Monday, September 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ​​​​​​​በአዲሱ የዴልታ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ በአንድ ቀን ብቻ 38 ሰዎች  ለሕልፈተ ሕይወት ተዳረጉ

​​​​​​​በአዲሱ የዴልታ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ በአንድ ቀን ብቻ 38 ሰዎች  ለሕልፈተ ሕይወት ተዳረጉ

ቀን:

  • በአንድ ሳምንት ውስጥ 204 ግለሰቦች ሞተዋል

የኮቪድ-19 ቫይረስ ዝርያ በሆነው ዴልታ በኢትዮጵያ በአንድ ቀን ብቻ ማለትም መስከረም 3 ቀን 2014 ዓ.ም. 38 ግለሰቦችን ለሕልፈተ ሕይወት መዳረጋቸው ተገለጸ፡፡

ከዚህም ሌላ ከጳጉሜን 1 ቀን እስከ ጳጉሜን 5 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ 121፣ ከመስከረም 1 ቀን እስከ መስከረም 3 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ 83 በድምሩ 204 ግለሰቦች በዚሁ ቫይረስ ዝርያ መሞታቸው ተረጋግጧል፡፡

የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳሬክተር አቶ አስቻለው ዓባይነህ እንደገለጹት፣ ባለፈው አንድ ሳምንት ብቻ 9,164 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ከመያዛቸውም በላይ በሳምንቱ ቀናት በአማካይ 737 የሚሆኑ ሰዎች ወደ ፅኑ ሕሙማን ክፍል ገብተው ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛሉ፡፡ እንዲሁም 158 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ምክንያት ሕይወታቸውን ማጣታቸውን፣ በተጠቀሰው ሳምንት በአማካይ በቫይረሱ የመያዝ ምጣኔ በ17.7 በመቶ የደረሰ መሆኑን፣ ይህም ከወዲያኛው ሳምንት ጋር ሲነፃፀር ከፍ ያለ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በሌላ በኩል የሞት ምጣኔ በአማካይ 1.6 በመቶ መድረሱን አኃዞች ያሳያሉ ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ ‹‹ዴልታ›› የተሰኘው ይህ የኮቪድ-19 ቫይረስ ዝርያ ከሰው ወደ ሰው የመተላለፉ ሁኔታው ቀደም ሲል ከነበሩት አልፋና ቤታ ዝርያዎች በሁለት እጥፍ እንደሚያድግ፣ በወረርሽኙ የመያዝ ምጣኔውም እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ወቅታዊ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን አስመልክቶ ማክሰኞ መስከረም 4 ቀን 2014 ዓ.ም. በተካሄደው ሳምንታዊ የጋዜጣ መግለጫ ላይ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ እንደተናገሩት፣ የኮቪድ-19 ቫይረስ ሁለት ዝርያዎች ማለትም ‹‹አልፋ›› እና ‹‹ቤታ›› ያጠቁ የነበሩት ዕድሜያቸው የገፋና ተጓዳኝ በሽታ ያደረባቸውን ነበር፡፡ ‹‹ዴልታ›› የተሰኘው የአሁኑ ዝርያ ግን የዕድሜ ክልል እንደሌለውና ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍል እኩል የሚያጠቃ ወይም ለበሽታ የሚዳርግ ነው ብለዋል፡፡

ለዴልታ ዝርያ ተብሎ የተዘጋጀ ሌላ ክትባት በዓለም ላይ እንደሌለ፣ ቀደም ሲል የነበሩት ክትባቶች አሁንም የዴልታን ዝርያ ለመከላከል እንደሚያገለግሉ፣ ይህም ሆኖ ግን ክትባት ተወስዶ ተገቢው ጥንቃቄ ካልተደረገ በቫይረስ የመያዝ ዕድል እንደሚኖር ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ይህም ሆኖ ግን ሕመሙ ኃይለኛ እንደማይሆንባቸው፣ ወይም የከፋ እክል ሳያጋጥማቸው የመዳን ዕድል ሊኖራቸው እንደሚችልና የሞት ምጣኔውንም እንደሚቀንስ ከምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በመሆኑም የኮቪድ-19 ቫይረስ ዝርያ የሆነው ዴልታ እያደረሰ ያለውን ከፍተኛ ችግር ለመግታትና ለመቆጣጠር እንዲቻል በማኅበረሰቡ ዘንድ ያሉትን የተሳሳቱ ግንዛቤዎችና አመለካከቶች በማስወገድ፣ ከአሁን በፊት ሲተገበሩ የቆዩና በመካከሉም እየተዘነጉ የመጡትን የመከላከያ መንገዶችን በተገቢው መንገድ ተግባራዊ ማድረግና የኮቪድ-19 ክትባት መውሰድ አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን ነው ያመለከቱት፡፡

በተለይም የተቀመጡ መመርያዎችን ያላገናዘቡ ስብሰባዎች፣ ሥልጠናዎች፣ በተጨናነቀ ሁኔታ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ የሚሳተፍባቸው ሃይማኖታዊና ሕዝባዊ የአደባባይ በዓላት ላይ ርቀትን የመጠበቅ፣ ማስክ የማድረግና በሳኒታይዘር ወይም በሳሙናና በውኃ የእጅን ንፅህና መጠበቅ እጅግ አስፈላጊ ከመሆኑም በላይ፣ ግዴታም ጭምር መሆኑን ማወቅ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ላልሆኑ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው መመርያ 803/2013 ዓ.ም. ላይ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባቸው ነው የገለጹት፡፡

በአጠቃላይ በሁለት ዙር 2,794,490 ክትባት ለኅብረተሰቡ መስጠት መቻሉን፣ በሚቀጥሉት ሁለትና ሦስት ሳምንታት በኋላ ሦስት ሚሊዮን ዶዝ ክትባት ወደ አገር የሚገባ መሆኑን፣ ሰዎች በሁሉም የመንግሥት ጤና ተቋማት መከተብ እንደሚገባቸው ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አሳስበዋል፡፡

እንደ አቶ አስቻለው ማብራሪያ ለኮቪድ-19 ቫይረስና ሌሎችም በሽታዎች ፍቱን ናቸው ተብለው ለኢንስቲትዩቱ የቀረቡ 20 የባህል መድኃኒቶች የክሊኒክ ሙከራ እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሙከራው መቼ ይጠናቀቃል ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ ‹‹ትክክለኛውን ቀን ለማወቅ ያስቸግራል፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...