የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቅርቡ የተለያዩ መመርያዎችን ማውጣቱ ይታወሳል፡፡ እነዚህ መመርያዎች የፋይናንስ ተቋማትን ሊጫኑ ይችላሉ የሚሉ አስተያየቶች እየተሰሙ ነው፡፡ ከእነዚህ መመርያዎች መካከል ባንኮች በብሔዊ ባንክ ማስቀመጥ ያለባቸው የመጠባበቂያ ገንዘብ መጠን በእጥፍ እንዲያድግ መደረጉ አንዱ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ባንኮች ከሚሰጡት ብድር አንድ በመቶውን ለቦንድ ግዥ እንዲያውሉ የሚያስገድድ መመርያ ሲሆን፣ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ደግሞ ከዓመታዊ ትርፋቸው 15 በመቶውን ለቦንድ ግዥ ማዋል እንዳለባቸው የሚደነግገው መመርያም ይጠቀሳል፡፡ በእነዚህ መመርያዎችና በወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ ላይ ጎምቱውን የኢንሹራንስ ባለሙያ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉን ዳዊት ታዬ አነጋግሯቸዋል፡፡ አቶ ኢየሱስ ወርቅ በአሁኑ ወቅት ኅብረት ባንክ ቦርድ ሊቀመንበር፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ የባንክ ዳይሬክተሮች የምክክር ማኅበር ሰብሳቢ በመሆንም እየሠሩ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ኢንዱስትሪውን የተመለከቱ አዳዲስ መመርያዎችን ሰሞኑን አውጥቷል፡፡ እነዚህ መመርያዎችን በተመለከተ የሚነግሩን አለ? እነዚህ መመርያዎች በፋይናንስ ኢንዱስትሪው ላይ ጫና ያሳድራሉ የሚልም ሐሳብ የሚሰነዝሩ አሉ፡፡ እርስዎ በዘርፉ ውስጥ የቆዩ ስለሆነ በተለይ በመጠባበቂያ ገንዘብ ጭማሪ ወጪና አዲስ በወጡት የቦንድ ግዥ መመርያዎች ላይ ያለዎት ሐሳብ ምንድነው?
አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- ከኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር የተሻለ ነገር እጠብቅ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በኩል የወጡት መመርያዎች ከድሮ የተሻሉ አልሆኑም፡፡ ምናልባትም እንደተባለው ብዙዎቹም እያመለከቱ እንዳሉት ወደኋላ የሄደ ይመስላል፡፡
ሪፖርተር፡- ወደኋላ እየሄደ ነው የሚባለው ከምን አንፃር ነው?
አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- ብሔራዊ ባንክ ሰሞኑን ካወጣቸው መመርያዎች አንዱ፣ ከዚህ ቀደም ባንኮች በብሔራዊ ባንክ ይቀመጥ የነበረውን የመጠባበቂያ ገንዘብ ይመለከታል፡፡ አምስት በመቶ እንደ መጠባበቂያ (ሪዘርቭ) ተደርጎ በብሔራዊ ባንክ እንዲያስቀምጡ ይገደዳሉ፡፡ ይህንን ገንዘብ ያለ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ባንኮቹ በምንም መንገድ ሊነኩት አይችሉም፡፡ አሁን የመጠባበቂያ ገንዘቡ በእጥፍ እንዲጨምርና አሥር በመቶ እንዲሆን አደረጉት፡፡ የዚህ መነሻው ምንድነው ብለን ስንጠይቅ፣ ብዙ ነገሮችን ያስታውሰናል፡፡ በ2008 ዓ.ም. የነበረውን እዚህ ላይ ላስታውስህ፡፡ የፋይናንስ ዘርፉ የተወሰኑ ሰዎች ተፅዕኖ ስላመጡ ይህንን መለወጥ አለብን በሚል፣ በስም ተጠቅሰው በነበሩ ሰዎች ምክንያት መመርያ እስከ ማስተካከል የደረሱበት ጊዜ ነበር፡፡ በወቅቱ እንደተነገረኝ እነዚህ ተፅዕኖ ይፈጥራሉ የተባሉ ሰዎች የማንፈልገውን ዓይነት ተፅዕኖ እያመጡ ስለሆነ፣ ሕጉን እናስተካክላለን በሚል ብዙ ነገሮችን አደረጉ፡፡ ከእነዚህም መካከል አንዱና መነሻው ራሱ ትክክል አይደለም ብዬ የማምነው፣ የብሔራዊ ባንክ ተጠሪነትን ለፖለቲካው እንዲሆን አደረጉት፡፡
ሪፖርተር፡- ግልጽ ቢያደርጉልኝ? የብሔራዊ ባንክ ተጠሪነት ለማን መሆን ነበረበት ይላሉ?
አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- በእኛ አገር ብሔራዊ ባንክ ቀጥታ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲሆን ነው የተደረገው፡፡ በዓለም ላይ ያሉት አብዛኞቹ ብሔራዊ ወይም ማዕከላዊ ባንኮች ለፓርላማ ነው ሪፖርት የሚያደርጉት፡፡ ምክንያቱም የአስተሳሰብም፣ የድርጊትም ነፃነት እንዲኖራቸው በሚል በብዙ አገሮች ማዕከላዊ ባንኮች ለፓርላማ ሪፖርት እንዲያደርጉ ሆነው ነው የሚሠሩት፡፡
ሪፖርተር፡- አሁንም እኮ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለፓርላማ ሪፖርት ያደርጋል፡፡
አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ የተቀመጠውን ነው የምነግርህ፡፡ በፊት የነበረው ተቀይሮ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪፖርት እንዲያደርግ ነው የሚጠቅሰው፡፡ ይህ ማለት የፖለቲካ መሪው ኢኮኖሚውን እንደፈለገ እንዲያደርገውና ገንዘብ ማሠራጨት እንዲችል ሁሉ ነው የፈቀደው ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ይህ ከሆነ ትንሽ ቆይቷል፡፡ በ2008 ዓ.ም. የተደረገ ነው፡፡ ለማንኛውም የፋይናንስ ዘርፉን የሚመለከቱ የተለያዩ ነገሮች ተደረጉ፡፡ አንድ ሰው በሁለት የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ዳይሬክተር አይሆንም ብለው ያወጡትም መመርያ የሚታወስ ነው፡፡ የዳይሬክተሮችን የአገልግሎት ዘመን እንዲገድብ ማድረጋቸውም አይዘነጋም፡፡ እንዲህና ሌሎች ብዙ ነገሮችን ለመገደብ መመርያ አወጡ፡፡ ይህንን ሁሉ ችለን ተቀምጠን ነበር፡፡ ከጥቂት ጊዜ በፊት ምናልባት አሁን ያለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አመራር ቁምነገር ሠራ ብለን ያሰብነው፣ ባንኮች በግዳጅ ከእያንዳንዱ ከሚሰጡት ብድር 27 በመቶ አሥልተው ቦንድ ይግዙ የሚለውን እንዲቀር ማድረጉ ነበር፡፡ 27 በመቶ በሚወሰድበት ጊዜ ራሱ እጅግ በጣም ፍትሐዊ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ባንኮቹ ለቆጣቢዎች አምስት በመቶ ወለድ እንዲከፍሉ ትዕዛዝ አወጡና እነሱ ግን የሚወስዱትን 27 በመቶ፣ ሦስት በመቶ የሚታሰብበት አድርገው ያዙት፡፡ ከጊዜ በኋላ ለአስቀማጮች ሰባት በመቶ እንዲከፈል ብለው መመርያ ሲያወጡ፣ ከባንቹ የሚወስዱት 27 በመቶ የቦንድ ግዥ አምስት በመቶ እንዲታሰብለት አደረጉ፡፡ እዚህ ላይ መነሳት ያለበት ነገር ከየባንኮቹ ለቦንድ ግዥ ተብሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይሰበስብ የነበረው ገንዘብ እንዳለ ሆኖ፣ ባንኮች ከብሔራዊ ባንክ ብድር ሲጠይቁ የሚታሰብባቸው ወለድ ከፍተኛ ሆኖ መገኘቱ ነው፡፡ ይህም ባንኮች አንዳንዴ የገንዘብ እጥረት ይገጥማቸዋልና እጥረታቸውን ለመወጣት ከብሔራዊ ባንክ ገንዘብ የሚበደሩበት አሠራር አለ፡፡ እንግዲህ ቀደም ሲል በሦስት በመቶ፣ በኋላ ደግሞ በአምስት በመቶ ወለድ የሚወስዱትን ገንዘብ እንደገና ብሔራዊ ባንክ ለባንኮቹ ሲያበድር 13 በመቶ ወለድ አስቦ ነው የሚበድሯቸው፡፡ ይህ ማለት ብሔራዊ ባንክ ይህንን የሚያደርገው ባንኮች የገጠማቸውን ጊዜያዊ የገንዘብ እጥረት እንዲወጡበት ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ትርፍ መሥሪያ ይጠቀምበት እንደነበር ነው፡፡ ስለዚህ ቀደም ብሎ ይተገበር የነበረው አስፈላጊ ያልሆነ ነገር ባንኮች ላይ የፈጠረው ጫና ሳያንስ፣ አሁን እንደገና በሌላ መንገድ እንደ ሰሞኑ ያሉ አስገዳጅ መመርያዎች መውጣታቸው ፈጽሞ ተገቢ አይደለም በማለት ፈልጌ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ከሰሞኑ መመርያዎች አንዱ ባንኮች በብሔራዊ ባንክ የሚያስቀምጡትን የመጠባበቂያ ገንዘብ መጠን፣ ከአምስት ወደ አሥር በመቶ እንዲያድግ መመርያ መውረዱ ነው፡፡ ይህ በእርስዎ ምልከታ አንድምታው ምንድነው? መመርያው ባንኮች ለዋጋ ግሽበቱ አስተዋጽኦ ነበራቸው የሚል ይመስላል፡፡
አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- መጠባበቂያ የሚቀመጠው አምስት በመቶ ገንዘብ ምንም ወለድ አይከፈልበትም፡፡ ይህ አንድ ጉዳይ ነው፡፡ ብሔራዊ ባንክ ይህንን ገንዘብ ዝም ብሎ ነው የሚወስደው፡፡ ገንዘብ ባዶውን ወይም ፆሙን አያድርም፡፡ አንድ ቦታ ተዘግቶ አይቀመጥም፡፡ መንግሥት ለፈለገው ነገር እንዲውል ነው የሚያደርገው፡፡ ‹‹አንቺው ታመጪው አንቺው ታሮጪው›› ሆነና፣ አሁን ባንኮችን ለዋጋ ንረት ተጠያቂ ማድረግ አይገባም፡፡ በመጀመርያ ደረጃ ለዋጋ ንረቱ መባባባስ ተጠያቂው ማነው? ባንኮች የሚያበድሩት ገንዘብ ነው ተብሎ አይታሰብም፣ አይሆንምም፡፡
ሪፖርተር፡- ሊሆን የሚችልበት ዕድል ግን ይኖራል፡፡ ምክንያቱም ባንኮች ለሚሰጡት ብድር የሚጠይቁት የወለደ ምጣኔ ከፍ እያለ ከመጣ የዋጋ ንረት ምክንያት ሊሆኑ እኮ ይችላሉ?
አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- እሱ ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ በቲዮሪ ሊሆን ይችላል፡፡ አሁን ግን ይኼ የሆነው በእሱ የመጣ ጉዳይ ሳይሆን፣ ወይም ስለመጣ ለመሆኑ ምንም ማረጋገጫ በሌለበት ያንን መጠባበቂያ የተባለውንና ከአምስት በመቶ ወደ በአንድ ጊዜ አሥር በመቶ ማድረጉ ተገቢ አይደለም፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት ባንኮችን ችግር ውስጥ አስገብቷቸው የነበረው፣ ተበዳሪዎቻቸው በተለያዩ ምክንያቶች ቃል በገቡበት ጊዜ ብድሩን መክፈል ባለመቻላቸው ነው፡፡ መክፈል ሲያቅታቸው የማስታመሚያ ጊዜ እየተባለ እስከ ሦስት ጊዜ ድረስ ማስተካከያ ይደረግላቸው ነበር፡፡ ይህንን ሦስት ጊዜ የነበረውን ስድስት ጊዜ እንዲሆን አደረጉት፡፡ በተለይ ኮቪድ-19 ከመጣ በኋላ ተበዳሪዎች ችግር ውስጥ እየገቡ ስለሆነ ሊወድቁ ይችላሉና እስከ ስድስት ጊዜ የማገገሚያና የማስታመሚያ ጊዜ ይሰጥ ተባለ፡፡ ይህ ማለት ውጭ ያለው ገንዘብ እያደገ፣ እያደገ ይመጣል፡፡
ሪፖርተር፡- ይህ ማለት የብድሩ ጊዜ በመራዘሙ ወለዱ እየጨመረ ስለሚሄድ ማለት ነው?
አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- አዎ፡፡ ምክንያቱም በብድር የተሰጠና ውጭ ያለው ገንዘብ በጊዜው ካልተከፈለ እያበጠና እየጨመረ ነው የሚሄደው፡፡ እንዲህ ያለ ሁኔታ ባለበት ጊዜ የውጭ ተወዳዳሪ ባንኮች እንዲገቡ ስላልፈቀድን ነው ባንኮች ትልልቅ ትርፍ እያገኙ ያሉት፡፡ ይህንን እንደ አንድ ልዩ ነገር እንዲያደርጉ እየተቆጠረ ባንኮች በዚህ በኩል ይህንን አድርጉ፣ በዚያ በኩል ያንን አድርጉ እየተባሉ ነው፡፡ እኔ በእውነቱ ባንኮች የራሳቸው የኮርፖሬት ማኅበራዊ ኃላፊነት አላቸው፡፡ ከባቢው ጥሩ ሆኖ እንዲቆይ፣ ኢኮኖሚ እንዳይጎዳ፣ አልፎ አልፎ ሕዝብ ላይ ጉዳት በሚደርስበት ጊዜ መደጎሚያና መቋቋሚያ ባንኮች የሚቻላቸውን ያህል ማድረጋቸው አይገባም ብዬ አልከራከርም፡፡ ነገር ግን ለሁሉም ነገር ለከት ያስፈልገዋል፡፡ እንዲያው ዝም ብሎ በነጋ በጠባ ምክንያት እየፈጠሩ ባንኮቹ ላይ አላስፈላጊ ጫና ማድረግ፣ በባንኮቹ በኩል ይደረግ የነበረውን ወይም የማድረግ ፍላጎት በሚታይ ደረጃ ሊቀንሰው ይችላል ብዬ አስባለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- እነዚህ መመርያዎች የዚህን ያህል ጫና ሊኖራቸው ይችላል ብለው ያምናሉ?
አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- አዎ፡፡ ምክንያቱም በብሔራዊ ባንክ የሚቀመጠው መጠባበቂያ አምስት በመቶ ተቀማጩን አሥር በመቶ ማድረግ፣ ይህ ገንዘብ ደግሞ ያለ ምንም ወለድ የሚቀመጥ በመሆኑ በባንኮች ላይ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡ ለምሳሌ ጠቀም ያለ ገንዘብ ለረዥም ጊዜ የሚያስቀምጡ ቆጣቢዎች እስከ 13.5 በመቶ ወለድ እየተሰጣቸው ነው፡፡ ባንኮች እስከ 13.5 በመቶ ወለድ ከፍለው የሰበሰቡትን ገንዘብ ነው እንግዲህ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያለ ምንም ወለድ ወስጄ እኔ ለምፈልገው ነገር አውለዋለሁ የሚለው፡፡ ይህ ትልቅ ተፅዕኖ ነው የሚሆነው፡፡ ይኼ ራሱ ለባንኮቹ በሒደት የሚታይ ትንሽ ነው የማይባል ተፅዕኖ ያሳድርባቸዋል ብዬ እሠጋለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- ከሰሞኑ ከወጡ መመርያዎች ሌላው ደግሞ ባንኮች ከሚያበድሩት ገንዘብ አንድ በመቶ ለቦንድ ግዥ ማዋል አለባቸው የሚለው ነው፡፡ ይህ መመርያ ከዚህ ቀደም ባንኮች 27 በመቶ የቦንድ ግዥ ይፈጽሙ ተብሎ ይሠራበት ከነበረው አሠራር ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ እየተገለጸ ነውና ይህንን መመርያስ እንዴት አዩት?
አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- ሌላው አሳዛኝ ነገር ደግሞ ይህ ነው፡፡ ባንኮቹ ከአሁን ጀምሮ ካበደሩት ጠቅላላ ገንዘብ አንድ በመቶ የሚሆነውን የልማት ባንክ ቦንድ እንዲገዙ አስገዳጅ ሆኖ መምጣቱ እጅግ በጣም የሚከብድ ነው፡፡ ይህ እጅግ በጣም የሚደንቅ ነገር ነው የሆነብኝ፡፡ በተለይ ልማት ባንክ ከሚያበድረው ገንዘብ አብዛኛው የተበላሸ ብድር ሆኖ የትም ተበትኖ የቀረ ነው፡፡ እንዲያውም መጥፎ ብድሮች በተቻለ መጠን ወደ ልማት ባንክ እንዲዛወሩ እየተደረገ፣ የማይከፈሉ ዕዳዎች ሆነው ተቀምጠዋል፡፡ ባንኩ አሁን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተሻለ ሥራ ሠራ ቢባልም፣ አሁንም ችግር አለበት፡፡ አንደኛ ነገር ልማት ባንክ የሚያበድራቸው ተበዳሪዎች እኮ የግል ባንኮችም ተበዳሪዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ የልማት ባንክን ቦንድ የሚገዙበት ምክንያት ምንድነው? ያው እንግዲህ መጀመርያውኑም በብሔራዊ ባንክ የነበረ አስተሳሰብ ነው፡፡ አሁንም በልማት ባንክ በኩል የሚታየው ደግሞ የሚደንቀው ይህንን ተቀማጭ ገንዘብ ቦንድ ይገዛበት የተባለው፣ በአሁኑ ጊዜ በኢንሹራንስ ኩባንያዎች ላይም አድርገውታል፡፡ ኢንሹራንሶቹን የሚመድብ እንዲሆን በመጀመርያ ደረጃ የተከፈለ ካፒታላቸውን 15 በመቶ የሚሆነውን ‹‹ሳቹተሪ ዲፖዚት›› በሚል ስም ብሔራዊ ባንክ ሲሰበስብ ቆይቷል፡፡ አሁን እንደገና ከዓመታዊ ትርፋቸው 15 በመቶ የልማት ባንክን ቦንድ እንዲገዙ ተብሏል፡፡ ልማት ባንክ አሁን ባለው ሁኔታ ወለድ የሚከፍለው ቢበዛ ዘጠኝ በመቶ ነው፡፡ ለአስቀማጭ የሚከፈለው ሰባት በመቶ ስለሆነ ሁለት በመቶ ነው ተጨማሪ ይከፍላል የሚባለው፡፡ ስለዚህ ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት በባንኮች በኩል 13.5 በመቶ በሚሆን ወለድ ጭምር ተቀማጭ ገንዘብ እያሰባሰቡ፣ በዘጠኝ በመቶ ብድር መስጠት በምንም ሁኔታ ትክክል አይደለም፡፡ አዲሱ መመርያ የሚለየው ደግሞ ቦንድ የሚገዙት ከሚሰጡት የብድር መጠን ላይ ተሰልቶ መሆኑ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ባንኮቹ ያላቸው የብድር መጠን በብዙ ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ከምታበድሩት ብድር አንድ በመቶውን ለቦንድ ግዥ አውሉ ሲባል፣ ይህ ገንዘብ ቀላል የሚባል ገንዘብ አለመሆኑን ያሳያል፡፡ በጣም ብዙ ገንዘብ ነው፡፡ ባንኮች በትልቅ ወለድ የሰበሰቡትን እየወሰደ በአነስተኛ ወለድ እንደ ተወዳዳሪ የሚታይ ባንክን ቦንድ ግዙ መባሉ ራሱ በፍፁም አይገባኝም፡፡
ሪፖርተር፡- ከለውጡ ወዲህ ብሔራዊ ባንክ በርካታ ለውጦችን አድርጓል፡፡ እያካሄደ ባለው ሪፎርም ብዙ ነገር ማስተካከሉ ይታወቃል፡፡ ከዚሁ አንፃር እርስዎም በአንድ ወቅት ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነግረውኝ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ አሁን ያወጣቸው መመርዎች ደግሞ ነገሮችን ወደኋላ የሚመልሱ ናቸው ብለውኛል፡፡ ብሔራዊ ባንክ ለውጥ አሳይቷል ተብሎ ከሚጠቀሱት ውስጥ ደግሞ፣ ከለወጡ በኋላ ባንኩ በሚያወጣቸው መመርያዎች ላይ ባንኮች እንዲመክሩበት ማድረጉ ስለሆነ ከሰሞኑ ባወጣቸው መመርያዎች ላይ ምክክር ተደርጓል?
አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- በእርግጥ ብሔራዊ ባንክ ያሻሻላቸው ነገሮች ነበሩ፡፡ አሁን ግን ይህ አልሆነም፡፡ ብሔራዊ ባንክ እነዚህን መመርያዎች ሲያወጣ አልተመከረባቸውም፡፡ እኔ እንደሚገባኝ ግን የእነዚህ መመርያዎች ተነሳሽነት ከብሔራዊ ባንክ አይደለም፡፡ የእሱ ውሳኔም አይደለም፡፡
ሪፖርተር፡- እንዴት? መመርያዎቹን ያወጣው እኮ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ነው፡፡
አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- ይህንን ልነግርህ እችላለሁ፡፡ የፈለገ መሥሪያ ቤት ሊጠይቀኝ ይችላል፡፡ በቅርቡ የወጡት አስገዳጅ መመርያዎች የብሔራዊ ባንክ ውሳኔዎች አይደሉም፡፡ የአጋጣሚ ነገር ሆነና የዛሬው ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቺፍ ኢኮኖሚስትና ምክትል ገዥ ነበሩ፡፡ እስካሁን እስከማውቀው ድረስ በቀጥታ ለማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ ነው የሄደው፡፡ ውሳኔውም የተሰጠው በማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ ነው፡፡ በዚህ እጅግ በጣም አዝናለሁ፡፡ ከዚህ ቀደም ዕድል ተሰጥቶኝ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፊት የተናገርኩት ነው፡፡ የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ አባላትን አንድ በአንድ የማውቃቸው፣ የምወዳቸውና የማከብራቸውም ሰዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን በዚህ ጉዳይ ሌላው ቢቀር ውይይት እንዲደረግበት ያስፈልግ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ እዚህ ዘርፍ ውስጥ እንደቆየ ኢትዮጵያዊ ስመለከት፣ ስለግል ዘርፉ ከመወራቱና ከመዘመሩ በቀር አሁንም ቀደም ያለውን የዕዝ አኮኖሚ ነው በተግባር የማየው በበኩሌ፡፡ ይህንንም ያለ ምንም ፍራቻና ይሉኝታ እናገራለሁ፡፡ በፋይናንስ ዘርፉ የአስተሳሰብ ለውጥ የለም፡፡ የፋይናንስ ዘርፉ በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ ምንጊዜም ጫጩት፣ አቅም የሌለንና የመወዳደር ዕውቀቱም ሆነ ጉልበቱ የሌለን ባንኮች ሆነን እንቆያለን፡፡ በዚህ ሁኔታ ተወዳዳሪ ባንክ ለመፍጠርም አስቸጋሪ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሰሞኑን መመርያዎች ለማውጣት ምክንያት ከሆኑት ጉዳዮች በዋናነት ያስቀመጠው የዋጋ ንረትን ለመከላከል ሲባል የወሰድኩት ዕርምጃ ነው የሚል ነው፡፡ ይህ ምክንያቱ ጥያቄ ሊያስነሳ ቢችልም አሁን ለሚታየው የዋጋ ንረት ባንኮችም የራሳቸው አስተዋጽኦ እንዳላቸው ግን ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ለማንኛውም ወቅታዊው የኢትዮጵያ አጠቃላይ የዋጋ ንረት መንስዔስ ምንድነው ብለው ያምናሉ?
አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- በዚህ ጉዳይ ላይ ሥረ መሠረቱን መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ የዋጋ ንረት መንስዔው ምንድነው? ማነው የፈጠረው? የዋጋ ንረት ዛሬ የጀመረ አይደለም፡፡ ቀደም ብሎም የነበረ ነው፡፡ ኢንቨስትመንት በሙሉ በባንክ ዘርፍ ላይ ሳይሆን፣ ለዕይታ ደስ የሚሉ ነገሮች አሉ፡፡ እጅግ በጣም ብዙ ገንዘብ እየወጣባቸው ያሉ ማለት ነው፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች ግን ሕዝቡ በሚፈልጋቸው የፍጆታ ዕቃዎችም ሆነ አገልግሎቶች ላይ አንድ ኪሎ የሚጨምሩ አይደሉም፡፡ ስለዚህ አሁን በአገራችን የሚታየው የዋጋ ንረት መሠረቱ የፍጆታ ዕቃዎች መወደድ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ምግብ ነክ ምርቶች ላይ በሰፊው ይታያል፡፡ እዚህ ላይ መነሳት ያለበት እርሻ የሚፈልገውን ትኩረት ሰጠን ወይ? የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በመጀመርያው የኢሕአዴግ ፕሮግራም ‹‹አግሪካልቸራል ዴቨሎፕመንት ኢንዱስትራላይዜሽን›› ተብሎ በሚጀመርበት ጊዜ አንዳንዶቻችን ጣታችንን አውጥተን፣ ‹ያሉንን ይበሉን ብለን ይህንን ማለታችሁ ጥሩ ነው፡፡ በአጠቃላይ ትኩረታችሁ ግን አርሶ አደሩ ላይ ነው፡፡ ይህም ቢሆን ይደገፋል፡፡ መጥፎ አይደለም፡፡ ነገር ግን መንግሥት ይህንንን ድጋፍ ለደሃው ለአርሶ አደር እንደ መስጠቱ በግል በአነስተኛ ደረጃም ቢሆን 50፣ 100 እና 200 ሔክታር ኮሜርሻል ፋርሚንግ (ትርፋማ አምራቾች) ውስጥ መግባት የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን በበጀት ድጋፍ ባትሰጧቸው መሰናክል አትሁኑባቸው፣ አበረታቷቸው› ብለን ነበር፡፡ ምክንያቱም ከሚበሉትና ከሚጠጡት ውጪ ምርት ማምረት የሚችሉት ትርፋማ አምራቾች ናቸው፡፡ ይህ ይታወቃል ብለናል፡፡ በስልሳዎቹ እኮ ‹‹ግሪን አግሪካልቸር›› ተብሎ ደሃ አርሶ አደሩ ላይ ብቻ በተሠራበት ጊዜ ለአገሩ ሕዝብ ትንሽ ተጨማሪ ሩዝ እንጂ የተፈለገውን ለውጥ አላመጣም ነበር፡፡ እኛም አገር የሆነው ይኼው ነው፡፡ አሁንም የፍጆታ ዕቃዎች ምርት ላይ ኢንቨስትመንቱ ካላጋደለ ችግራችን አይቀረፍም፡፡ ሌላው ‹‹ኢንፖርትድ›› የዋጋ ንረት የሚባል ነገር አለ፡፡ በተለይ ከውጭ የምናስገባቸው ዕቃዎች አሉ፡፡ ለነገሩ ሁልጊዜ የሚወራውና የምንሰማው ከወጪ ንግድ የምናገኘው ገቢ እያነሰ መሄድ ነው፡፡ ረሚታንስ ቀነሰ ብለን ስናማርር ነው የሚታየው፡፡ ግን ያለንን የውጭ ምንዛሪ በጥሩ ሁኔታ እያስተዳደርነው ነው ወይ? ሜዳ ላይ የሚታየው ብልጭልጭና የፕላስቲክ ዕቃ በምንድነው የሚመጣው? ሌላው ቢቀር እንኳን አገራችን በዓለም ደረጃ ታዋቂ የሆነ አበባ አምራች ሆና ሳለ፣ ወረቀትና የፕላስቲክ አበባ በውጭ ምንዛሪ እየተገዛ ሲገባ ያሳዝናል፡፡ እንዲህ ባለው ጉዳይ አዝናለሁ፡፡ አገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም የሚለውን ተከትዬ በጣም ፖዘቲቭ መሆን ጀምሬ ነበር፡፡ ግን አዲስ የኢኮኖሚ መርህ ሳይሆን የድሮው ዕሳቤ ነው እስካሁን ድረስ አሸናፊ ሆኖ ያለው፡፡ እናም አዲሶቹ ወጣት የኢኮኖሚ ዘዋሪ ምሁራንና ሹማምንቶቻችን ከድሮዎቹ መዳፍ ውስጥ አምልጠው መውጣት አልቻሉም ብዬ ነው የማስበው፡፡
ሪፖርተር፡- ከውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምና እርስዎ እንዳሉትም ለብልጭልጭ ነገሮች ግዥ የውጭ ምንዛሪ ማውጣቱ ሲታሰብ፣ ከውጭ የሚገቡ ሌሎች ዕቃዎች የሚገቡት ባንኮች በሚፈቅዱት የውጭ ምንዛሪና ብድር ነው፡፡ እንዲሁም እርስዎ እንደጠቀሱልኝ ለተቀማጭ እስከ 13.5 በመቶ ባንኮች ወለድ መክፈላቸው ራሱ የሚያሳየው፣ በዚህን ያህል ወለድ ያስቀመጡትን ገንዘብ መልሰው ሲያበድሩ የወለድ ምጣኔው ከፍተኛ መሆኑ አይቀርም፡፡ እንዲህ ያሉ አሠራሮች ባንኮች ለዋጋ ንረቱ መንስዔም ናቸው የሚል ሥዕል አይሰጡም? ለዚህ የባንኮቹ ሚና አይኖርም ይላሉ?
አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- ባንኩ እኮ ፖሊሲ አይሠራም፡፡ ወደ አገር የሚገቡት ዕቃዎች ምን መሆን አለባቸው? ምን መሥፈርት መሟላት አለባቸው? የሚለውን ባንኮች ሳይሆኑ መንግሥት ነው ይህንን ማስተካከል ያለበት፡፡ በእውነቱ በዚህ ረገድ ባንኮቹን ማማቱ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ የሆነው ሆኖ ከሰሞኑ የወጣው ኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያ አለንጋውን በሙሉ ባንኮች ላይ ማሳረፍ አይገባውም፡፡ በመሠረቱ ኢንቨስተሮቹ ባለቤት ነን ብለን ብናስብም፣ በአሁኑ ጊዜ ባለቤትነታችንን በብጣሽ ወረቀት ብሔራዊ ባንክና ልማት ባንክ እየገፈፉን ነው፡፡ ኢንሹራንሶችም ቢሆኑ አትርፋችሁ 15 በመቶውን የልማት ባንክ ቦንድ ይገዛበት የሚባለው ነገር፣ ሥራ ተሠርቶ ዓመት ጠብቀን ተገኘ የተባለው ትርፍ እንዲህ ነው የሚሆነው? ስታስበው እኮ አብዛኞቹ ባንኮች ራሳቸው ትልቅ ትርፍ ሠሩ የሚባሉት የዋጋ ንረቱን ያህል የትርፍ ክፍፍል (ዲቪደንድ) አያገኙም፡፡
ሪፖርተር፡- እንዴት?
አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- በአሁኑ ጊዜ እኮ የዋጋ ንረቱ ከ20 በመቶ በላይ ነው፡፡ አንዳንድ ባንኮች እኮ ዲቪደንት የከፈሉት ከ20 በመቶ በታች ነው፡፡ የተወሰኑት እኮ ናቸው ብዙ የሚከፍሉት፡፡
ሪፖርተር፡- የባለቤትነት ነገር ከተነሳ በተደጋጋሚ እየቀረበ ያለ አንድ ነገር አለ፡፡ ይህም ባንኮች ካላቸው ጠቅላላ ሀብት አንፃር የየባንኩ ባለአክሲዮኖች አስተዋጽኦ ሲታይ አሥር በመቶ የሚሞላ አለመሆኑ ነው፡፡ ይህንን ዓይነቱን ምልከታ ጠቅላይ ሚኒስትሩና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥም ሲናገሩ ተሰምቷል፡፡ በተለይ ገዥው ባንኮች ከያዙት ሀብት ውስጥ የባለአክሲዮች ድርሻ 10 በመቶ አካባቢ በመሆኑ ቀሪው የሕዝብ ሀብት ስለሆነ፣ ይህንን የመቆጣጠር ኃላፊነት አለብን ብለዋል፡፡ ይህንን አባባል እንዴት ይመለከቱታል?
አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- በመጀመርያ ደረጃ ባንክ አቋቁሜ በምሠራበት ጊዜ፣ ከገንዘብ አስቀማጮች ገንዘብ ሰብስቤ በምሠራበት ጊዜ ብክነት ገጥሞኝ፣ ወይም ሳላውቅበት ያለ አኳኃኑ የሥራ ጉድለት ገጥሞኝ ብከስር ባለአክሲዮን እንጂ ብሔራዊ ባንክ አይደለም የሚጠይቀው፡፡ እኛ እኮ ነን ኃላፊነት የወሰድነው፡፡ ኃላፊነቱ የባለአክሲዮኖች ነው፡፡ ባለሀብቶች ያላቸው መጠን ይህንን ያህል ነው መባሉ የብዙ ግራ ዘመም አስተሳሰብ ያጠቃቸው ምሁራንና ተማሪዎች አስተሳሰብ ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ኃላፊነት ወስደን ነው ገንዘብ ከአስቀማጮች የምንሰበስበው፡፡ የችግሩ ገፈት ቀማሾች ባለቤቶች ናቸው፡፡ እኛ ዓለም አቀፍ አሠራር ነው የምንከተለው፡፡ ኢትዮጵያውን ከሌላው ዓለም አቀፍ አሠራር ተለይተን እንሥራ ብንል ከሌላው አገር ጋር ተወዳዳሪ አንሆንም፡፡ ይህ የግንዛቤ ክፍተት ነው የሚመስለኝ፡፡ በአጠቃላይ አሁን ያለው ሁኔታ እንዴት እንደሚስተካከል አላውቅም፡፡ ያው የኢንሹራንስ ሰው በመሆኔ ሁልጊዜ ነገ ከዛሬ ይሻላል ብዬ የማምን በመሆኑ እስከ ዛሬ ኖሬያለሁ እንጂ፣ አንዳንድ ጊዜ ነገሮች ተስፋ አስቆራጭ ሆነው ነው የማያቸው፡፡ አሥር በመቶስ ቢሆን ማንን ይጎዳል? እንዲህ ዓይነት ሐሳብ አለ፡፡ ይህንን በኢኮኖሚው ሁኔታ አገናዝበን ተንትነን ስንመለከተው፣ ይኼ ቢሆን ይኼ ይሆናል ማለት ምን ይገዳል? ዞሮ ዞሮ ሥልጣኑ ባለንበት ሁኔታ እሺም አልን ዕንቢ ያው በትዕዛዝ መልክ ነው የሚመጣው፡፡ ነገር ግን መመካከር ጥሩ ነበር፡፡
ሪፖርተር፡- እንደ ገለጻዎ ከሰሞኑ የወጡት መመርያዎች ጫና የሚፈጥሩ ከሆነ መፍትሔውስ ምንድነው ይላሉ?
አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- እኔ ብቻዬን ይህ ይሁን የምለው ነገር አይደለም፡፡ ባንኮቹ ባለቤት አላቸው፡፡ እነዚህ ባለቤቶች የሠለጠነ የባንክ ባለሙያ ቀጥረዋል፡፡ ባለቤቶችና የባንክ ሥራ አስፈጻሚዎች አንድ ላይ ሆነው መምከርና ይበጃል የሚሉትን ሐሳብ መስጠት ነው ያለባቸው፡፡ ለምሳሌ እኔ ነገሩ ስለረበሸኝ በአሁኑ መንፈሴ መልሱ ይኼ ነው ብዬ አልልህም፡፡
ሪፖርተር፡- የመመርያዎቹ ተፅዕኖ ምን ሊያደርስ ይችላል?
አቶ ኢየሱስ ወርቅ፡- እንደ ግለሰብ አሁን ባለኝ መንፈስ ቢበዛ ያለኝን ኢንቨስትመንት ይዤ እቀጥላለሁ እንጂ፣ አሁን በማየው ሁኔታ ባንክ ወይም ኢንሹራንስ ውስጥ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት አላደርግም፣ ተፅዕኖው እስከዚህ ድረስ ያስኬዳል፡፡