Sunday, April 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

ባህላዊ እሴቶችና አገር በቀል ዕውቀቶችን ለማኅበራዊ ትስስር

ኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገቷ አንድ ዕርምጃ ከፍ እንዲል የአንበሳውን ድርሻ ከሚወጡት መካከል የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ቢሆንም፣ ዘርፉ ላይ ግን የተለያዩ ችግሮች እየታዩ ይገኛሉ፡፡ ይህንንም ችግር ለመቅረፍ የአሥር ዓመቱን መሪ ዕቅድ አዘጋጅቶ እየሠራ ይገኛል፡፡ የሚኒስቴሩን ሥራ በተመለከተ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ዓለማየሁ ጌታቸውን ተመስገን ተጋፋው አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ለኅትመት የበቁ የጥናትና የምርምር ሥራዎችን በዓመታዊ ጉባዔያችሁ ስትገለጹ ነበር፣ በምን ላይ ያተኮሩ ናቸው? ተደራሽነታቸውስ?

አቶ ዓለማየሁ፡- በ2011 ዓ.ም. በወጣው አዋጅ መሠረት በሚኒስቴሩ ሥር አምስት ተጠሪ ተቋማት እንዲኖሩት ተደርጓል፡፡ እነዚህም ተቋማት በ2013 ዓ.ም. በጀት ዓመት ላይ ያተሟቸው ኅትመቶች ምንድን ናቸው? የሚለውን በወቅቱ ማየት ተችሏል፡፡ ለአብነት ያህል የስፖርት ኮሚሽን የአሥር ዓመት መሪ ዕቅዱ ምን እንደሚመስልና ምን ዓይነት ሥራዎችን መሥራት እንዳለበት አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም ሌሎቹም ተቋማት የራሳቸውን የሆነ መሪ ዕቅድ አስቀምጠዋል፡፡ በተለይም በየዘርፋቸው ያለውን ክፍተት በመገምገም የኢትዮጵያን የቱሪዝም መስህብ ማሳደግ የግድ ይላል፡፡ ሚኒስቴሩም የራሱን የሆነ አሠራር በመዘርጋት በቀጣዮቹ ዓመታት ሰፊ ሥራዎችን ለመሥራት ቅድመ ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡ ሚኒስቴሩም ከ2013 እስከ 2022 ዓ.ም. የአሥር ዓመታት ዕቅድ አዘጋጅቶ፣ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ በእርግጥ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ቦታዎች ላይ የሚታዩ ችግሮች አሉ፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህን ችግሮች ወደኋላ በመተው ዘርፉ ላይ ለውጥ ለማምጣት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ቀን ከሌሊት መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ይኼ ከሆነ ዘርፉን አንድ ዕርምጃ ከፍ ማድረግ ይቻላል፡፡  

ሪፖርተር፡- በጥንታዊው የግዕዝ ቋንቋ ላይ ጉባዔ ከማካሄድ ባለፈ ምን ምን እያከናወናችሁ ነው?

አቶ ዓለማየሁ፡- ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ ስድስት ጉባዔዎችን ማከናወን ተችሏል፡፡ ከዚህም ባሻገር በአሁኑ ወቅት አምስተኛው የግዕዝ ጥንቅር ለማሳተም ሒደቶችን ጀምረናል፡፡ በእርግጥ ጉባዔው ‹የግዕዝ ጉባዔ› ተብሎ ይታሰብ እንጂ፣ ‹የጥንታዊ ቋንቋዎች ጉባዔ› አካቶ የያዘ ነው፡፡ ዋናው ነገር ግን እየጠፋ የመጣውን የግዕዝ ቋንቋ ለማኅበረሰቡ በማስገንዘብና ትምህርቶችን መስጠት ነው፡፡ እስካሁን በአክሱም፣ በባህር ዳር፣ በጅማ፣ በወልቂጤና በመቐለ ከተሞች የሚገኙ የባህልና ቱሪዝም ተቋማት ጋር ቅንጅት በመፍጠር ጉባዔዎችን ማከናወን ችለናል፡፡ በ2013 ዓ.ም. ደግሞ ስድስተኛውን ጉባዔ በጎንደር ከተማ ማከናወናችን ይታወሳል፡፡ አሁን ላይ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ አምስት የጉባዔ ጥንቅር አውጥተናል፡፡ ይኼም የጉባዔ ጥንቅር ዓላማው ስለትምህርት፣ ስለፍልስፍና፣ ስለሕክምናና ስለሌሎች ጉዳዮች በግዕዝ የተጻፉ መጻሕፍት እንዳይጠፉ  ለማድረግ የምንሠራ ይሆናል፡፡ የግዕዝ ቋንቋ ዕውቀት ያላቸው ሰዎችን በመጠቀም፣ ዘመናዊ የትምህርት ሥርዓት ኖሮት እንዲቀጥል እናደርጋለን፡፡ በዚህም አብዛኞቹ የሚመለከታቸው አካላት ትልቅ አስተዋጽኦ ለማበርከት ቅድመ ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል፡፡ ከባህላዊ እሴቶች አንፃርም በኦሮሚያ የ‹‹ስንቄ›› ሥርዓትን በተመለከተ ሚኒስቴሩ ጥናት አጥንቶ ማሳተም ችሏል፡፡ ይኼም ባህላዊ እሴቶቻችንና አገር በቀል ዕውቀቶቻችን ለማኅበራዊ ትስስሮቻችን ያላቸው ሚና ምንድነው? የሚለውን ለማሳየት የጎላ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ይኼም እርስ በርስ በቋንቋ፣ በባህልና በሌሎች ነገሮች እንድንተሳሰር መንገዶችን ይከፍትልናል፡፡ መንግሥት በጀት በመመደብ የጥናትና የምርምር ጉባዔዎች ጥንቅር እንዲታተም ጉልህ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ አንዳንድ ነገሮች ከመድረክ ባለፈ ለኅትመት በቅተው ለማኅበረሰቡ እንዲደርሱ በማድረግ ዘርፉን ለማሳደግ የምንሠራ ይሆናል፡፡  

ሪፖርተር፡- የ2013 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረባችሁ ወቅት የቱሪዝም ዘርፍ ላይ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ መሥራት እንደቻላችሁ ተናግራችኋል፡፡ በወቅቱ ምን ዓይነት ተግዳሮቶች ገጥሟችኋል?

አቶ ዓለማየሁ፡- በእርግጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ትልቅ ተግዳሮት ሆኖብናል፡፡ በተለይም በቱሪዝም ዘርፍ ላይ ማግኘት የሚገባንን ጥቅም ልናጣ ችለናል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን መልካም ነገሮችን ይዞልን መጥቷል፡፡ ለምሳሌ ያህል መንግሥት ዘርፉ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራ መነሻ ሆኖናል፡፡ በከተማም ሆነ በተለያዩ ቦታዎች ላይ የቱሪዝም ዘርፍን የሚያነቃቁ ፕሮጀክቶች ዕውን እንዲሆን ተደርጓል፡፡ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝም መከሰት ምክንያት የቱሪስት እንቅስቃሴ ሊገደብ በመቻሉ፣ የቱሪዝም መስህቡ ላይ ከፍተኛ የሆነ ቀውስ ሊከሰት ችሏል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ሚኒስቴሩ ያሉበትን የአሠራር ክፍቶች፣ የቱሪዝም ዘርፍ ልማት ሥራዎችና የአቅም ግንባታዎች ላይ ትኩረት እንዲሰጥ ዕድል ከፍቶልናል፡፡ በተጨማሪ ፖሊሲዎችን እንደ አዲስ እንድንቀርፅ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮልናል፡፡ በቀጣይም ኢትዮጵያ የቱሪዝም መዳረሻ ቦታ ሆና ከተለያዩ አገሮች የሚመጡ ቱሪስቶች የምታስተናግድ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- የኪነ ጥበብ ሽልማት የሚለው እንቅስቃሴያችሁ ምን ይመስላል?

አቶ ዓለማየሁ፡- ኪነ ጥበብ ሽልማትን በተመለከተ ሚኒስቴሩ ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ የተለያዩ ሥራዎች ማከናወን ችሏል፡፡ ይሁን እንጂ ሲንከባለል በመጣ ችግር ምክንያት የሽልማት ሒደቱ ተግባራዊ ሳይደረግ ቆቷል፡፡ በ2013 ዓ.ም. ብሔራዊ ኮሚቴ ማቋቋም  ችለናል፡፡ የተለያዩ ማኅበሮችን ባሉበት ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ የተዘጋጁ መመርያዎችን በ2006 ዓ.ም. በማፅደቅ አንድ የሆነ ኮሚቴ ማዋቀር ችለናል፡፡ መመርያው በዓቃቤ ሕግ አማካይነት ሊፀድቅ ችሏል፡፡ በኢትዮጵያ አገር አቀፍ የባህልና የኪነ ጥበብ ሽልማትን ማኅበር እንዲቋቋም መንግሥት ከበፊት ጀምሮ ትልቁን ድርሻ ሲወጣ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም የባህልና ቱሪዝም ኮሚቴዎችን በማዋቀር በ2013 ዓ.ም. የመጀመርያውን የሽልማት መርሐ ግብር ማከናወን ችሏል፡፡ በእርግጥ በሽልማት መርሐ ግብሩ በተከናወነ ወቅት የተለያዩ ቅሬታዎች ተነስተዋል፡፡ ነገር ግን ይህ የሽልማት መርሐ ግብር እንደ መልካም አጋጣሚ በማየት ፕሮግራሙን ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡ የሽልማት መርሐ ግብሩም ዋናው ግቡ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን ማበረታታት ነው፡፡ ይህም ከዚህ በኋላ በየዓመቱ ተግባራዊ የሚደረግ ይሆናል፡፡  

ሪፖርተር፡- ዘንድሮ የዓለም ቱሪዝም ቀን እንዴት ይከበራል?

አቶ ዓለማየሁ፡- ዘንድሮ የዓለም ቱሪዝም ቀን በሲዳማ ክልል የሚከበር ሲሆን፣ ከዚህ በፊት ሲከበር ከነበረው ለየት ባለ መልኩ ለማክበር ቅድመ ዝግጅቶችን እያደረግን ነው፡፡ ዘንድሮም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ42ኛ ጊዜ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ለ34ኛ ጊዜ፣ ‹‹ቱሪዝም ለሁለንተናዊ ዕድገት›› በሚል መሪ ቃል በሲዳማ ክልል ለማክበር ተዘጋጅተናል፡፡ ከዚህ በፊት የተለያዩ ክልሎች ላይ ማክበር ችለናል፡፡ በእርግጥ ከዚያ በፊት በአዲስ አበባ ለረዥም ጊዜ በተለያዩ ፕሮግራሞች ሲከበር መቆየቱ ይታወሳል፡፡ በዘንድሮ ዓመት የሚከበረው የቱሪዝም ቀን የተለያዩ የቱሪዝም መስህቦችን በመቃኘት፣ ሲምፖዚየም ማካሄድና የስፖርት ውድድሮች በማከናወን እንዲሁም በሲዳማ ክልል የሚገኙ የመዳረሻ ቦታዎችን በማየት ተግባራዊ የሚደረግ ይሆናል፡፡ ይህም በየአካባቢው የሚገኙ የቱሪዝም መስህቦችን ለማስተዋወቅ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ዕቅዳችሁ ምን ይመስላል?

አቶ ዓለማየሁ፡- ቱሪዝም በዓለም ኢኮኖሚ የላቀ ድርሻ ከሚሰጣቸው ዘርፎች አንዱ በመሆኑ ሚኒስቴሩ ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራ ይሆናል፡፡ ዘርፉም በአገር ኢኮኖሚ ውስጥ የሥራ ዕድልን በመፍጠርና የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ረገድ ትልቁን ድርሻ ይይዛል፡፡ ይህንንም ተከትሎ የአገር ውስጥ ቱሪዝም ማጠናከር፣ የፀደቁ መመርያዎች ተግባራዊ ማድረግ፣ የቱሪዝም ልማት ማጎልበት፣ እንዲሁም ሌሎች ተግባሮችን ለማከናወን ዕቅዶችን ይዘናል፡፡ የስፖርት ዘርፉንም በመደገፍ ትኩረት ሰጥተን የምንሠራ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- በተለያዩ ቦታዎች ላይ እየፈረሱ ያሉ ቅርሶች አሉ፡፡ እነዚህን ቅርሶች ለመታደግና ጠብቆ ለማኖር ምን አስባችኋል?

አቶ ዓለማየሁ፡- መንግሥት የቅርስ ጥበቃና ልማት በተመለከተ ፖሊሲዎችን ቀርፆ እየሠራ ይገኛል፡፡ ከዚህ በፊት ተጓድለው የቀሩ ፖሊሲዎችን እንደ አዲስ በመከለስ ተግባራዊ እንዲሆኑ ለማድረግ ቅድመ ሁኔታዎችን አመቻችቷል፡፡ በአገሪቱ የሚገኙ ተዳሳሽንና ተንቀሳቃሽ ቅርሶችን ለመመዝገብ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያም በየቦታው የሚገኙ ቅርሶችን ለመጠበቅ ከቅርስና ጥበቃ ጋር በቅንጅት እየሠራን ነው፡፡ ወደፊትም የተለያዩ ሥራዎችን የምንሠራ ይሆናል፡፡  

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ከውጭ ይገቡ የነበሩ 38 ዓይነት ምርቶች እንዳይገቡ ዕግድ ተጣለ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ 38 ከውጪ የሚገቡ ምርቶች ላይ ዕገዳ...

በደቡብ አፍሪካ የተጀመረውን የሰላም ንግግር አሜሪካንን ጨምሮ ተመድና ኢጋድ እየታዘቡ ነው

ለሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ሰላማዊ መፍትሔ ለማምጣት በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት...

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ18 ቀናት ግዢ መፈጸሚያ ብቻ እንደሚሆን አይኤምኤፍ ተነበየ

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ0.6 ወር ወይም...

ጥቁር የመልበስ ውዝግብና የእምነት ነፃነት በኢትዮጵያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ኅዳር ወር ላይ በፓርላማ...