Thursday, March 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የዋጋ ንረት ከህልውና ማስከበር ያልተናነሰ ቦታ ሊሰጠው ይገባል

የተጠናቀቀው 2013 ዓ.ም. እንደ አገር በብርቱ የተፈተነበት ዓመት ነው፡፡ እዚህም እዚያም የሚለኮሱ ሰው ሠራሽ ፀቦች አገር ተለብልባለች ዜጎች ተጎድተዋል፡፡ ከአንድነት ይልቅ ከፋፍለህ ግዛው በሚል የሰከሩ ቡድኖች ስቃይዋን ለማባስ ብዙ የደከሙበት፣ አይሳካላቸው እንጂ ይችን አገር ለመበታተን ያሴሩት ሴራ አገርን በእጅጉ ጎድቷል፡፡ ኢትዮጵያ ስትፈልግ ትፍረስ በማለት በግልጽ በአባባይ ለጆሮ ሰቅጣጭ የሆኑ ቃላትን ደግመን በመስማት በእኩይ ኢትዮጵያውያኑ ድርጊት የተቆጨንበት ዓመት ነው፡፡ የኢትዮጵያን እንደ አገር መቀጠል ደንታቸው ያልሆኑ ወገኖች የሸረቡበት ሴራ ይህንንም አደገኛ አመለካከታቸውን ለመቀየር የሄዱበት ርቀት ግን አሁንም ዋጋ ማስከፈሉ አልቀረም፡፡ አሁንም እያስከፈላት ነው፡፡ ለአንድ አገር ከዚህ የበለጠ አደጋ የለም፡፡ ኢትዮጵያ ግን እነሱ እንዳሰቡት የምትፈርስ አይደለችም፡፡ ሕመሟ ቢበረታ እንኳን የማትፈርስ መሆኑን ልጆቿ አንድ ሆነው በመነሳት ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሱ አካላትን ሁሉ ማስደንገጥ ችለዋል፡፡ እኛ እያለን ኢትዮጵያ አትፈርስም ብለው በአንድነት መነሳታቸው በዚህ ዓመት በተለየ የሚታይ ታሪካዊ ተግባር ያየንበት ዓመት ነው፡፡

ጦርነት በምንም መሥፈርት ምርጫ ባይሆንም ለአገር ህልውና ሲባል የማይፈለግ ጦርነት ውስጥ ተገብቷል፡፡ ጦርነት ሲከፈትበት እጅ አጣጥፎ የሚቀመጥም ስለሌለ ዛሬ አገራችን የገባችበት ጦርነት ባትፈልገውም የሆነ ነው፡፡ በቶሎ እንዲቋጭ ግን ግድ ነው፡፡ የአገር ህልውናን ለማስጠበቅ የሚደረገው ፍልሚያ ደግሞ የአገር ሀብት ይባላል፡፡ ከሁለቱም ወገን ሰው ያሳጣል፡፡ አገርን ወደ ኋላ እንድትጎተት ምክንያት መሆኑም ግልጽ ነው፡፡

የጦርነቱ በምንም ሁኔታ ቢሆን መቋጨቱ ባይቀርም ችግሩ በጦርነቱ ወቅት ብቻ የተገደበ ያለመሆኑና ይዞት የሚመጣው ጣጣ ወይም የወደፊት መንገዳችንም ላይ ጋሬጣ መሆኑ አይቀርም፡፡ ይህም ቢሆን ግን አገር እንደ አገር ትቀጥላለች፡፡ ኢትዮጵያም ታሸንፋለች፡፡ በጦርነት ወቅትም ቢሆን አገር መቀጠሏ፤ የተለመደ እንቅስቃሴዋም አይቀርም፡፡ በተለይ እዲህ ያሉ ጦርነቶች የአገር ኢኮኖሚን በመብላት ያላቸው አቅም ከፍተኛ ነውና ከጦርነቱ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች እንዳይብሱ መሥራትን ይጠይቃል፡፡

ከዚህ አንፃር 2013ን ስናስብ እንደ አገር የገባንበት ጦርነት አንድ ነገር ሆኖ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎቻችንንም ጤናማ ለማድረግ የሚደረገው ፍልሚያ እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አይሆንም፡፡ ጉዳቱ በርካታ ቢሆንም በአገር ደረጃ የታየው የዋጋ ንረት አንድ ምሳሌ ሆኖ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

በዓመቱ መጀመርያ ከ15 እስከ 18 በመቶ የነበረው የዋጋ ንረት በየጊዜው እያደገ አሁን ላይ ወደ 30 በመቶ እየደረሰ ነው፡፡ አንዳንድ ምርቶችን ነጥለን ካየን ደግሞ 40 እና 50 በመቶ ደርሰዋል፡፡ ከዚያም ያለፈ የተጋነነ የዋጋ ንረት የታየባቸው ምርቶች እንዲህ ቀላል አይደለም፡፡ ይህ ለምን ሆነ? ለሚለው ጥያቄ ችግሩ ዛሬ የጀመረ ሳይሆን ለዓመታት ሲንከባለል መጥቶ እዚህ የደረሰ መሆኑን ብንገነዘብም አሁን ያለንበት ወቅታዊ ሁኔታም የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለው ወይም ንረቱን በእጅጉ ማባሱ ግልጽ ነው፡፡

ስለዚህ የችግሩ መንስዔ ምንም ይሁን ምን የዋጋ ንረቱ ኢትዮጵያ በእጅጉ የፈተናት ሆኖ 2013ን አጠናቋል፡፡ ይህን ብዙዎቻችን ለምሬት የዳረገ የአገር ችግር ለመቅረፍ መንግሥት የበኩሉን ጥረት እያደረገ ቢሆንም አሁንም ከዚህ ችግር ለመወጣት አልተቻለም፡፡ መንግሥት መፍትሔ ይሆናሉ ያላቸውንና ዕርምጃዎች እየወሰደ መሆኑን እንዲሁም ችግሩን የሚያባብሱ ያላቸውን ጉዳዮች ለመቆጣጠርም ጥረት ተደርጓል፡፡ ይህ በግልጽ የሚታይ ቢሆንም ዕርምጃው ያስገኘው ውጤት ገበያው ላይ አይታይም፡፡ ዓመቱን ሙሉ ሲደረጉ የነበሩ የተሞከሩ ጥረቶች ለምን ተገቢውን ያህል ውጤት አላመጡም ብሎ ቆም ብሎ መጠየቅ አስፈላጊ ይሆናል፡፡

ችግሩ ከዚህም የባሰ ጉዳት እያደረሰ እንዳይቀጥልና በአዲሱ ዓመትም የአገር ፈተና ሆኖ እንዳይቀጥል ለማድረግ የዋጋ ንረቱን በአግባቡ በመመልከት መፍትሔ የሚሆኑ አሠራሮችን መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ ችግሩ ዛሬ የጀመረ ባይሆንም አሁን ባለበት ሁኔታ ግን የዋጋ ንረቱ በጊዜያዊ መፍትሔዎች ብቻ የሚታ ያለመሆኑን በመገንዘብ ምን ይደረግ? በማለት አሁንም አድምቶ መሥራትን ይጠይቃል፡፡ አዲሱ መንግሥትም በብርቱ ሊያስብበት ከሚገቡ ጉዳዮች አንዱም ይህ የዋጋ ንረት ከጊዜ ወደ ጊዜ ለሕዝብ ፈተና የሆነውን የዋጋ ግሽበት ለመቆጣጠር የሚያስችል አሠራርና መፍትሔ ማስቀመጥ ላይ መሆን አለበት፡፡ ባለፈው ዓመትም በተመሳሳይ ሐሳብ ቀርቦ የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠር መንግሥት እሠራቸዋለሁ ያላቸውን በዝርዝር አቅርቦ ነበር፡፡ ውጤቱ ግን አሁን እንደምናየው ነውና በአዲሱ ዓመትም በትክክል የዋጋ ንረቱን ለመቀነስ ይረዳሉ የተባሉ መፍትሔዎችን በትክክል መፍትሔ ስለማምታጣቸው በመመዘን ሊተገብረው ይገባል፡፡ ጉዳዩ ከህልውና ማስከበር ያልተናነሰ ቦታ ሊሰጠው ይገባል፡፡

እንዲህ ያሉ ፈተናዎች ደግሞ በአንድ በመንግሥት ብቻ የሚፈታ አይሆንም፡፡ ዜጎች የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት አለባቸው፡፡ ዛሬ ለህል ውኃ ዘመቻ የታየው ትብብር በሌሎች መስኮችም መታየት አለበት፡፡ አንድ መሆንና መተሳሰብ መልካም ውጤት ያመጣልና አገር ስትፈተን ፈተናዋን እንድታልፍ በሁሉም ረገድ መተባበር አስፈላጊ ነው፡፡ አዲሱ ዓመትንም በዚህ መንፈስ እንቀበለው፡፡ 2014 የድልና በሁሉም ረገድ አሸናፊ የምንሆንበት ይሁን፡፡ መልካም አዲስ ዓመት!

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት