Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርበአዲስ ዓመት አዲስ የመደማመጥ መንፈስ ይስፈልገናል!

በአዲስ ዓመት አዲስ የመደማመጥ መንፈስ ይስፈልገናል!

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው

     ይህን ጽሑፍ የ2014 ዓ.ም. የመቀበያ በዓል ከማክበራችን በፊት አጠናቅቄ ለአርታኢው ለማድረስ ነበር ሐሳቤ፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ሳይሳካ ቀረና እነሆ አዲሱን ዓመት በተቀበልን ማግሥት ልልከው ተገድጃለሁ፡፡ ለመላው ኢትዮጵያዊያንና ወገኖቻችን ሁሉ በያላችሁበት እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሳችሁ በማለት ጽሑፌን ጀምሬያለሁ፡፡

     መቼም ሪፖርተርን ያህል ጋዜጣ ላይ ስለአዲስ ዓመት ሳወራ፣ ፖለቲካ ኢኮኖሚውን ወደ ጎን ለማለት አልችልምና እሱው ላይ ማተኮር ነው የምሻው፡፡ በተለይም ስለመነጋገርና መደማማጥ፡፡ እናም ራሴን እንደ አንድ ዜጋ ብቻ ሳይሆን፣ ለአገር ሰላምና ዕድገት እንደሚቆረቆር ጸሐፊ በመቁጠር ለውይይት በር የሚከፍቱ ሓሳቦችን ለማስመቀጥ እወዳለሁ፡፡

   እንደ አገር ያሳለፍነው ዓመት ብቻ ሳይሆን ያለፉት ሦስት ዓመታት ተኩል የሚሆኑ የለውጥ ጊዜያትም በአገር ላይ ያሳደሩብን ጫና በቀላል የሚታይ አይደለም፡፡ እነዚያን የበዙ የመከራና የፈተና ጊዜዎችን ደግሜ በማንሳት አንባቢያንን የሐዘን ስሜት ውስጥ መክተት ስለማልሻ፣ መጪውን ጊዜ እንዴትና በምን ዓይነት ጥረቶችና መደማመጦች፣ ያውም የሕግ የበላይነትን ጠብቀንና አስተካክለን ወደፊት እንራመድ የሚሉ ጭብጦች ላይ አተኩራለሁ፡፡

     እናም ከምንገኝበት አገራዊ ሁኔታ አንፃር አዲሱን ዓመት የምንቀበለው በአሮጌ የባህሪ አቁማዳችን እንዳይሆን ለመንግሥትም ሆነ ለፖለቲከኞቻችን፣ እንዲሁም ለሕዝባችን ጭምር  ልብ እንዲሰጥልን በአንክሮ በመመኘት እንደረደራለሁ፡፡

    በእርግጥ እስከ ጳጉሜን መጨረሻ 2013 .. ድረስ  በአገራችን የተፈጠረው የመካረር ፖለቲካ (በተለይ የሕወሓትና የሸኔ ለያዥ ለገናዥ ማስቸገር) ምኑ ተለወጠና በቀናት አዲስ ነገር ይጠበቃል ሊባል ይችላል፡፡ ነገር ግን አዲስ የተስፋ ዓመት ስንቀበል ድፍረን የምንመኘው ለውጥና መሻሻልን ስለሆነ፣ መጭውን ዕድላችንን የምንወስንበትን ይህንኑ የመነጋጋርና የመደማመጥ ተግባር ይቅደም እላለሁ፡፡

       አዲሱን ዓመት በአሮጌ ባህሪና አካሄድ መቀበል ማለት በአሮጌ አቁማዳ ውስጥ አዲሱን ወይን ጠጅ እንደ ማኖር ነው፡፡ አሮጌውን ልብስ በአዲስ እራፊ እንደ መጣፍ (እንደ መደረት) ነው፡፡ ጉዳት እንጂ ጥቅም አያመጣም የሚለው ዕይታ ሃይማኖታዊ ብቻ ሳይሆን ምድራዊ ነው፡፡ ምናልባትም ለባለፉት በርካታ ዓመታት በተመላለስንበት የጦርነትና የግጭት አዙሪት ውስጥ መግባታችን ነው አሮጌው አቁማዳ፡፡ በተለይ በርከት ላሉ ዓመታት ተንፈስ ያለን ሕዝብ ለስደት፣ ለሞትና ለእንግልት እየዳረገ ያለው የሰሜኑ ጦርነት ጉዳይ አንዳች ዕልባት እንዲያገኝ ካልተደረገ ከአሮጌም አሮጌ ዕይታ ያለው ኃይል እንዳሸነፈ ይቆጠራል፡፡

      በተለይ ሕወሓት በትግራይ ሕዝብ እየማለና እየተገዘተ ከአራት አሥርት ዓመታት በፊት በአሥር ሺዎች ሚቆጠሩ የትግራይ ወጣቶችን ገብሮ የፖለቲካ ሥልጣን ያዘ፡፡ ይዞም በአገር ላይ ኢፍትሐዊነትና የመልካም አስተዳዳር ዕጦትን ከማንገሥ በላይ፣ ይከተል የነበረው የዘውግ ፌደራሊዝም ተብዬ የተቃርኖ ሥርዓት የአገር አንድነትና የሕዝብን አብሮነት ክፉኛ የጎዳ ነበር፡፡ ይህ አስቸጋሪ ሁኔታ ደግሞ አገርን ወደ ከፋ ጫፍ ከመውሰድ ባሻገር፣ ሕወሓት መራሹን መንግሥት በሕዝብ ማዕበል እስከ መጠረግ አድርሶታል፡፡ ይህ እግዲህ የአሮጌ አቁማዳ ጣጣ ነው፡፡

   ‹‹በአረጀ ልብስ ላይ አዲስ እራፊ የሚያኖር የለም፣ መጣፊያው ልብሱን ይቦጭቀዋልና፡፡ መቀደዱም የባሰ ይሆናል፡፡ በአረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፣ ቢደረግ ግን አቁማዳው ይፈነዳል፣ የወይን ጠጁም ይፈሳል፣ አቁማዳውም ይጠፋል፣ አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ያኖረዋል…›› (ማቴዎስ ምዕራፍ 9 ቁጥር 16-17፡፡ ከተባለው ዕሳቤ ውጪ የሆነው ይህ ኃይል ተደራድሮም ሆነ የሕግ የበላይነትን አክብሮ የፖለቲካ ሥልጣኑን ማስቀጠል ሲገባ፣ መልሶ የትግራይን ሕዝብ ወደ እሳት መማገዱ በእጅጉ የሚያስቆጭ ነው፡፡

      ስለዚህ አዲሱ ዓመት ይዞልን የመጣውን የአዲስ ሕይወትና አካሄድ ወይን ጠጅ በአግባቡ ለመጠቀም፣ ሕወሓትም ሆነ መንግሥት በውስጣችን ያለውን አሮጌ አስተሳሰብና አመለካከት በማቆም የአሠራር ልምድና አካሄድ አቁማዳችንን መቀየርና ለአዲስ ዓመት የሚመጥን ባህሪ፣ ዘዴ፣ ታክቲክና ስትራቴጂ ይዘው መቅረብ አለባቸው፣ ግድም ይላቸዋል፡፡ አንድም ከግትርነትና ከእልህ ወጥተው ንፁኃንን እየፈጁና እስፈጁ ያሉ ኃይሎች ከሕገወጥ ድርጊታቸው መታቀብ ይኖርባቸዋል፡፡ በመንግሥት በኩልም አንድም ጉዳት የቀነሰና ውጤት የሚያመጣ ሕጋዊ ዕርምጃ ማጠናከር ወይም ለመነጋጋር ዝግጁ መሆን አለበት፡፡

      በእርግጥ መንግሥት በኩል (ሕወሓትም የክልል መንግሥት እንደነበር ባይካድም) በአዲሱ ዓመት የሚያደርገውን በርካታ ተግባራት ያቅዳል፡፡ ‹‹ፋብሪካ እገነባለሁ፣ የመኖሪያ ቤት ችግር እቀርፋለሁ፣ መንገድ እሠራለሁ፣ ስልክ፣ መብራት፣ ውኃ፣ አስገባለሁ፡፡ ትራንስፖርት አሻሽላለሁ፣ ግድብ እገነባለሁ፣ ትምህርት፣ ጤና፣ እርሻበገጠርና ከተማ አዳርሳለሁ፡፡ መከላከያና ደኅንነትን አጠናክራለሁ፣ ዓለም አቀፋዊ ግዳጆቼን እወጣለሁ፣ የውጭ ግንኙነቴን አበረታለሁ፣ ለዚህም በቂ በጀት ይዣለሁ›› እያለ ይተጋል፡፡ እነዚህ ሁሉ ዕውን የሚሆኑት ግን አገር ሰላም ውላ ማደር ስትችል፣ ሕዝብም ዕፎይ ሲል ብቻ  ነው፡፡

    ለመንግሥትም ሆነ ለአገር ዕቅዶች መሳካት ደግሞ ሕዝብና መንግሥት ብቻ ሳይሆኑ፣ ራሳቸው ፖለቲከኞችና ምሁራንም በየፊናቸው ድርሻቸውን መወጣት አለባቸው፡፡ በተለይ ሁሉም ከአሮጌ አቁማዳ ውስጥ ወጥተው፣ የአመለካከትና የተግባር ችግርን ከየውስጣቸው አውጥተው፣ በአዲስና የተሻለ የአሠራር ሒደት ለመቀየር ራሳቸውን ሊመረምሩና ሊደማመጡ ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከመሀል ተው ባይና እስኪ በዚህ ይሁን የሚል አማራጭ ያለው ኃይል ብቅ ብሎ አዲስ ምዕራፍ መክፈት ግድ ይሆናል፡፡ በውጭ ያለው አድሎአዊ የሴራ ማደራደር ተፅዕኖን በማስቀረት ማለት ነው፡፡

        እዚህ ላይ በጥብቅ መስተዋል ያለበት ለማንም ሆነ ለምንም ቀይ መስመር መቀመጥ ያለበት ሕግና ሥርዓትን የማክበሩ ጉዳይ ነው፡፡ በተለይ ተፋላሚ ወገኖችም ሆኑ በግጭቱ ተጎጂ የሆኑ ሰዎች የአንድ አገር ዜጎች እንደ መሆናቸው፣ አገር የምትመራበትን ሕገ መንግሥት መጠበቅና ማስጠበቅ የሁሉም ግዴታ ነው መሆን ያለበት፡፡ ለድርድር የማይቀርበው አሮጌም ይባል አዲስ አቁማዳው ማሰሪያ ይኼው ነው፡፡

    ይህ የሚሆነው ደግሞ  ሕዝብም ሆነ መንግሥት የተፈጠረው ለታላቅ ምድራዊና ሰማያዊ ዓላማ በመሆኑ ነው፡፡ አሁን በተጨባጭ እየታየ እንዳለው ማንም ዝም ብሎ እንዲፈነጭ፣ ቀጪና ተቆጪ ሳይኖረው እንደ እንስሳ ያገኘውን እየበላ መረን ሆኖ እንዲኖር አልተፈጠረም፡፡ የየራሱን ፍላጐትና ጥቅም ብቻ እያሳደደ ሕዝብ በመንግሥት ላይ፣ መንግሥትም በሕዝቡ ላይ ጣቱን እየቀሰረ፣ የተወሰነ የኅብረተሰብ ክፍል መንግሥትን እያስቸገረና እያማረረ፣ መንግሥትም በሕዝብ ላይ እንደ ልቡ እየዘለለና እየጨፈረ እንዲኖር አልተፈጠረም፡፡

    ሕዝብ እርስ በርሱ በፍቅርና በሰላም ተቻችሎ መኖር እንዳለበት በምድር ብቻ ሳይሆን በሰማይ የተደነገገ እውነት ነው፡፡ በመልክ፣ በፆታ፣ በዘር፣ በቋንቋ፣ በእምነት፣ በባህል፣ በአካልና በአዕምሮ ተለያይቶ የተፈጠረው እርስ በርሱ እንዲተዋወቅና አብሮ እንዲኖር መሆኑ በቁርዓንም/በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሠፈረ ነው፡፡ ይህ ልዩነት ጌጥ እንጂ ሸክም አለመሆኑ እየታወቀ ፅንፈኞች ሕዝብን ዒላማ አድርገው ማጥቃታቸውም ሆነ ማለያየታቸው የአሮጌ አቁማድ ዕሳቤ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ በምንም መለኪያ ተባይነትም የለውም፡፡

    አምላክ አለያይቶ የፈጠረውን ሕዝብ የግድ አንድ ዓይነት ለማድረግ የእኔን እምነት፣ የእኔን ባህል፣ የእኔን መንገድ መከተል አለበት ማለት ፈጣሪን መዳፈር ብቻ ሳይሆን እጅግ የበዛ ድንቁርና ነው፡፡ በልዩነታችን ኮርተን፣ በአንድነታችን ፀንተን ተከባብረንና ተደማምጠን የመኖር ግዴታ ያለብን መሆናችንም ለድርድር የማይቀርበው ከዚሁ አንፃር ነው፡፡ ጎበዝ አንታለል፡፡ ለምድራዊ ቆይታችንም ሆነ ለሰማዩ ቤታችን የሚጠቅመንን ነገር አንዘንጋ፡፡

     ለዚህ ደግሞ ተመራጩ መንገድ ራስን መመርመር (መገምገም) እና ራስን መታገል እንጂ፣ አንዱ በሌላው ላይ እያላከከና ጣት እየተቀሳሰረ ባለፈው ዓመት ጆሮ እየሰማ መጥፎ አሠራርን መቀጠል አይደለም፡፡ በተለይ ሕወሓትንና ኦነግ ሸኔን በህቡዕም ሆነ ፊት ለፊት የሚደግፉ ኃይሎች ሕዝብ እንደ ሕዝብ የተፈጥሮ በረከቶችንና ሕገ መንግሥታዊ መብቶችን ማስከበር  እንደሚቻል ማጠየቅ አለባቸው፡፡

    እንዲህ ያሉ ኃይሎችን ሕዝቡ መታገሉ ደግሞ በራሱም ሆነ በሌሎች ላይ የሚደርሱ የመብት ጥሰቶችን መዋጋት ግዴታውና የህልውና ዋስትናው ስለሆነ ነው፡፡ በመንግሥት ውስጥ የሚታይን ፍትሐዊነትን፣ አለመከባበርን፣ አለመተባበርንና ለሰላም እንቅፋት መሆንን ራሱ መታገል  አለበት፡፡ ከአሮጌ አቁማዳ ወጥቶ ሕዝብ መብቱን በራሱ ማስከበር ካልቻለ፣ መብቱ ሲነካ ‹‹ለምን?›› ብሎ ካልጠየቀ፣ ሕገወጥነትን ካልተቃወመ በቀር የሌቦች፣ የነፍሰ ገዳዮችና የሕገወጦች መፈንጫ መሆኑን ሊዘነጋ አይገባም፡፡

    ከዋናው የደኅንነትና የመኖር ዋስትና በተጨማሪ ሕዝብ ነቅቶ ካታገለ የትራንስፖርት ታሪፍ ቀርጣፊዎች፣ የአሻጥረኛ ነጋዴዎች መጫወቻ መሆኑም ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ እዚህ ላይ የሕግ ጥሰቱ በፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆን በሕዝብ ውስጥም ስለሚኖር፣ ሁሉም ሕግጋትን የማስከበር ኃላፊነት አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ በአዲሱ ዓመት አዲስ ምዕራፍና መንፈስ ከፍቶ መረባረብ ነው የሚበጀው፡፡

      እንደ ዜጋ ትንሹም ትልቁም የራሱን ሚና ሳይጫወትና የራሱን ኃላፊነት ሳይወጣ ለትልቁም፣ ለትንሹም የመንግሥትን እጅና ጣልቃ ገብነት መጠበቅ የማይበጀውም ከዚህ አንፃር ነው፡፡ አገርን ወደ ግጭትና ትርምስ፣ ሕዝብን ወደ ሥቃይና መከራ የሚገፉና በየጊዜው በክፉ ሰዎች እየተፈበረኩ ለሚሠራጩ ያልተረጋገጡ ወሬዎች ሰለባ ከመሆን፣ ራሱን መጠበቅ የሕዝቡ የአዲሱ ዓመት ግዴታ መሆን ነው ያለበት፡፡

     በየትኛውም ውዥንብርና የአረጀ ፕሮፖጋንዳ ሳይወናበዱ፣ መሬት ላይ ያለውን እውነት ለማወቅ ጥረት ማድረግ አለበት፡፡ እንዲህ ያለ የመረጃ ማሳሳትና አገርን ወደ ስህተት የሚወስድ የመረጃ ፍሰት በመንግሥታዊ አካል ከተፈጸመም ሁሉም በሕግ መጠየቅ አለበት፡፡ የመንግሥት መረጃ  አስቀድሞ አለዚያም ቢዘገይም ተገቢ  በሆነ መንገድ ለሕዝብ በግልጽ መነገር አለበት፡፡ ይህን አካሄድ ደግሞ ማረምና ማስተካከል የሚያስፈልገው፣ በአዲሱ ዓመትና በአዲስ መንፈስ ሊሆን ይገባል፡፡

      ለነገሩ የመንግሥትን ብቻ ሳይሆን  የእምነት አባቶቻችንና ሚዲያዎቻች (መርህና በሥነ ምግባር እስከ ሠሩ ድረስ) የሚነግሩንን እየሰማንና እውነቱን እያረጋገጥን መጠቀም እንደ ሕዝብ ይጠበቃል፡፡ አሳዋቂ፣ አስተማሪና አስጠንቃቂ መልዕክቶችን በጥሞና ማዳመጥም ግዴታችን ነው፡፡  በተለይ የፖለቲካ ሰዎችና ሚዲያዎች የተለያዩ ስም አጥፊ ቅፅሎችን እየለጠፉ ከመተቸትና ከማጣጣል ይልቅ፣ አገርን ማስቀደም የሁሉም ግዴታ መሆን አለበት፡፡

     በተለይ እየተከሰተ ያለውን ግጭት ለመባባስ ነዳጅ የሚያርከፈክፉ ተራ የዩቲዩብ ነጋዴዎችና የፖለቲካ ሸቃጮች ከመልዕክቱ በስተጀርባ ሊኖር ስለሚችለው ሥውር ዓላማ ከመጨነቅ ይልቅ፣ ፊት ፊት በግልጽ የተላለፈውን መልዕክት በቁሙ (At Its Face Value) ማየትና የተሻለውን መምረጥ፣ ከአድሎና ኢሚዛናዊነት መለየት የእኛ ኃላፊነት ነው፡፡ በአዲሱ ዓመት ወደ አዲስ መንፈስ መሸጋገር የሚባለው አንዱ ጭብጥ ይኼው ነው፡፡

       እስከ ዛሬ በነበረው የአሮጌ አቁማዳ አስተሳሳብ መንግሥት ሲነግረን ‹‹ውሸቱን ነው›› እያልን፣ መንግሥትም ሲነግሩት ‹‹ስሜን ሊያጠፉ ነው፣ ቀጣፊዎች ናቸው›› እያለ መዝለቁ ነው፡፡ ይህ መጣረስ ደግሞ የሕዝብንና የመንግሥትን ቋንቋ ያዛንፋል፡፡ ውኃ አምጣ ሲሉት ድንጋይ መቀባበልንም ያስከትላል፡፡ በዚህ ዓይነት መሳከር ከቀጠልን ግን ውድቀታችን ከባቢሎን የባሰ ነው የሚሆነው፡፡ ስለሆነም ወደ ቀጣይ ምዕራፍ ለመሻገር ይህ ነገር መታረም አለበት፡፡

       ሕዝብ (በውስጡ ልሂቁና ፖለቲከኛው እንዳለ ልብ ይሏል) እና መንግሥት መደማመጥ አለባቸው፡፡ አረረም መረረም ሕዝብ መንግሥትን፣ መንግሥትም ሕዝብን መስማት አለበት፡፡ ሕዝብ እንደ ሰው ሲፈጠር ሁለት ጆሮና አንድ አፍ እንዲኖረው ተደርጐ ነው፡፡ ይህም ከሚናገረው እጥፍ እንዲሰማ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የራሳቸውን መገናኛና አክሳሪ ዓላማ በሕዝብ ላይ ለመጫን የሚሹ ኃይሎችን አንቅሮ መትፋትና ለጋራ ሰላምና ለአገር ደኅንነት ዘብ መቆም ከሁላችንም ይጠበቃል፡፡

    በእርግጥ መንግሥት የራሱ መስሚያዎች (ጆሮዎች) አሉት፡፡ የእሱ ጆሮዎች ቁጥር ደግሞ ከሁለት በላይ ናቸው፡፡ ዋንኛው የመንግሥት ጆሮ ሕዝብ ነው፡፡ በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚተውኑ ተቃዋሚ ቡድኖችና ግለሰቦች፣ ገለልተኛ የሆኑና ሐሳባቸውን በነፃነት በመግለጽ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን የሚጠቀሙ ዜጐች፣ የውስጥና የውጭ ሚዲያዎችና የራሱ በርካታ ተቋማት በሙሉ መንግሥት ስለባህሪው የሚሰማባቸው ዕድሎቹ ናቸው፡፡ ስለዚህ አድማጭ መንግሥት መፈጠር አለበት፡፡

      ‹‹እኔ ብቻ ልናገር፣ የእኔን ብቻ ስሙ…›› የሚል አካሄድ የአሮጌ አቁማዳ ዕሳቤ ነው፣ ጥቅም የለውም፡፡ በታሪካችንም ሆነ በብዙ አገሮች እንዳየነው ምላስ ብቻ እንጂ ጆሮ ያልፈጠረበት መንግሥት ፍቅር አያገኝም፡፡ ለራሱ የሚጠቅመውን ብቻ እየመረጠ የሚሰማ መንግሥት ለሕዝብ ጥያቄዎች ተገቢ መልስ መስጠትም  ይሳነዋል፡፡ በዚህም ሕዝቡ ይንቀዋል፣ ይጠላዋል፡፡ ለንግግሩም ጆሮውን ይነፍገዋል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ዓይነት መንገዳገድ እንዳይከሰት ራስንና ውስጥን መፈተሸ በሕዝብ ከተመረጠው መንግሥት ይጠበቃል፡፡

     በመሠረቱ የብዙዎቹ የሠለጠኑና ያደጉ አገሮች የሥልጣኔያቸው፣ የአንድነታቸው፣ በዓለም ፊት ለመቅረብ ያበቃቸው፣ የሰላማዊ ኑሮአቸው፣ የሀብታቸው ምንጭ መመርያ መነጋጋርና በሰላማዊ አማራጭ መታገል ነው፡፡ ከሁሉም ነገር በፊት አገርና ሕዝብን ማስቀድም እንጂ፣ እልህና ካልበላሁት ልድፋው የሚል ግትርነት አይደለም፡፡ እኛ ያሳለፍነው ታሪክ ግን ከዚህ የተቃረነ ኃይልና ጉልበት ሳይፈትኑ በዘርና ብሔር እየተቦደኑ መተጋተግ ስለነበር ይህን ኋላቀር አካሄድ አውልቆ መጣል ከሁሉም ይጠበቃል፡፡

ማጠቃለያ

የገባንበት አገራዊ ግጭትና ጦርነት አንድ ቦታ ላይ የሚቆምበት ነገር በአዲሱ ዓመት መምጣት አለበት፡፡ 2014 .. ከነባር ችግሮቻችን ለመላቀቅ ሕዝብ እንደ ሕዝብ፣ መንግሥትም እንደ መንግሥት ራሳችንን እንመረምር፡፡ ከሐሰተኛ ወዳጅ እውነተኛ ጠላት ይሻላል የሚለውን ሁሉም ፖለቲከኞቻችን አጢነው፣ በውጭ ኃይሎች ከመነዳት መቆጠብም ለሁሉም ተፋላሚዎች መነገር ያለበት ጉዳይ ነው፡፡

    ዋናው ነገር አንዳችን ሌላኛችንን የምንሰማ ብሔራዊ ራዕይ ያለን ዜጎች እንሁን፡፡ አጉል የመንግሥትን ጀርባ ሳይበላው የሚያክኩም ሆነ፣ ሁሉንም ነገር ለመተቸትና ለመቃወም ያውም በኃይልና አመፅ ለመፋለም ብቻ የተዘጋጁ ኃይሎች እንዳንሆን መልካሙን መካከለኛ መንገድ የምንከተል እንሆን ዘንድም እንደማመጥ፡፡ የዛሬን ብሥራት በአሮጌ ጆሮ የማዳመጥ ባህል አይጠቅመንምና ይቅርብን፡፡ ያለፈው አልፏልናዳግም ላይመለስ ሄዷልናአዲሱን ዓመት በአዲስ መደማመጥ ተቀብለን እናስተናግደው! አሜን!

ከአዘጋጁ፡– ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...