Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኤምባሲዎችን እንደገና ለማደራጀት ወደ አገር ቤት የተጠሩ ዲፕሎማቶች ሥልጠና ጀመሩ

ኤምባሲዎችን እንደገና ለማደራጀት ወደ አገር ቤት የተጠሩ ዲፕሎማቶች ሥልጠና ጀመሩ

ቀን:

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዋና መሥሪያ ቤትን ጨምሮ በውጭ አገሮች ኢትዮጵያን የሚወክሉ ኤምባሲዎችንና የቆንስላ ጽሕፈት ቤቶችን እንደገና ለማደራጀት፣ ወደ አገር ቤት የተጠሩ ዲፕሎማቶች የአሥር ቀን ሥልጠና ጀመሩ፡፡

ኢትዮጵያን በውጭ አገር የሚወክሉ ሚሲዮኖችን በአዲስ አደረጃጀት ወጪ ቆጣቢ በማድረግ ለማዋቀር ሲያካሄድ የነበረው ጥናት መጠናቀቁን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቆ ነበር፡፡

ወደ ዋና መሥሪያ ቤት የተጠሩ ዲፕሎማቶች በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች፣ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲና ደኅንነት ላይ ወቅቱንና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታውን በጠበቀ መንገድ ለመሥራት የሚያስችሉ ሥልጠናዎችን እንዲያገኙ ያስችላል የተባለው ሥልጠና፣ ሱልልታ በሚገኘው የአፍሪካ ሥራ አመራር አካዴሚ ከመስከረም 3 ቀን 2013 ዓ.ም. ተጀምሯል፡፡

በሥልጠናው ማስጀመርያ ወቅት ንግግር ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዋና መሥሪያ ቤት የዲፕሎማሲ ሞተር ሆኖ እንዲቆም ይሠራል ብለዋል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችን አደረጃጀት የምናስተካክለው ከተፅዕኖ ፈጣሪነት አንፃርና ከብሔራዊ ጥቅም እንጂ ለሌላ ብለን አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ደመቀ፣ ‹‹የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጣም ትልቅ፣ ብዙ ልምድና ከፍተኛ ትምህርት ያለበት በመሆኑ፣ ከእነዚህ መልካም ማዕዘናት በመነሳት በተቋሙ በኤምባሲዎች ላይ የሚታዩ ድክመቶችን ለማረምና ለበለጠ ውጤታማነት ለመሠለፍ እንጂ፣ በጠቅላላው ፈርተን በመሸነፍ መጨረሻው ጠፍቶብን የመዳከር ነገር አይደለም፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እያከናወነ ያለው ሥራ በትክክለኛ ቁመና ላይ ለመገኘትና ክፍተትን ለመሙላት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ይሁን እንጂ የውጭ ጉዳይ ዋና መሥሪያ ቤት የውጭ ምደባ እስኪደረግ ለሦስት ወይም ለአራት ዓመታት የመቆያ ጊዜ እንዳልሆነ በመግለጽ፣ ይህ ትክክለኛ አካሄድ ባለመሆኑ ሊስተካከል ይገባል ብለዋል፡፡

ነገር ግን ሁሉም የየራሱን ሥራ ቆጥሮ መሥራት እንጂ የመወቃቀስ ባህል ፈጽሞ መለወጥ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

በዚህም መመዘኛውና የውጤታማነት ማሳያው ነባር ሰው በመሆን ብቻ የሚገኝ ፍፁማዊነት እንዳልሆነ፣ እንዲሁም አዲስ ሰው ሲመጣ ጉድለት ያለበት አድርጎ የማየት ክፍፍል እንዳለ በመግለጽ ይህ መሰበር አለበት ብለዋል፡፡

‹‹ቀድሞ መኖር መቶ በመቶ ፍፁማዊነትንና የተሟላ መሆንን እንደማያመላክት፣ አዲስ የመጣው ደግሞ ምንም የሌለውና መጥቶ የወደቀብን ዓይነት ተደርጎ መውሰድ አይገባም፤›› ያሉት አቶ ደመቀ፣ አዲስ የመጣውም ደግሞ የተለየና ተቆርቋሪ መስሎ አድራጊ ፈጣሪ ሆኖ እንዲሠራ አይፈቀድለትም ሲሉ አክለዋል፡፡

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ (አምባሳደር) በተለያዩ ሚዲያዎች ዲፕሎማቶች ሊበተኑ ነው የሚለው ወሬ ትክክል አለመሆኑን፣ ይህ ዓይነቱ አሠራር የተለመደና   ሁልጊዜም ቢሆን ዲሎማቶችን ወደ ዋናው መሥሪያ ቤት በመጥራት እንደገና የመላክ አሠራር የተለመደ መሆኑን በመጥቀስ፣ አሁን እየተደረገ ያለው አደረጃጀት ሠራተኞችን በማስተካከል ውጤታማነትን መሠረት ያደረገ ሥራ ለመሥራት እንጂ የሚበተን ነገር የለም ብለው ነበር፡፡

በአዲሱ አመዳደብም አገሪቱ አሁን ያሏትን ወደ 60 የሚጠጉ የኤምባሲና የቆንስላ ጽሕፈት ቤቶች እንደገና በማዋቀርና ቁጥራቸውን በመቀነስ፣ በአንዳንድ አገሮች በኢትዮጵያ ብር እየተከፈለው ተመላላሽ አምባሳደር (Laptop Ambassador) የሚኖርበት አሠራር እንደሚኖር፣ ቃል አቀባዩ ከዚህ ቀደም ለጋዜጠኞች መናገራቸው ይታወሳል፡፡

ለአብነትም እንደገና ከሚደረጁት መካከል በቻይና የተለያዩ ከተሞች የሚገኙ የቆንስላ ጽሕፈት ቤቶችን በመዝጋት በቤጂንግ ብቻ ኤምባሲ  እንዲሠራ ማድረግ፣ እንዲሁም በአሜሪካም በሎስ አንጀለስና በሚኒያፖሊስ ያሉ ቆንስላዎችን መዝጋት፣ በዋሽንግተን የሚገኘውን ኤምባሲና በኒውዮርክ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚያገለግለውን ኤምባሲ ማስቀጠል ይቻላል ማለታቸው አይዘነጋም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...