Saturday, June 10, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

​​​​​​​በኃላፊነት ቦታቸው ባልተገኙ የወጋገን ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ምትክ ተጠባባቂ ተሾመ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ወጋገን ባንክ ለአሥር ወራት በተጠባባቂ ፕሬዚዳንትነትና ዋና ሥራ አስፈጻሚነት ሲመሩ በቆዩት ወ/ሮ ብርቱካን ገብረእግዚ ምትክ፣ አዲስ ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መሰየሙ ታወቀ፡፡

የወጋገን ባንክ ቦርድ ከሾማቸው አንድ ዓመት እንኳን ያልሞላቸውን ወ/ሮ ብርቱካንን አሰናብቶ አዲስ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት የሰየመበት ምክንያት ባይገለጽም፣ ባንኩ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት አድርጎ የሰየማቸው በባንኩ ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ሲያገግሉ የቆዩትን አቶ አክሊሉ ውበትን ነው፡፡

ወ/ሮ ብርቱካን ወጋገን ባንክን በፕሬዚዳንትነት እንዲመሩ የወጋገን ባንክ ቦርድ አግባብቶ ያመጣቸው ከእናት ባንክ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ወ/ሮ ብርቱካን ወጋገን ባንክን ከመቀላቀላቸው በፊት በእናት ባንክ ውስጥ በምክትል ፕሬዚዳንትነት ሲያገለግሉ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ከሰሞኑ ግን ባንኩ ወ/ሮ ብርቱካንን አሰናብቶ አቶ አክሊሉን ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አድርጎ በመሰየም ውሳኔውን ብሔራዊ ባንክ እንዲያፀድቅለት ጠይቋል፡፡

ወ/ሮ ብርቱካን ወጋገን ባንክን እንዲመሩ በቦርዱ የታጩት ለዓመታት ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ዓባይ መሐሪ ኃላፊነታቸውን ለመልቀቅ በተደጋጋሚ ያቀርቡት የነበረውን ጥያቄ፣ ከአንድ ዓመት በፊት ተቀብሎ እንዲሰናበቱ ከወሰነ በኋላ ነው፡፡

አቶ ዓባይን ተክተው የባንኩ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሆነው የተሰየሙት ወ/ሮ ብርቱካን፣ በዚህ ኃላፊነታቸው አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በሌላ መተካታቸው ግን ለብዙዎች እንቆቅልሽ ሆኗል፡፡

እንደ ምንጮች ገለጻ ግን አዲስ ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የተሰየመው፣ ወ/ሮ ብርቱካን ወደ አሜሪካ በመሄድ በዚያው በመቅረታቸው ነው፡፡ ወ/ሮ ብርቱካን ወደ አሜሪካ ከሄዱ በኋላ መምጣት አለመምጣታቸውን ባለማሳወቃቸው፣ ቦርዱ ሥራቸውን እንደለቀቁ በማመኑ ዕርምጃውን እንደወሰደ ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

እንደ ምንጮች ገለጻ፣ አቶ አክሊሉ በቅርቡ የባንኩ ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ከመሰየማቸው በፊት አቶ ዓባይ መሐሪን ተክተው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ይሆናሉ ተብለው ታጭተው የነበረ ቢሆንም፣ በመሀል ወ/ሮ ብርቱካን ተሹመዋል፡፡

የአቶ አክሊሉ ሹመት የሚፀናው በብሔራዊ ባንክ ከፀደቀ በኋላ ሲሆን፣ እስከዚያው ግን ባንኩን በተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚነት እያገለገሉ ይቆያሉ፡፡ ከአቶ አክሊሉ ሹመት ጋር ተያይዞ የተገኘው መረጃ የሚያመለክተው፣ በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በተለያዩ ተቋማት ውስጥ ማገልገላቸውን ነው፡፡

አቶ አክሊሉ ካገለገሉባቸው የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ በአቢሲኒያ ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት፣ በወጋገን ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንትና በናይል ኢንሹራንስ ኩባንያ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ በመሆን ማገልገላቸው ይጠቀሳል፡፡ በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ሲሠሩ የነበሩት አቶ አክሊሉ በአንበሳ ባንክ ውስጥ በተመሳሳይ ኃላፊነት ይሠሩ እንደነበር ተመልክቷል፡፡  

አቶ አክሊሉ በኢኮኖሚክስ የመጀመርያ ዲግሪ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በቢዝነስ አስተዳደር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያገኙ ሲሆን፣ ላለፉት 30 ዓመታት በፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ አገልግለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች