Monday, July 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሸማቾችን የመግዛት አቅም የፈተነው የአዲስ ዓመት ገበያ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኤልያስ ተገኝና በሔለን ተስፋዬ

የተጠናቀቀው 2013 ዓ.ም. ከበርካታ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ክስተቶቹ በተጨማሪ በሰዎች ኑሮ ላይ ከበድ ያለ የዋጋ ንረት የታየበት ነው፡፡

በተለይ የምግብ ነክ ምርቶች ዋጋ ንረት ማየል ከጀመረ ሰነባብቷል ብቻ ሳይሆን ከርሟል ማለት ይቻላል፡፡ የአዲስ ዓመት በዓል መድረስ ደግሞ የዋጋ ንረቱን የበለጠ አማራሪ፣ የሸማቾቹን የመግዛት አቅም ደግሞ በፈተና የተሞላ አድርጎታል፡፡ በተለይም በመስከረም ወር ተደራራቢ ወጪዎች ለሚጠብቃቸው ሸማቾች ከበድ ብሏል፡፡

የነሐሴ ወር አጠቃላይ ግሽበት በዓመቱ ውስጥ ከታዩት ወራት እጅግ ከፍተኛው እንደሆነ፣ የማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ በነሐሴ ወር መጨረሻ ይፋ ያደረገው የአገር አቀፍ የክልሎችና የሸማቾች ዋጋ መመዘኛ ኢንዴክስ ያመላክታል፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ የተከናወነው የአዲስ ዓመት ገበያ የዋጋ ንረት ላይገርም ይችላል፡፡ ሪፖርተር ባደረገው የከተማዋ ዋና ዋና የገበያ ቦታዎች ቅኝት ይህንኑ መታዘብ ተችሏል፡፡ ሸማቾችም የገመያውን ክብደት ገልጸዋል፡፡

ከአናታቸው ላይ ጣል ያደረጉት ሻሽ አደፍ ብሏል፡፡ የእሳቸውንና የጎረቤታቸውን ለበዓል የሚሆኗቸውን ኮረሪማ፣ ፈንድሻና ሩብ ኪሎ ቡና ሦስት ጊዜ እንዲመዝንላቸው በመርካቶ ቅመም ተራ ባለ መደብር የሆነውን ወጣት ይነግሩታል፡፡ እሱም እየተነጫነጨ በሩብ ኪሎ የተቋጠሩትን ሸቀጦች ሦስት ጊዜ መዘነላቸው፡፡ ከወየበው ትልቁ ቦርሳቸው ውስጥ የተበጣጠሰ አነስተኛ ቦርሳ አውጥተው የተጨማደደውን የ200 ብር ኖት ከፈሉት፡፡

እኚህ እናት ወ/ሮ ታደለች ገረመው የሚባሉ ሲሆን፣ እንደ አብዛኛው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ኑሮ ልጆቻቸውን የሚያሳድጉ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ ባለቤታቸው በሕይወት ከተለዩዋቸው በኋላ ልጆቻቸውን የሚያሳድጉት በአንድ የግል መሥሪያ ቤት በፅዳት ሠራተኝነት በሚያገኙት አነስተኛ ገቢ እንደሆነ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

ለእሳቸው ኑሮ የተወደደው ከበዓል በፊት መሆኑን የሚናገሩት ወይዘሮዋ፣ ‹‹አዲስ ዓመት ሲመጣ ከምግብና ከመጠጡ በተጨማሪ የልጆች ትምህርት ቤት ስለሚከፈት ብዙ ወጪ ይጠብቀኛል፤›› ይላሉ፡፡

ወ/ሮ ታደለች እንደሚሉት የሚሠሩበት ድርጅት ምንም ዓይነት የደመወዝ ጭማሪ አላደረገላቸውም፡፡ ነገር ግን ገበያው ውስጥ በየዕለቱ በሚታየው የዋጋ ጭማሪ ምክንያት ልጆቻቸውን ማስተማር ቀርቶ መመገብ እንዳቃታቸው ገልጸዋል፡፡

የዘንድሮ አዲስ ዓመት ብዙ ነገሮች የተደራረቡበት መሆኑን የሚናገሩት ወ/ሮ ታደለች የሚያገኙት ወርኃዊ ደመወዝ 2,560 ብር ከ35 ሳንቲም እንደሆነ፣ ከዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ለበዓል ወጪ አውለውታል፡፡ ሆኖም ከበዓል ወጪ የቀራቸውን ጥቂት ገንዘብ እንዴት እስከ ቀጣዩ ወር ድረስ እንደሚያብቃቁት ግራ እንደገባቸው አክለዋል፡፡ ወይዘሮዋ በአነስተኛ የደመወዝ ገቢ ሌሎች መሰል ገቢ ያላቸው ነዋሪዎች በዓሉን እንዴት እንደሚያሳልፉ ማሳያ ናቸው፡፡

ሪፖርተር በአፍሪካ ትልቁ ክፍት ገበያ እንደሆነ በሚነገርለት መርካቶ የአዲስ ዓመት መዳረሻ ገበያ ምን እንደሚመስል ተዘዋውሮ ሻጮችንና ሸማቾችን በማነጋገር የገበያውን ሁኔታ ተረድቷል፡፡

ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ በመርካቶ ቅመም ተራ ነጋዴ የሆነው ወጣት ለሪፖርተር በዋጋ ደረጃ በሚሸጣቸው ምርቶች ላይ ከቀደሙት ሳምንታት ብዙም ያልተለየ ዋጋ መኖሩን ገልጾ፣ ሆኖም የሸማቾች የመግዛት አቅም እንደተዳከመና በፊት ወደ መደብሩ ለሸመታ የሚመጡ ሰዎች ከሚጠይቁት የመግዛት መጠን በግማሽ ቀንሰው እንደሚገበያዩ ታዝቧል፡፡ ያም ሆነ ይህ እሱም ሆነ በእሱ መደዳ የሚገኙ ነጋዴዎች ኮረሪማ በኪሎ ከ140 እስከ 150 ብር፣ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ተስተውሎበታል የተባለውን ሚጥሚጣ ከ280 እስከ 285 ብር በኪሎ፣ ቡና የታጠበውን ከ250 እስከ 260 ብር፣ ያልታጠበውን ከ210 እስከ 220 ብር በኪሎ እየሸጡ ነበሩ፡፡

ለበዓሉ ከሚያስፈልጉት ውስጥ ዶሮ ተጠቃሽ ነው፡፡ በበዓሉ መዳረሻ የዋዜማ ቀናት በነበረው ገበያ ትልቅ የሚባል ዶሮ በመርካቶ 550 ብር፣ መካከለኛው 500 ብር፣ እንዲሁም አነስተኛ የሚባሉት በ450 ብር ተሽጠዋል፡፡ የዶሮ ግብይት በአብዛኛው የሚደረገው በበዓሉ የመጨረሻ ዋዜማ ቀናት ላይ በመሆኑ ዋጋው ሊጨምር ይችላል የሚል ሥጋት ያደረባቸው ሸማቾች፣ ከረቡዕ ጳጉሜን 3 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የዶሮ ገበያን ያዘወትሩ ነበር፡፡ ምክንያቱም ብዙ ሸማቾች የዶሮ ግብይት የሚያከናውኑት በበዓሉ መዳረሻ የመጨረሻዎቹ ሁለት ቀናት በመሆኑ ነው፡፡

በተመሳሳይ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካሉት ገበያዎች መካከል የካ ክፍለ ከተማ የሚገኘውን ሾላ ገበያ የበዓል ግብይት ምን እንደሚመስል ተቃኝቷል፡፡

በዚህም መሠረት በሾላ የነበረው የዶሮ ገበያ ከመርካቶው የተለየ ነበር፡፡ በሾላ ገበያ የአገር ውስጥ ዶሮ ከ500 እስከ 600 ብር፣ ድቅል ከ600 እስከ 700 ብር፣ የፈረንጅ የሚባሉ ዶሮዎች ከ300 ብር ጀምሮ ሲሸጡ ነበር፡፡

በሾላ ገበያ ለስድስት ዓመታት ያህል ዶሮ በመሸጥ የሚተዳደረው አቶ ተስፋዬ ዓለሙ ለሪፖርተር እንደተናገረው አብዛኞቹ ዶሮዎች ከነጌሌ፣ ከዶሎመና፣ ከአርባ ምንጭና ከወላይታ የሚመጡ ናቸው፡፡ ከደሴና ከዳንግላ የሚመጡ ነጋዴዎች ግን በዚህኛው በዓል የሉም ብሏል፡፡ አቶ ተስፋዬ የዶሮ ዋጋ ቀድሞ ከነበረው ብዙም ጭማሪ እንደሌለው አስረድቶ፣ እስከ ጳጉሜን 4 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ የነበረው ገበያ ግን መቀዝቀዙን ተናግሯል፡፡

በዚህም ብዙ ሰዎች ዋጋ በመጠየቅና ለረዥም ጊዜ ቅናሽ እንዲያደርግ ተከራክረውት እንደሚሄዱ አስረድቷል፡፡ ከዚህ በፊት በነበሩ በዓላት ደንበኞች ተከራክረው ዋጋ አስቀንሰው ገዝተው እንደሚሄዱ፣ በአዲስ ዓመት ገበያ ደንበኞች የመግዛት አቅማቸው አነስተኛ በመሆኑ ለመግዛት የሚደፍሩ ጥቂቶች እንደሆኑ ገልጿል፡፡

የአገር ውስጥ የሚመረት ሽንኩርት ዋጋው እንደሚመጣባቸው የክልል ቦታዎች የሚለያይ ሲሆን፣ በመርካቶ ሽንኩርት ተራ በብዛት ለገበያ የቀረበው ሽንኩርት ቀላፎ የተባለው ዝርያ ነው፡፡ አንድ ኪሎ ቀላፎ ሽንኩርት 35 ብር፣ የሐበሻ ቀይ ሽንኩርት የሚባለው ደግሞ 34 ብር ተሸጧል፡፡ በኩንታል ለሚገዙ ገዥዎች ሽንኩርት በ33 ብር ሲጫን ለማየት ተችሏል፡፡

በሾላ ገበያ የሐበሻ የሚባለው ሽንኩርት አንድ ኪሎ 40 ብር፣ ነጭ ሽንኩርት ከ90 እስከ 120 ብር በኪሎ እየተሸጠ ነበር፡፡ በሾላ ገበያ ዞን አንድ ተራ በሚባለው ኮረሪማ፣ በርበሬ፣ ነጭ ሽንኩርት፣ ቅቤ፣ የሐበሻ ሽንኩርና ሌሎችም የምግብ ግብዓቶች የሚሸጡበት ቦታ ነው፡፡

የካፋ አካባቢ ኮረሪማ አንድ ኪሎ 160 ብር፣ የጅማ 150 ብር፣ የጎፋ 170 ብር ለገበያ የቀረበ መሆኑን፣ የበርበሬ ዋጋ ደግሞ የፀዳሌ አንድ ኪሎ 250 ብር፣ እንዲሁም የቻይና የሚባለው 250 ብር እየተሸጠ ነበር፡፡

በመርካቶ ቅመም ተራ ኮረሪማ 150 ብርና ከዚያ በላይ፣ ጥቁር አዝሙድ 260 ብር ከዚያ በላይ፣ ነጭ ሽንኩርት 80 ብር እየተሸጠ ነበር፡፡ ነጭ ሽንኩርት በጀምላ ለሚወስዱ ኪሎውን ከ40 እስከ 50 ብር ለጋዴዎች እንደሚጭኑ ሻጮች ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

የዓውድ ዓመት መሠረታዊ ግብዓቶች ተብለው ከሚወሰዱትና ለዓል ከሆኑ ግብዓቶች መካከል ቅቤ ተጠቃሽ ነው፡፡ በመርካቶ ገበያ በዘንድሮው የአዲስ ዓመት ገበያ ከቀደሙት በዓላት በዋጋ ደረጃ ቅናሽ የታየበት የበዓል ግብዓት ቢኖር ቅቤ ነው፡፡ በመርካቶ ቅቤ በረንዳ መካከለኛ የሚባለው 420 ብር፣ ለጋው 450 ብር በኪሎ ሲሸጥ ነበር፡፡

በሳል፣ መካከለኛና ለጋ ቅቤ ከዚህ ቀደም ከነበረው ዋጋ መቀነሱን የሚናገሩት የሾላ ገበያ ቅቤ ነጋዴዎች፣ ለጋውን 500 ብር (የሸኖ)፣ መካከለኛ 460 ብር (የጎጃም) እና በሳል 450 ብር (የወለጋ) ቅቤ ሲሸጡ መሰንበታቸውን ተናግረዋል፡፡

ቅቤ በሾላ ገበያ ጳጉሜን ከመግባቱ አስቀደሞ ይሸጥ የነበረው ለጋው 580 ብር፣ መካከለኛው 520 ብርና በሳሉ ደግሞ 500 ብር በኪሎ እንደነበር አስረድተዋል፡፡ በሌላ በኩል በብዙዎች ተፈላጊ የሆነው የማረቆ በርበሬ ገበያ ውስጥ አለመኖሩን ሪፖርተር ያነጋገራቸው ነጋዴዎች ገልጸዋል፡፡

ሪፖርተር በተለያዩ የገበያ አዳራሾችና አትክልት ተራዎች ባደረገው ቅኝት፣ የምግብ ዘይት ዋጋ በሁሉም የንግድ ሥፍራዎች በሚባል ደረጃ ቀድሞ በከፍተኛ ሁኔታ ከጨመረበት ጊዜ የ20 እና 30 ብር ቅናሽ እንደታየበት ተስተውሏል፡፡ ሆኖም ዋጋው ከቀደሙት በዓላት ማለትም ከትንሳዔና ከዓረፋ በዓላት ጋር ሲነፃፀር ጭማሪው ከፍተኛ እንደሆነ ሸማቾች አስረድተዋል፡፡ ለአብነት ያህል በመርካቶ ሸማ ተራ አካባቢ ባለ አምስት ሊትር ዘይት ከ550 እስከ 620 ብር ሲሸጥ ነበር፡፡ ቀደም ባሉት የበዓል ገበያዎች ማለትም በተለይ የትንሳዔ በዓል ሲከበር እስከ 390 ብር ይሸጥ የነበረው አምስት ሊትር ዘይት መንግሥት ከቀረጥ ነፃ እንዲገባ ከፈቀደ በኋላም፣ የሚሸጥበት ዋጋ ይህ ነው በሚባል ደረጃ ያልቀነሰና በአምስትና በስድስት መቶዎቹ  ብር ውስጥ እንደሆነ ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡

ሪፖርተር በሾላ ገበያ በግ ተራ የነበረውን ግብይት ሁኔታ የቃኘ ሲሆን፣ በመጠን ትንሽ የሚባለው በግ ከ2,800 እስከ 3,000 ብር ሲሸጥ፣ መካከለኛ የሚባለው ከ4,500 እስከ 5,000 ብር ነበር፡፡

የዓውደ ዓመት ገበያ

በአንፃሩ በቄራ በግ ተራ አካባቢ ለአዲስ ዓመት ግብይት ከገቡ በጎች አነስተኛ የሚባሉት 3,500 ብር፣ መካከለኞቹ 4,500 ብር፣ እንዲሁም ሙክት የሚባሉት መነሻቸው 5,500 ብርና ከዚያ በላይ ተሸጠዋል፡፡

በሾላ ገበያ ትልቅ የሚባለው በግ ከ8,000 እስከ 10,000 ብር ድረስ ሲሸጥ፣ አነስተኛ በሬ 17,000 ብር፣ መካከለኛ ከ30,000 እስከ 50,000 ብር፣ ትልቅ ሠንጋ ደግሞ ከ70,000 እስከ 90,000 ሺሕ ብርና ከዚያ በላይ እየተሸጠ ነበር፡፡

ከአራት ወራት አስቀድሞ በተከበረው የትንሳዔ በዓል ሪፖርተር በሾላ ገበያ ባደረገው ቅኝት ከዱበር፣ ከወላይታ፣ ከጊንጪ፣ ከወሊሶና ከአርባ ጉጉ የመጡ በጎች በአማካይ እስከ ስድስት ሺሕ ብር ሲሸጡ ነበር፡፡ በወቅቱም ዝቅተኛው የበግ ዋጋ 3,000 ብር ጀምሮ የነበረ ሲሆን፣ መካከለኛው 3,500 ብር፣ እንዲሁም ትልቅ የሚባለው እስከ 9,500 ብር ሲሸጥ ነበር፡፡ ቁም እንስሳት ረገድም የበሬ ዋጋ ዝቅተኛው 40,000 ብር፣ መካከለኛ 60,000 ብርና ትልቁ ደግሞ እስከ 90 ሺሕ ብርና ከዚያ በላይ ለገበያ መቅረቡን መዘገቡ ይታወሳል፡፡

ባለፈው ዓመት የአዲስ ዓመት በዓል አደይ አበባ ስታዲየም አካባቢ ባለው የበግ ተራ ገበያ ዝቅተኛው የበግ ዋጋ 2,000 ብር፣ ከፍተኛው 6,000 ብርና ከዚያ በላይ እየተሸጠ መሆኑን ነጋዴዎች በወቅቱ ለሪፖርተር መናገራቸው ይታወሳል፡፡ በዚያን ጊዜና በአሁኑ በነበሩት የአዲስ ዓመት ገበያዎች በግ ትንሽ በሚባለው ከ1,000 እስከ 1,500 ብር፣ ትልቅ በሚባለው በግ እስከ 4,000 ብር የሚደርስ የዋጋ ልዩነት መኖሩን ማየት ተችሏል፡፡

ሾላ ገበያ በግ ለመግዛት የተገኙ አንድ አባት ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የበግ ዋጋው ብዙም የዋጋ ጭማሪ ባይኖረውም የእሳቸው ሥራ በመቀዛቀዙ በፊት ከሚገዙት በመጠን አነስ ያለ ለመግዛት ወስነዋል፡፡ ለበዓል ለልጆቻቸው በግ መግዛት ማስለመዳቸውን የሚናገሩት እኚህ አባት፣ ካለባቸው የኑሮ ጫና አኳያ ባይገዙ እንደሚመርጡ ተናግረዋል፡፡

ሪፖርተር እንደ ክፍት ገበያዎች ሁሉ በተለምዶ አጠራር በሱፐር ማርኬቶች ቅኝት አድርጓል፡፡ አትላስ አካባቢ በሚገኘው የሴፍዌይ ሱፐር ማርኬት የአገር ውስጥ ዘይት አምስቱ ሊትር 589 ብር፣ እንዲሁም ከውጭ የሚገባው ዘይት በ699 ብር ሲሸጥ ነበር፡፡ የሱፐር ማርኬቱ ኃላፊ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ ዘንድሮ በዓሉን በማስመልከት በብዙ ምርቶች ላይ የተደረገ ቅናሽ የለም፡፡ ነገር ግን መንግሥት አንዳንድ ምርቶችን በቅናሽ እንዲሸጡ ባዘዘው መሠረት፣ ለምሳሌ ዕንቁላል በማያዋጣ ዋጋ ማለትም በ8.30 ብር የገዙትን በሰባት ብር እየሸጡ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በተበለቱ ዶሮዎች ዋጋ ላይ የተደረገ ቅናሽ መኖሩን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

በላፍቶ አከባቢ የሚገኘውን የሸዋ ሱፐር ማርኬት ቅኝት ከተደረገባቸው ቦታዎች አንዱ ሲሆን፣ በሱፐር ማርኬቱ ውስጥ እንደ ዘይት፣ ዕንቁላልና አትክልት ያሉት ምርቶች የሉም ነበር፡፡ ሆኖም ሥጋና የወተት ውጤቶች የሚባሉት ምርቶች በቂ ሁኔታ ቢገኙም፣ እንደ ቀደሙት በዓላት የበዓል ቅናሽ አንዳልተደረገባቸው ሪፖርተር የድርጅቱ ሠራተኛን በማነጋገር መገንዘብ ተችሏል፡፡

 ጠንካራው ክረምት ተገባዶ ወደ አዲስ ዓመት የሚደረገውን ጉዞ ለማጀብ ዓምና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰት ሳቢያ ቀርተው የነበሩት የኤግዚቢሽን፣ የባዛር ግብይቶችና የሙዚቃ መሰናዶዎች በተለያዩ የከተማዋ አውራ ጎዳናዎች ላይ እየተከናወነ የአዲስ ዓመት የገበያ ቅኝት ተገባዷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች