብ ላይ የተንፈራጠጠ ጌትነት እንዳይሆን የማድረግ አቅምን እናጎለብታለን፡፡

ማሽቆጥቆጥ ማንም አደረገው ማን የማይፈለግ የበዳይነት መጀማመሪያ ነው፡፡ የአገልጋይና የሹም ‹‹ሽቁጥቁጥ››/ሥጉ መሆን ግን አስተዳደራዊ የበደል ዓይነቶችን፣ የሥራ ምግባር ልሽቀትንና ሙስናን ለማሸነፍ፣ እናም ሰውና ሕዝብ አክባሪነትን ለማንገሥ አስፈላጊ ነው፡፡ የሕዝብ አገልጋዮችና ሹሞች ከታች እስከ ላይ እዚህ አጠቃላይ እሴት ውስጥ መግባትና አለመግባታቸው ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት ውስጥ መሆን አለመሆናችንንም ይጠቁማል፡፡ አንዳንዶች አገረ መንግሥት ወደ ተባያዊ ኑሮ ውስጥ መግባት አለመግባቱን የማወቅ ነገር የጥናትና ምርምር ነገር ይመስላቸዋል፡፡ የሹም ሰንሰለቱ የመንዘራጠጥና ማጅራት የመቆነን ሰንሰለት ከሆነ ተገልጋይ ማመላለስ፣ ሥራና ጉዳይ ማስተኛት የተለመደ የብዙ ሥፍራ እውነታ ከሆነ ልሽቀት መንሰራፋቱ አያከራክርም፡፡ ጥናት የሚያሻ ከሆነ የሚያሻው፣ የልሽቀቱን ጥልቀትና ስፋት በርብሮ ለመረዳት ነው፡፡ የለውጣችን አንዱ ሁነኛ ዒላማ ይህንን ሰዎችንና ተቋማትን ያላሸቀ ችግር እንዳያገረሽ አድርጎ መቀየር ነው፡፡

እዚህ መስመር ውስጥ መግባትና ታዳጊ ውጤት ማምጣት ከጀመርን፣ ዴሞክራሲያችንም ፍትሕን እኩልነትንና የዜጎች ጉልምስናን ሁለመና ተልዕኳቸው ያደረጉ ጠንካራ ፓርቲዎችን ማፍራት ከቻለ፣ ከ2014 እስከ 2018 ዓ.ም. ባለው ጊዜና ከዚያም በኋላ፣ ማኅበራዊ ንቃታችንና የዴሞክራሲ ጉንጫችን በሚችለው ልክ መጥኖ መሰነቅንና መተግበርን ካወቅንበት በእርግጥ ተስፋ አለን፡፡ ተስፋችን ደግሞ ኪሽ ኪሽ ተስፋ አይደለም፡፡ አገረ መንግሥትን እንዳይነቅዝና ከሕግ በላይ እንዳይሆን አድርጎ የማደራጀትና ነቅቶ የመጠበቅ የአሁን ፈተናችንን በውጤታማነት አልፈን፣ ኅብረተሰብን በመንከባከብ ባህርይ የጎለመሰ አገረ መንግሥት የምንጎናፀፍበት ጊዜ ይመጣል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...