ኢትዮጵያና ሱዳን ለማደራደር የሚፈልጉ የጎረቤትና የወዳጅ አገሮች ሱዳን ወደ ነበረችበት የራሷ መሬት እንድትመለስ ካደረጉ፣ ኢትዮጵያ ለመነጋገር ዝግጁ መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ (አምባሳደር) ሐሙስ ጳጉሜን 4 ቀን 2013 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ ‹‹በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብ የሚንቀሳቀሱ ማናቸውም ወዳጅ አገሮችን የምናደንቅ ቢሆንም፣ ከድርድሩ ቀድሞ ግን ሱዳን ወደ ነበረችበት የራሷ ድንበር እንድትመለስ ያድርጉ፤›› ብለዋል፡፡
በሁለቱ አገሮች መካካል የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት ከዚህ በፊት በካርቱም፣ በአዲስ አባባ ወይም በገለልተኛ አገር ሲካሄድ የነበረው የውይይት መንገድ አዋጭ በመሆኑ፣ አሁንም የድንበሩን ውዝግብ ለመፍታት ሱዳን የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ግዛት ለቃ ስትወጣ መወያየት ይቻላል ሲሉ አስታውቀዋል፡፡
‹‹ሱዳን ያላግባብ የያዘችው መሬት ከሱዳን ሕዝብ ፍላጎት ጋር አብሮ የማይሄድና የሱዳንን ጥቅም የማያስከብር ከመሆኑም በላይ፣ ከኋላ ሆነው በሚገፉ ኃይሎች እንደ ጋሪ ፈረስ እየተገፋችሁ አታምጡ ነው የምንለው፤›› ብለዋል፡፡
በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በትግራይ ክልል በጥቅምት 2013 ዓ.ም. በነበረው የሰሜን ዕዝ ላይ ሕወሓት ጥቃት በማድረሱ ምክንያት የፌዴራል መንግሥት የሕግ ማስከበር ዘመቻ በጀመረችበት ጥቅምት 2013 ዓ.ም. አካባቢ፣ ሱዳን የይገባኛል ጥያቄ የምታነሳበትን የኢትዮጵያ መሬት በቁጥጥር ሥር ማዋሏ ይታወሳል፡፡
ከኢትዮጵያ በኩል በተደጋጋሚ ሱዳን ከያዘችው የተሳሳተ መንገድ እንድትመለስ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በትዕግሥትና በአድናቆት ሲከታተለው እንደቆየ ቃል አቀባዩ አስታውሰዋል፡፡
በተጠናቀቀው ዓመት ሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ዘልቃ መግባቷ አንዱ ትልቅ ችግር እንደነበር በመጥቀስ፣ ምንም እንኳ ችግሩ ባይፈታም ኢትዮጵያ ጉዳዩን በበሳል የዲፕሎማሲ ዕይታ ስትከታተለው መቆየቷን ተናግረዋል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ ከሰሞኑ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሱዳን ሕገወጥ የጦር መሣሪያ አጓጉዟል ተብሎ የተነዛው ወሬ፣ እንዲሁም በሱዳን ባለሥልጣናት መያዙ ግልጽ ያልሆነ ድራማና የአየር መንገዱን ዝና ለማጥፋት ያለመ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ እሑድ ነሐሴ 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ወደ ሱዳን በነበረው በረራ የተጠቀሰውን መሣሪያ እንዳጓጓዘ በሱዳን የዜና ምንጮች የተዘገበ ቢሆንም፣ አየር መንገዱ አጓጓዘው የተባለው መሣሪያ ለአደን አገልግሎት የሚውል ሕጋዊ መሣሪያ መሆኑኑን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ የሱዳን መንግሥት ባለሥልጣናት ማረጋገጫ እንዳለውም ገልጿል፡፡