የገንዘብ ሚኒስቴር መሠረታዊ የምግብ ፍጆታዎች ላይ ከቀረጥና የታክስ ማሻሻያ ማድረጉን ተከትሎ ምርቶች በብዛት ለገበያ ከቀረቡ ዋጋቸው ሊቀንስ እንደሚችል የአዲስ አበባ ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
የምግብ ፍጆታዎቹ የዋጋ ንረት ለመቀነስ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የዳቦ ዱቄት፣ ማካሮኒና ፓስታ ከሚያመርቱት ፋብሪካዎች ጋር የማስተሳሰር ሥራ መሠራቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ ሲሳይ አረጋ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ የሚገኙ አሥሩም የኅብረት ሥራ ዩኒየኖች 8,000 የዳቦ ዱቄት፣ 6,500 ማካሮኒና 25,900 ኩንታል ፓስታ ለአንድ ወር ተለይተው ለንግድ ቢሮ የቀረቡ መሆኑን፣ በቅርቡ ለኅብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ ይደረጋል ተብሏል፡፡
ከፋብሪካዎች አንድ ፓስታ በ25 ብር፣ አንድ ኪሎ ማካሮኒ በ42 ብርና አንድ ኪሎ የዳቦ ዱቄት 35 እስከ 38 ከፋብሪካዎች ለመግዛት ስምምነት ላይ መደረሱን ተጠቁሟል፡፡
በዚህም ብዙ ፋብሪካዎችና አስመጪዎች ምርቶችን በብዛት ለገበያ ሲያቀርቡ በሸቀጦቹ ላይ የዋጋ ቅናሽ ሊኖራቸው እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
የሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ለ2014 የዘመን መለወጫ በዓል ከ201 ሚሊዮን ብር በላይ ግብይት ማድረጉ ይታወሳል ።
የኅብረት ሥራ ማኅበራቱ በክልሎች ከሚገኙ የግብርናና የኢንዱስትሪዎች ጋር በተፈጠረላቸው ቀጥታ የገበያ ትስሰር ለኅብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቶችን እንዲያቀርቡ መደረጉን፣ በዚህም 95 ሚሊዮን ብር የሚሆን የግብርና ምርቶች፣ በ9 ሚሊዮን የእንሰሳትና የእንሰሳት ተዋጽኦ ውጤቶች እና 97 ሚሊዮን ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የኢንዱስትሪ ምርቶችን ደግሞ ከአምራች ኢንዱስትሪዎች ጋር ቀጥታ የገበያ ትስስር በመፍጠር የዋጋ ንረትን በመቀነስ በማኅበራቱ ሥር ላሉ አባሎቻቸውና ለኅብረተሰቡ ማቅረባቸውን ተገልጿል።
በቀጣይም የኅብረት ሥራ ማኅበራቱን በክልሎች ከሚገኙ የግብርናና የኢንዱስትሪዎች ጋር በማስተሳሰር በአሁኑ ሰዓት በከተማዋ የሚስተዋለውን የዋጋ ንረት በዘላቂነት ለመቀነስ በልዩ ትኩረት እየተሠራ መሆኑን መረጃ ያመላክታል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኅብረት ሥራ ማኅበራት ያለባቸውን የፋይናንስ እጥረት ለመቅረፍና የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በሱቆቻቸው በማስገባት ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ የግማሽ ቢሊየን ብር ብድር መስጠቱ ይታወሳል።