Thursday, June 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ብሔራዊ ባንክ ከሰሞኑ ባወጣቸው መመርያዎች የዋጋ ንረቱን ማከም እንደማይችል የፋይናንስ ተቋማት አመራሮች ገለጹ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሰሞኑን የፋይናንስ ኢንዱስትሪውን የተመለከቱ የተለያዩ መመርያዎችን በማውጣት እንዲተገበሩ አዟል፡፡

መመርያው ወቅታዊ አገራዊ ሁኔታን መሠረት ያደረገና በተለይ የዋጋ ንረትን ለመከላከልና መቆጣጠር ታሳቢ በማድረግ ስለመውጣቱም የመመርያዎቹ መግቢያዎች ያመለክታሉ፡፡

ይህንንም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በአዋጅ ከተሰጡት ተልዕኮዎች መካከል የገንዘብ ፖሊሲ በመቅረፅ ኢኮኖሚው ውስጥ የሚዘዋወረውን የገንዘብ መጠን የዋጋ ንረት የማያስከትል መሆኑን ማረጋገጥ መሠረታዊ ኃላፊነቶች በመሆኑ መመርያዎቹን በማውጣት ወደ ትግበራ መግባቱን ባንኩ አመልክቷል፡፡ እንደሚታወቀው የዋጋ ንረት የብዙ ምክንያት ድምር ውጤት ሲሆን፣ የምርት አቅርቦት እጥረት፣ የሎጂስቲክ አለመሳለጥ፣ የገንዘብና የፊዚካል ፖሊሲ አቋም ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

የዋጋ ግሽበትን ለመግታት መንግሥት ዘርፈ ብዙ ጥረቶችን እያደረገ ቢሆንም፣ ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መጥቷል፡፡ ይህም ታውቆ አስፈላጊው የፖሊሲ ማሻሻያ መደረግ እንዳለበት በመታመኑ፣ በኢኮኖሚው ውስጥ የሚዘዋወረውን የገንዘብ ሥርጭት ለመቀነስ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ ተግባራዊ ለማድረግ ወስኗል፡፡ መመርያዎቹ ባንኮች በብሔራዊ ባንክ የሚያስቀምጡትን የመጠባበቂያ ገንዘብ ከአምስት በመቶ ወደ አሥር በመቶ እንዲያድግ ማድረጉ አንዱ ነው፡፡ በተጨማሪም ባንኮችና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች የልማት ባንክ ቦንድን (የዕዳ ሰነድ) እንዲገዙ የሚያስገድደው መመርያ ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከወጡ መመርያዎች መካከል ሌላው ነው፡፡ ባንኮች ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ ግማሽ ያህሉን በዕለታዊ የምንዛሪ ዋጋ ለብሔራዊ ባንክ እንዲያስገቡ የሚያስገድደው መመርያም ከሰሞኑ የብሔራዊ ባንክ ዕርምጃዎች መካከል ተጠቃሽ ነው፡፡

ባንኮች ደንበኞቻቸውን በደንብ ማወቅ እንደሚጠበቅባቸውና ይህም እንዴት ተፈጻሚ እንደሚሆን የሚያመለክተው ሌላው የብሔራዊ ባንክ መመርያ ካለፈው ሳምንት አንስቶ  መተግበር ጀምሯል፡፡

እነዚህ በአንዴ የወጡት መመርያዎች ለብዙዎች ዱብ ዕዳ እንደሆነ ያነጋገርናቸው የባንክ የሥራ ኃላፊዎች ይገልጻሉ፡፡ ብዙዎቹ ከአንድ መመርያ ውጭ ሌሎቹ ይወጣሉ ብለው ያልገመቱት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ የኅብረት ባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ በዚህ ወቅት ይወጣል ብለው ያልገመቱትና አጠቃላይ የፋይናንስ ዘርፉን ወደ ኋላ የሚጎትት ሆኖ እንዳገኙት ይጠቅሳሉ፡፡

ሌላው የአንድ ባንክ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መሻሻል እያሳየና ብዙ ለውጦች እያደረገ መሆኑን እየተናገርን ባለንበት ሰዓት እነዚህን ያልተጠበቁ መመርያዎች ተግብሩ ማለቱ እንዳስገረማቸው ያመለክታሉ፡፡

መመርያዎቹ በአጠቃላይ ሲታዩ ከወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ጋር ተያይዞ መንግሥት ፖለቲካዊ ውሳኔ የሰጠባቸው እንደሚመስሉ ያነጋገርናቸው የኢንዱስትሪው ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ አክለውም ስለመመርያው መወጣት ምንም ግንዛቤ ያልነበራቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ብሔራዊ ባንክ ከለውጡ ወዲህ አሠራሩን አሻሽሏል ብለው ከሚጠቀሱለት ጉዳዮች አንዱ ብዙዎቹን መመርያዎች ከማውጣቱ በፊት የባንክ የሥራ ኃላፊዎች ይመክሩበት የነበረ መሆኑ ነው፡፡ ሰሞኑን ግን ከአንዱ መመርያ ውጭ በሌሎቹ መመርያዎች ላይ አስተያየት ስጡበት አለማለቱንና መመርያዎቹ እንዳልተመከረባቸው ገልጸዋል፡፡

ይህ አንድ ክፍተት ነው የሚሉት የዘርፉ ባለሙያዎች መመርያዎቹ ኢንዱስትሪው ላይ ጫና ያሳድራሉ ብለው ያምናሉ፡፡

አቶ ኢየሱስ ወርቅ ደግሞ እነዚህ መመርያዎች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተዘጋጁ ያለመሆናቸው ውሳኔ በማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ የተላለፈ ስለመሆኑ እርግጠኛ ሆነው ይናገራሉ፡፡

መመርያዎቹ በየትኛውም ወገን ፍላጎትና ውሳኔ ይውጡ አጠቃላይ ይዘታቸው ሲታይ ግን ባንኮች ላይ ጫና መፍጠሩ እንደማይቀር ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ በተለይ ለመመርያዎቹ መውጣት እንደ ምክንያት ከተጠቀሱት አንዱና መሠረታዊው አሁን ላለው የዋጋ ንረት መፍትሔ መስጠት መሆኑን አይቀበሉም፡፡ የዋጋ ንረቱን እንዲህ ያሉ መመርያዎችን በማውጣት ማከም ይቻላል ብለው አያምኑም፡፡

ካነጋገርናቸው የባንክ የሥራ ኃላፊዎች መረዳት እንደተቻለው መመርያዎቹ የባንኮች አቅም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ናቸው፡፡ በተለይ የመጠባበቂያ ገንዘቡ ከአምስት በመቶ ወደ አሥር በመቶ ማደጉ ባንኮች በሰባት በመቶና ከዚያም በላይ እስከ 14 በመቶ ወለድ እየከፈሉ የሚሰበስቡትን ተቀማጭ ገንዘብ አሥር በመቶውን ምንም ወለድ በማይታሰብበት መንገድ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንዲያስገቡ መገደዳቸው እንደሚጎዳቸው ገልጸዋል፡፡

የመጠባበቂያ ገንዘቡ በእጥፍ መጨመሩ ብቻ ሳይሆን፣ ይህ በመጠባበቂ መልክ እንዲጠቀስ የሚሆነው የባንኮቹ ገንዘብ ያለምንም ወለድ የሚቀመጥ መሆኑ ለባንኮቹ ፈታኝ እንደሚሆን ያመለክታሉ፡፡ ወለድ የከፈሉበት ገንዘብ ያለወለድ ለብሔራዊ ባንክ ገቢ እንዲሆን መወሰኑ ተገቢ እንዳልሆነም ይሞግታሉ፡፡

ይህ ብቻ አይደለም፣ ባንኮቹ እስካሁን ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ 30 በመቶውን በዕለታዊ የምንዛሪ ዋጋ ለብሔራዊ ባንክ እንዲያስገቡ የሚያስገድደው መመርያ ወደ 50 በመቶ ማደጉም ሌላው የባንኮች የራስ ምታት እንደሚሆን ይገልጻሉ፡፡

መጠኑ ጨምሮ የመጣው ይህ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያ በ30 በመቶ በነበረበት ወቅት ራሱ ሲያከራክር የቆየ እንደነበርም ይጠቅሳሉ፡፡

በዚህም ምክንያት ባንኮች ከምናገኘው የውጭ ምንዛሪ 30 በመቶውን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስገቡ መባላችን አግባብ አይደለም በማለት መመርያው እንዲነሳ በባንኮች ማኅበር በኩል ለብሔራዊ ባንክ መቅረባቸውንም ገልጸዋል፡፡

ባንኮችም ይህ መመርያ ይነሳል የሚል እምነት እንደነበራቸው ካነጋገርናቸው የባንክ ባለሙያዎች ለመገንዘብ ችለናል፡፡

ጭራሽ መጠኑ ጨምሮ መምጣቱም ያስደነቃቸው መሆኑን ነው የገለጹት፡፡ ባንኮች ከፍተኛ ወጪ እያወጡ ጭምር የሚያገኙትን የውጭ ምንዛሪ በዕለታዊ የምንዛሪ ዋጋ ማስገባታቸው ብቻ ሳይሆን የውጭ ምንዛሪውን ለደንበኞቻቸው አበድረው ያገኙ የነበረውን ትርፍ እንዲያገኙ እንደሚያደርጋቸው ይገልጻሉ፡፡ በባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከፍተኛ ትርፍ ይገኝበታል ተብለው ከሚጠቀሱት አገልግሎቶች መካከል የውጭ ምንዛሪን ለደንበኞች በማቅረብ የሚገኘው ጥቅም ነው፡፡

ስለዚህ ይህ መመርያ ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ ግማሽ ያህሉን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሚያቀርቡ በመሆኑ ባንኮች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር በእርግጠኝነት ይናገራሉ፡፡

ከዚህ መመርያ ጋር በተያያዘ አንድ የባንክ የሥራ ኃላፊ እንደገለጹት ‹‹ከምታገኙት የውጭ ምንዛሪ 50 በመቶውን ለብሔራዊ ባንክ አቅርቡ መባሉ ከዚህ ዘርፍ ባንኮች ያገኙ የነበረው ጥቅም በግማሽ ይቀንሳል ማለት ነው፤›› ሲሉ መመርያው ምን ያህል ጫና እንደሚያመጣ ያመለክታሉ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዚህን መመርያ አስፈላጊነትና አዲሱን መመርያ እንዲህ በማለት ይገልጸዋል፡፡

ባንኮች ከወጪ ንግድ፣ ከግለሰብ ሃዋላና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ ውስጥ 50 በመቶውን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገቢ እንዲያደርጉ ተወስኗል፡፡

የውጭ ምንዛሪ ያስገኘ ማንኛውም የባንክ ደንበኛ ቀደም ሲል በውጭ ምንዛሪ ሒሳብ ውስጥ ያለ ጊዜ ገደብ መያዝ የሚችለው የውጭ ምንዛሪ መጠን 1.5 በመቶ ወደ 40 በመቶ ከፍ እንዲል የተወሰነ ሲሆን፣ ቀሪውን አሥር በመቶ ባንኮች በውጭ ምንዛሪ የሚጠቀሙት ይሆናል፡፡

ይህ መመርያ የውጭ ምንዛሪ አመንጪ ደንበኞች ሲያገኙት የነበረው ድርሻ አነስተኛ ነው የሚለውን ቅሬታ በተወሰነ መልኩ የሚፈታ፣ የመንግሥትን የውጭ ምንዛሪ ግኝት አቅም በማሳደግ የውጭ ዕዳ ክፍያ ግዴታዎችን ለመወጣት፣ የአገሪቱን ትልልቅ ፕሮጀክቶች ለማገዝና አስፈላጊ የፍጆታ ዕቃዎችን ከውጭ ለማስገባት የሚያስችል መሆኑ ታምኖበታል፡፡ በተጨማሪም ከባንኮች በተደጋጋሚ የሚቀርበውንና ‹‹ከውጭ ኢንቨስትመንት፣ ከዳያስፖራ ሒሳብና ከውጭ ብድር የሚገኝ የውጭ ምንዛሪ ተቀንሶ ወደ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገቢ መደረግ የለበትም›› የሚለውን ጥያቄም የሚመልስ ነው ይላል፡፡

የሰሞኑ መመርያዎች የባንኮችን ፈተና የሚያበረታ ነው እንዲሉ ያደረጋቸው ሌላው ጉዳይ ደግሞ ከዚህ ቀደም ባንኮች በአስገዳጅነት ይፈጸሙ የነበረው የ27 በመቶ የቦንድ ግዥን መልሶ ያወጣ መሆኑ ነው፡፡

ባንኮች በየዓመቱ ከሚሰጡት ብድር ላይ 27 በመቶውን ለቦንድ ግዥ እንዲያውሉ የሚያስገድድ የነበረውን የቀድሞውን መመርያ ተገቢ አይደለም በማለት በመሟገት እንዲሻር አድርገው ነበር፡፡ አሁን ደግሞ መጠኑ አነስተኛ ቢሆንም ባንኮች ከሚሰጡት አጠቃላይ ብድር አንድ በመቶን ቦንድ እንዲገዙ ይህም ከወቅታዊው የብድር መጠን አንፃር ባንኮችን ለከፍተኛ የቦንድ ግዥ ያደርጋቸዋል የሚል ሥጋት ፈጥሯል፡፡

አሁንም ችግሩ አንድ በመቶ ብቻ መሆኑ ሳይሆን ለቦንድ ግዥ የሚታሰብላቸው ከዘጠኝ በመቶ በላይ ያለመሆኑ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ መመርያ በቦንድ ግዥ ጉዳይ ጫን ያለው የኢንሹራንስ ዘርፉን ነው፡፡ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከዚህ በኋላ እያንዳንዱ ዓመታዊ ትርፋቸው 15 በመቶውን ለቦንድ ግዥ እንዲያውሉ መደንገጉ ነው፡፡

ከባንኮች አንፃር በቦንድ ግዥው ዙሪያ መከራከሪያ የሚነሳበት ባንኮች ተቀማጭ ገንዘባቸውን እስከ 14 በመቶ ጭምር ወለድ በመክፈል የሚሰበሰቡ ሆኖ ሳለ ገንዘባቸውን ለቦንድ ግዥ ሲያውሉ የሚያገኙት የወለድ መጠን አነስተኛ መሆኑ የሚፈጥረው ጉዳት ነው፡፡

ሌላው የሰሞኑ መመርያ ውስጥ የተካተተው ጉዳይ ባንኮች የገንዘብ እጥረት ችግራቸውን ለመፍታት ከብሔራዊ ባንክ በሚያገኙት ብድር ላይ የተጣለው የወለድ መጠን ከፍ ማለቱ ነው፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች ባንኮች የገንዘብ እጥረት በሚያጋጥማቸው ጊዜ ይህንን ጊዜያዊ ችግር ለመቅረፍ ከብሔራዊ ባንክ መበደር ይችላሉ፡፡ እንዲህ ያለውን ገንዘብ ሲበደሩ እስካሁን በ13 በመቶ ወለድ ይጣልባቸው የነበረ ሲሆን፣ አሁን ግን ይህ የወለድ መጠን ወደ 16 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡ ይህንን  ተገቢ ያልሆነ ውሳኔ በማለት ተቃርነውታል፡፡

 የፋይናንስ ተቋማት ደንበኞቻቸውን ጠንቅቀው እንዲያውቁ ብሔራዊ ባንክ ያወጣውን ሌላው መመርያ ግን ባንኮቹ ላይ የሥራ ጫና ካልፈጠረ በቀር መተግበር ያለበት ጉዳይ መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች