Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርለተቸረ የደግነት ጥግ የተከፈለ የክፋት ጥግ

ለተቸረ የደግነት ጥግ የተከፈለ የክፋት ጥግ

ቀን:

በሁሴን አዳል መሐመድ (ዶ/ር)

ከሳህል በረሃ መስፋፋት ጋር ተያይዞ የሰሜኑ የአገራችን ክፍል ዝናብ አጠር ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ በዓለም ላይ ለተከሰተው የአየር ንብረት ሚዛን ለውጥ ቀድሞ ተጋላጭ የሆነው የትግራይ ፍለ ሀገር ቀጥሎም ወሎ ፍለ ሀገር ነው፡፡ ትግራይና ወሎ ፍለ ሀገሮች በተደጋጋሚ ጊዜ በድርቅ እየተጠቁ  በየዙሩ በርካታ ሕዝብ በረሃብ ጠኔ አልቆባቸዋል፡፡ የወሎ ረሃብ እየተባለ የሚጠራውን ረሃብ ያስታውሷል፡፡ የደርግ መንግሥት በአገራችን በድርቅ የሚከሰት ችግርን ለመቋቋም አንድ መፍትሔ አድርጎ የወሰደው፣ በየክፍለ ሀገሩ የዕርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን ሕፈት ቤት መክፈት ነበር፡፡

በዚህም መሠረት በወሎ ፍለ ሀገር አንድ ብሎ የተጀመረው ሕፈት ቤት የማቋቋም ተግባር ከጎጃም ፍለ ሀገር በስተቀር ኤርትራን፣ ጨምሮ 13 ፍለ ሀገሮች ተቋቋመ፡፡ ነገር ግን እስካሁንም በድርቅ የተነሳ ሕዝብ ይራባል፣ ይሞታልም፡፡ በዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍእንዲሉ የተፈጥሮ ድርቅ ሳያንስ ደረቅየብሔር ፖለቲካበድርቅ ላይ ተጨምሮ የአካባቢው ሕዝብ አልፎ ተርፎም የኢትዮጵያ ሕዝብ በድርብ ተያያዥ ችግሮች ለዘመናት እየተፈተነ ይገኛል፡፡ የዚህየብሔር ፖለቲካመነሻም ይኸው የሰሜኑ የአገራችን ክፍል ነው፡፡ በተቀረው የአገራችን ክፍልም አለ ቢባል እንኳ የተሠራጨው ከዚሁ የሰሜኑ የአገራችን ክፍል ነው፡፡

- Advertisement -

የሰሜኑ የአገራችን ክፍል ለረዥም ዘመን ሕዝብ የሠፈረበት በመሆኑና መሬቱ ለዘመናት በመታረሱ ለምነቱ ተሟጥጧል፡፡ በተለይም በትግራይ ችግሩ በጣም የከፋ በመሆኑ፣ አርሶ አደሩ በቂ ምርት አምርቶ በምግብ ራሱን መቻል ከተሳነው ቆይቷል፡፡ በዚህ የተነሳ በዚያን ወቅት የትግራይ አርሶ አደር በድርቅ ወቅት የሚያጋጥም የቀለብ እጥረት ችግር መቋቋሚያ አማራጭ መፍትሔ (Coping Mechanisms) ነበረው፡፡ ይኸውም በምርት መሰብሰቢያ ወቅት ምርት ወደ አላቸው አጎራባች በወሎናጎንደር አካባቢዎች በመሄድ የተለመደ ሥራ መሥራት ነው፡፡ 

ንቃት ያላቸውና የተማሩት ትግሬዎች ወደ ከተማ በመሰደድ ከተሞች በዘረጉት ሥልተ ምርት ተሳታፊ በመሆን፣ በልዩ ልዩ የሙያናጉልበት ሥራዎች እንደ ችሎታቸው ተሠማርተው በየደረሱበት ከተማ በቋሚነት ለመኖር ከአካባቢው ኅብረተሰብ ጋር ይተሳሰራሉ፡፡ በግብርና ከሚተዳደሩት መካከል ግን በአጎራባች ወደሚገኙ  የወሎናጎንደር የገጠር አካባቢዎች በተመላላሽነት በመዘዋወር የሚከተሉትን ሁለት ዋና ዋና የኑሮ ጉድለት ማሟያ ዘዴዎች ይጠቀሙ ነበር፡፡ አንዱ ጥቂት ሲሚንቶ በከረጢት በመቋጠር ወደ አካባቢው በመምጣትሰባራ እንሥራ ያለሽእያሉ የአገሬውን ሰባራ የሸክላ ዕቃ ሁሉ (ጋን፣ አካፋይ፣ ኮሪት፣ ገንቦ፣ ድስት፣ ወጪት፣ ምጣድ፣ ረጀት፣ ቶፋ) በመጠገን ለሥራቸው ክፍያ በእህል ይቀበላሉ፡፡ በገንዘብ መክፈል አልተለመደም ነበር፡፡ ሌላው ይህን ክህሎት የሌላቸው ዓውድማ ዳር ለልመና በመቀመጥ ምርቱ ተነስቶ ሲጠናቀቅ  የሚሰጣቸውን እህል ይቀበላሉ፡፡

በአገሬው አባባል ዓውድማ ዳር ተቀምጦ እህል የሚቀበል ሰው ቧጋች ይባላል፡፡  ያኔ በገጠሩ ክፍል የግብርና ሥራ በገንዘብ ክፍያ ማሠራት ያልተለመደ ስለነበር ሰው በጉልበቱ የግብርና ሥራ  ሠርቶ በገንዘብም ይሁን በዓይነት የሚቀበለው ክፍያ አልነበረም፡፡ የተጨማሪ ሰው ጉልበት የሚያስፈልገው የግብርና ቤተሰብ ቢኖር ወንፈልና ደቦ/ጅጌ የሚባሉ የቡድን ሥራ ትብብር ሥልቶች ይጠቀማል፡፡ ችግር የማቃለያው መፍትሔ  ይህ ዓይነቱ የማኅበራዊ ትስስር ዘዴ ብቻ ነበር፡፡ 

አንድ ሰው ቧጋች ለመባል ከሩቅ አካባቢ ብቻ መምጣት የለበትም፡፡ ቀለቡን ለማሟላት ዓውድማ ተቀምጦ የሚለምን ማንኛውም መሬት የሌለው የአካባቢ ሰው ጭምር መጠሪያ ነው፡፡ ቢሆንም የአገሬው ሰው ዓውድማቧጋች ተቀምጧልየሚለው ለአካባቢው ሰው ሲሆን እንጂ፣ ለእንግዶቹ ሲሆን ግን ከትህትና አንፃር ዓውድማትግሬ መጥቷልነው የሚለው፡፡ ቧገታ የቀለብ እህል እጥረት ማሟያ የተለመደ ጤናማ የኑሮ ስትራቴጂ መሆኑ በኅብረተሰቡ ዘንድ ይታወቅ ስለነበር፣ ከዓውድማ እህል የሚለምን ሰው ዝቅ ተደርጎ ዓይታይም፡፡ ለምኖም ባዶ እጁን አይመለስም፡፡ ለቧጋች ያልተሰጠለት ምርት አይበረክትም ስለሚባል፣ ምርቱ ከዓውድማው ተነስቶ ጎተራ ገብቶ ሲያበቃ ዓውድማ ለተቀመጠ ቧጋች ሁሉ እህል ይሰጣል፡፡ ቧጋቹም ደስ ብሎት ሲሄድ የምርቱ ባለቤትም ማኅበረሰባዊ ግዴታውን ስለተወጣ እርካታ ይሰማዋል፡፡

አንድ የትሕነግ ፖለቲከኛ ነኝ ባይ በትግራይ ቴሌቪዥን ቀርቦ ሕዝብን ከሕዝብ ለማራራቅ ጥራዝ ነጠቅ ዕውቀቱን ተጠቅሞ፣ነፍጠኞች ቧጋች ይሉናልብሎ መርዙን ሲነሰንስ ሰምቼው በጣም አድርጌ አዘንኩ፡፡ ቧገታ እንዲህ ያለ የሀብት እጥረት ክፍተት መሙሊያ ችግር መቋቋሚያ አገር በቀል ስትራቴጂ  እንጂ ፀያፍ ቃል አልነበረም፡፡  የአማራ ሕዝብ ለየሁኔታው የሚስማማ ልዩ ልዩ የአደጋ ጊዜ መቋቋሚያ ስትራቴጂዎች ስለነበሩት፣እልፌስለሚባል አንድ ሌላ የችግር ጊዜ ስትራቴጂ ጨምሬ ልግለጽ፡፡ ይህ የመረዳጃ ስትራቴጂ ጧሪ ቀባሪ ለሌላቸው በዕድሜ የገፉ አረጋውያን መታደጊያ የሚውል የማኅበራዊ ኑሮ ትብብር ሥሪት ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ የሚገኝ  አረጋዊእልፌየሚባለው ሠርቶ ራሱን የማይችልበት ዕድሜ ላይ በመድረሱ ህልውናው መጠበቅ የሚችለው፣ በማኅበረሰብ ትብብርና ኃላፊነት መሆኑ ታውቆ በጎጡ ውስጥ ባለ አቅም ባለው አባወራ ቤት ሁሉ (እልፍ) በዙር እየተላለፈ እስከ ዕለተ ሞቱ በጥሩ እንክብካቤ ሲጦር ነው፡፡እልፌሲሞት ወይም ስትሞት ሕይወቱ ባለፈበት ተረኛ አባወራ ቤት አማካይነት ዕድሩ በክብር ይቀብረዋል፡፡

አሁን መቄዶኒያ የሚያደርገው አበርክቶት ዓይነት ማለት ነው፡፡ አንዳንዴ ተማርን የሚሉ አንዳንድ ሰዎች በማያውቁት ነገር ጥልቅ ብለው በመበጥረቅ፣ የቀድሞ ሰዎች የገነቡትን ጠንካራ የማኅበረሰብ ትስስር ድር ሲያጣጥሉና ሲበጣጥሱ ሳይ ይገርመኛል፡፡ የወቅቱ ተፅዕኖ ፈጣሪዎቹም ደግሞ እነርሱ መሆናቸው ይደንቀኛል፡፡
የተነሳሁበት ዓላማ ቀደም ሲል ስለነበሩሰባራ እንሥራ ያለሽእናቧገታወይምእልፌየኑሮ ስትራቴጂ ለመግለጽ ሳይሆን፣ በአማራናትግሬ ሕዝብ መካከል ስለነበረ የማውቀው ጤናማ የነበረ የማኅበረሰብ ግንኙነት ላካፍል ወድጄ ነው፡፡ በእኔ ዕድሜ ደረጃ ያሉ እዚያም እዚህም የሚኖሩ የኢትዮጵያአገሬ ሰዎች ቅንነት የጎደላቸው ካልሆኑ በስተቀር ያስታውሱታል ብዬ አስባለሁ፡፡ በዚህ ግንኙነት በርካታ የትግራይ ሰዎች ወደ ወሎ ይመጡ ነበር፡፡ እኔ ትውልዴ ቦረና ሳይንት አውራጃ ሲሆን፣ የተንቤን ሰዎች ነን የሚሉ ወደ አካባቢው ይመጡ እንደነበሩ ትዝ ይለኛል፡፡

ለሌሎች የወሎና ጎንደር አውራጃዎች የሚቀርቡትም የትግራይ አውራጃዎች ሰዎች እንደዚሁ ያደርጉ እንደነበር እሰማለሁ፡፡ ሰዎቹ የመጡበትን ጉዳይ አሳክተው እስከሚመለሱ ድረስ የሚቆዩት በአገሬው ቤት በእንግድነት በመቀመጥ ነው፡፡ የተለመደ ግንኙነት በመሆኑ ሰዎቹን በእንግድነት ለመቀበልም ይሁን ለመቀመጥ፣ ተቀባዮችንም ሆነ እንግዶችን የሚያጠራጥር ምንም ነገር አልነበረም፡፡ ዋስም ሆነ መታወቂያ አይጠየቁም፡፡ አንድ እንግዳ የሆነ ሰው ዓምና የተቀመጠበትን ቤተሰብ የራሱ አድርጎ በማየት፣ በሚቀጥለውም ዓመት ቢፈልግ ሰተት ብሎደህና ከረማችሁ ወይበማለት ገብቶ ፈታ ብሎ ይስተናገዳል፡፡ ቤት የእግዚአብሔር/የአላህ ነው ብሎ የሚያምን ወሎዬ ኅብረተሰብ በመሆኑ ከሩቅ የመጣው እንግዳ የት አርፋለሁ ብሎ አይጨነቅም ነበር፡፡

እንግዳው በአረፈበት ቤት ውስጥ ቤት ያፈራውን ይመገባል/ይጠጣል፣ ቡና ይፈላለታል፣ ሠርቶ የሚውለውንም ሆነ የቧገተውን እህል ያስቀምጣል፣ ወደ መኝታው ከመሄዱ በፊት የቤት ልጆች እግሩን ያጥባሉ፣ በተዘጋጀለት መኝታ ያድራል፡፡ በእኛም ቤት የሚደረገው እንዲሁ ነበር፡፡ የቤተሰብ ልጆች በየተራ የእንግዳ እግር እንዲያጥቡ ስለሚታዘዙ እኔም ተራዬ ሲደርስ አጥብ ነበር፡፡ የእንግዳውን እግር ለብ ባለ ውኃ አጥበን፣ አውራ ጣቱን ስመንና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም የጓጎለ እግሩን በቅባት ከአሸን በኋላ ምርቃት በመቀበል፣ እንግዳውን ወደ ተዘጋጀለት የመኝታፍራ ስንወስድ የነበረው አይረሳኝም፡፡

ትግሬና አማራ መሆንና አለመሆን ወይም የቋንቋ ተናጋሪነት ልዩነት ለግንኙነቱ ዕንቅፋት አልነበረም፡፡ በዚህ ሁኔታ እየተስተናገደ የቆየ እንግዳ የመጣበት ጉዳዩ ሞልቶለት ወደ አገሩ የመመለሻው ቀን ሲደርስ ሲያጠራቅም የከረመውን እህል በአቅራቢያሚገኝ ገበያ አውጥቶ በመሸጥ፣ አህያ ወይም በቅሎ ገዝቶ የተረፈውን ዳውላ እህል በገዛው እንስሳ/እንስሳት ጭኖ በእንግድነት ከከረመበት ቤተሰብ ጋር ተሳስቆና ተመራርቆ ይመለሳል፡፡ የመሰነባበቻ ቡና ተፈልቶ፣ ስንቁ በአገልግል ተቋጥሮለት ሽኝት ይደረግለታል፡፡ እንግዳው የመጣበትን ጉዳይ አከናውኖ በሰላም እየተመለሰ እንደሆነ የሚታወቅ ቢሆንም፣ ከቤተሰቡ ሲለይ የሚፈጠረው ስሜት የከረመ እንግዳ ወደ ቤቱ የሄደ ያህል ሳይሆን፣ አንድ የቤተሰብ አባል የተነጠለ ያህል ቅር ቅር ያሰኝ ነበር፡፡ ይህን ካለፈው 50 ዓመታት በፊት የነበረ ትዝታ የማቀርበው የወሎና የትግሬ ሰዎች በጠላትነት የሚተያዩ እንዳልሆኑ ለማሳየት ነው፡፡ የወሎን ሰው የደግነት ጥግ ለማሳየትም ጭምር ነው፡፡ ይህ ታሪክ ልቦለድ አይደለም፡፡

ቀደም ሲል የነበረ እውነተኛው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት፣ የኢትዮጵያዊያን የእንግዳ ተቀባይነት ባህሪ መግለጫ አብነት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንግዳ ተቀባይ ነው የሚባለው ከዚህ ነው የሚነሳው፡፡ እስከ ንጉሠ ነገሥቱ ዘመን ፍፃሜ ድረስ ብሎም እስከ 1980ዎቹ መጀመርያ የነበረው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ይንን የመሰለ ነበር፡፡ እዚህም እዚያም ያለው ሕዝብ እኩል የገዥ መደብ ጭቆና ቢኖርበትም፣ የገዥ መደብ ጭቆናው በሕዝብ መካከል የነበረውን መቀራረብና መፈቃቀር አላደበዘዘውም ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች መጤና ነባር በመባባል እየደረሰ ያለው ማግለልና መጠቃቃት፣ እንዲሁም በአገሩ እንደ ሰው ሞቶ እንደ ሰው መቀበር አለመቻሉ እጅግ አድርጎ ልብን ያደማል፡፡ ከንጉሡ ዘመን ፍፃሜ በኋላ በተከታታይ በመጡት ደርግና ኢሕአዴግ ወቅት በተከሰተው ተማሪ መራሽ የፖለቲካናኢኮኖሚ ሥርዓት ለውጥ ምክንያት ሁኔታዎች ተቀይረዋል፡፡

የፖለቲካ ኢኮኖሚው ሥርዓት ለውጥ  ያስከተለው  የሕዝብ ሆድ ለሆድ መሻከርና የኢኮኖሚ ግንኙነት ሚዛን ለውጥ፣ የነበረውን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ይዘትና መፈቃቀር ታሪክ አድርጎታል፡፡ ከሕዝብ አብራክ ወጣሁ የሚል ጠባብየብሔር ፖለቲከኛቡድን ሁሉ በፈጠረውዘመናዊ የኑሮ ስትራቴጂ” (በአቋራጭ መበልፀጊያ ስትራቴጂ) በሕዝብ በደል ላይ ተደላድሎ ይኖራል፡፡ በደርግ ዘመን በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የተደረገው ረዥም ጊዜ የወሰደ ጦርነት፣ በተለይም በትግራይ ሕዝብ ጉያ ውስጥ የበቀለ ትሕነግ የሚባል  አረም የወሎና የትግራይ ሕዝብ የነበራቸውን መፈቃቀርና መተሳሰብ  በጉልበት ነጥቋቸዋል፡፡ ትሕነግና ትሕነግ ያሳደጋቸው የብሔር ፖለቲከኞች የኢትዮጵያን ሕዝብ በቋንቋ ግድግድ አጥር ውስጥ ቀርቅረው ስለብሔር ጭቆና  ጉዳይ ያልገባቸውን  እየተበጠረቁ ወጣቱን በብሔር ጭቆና የአፍዝ አደንግዝ ትርክት ለፍርፋሪ ለቃሚነት፣ ኅብረተሰቡን በማጭበርበር ለሴፍቲኔት ተጠዋሪነት በመዳረግ እነርሱ ተረኛ ገዥ መደብ በመሆን በሕዝቡ ድህነት ላይ ተመቻምቸው ዓለማቸውን ቀጭተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት እየተደረገ ያለው የህልውና ጦርነት መንስዔ የትሕነግ የክፋት ሥራ ውጤትና ሁሉንም የፖለቲከኛ ትርክት  ያለ ማቅማማት እንደ ወረደ ቡና የሚጠጡ አፈኛ የሆኑ ሆድ አደር ደቀ መዝሙሮቿ ተታላይነት ወይም አገልጋይነት ውጤት ነው፡፡ ትሕነግ ሰፊ የጦርነት ዝግጅት በድብቅ ስታደርግ ቆይታ ሴራዋን በስለላ ቀድሞ ማክሸፍ ወይም አንፃራዊ ተመጣጣኝ ዝግጅት ማድረግ ሳይቻል ቀርቶ፣ በአጎራባች በሚኖረው የአማራና አፋር ሕዝብ ላይ መጠነ ሰፊና ድንገተኛ የጥቃት ዘመቻ ከፍታ በሕዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳትና ዕልቂት አድርሳለች፡፡ ከአማራናአፋር ሕዝብ ጋር ለዕልቂትና እንግልት የተዳረገው የትግራይ ሕዝብ ጭምር ነው፡፡

የደረሰው ጉዳትና ዕልቂት ለታሪክ ጸሐፊዎች ጥልቅ ትንተና የሚተው የመጨረሻው የክፋት ጥግ ነው፡፡ በመሆኑም ከወሎ ለተቸረው የደግነት ጥግ በትሕነግ አማካይነት የትግሬ ሰው በአምላሹ ለወሎዬው ወሰን ያለፈ የክፋት ጥግ ከፍሏል፡፡ የክፋት ጥጉ ለጎንደር ሕዝብም የተከፈለ ስለሆነ በአማራ ሕዝብ ደረጃ ሰፋ ብሎ ሊታይ ይችላል፡፡ የችግሩ ዳፋ በአጠቃላይ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ደርሷል፡፡ ይህ አስከፊ ተግባር የሰይጣን እንጂ ጭራሽ የሰው ልጅ ባህሪ አይመስልም፡፡ ነባሩን የትግራይ ሕዝብ ባህሪም አይገልጽም፡፡ ከትግራይ ሕዝብ አብራክ የወጡ ለክፋት የተፈጠሩ ጥቂት ሰዎች የተሰባሰቡበት ቡድን በአማራናአፋር ሕዝብ ላይ የፈጸመው የክህደት ሥራ እንጂ፡፡ የባንዳ የልጅ ልጆችን ያሰባሰበው ይህ ጠባብ ቡድን በአማራናአፋር ሕዝብ ላይ የፈጸመው ግፍ በአዶልፍ ፓርለሳክ ተጽፎ በተጫነ ጆብሬ መኮንን የተተረጎመውየአበሻ ጀብዱመጽሐፍ ላይ የሚነበበው ለጣሊያን ያደሩ ባንዳ አባቶቻቸውና አያቶቻቸው፣ በማይጨው ጦርነት ጊዜ በኢትዮጵያ አርበኞች ላይ የሠሩት ግፍ ቅጥያ ነው ማለት ይቻላል፡፡

እነዚህ የባንዳ ልጆችና የልጅ ልጆች ለዘመናት ሲያሴሩና በድብቅ ሲዘጋጁ ቆይተው ከትግራይ ሕዝብ አብራክ የወጡትን በማስገደድ/በማታለልና ከአማራና አፋር ወገንም ተባባሪ ሆድ አደር ባንዳዎችን በጥቅም በመደለል፣ አጎራባች በሆነው ወንድም የአማራና የአፋር ሕዝብ ላይ በታሪክ ተሰንዶ ዘለዓለም እየታወሰ የሚኖር መጠነ ሰፊ ግፍ ፈጽመዋል፡፡ የባንዳ ልጆችና የልጅ ልጆች ግብዓተ መሬት ተፈጽሞ ይህ የህልውና ጦርነት በኢትዮጵያ አሸናፊነት መጠናቀቁ አያጠራጥርም፡፡ ነገር ግን በተለይም የአማራና የአፋር ሕዝብ ቁስል እንደምን ሊድን ይችላል? የሕዝቡ የተከፋ ሆድስ እንደምን ይሽር ይሆን?  ከእንግዲህ ወዲህ አብሮ የሚኖረውስ እንዴት ይሆን? የመሳሰሉ አሳሳቢ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ፀሎቴና ምኞቴ ሕዝቡ በተቻለ ፍጥነት ቀድሞ ወደ ነበረበት ፍቅርና መተሳሰብ እንዲመለስ ነው፡፡ ሕዝብ የሕዝብ ጠላት አይደለም፡፡ እንደምናየው በሕዝብ መካከል ጥል የሚፈጥሩት ገዥ መደቦች ወይም ገዥ መደብ ለመሆን የሚቋምጡ መተዳደሪያቸውንየብሔር ፖለቲካያደረጉ ፖለቲካ አደሮች ናቸው፡፡   

ከተመለከትኩት “Is God Crazy?” የቪዲዮ ፊልም ተነስቼ የአገራችንየብሔር ፖለቲካበባዶ ኮካ ኮላ ጠርሙስ  የሚመስል ክስተት ይመስለኛል፡፡ ፊልሙ የተሠራው ካላሃሪ በረሃ በሚኖሩ ቡሽ ሜን (Bush Men) አገር በቀል ቤተሰብ ላይ ሲሆን፣ የፊልሙ ትርክት የሚጀምረው በበረሃው ሰማይ ላይ አውሮፕላን ያበርር የነበረ  ካፒቴን የጨለጠውን ባዶ ኮካ ኮላ ጠርሙስ ቁልቁል በመወርወር ነው፡፡ የወደቀችበትን ቦታ ከተመለከተው ቤተሰብ አባል አንዱ  ሮጦ በመሄድ ጠርሙሷን ያመጣል፡፡ ቤተሰቡ ከሰማይ የተወረወረችውን ባዶ ጠርሙስ እንደ ተዓምርና የፈጣሪ ስጦታ ተመለከተ፡፡ ሕፃናቱ እየተቀባበሉ የጠርሙሷን አፍ አንዴ እንደ ዋሽንት እየነፉ፣ አንዴ ደግሞ ወደ ሰማይ በመወርወር ይቦርቃሉ፡፡ እኔ እኔ በማለትርስ በርስ  ይፋጁባታል፡፡ ቀጥሎ በስስትና መጠላላት እርስ በርስ መደባደብ ጀመሩ፡፡ የቤተሰቡ መሪ በበኩሉ ከጫካ ፈልጎ ለሚያገኘው የሥራ ሥር ምግብ መፍጫነት ጠርሙሷ ጥሩ መሣሪያ ሆና ስላገኛት፣  እሱም በፊናው ለመጠቀም ጠርሙሷን ከሕፃናቱ እጅ ሲነጥቅ ሕፃናቱ ያለቅሱበታል፡፡ ቅናትና ስስት ያስከተለው የዘወትር ጭቅጭቅና ፀብ በሕፃናቱ መካከል፣ አንዲሁም በአዋቂዎችና በሕፃናቱ መካከል ነግሦ የቤተሰቡ የቀድሞ የሰላም ኑሮ ደፈረሰ፡፡

ከዚያ በፊት የጋርዮሽ የአኗኗር ሥልት በሚከተለው የቡሽሜን ማኅበረሰብ ዘንድ ፀብና ጭቅጭቅ አይታወቅም ነበር፡፡ አንድ  ቀን አንድ ሕፃን ወደ ሰማይ የወረወራት ጠርሙስ ወደ መሬት ተመልሳ ግንባሩን ፈንክታ ከሞት ምላሽ ጉዳት ስላደረሰችበት ሁኔታው ለመላ ቤተሰቡ መሪር ሐዘን ሆነ፡፡ በዚህም ምክንያት ቤተሰቡ ስብሰባ አድርጎ የችግሩን መንስዔ ሲያፈላልግ የችግሩ መንስዔ ጠርሙሷ ብቻ መሆኗን በግልጽ ለየ፡፡ ስለዚህ እንደ ወትሯቸው በሰላምና በፍቅር ለመኖር የሚችሉት ጠርሙሷን አርቆ በመወርወር ብቻ ሳይሆን፣ አርቆ በመቅበር መሆኑን በመስማማት ይህን ለማድረግ በጋራ ወሰኑ፡፡ የቤተሰቡ መሪ የቀናት መንገድ ተጉዞ ጠርሙሷን ሕፃናት በማይደርሱበት ቦታ ጉድጓድ ቆፍሮ አርቆ እንዲቀብራት ተስማሙ፡፡ በዚህም መሠረት ተፈጸመ፡፡ 

የብሔር ፖለቲካበአገራችን ታሪካዊ ጠላቶች ተጠንስሶ በእኛው ሆድ አደር ፖለቲከኞች የበለፀገ የእርስ በርስ መፋጂያ ባዶ የኮካ ኮላ ጠርሙስ ነው፡፡ ጠቃሚነቱ ለፖለቲካ አደሮቹና ከጀርባ ለቆሙ ድብቅ ዓላማ ላላቸው የአገራችን ታሪካዊ ጠላቶች እንጂ፣ ለማንም የኢትዮጵያ ብሔረሰብ ሆነ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አይደለም፡፡ ይህን ለመረዳት ያሳለፍነው የ30 ዓመት የፖለቲካ ጉዞ በቂ ትምህርት ሰጥቶናል፡፡ አሁን ልንሞክረው የሚገባ መፍትሔ አንድና አንድ ብቻ ነው፡፡ ይህም እንደ ኮካ ኮላ ጠርሙሷ የብሔር ፖለቲካእንዳይመለስ አድርጎ ከፈጣሪዎቹ አስተሳሰብ ጋር አርቆ መቅበር እንዲቻል፣ በአንዳንድ አገሮች እንደ ተደረገው ሁሉ በእኛም አገር በሕግ መገደብ ብቻ ነው፡፡ በዚህ ችግር እኛ ከሌሎች አገሮች በምን ጉዳይ እንለያለን? ይህ የማይደረግ ቢሆን ጥረታችን ሁሉየእንቧይ ካብወይምታጥቦ ጭቃየሚሆንብን ይመስለኛል፡፡

ከመስከረም 24 ቀን 2014 .ም. በኋላ የሚቋቋመው የተወካዮች ምክር ቤት ኃላፊነት በቅድሚያ መሆን የሚገባው የሚመስለኝ፣የብሔር ፖለቲካየሙጥኝ በማለት የትሕነግ ራዕይን ወደ መጪው ዘመን በፊናቸው ለማሻገርለብሔር ፖለቲካውዱላ ቅብብሎሽ ሩጫው የተሠለፉትን እዚያም እዚህም ያሉየብሔር ፖለቲካወራሴ ቡድኖችን ሥርዓት የሚያስይዝ አዋጅ ማውጣት፣ ሕዝቡ ያነሳቸውን ተንከባላይ ጥያቄዎችን መቋጨት፣ 30 ዓመቱ የሕዝብ ቁስል ሽሮ የተሸረሸረው የሕዝቡ አብሮነትና አንድነት ወደ ነበረበት ከፍታ እንዲመለስ ማድረግ፣ ሕዝቡ መክሮ ባፀደቀው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ሕዝብን የሚያስተዳድር ጠንካራ ሕዝባዊ መንግሥት ማቋቋም ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ተግባር ይመስለኛል፡፡

ኢትዮጵያ በክብር ለዘለዓለም ትኑር!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...