የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ዓምና ያነሳው ፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ አል ሂላልን አስተናግዶ ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል። አፄዎቹ ከመመራት ተነስተው ሁለት አቻ ተለያይተዋል።
በሻምፒዮንስ ሊግ የመጀመሪያ ተሳትፎን መስከረም 2 ቀን 2014 ዓ.ም. በባህር ዳር ስታዲየም ያደረገው ፋሲል፣ በጨዋታ የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረግ ችሏል። በጨዋታው ተደጋጋሚ የግብ ዕድል ለመፍጠር ሙከራ ሲያደርግ ከቆየ በኋላ አቻ ውጤት አጠናቋል።
የሱዳኑ ክለብ በ21ኛው እና 54ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥሮ መምራት ቢችልም፣ ፋሲሎች ተደጋጋሚ ያደረጉት ሙከራ ተሳክቶ በ66ኛው ደቂቃ በበረከት ደስታና 77ኛ ደቂቃ ላይ በኦኪኪ አፎላቢ ግብ አቻ ተለያይተዋል። አፄዎቹ ሁለተኛ የማጣሪያ ጨዋታቸውን እሑድ መስከረም 9 ቀን ኦምዱርማን ላይ ያደርጋሉ።
ሌላኛው በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ ወደ ዑጋንዳ ያመራው የኢትዮጵያ ቡና በዩአርኤ 2ለ1 ተሸንፏል።
ከረዥም ጊዜ በኋላ በአኅጉር ጨዋታ ላይ መካፈል የቻለው ኢትዮጵያ ቡና በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የጨዋታ የበላይነት ነበረው።
ሆኖም ባላጋራው 22ኛው እና 37ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠራቸው ግቦች 2ለ0 መምራት ችለዋል። ቡና በዊሊያም ሰለሞን አማካይነት በ55ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠራት ግብ ጨዋታው 2ለ1 ተጠናቋል፡፡
የኢትዮጵያ ቡና የሁለተኛው የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታውን መስከረም 9 ቀን በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ያደርጋል።