Friday, June 9, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮ ቴሌኮምን ከፊል ድርሻ ለመሸጥ ጨረታ ወጣ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የጨረታ ሰነዱ 20 ሺሕ ዶላር ይሸጣል

የኢትዮ ቴሌኮም ከፊል ድርሻን ለመሸጥ ከሦስት ዓመታት በፊት በኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በተወሰነው መሠረት፣ 127 ዓመታት ያስቆጠረውን ተቋም 40 በመቶ ድርሻ ለውጭ ባለሀብቶች ለመሸጥ ጨረታ ወጣ፡፡

በገንዘብ ሚኒስቴርና በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ማክሰኞ መስከረም 4 ቀን 2014 ዓ.ም. የወጣው የኢትዮ ቴሌኮም ከፊል ድርሻን ወደ ግል የማዛወር የመወዳደሪያ ሐሳብ መጠየቂያ ማስታወቂያ፣ ‹‹የኦፕሬሽን፣ የመሠረተ ልማት አስተዳደርና የቀጣይ ትውልድ ቴክኖሎጂ አቅሞችን በተመለከተ ያሉትን ምርጥ ተሞክሮዎች በማምጣት እሴት መጨመር የሚችሉ ፍላጎት ያላቸው›› ተጫራቾች እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ካሁን ቀደም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በዚህ ጨረታ ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸውን ድርጅቶች የፍላጎት መግለጫ ጠይቆ የነበረ ሲሆን፣ አሁን የወጣው ጨረታ ግን እነዚህን ፍላጎት የገለጹ አካላት ብቻ ሳይሆን ፍላጎት ያላቸውን ድርጅቶች በሙሉ ያሳትፋል ተብሏል፡፡

አንድ ድርጅት በጨረታው ለመሳተፍ 20 ሺሕ ዶላር በመክፈል ሰነድ መግዛት እንደሚችል የተነገረ ሲሆን፣ የሰነዱን ሚስጥር ለመጠበቅ የግዴታ ማረጋገጫ ማቅረብም ይጠበቅባታል ተብሏል፡፡

መንግሥት በአዋጅ ቁጥር 1206/2012 የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ለማዛወር ማዕቀፍ መዘርጋቱን የሚያወሳው ማስታወቂያው፣ ‹‹በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አነስተኛ የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ተደራሽነት በዚህ ሴክተር ያለውን ከፍተኛ ዕምቅ አቅም አመላካች ነው፤›› በማለት፣ ‹‹የኢትዮ ቴሌኮም ጠንካራ መሠረተ ልማትና የገንዘብ አፈጻጸም ተዳምሮ ሲታይ ለኢንቬስተሩ የተሻለ የተወዳዳሪነት ዕድል የሚፈጥር፤›› እንደሆነ ያትታል፡፡

ካሁን ቀደም በኢትዮጵያ በቴሌኮም ዘርፍ የሚሰማሩ አዳዲስ አገልግሎት ሰጪዎችን ለመጋበዝ በወጣ ጨረታ፣ ሁለት ተጫራቾች ቀርበው አንድ ተጫራች ብቻ ፈቃድ ማግኘቱ ይታወሳል፡፡ ለአገልግሎት ጨረታ ተጫራቾች 15 ሺሕ ዶላር በመክፈል ሰነድ መግዛታቸው ይታወሳል፡፡

መንግሥት የኢትዮ ቴሌኮምን ድርሻ ለመሸጥ ይፋ ሲያደርግ ከ60 የማያንሱ የውጭ ኩባንያዎች በጨረታ ሊሳተፉ እንደሚችሉ ተገልጾ፣ በተለይም በኔትወርክ መስክ በ3G እና በ4G ኔትወርክ ዝርጋታ ልምድ ያላቸው ኩባንያዎች ይመረጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ መገለጹ አይዘነጋም፡፡

በተገባደደው የ2012-13 በጀት ዓመት 56.5 ቢሊዮን ብር ትርፍ ያስመዘገበው ኢትዮ ቴሌኮም፣ ቴሌ ብር የተባለውን የሞባይል ገንዘብ መተግበሪያ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ የ5G ቴክኖሎጂ ለመጀመርም ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡ በተጨማሪም የግል የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ በመሆን ወደ አገር ውስጥ ከገባው የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ ጥምረት ጋር፣ የቴሌኮም መሠረተ ልማት ኪራይ ለማቅረብ ንግግር ጀምሯል፡፡

ከዓመታት በፊት ዕዳውን መክፈል አቅቶት መንግሥት ሲሸፍንለት የነበረው ኢትዮ ቴሌኮም፣ ለተለያዩ ፕሮጀክት ማስፋፊያ እንዲሆን ከተበደረው አጠቃላይ የውጭ ብድር ውስጥ 67 በመቶ (1.56 ቢሊዮን ዶላር) የሚሆነውን በ2013 በጀት ዓመት መክፈሉን አስታውቆ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ ከሁለት ዓመት በፊት ባወጣው መግለጫና አጭር የፖሊሲ ማብራሪያ ላይ፣ ‹‹መንግሥት የኢትዮ ቴሌኮምን ከፊል ድርሻ ለውጭ ባለሀብቶች ለመሸጥ የተከተለው ሒደት ግልጽነት የሌለውና የተጣደፈ መሆኑ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) እና የዓለም ባንክ ከዚህ ቀደም ሌሎች አገሮች ላይ ጫና በማሳደር ከተደረጉ ሪፎርሞች ጋር በእጅጉ የሚመሳሰል ነው። በዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) እና ዓለም ባንክ እየተገፉ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ያደረጉ አገሮች ከእነዚህ ተቋማት ጥገኝነት መላቀቅ አቅቷቸው አገራዊ ሉዓላዊነታቸው አደጋ ውስጥ መግባቱ ይታወቃል፤›› በማለት ሽያጩን ተቃውሞ እንደነበር ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች