Wednesday, February 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

​​​​​​​ሕጋዊ ፈቃድ የሚሰጣቸው የስፖርት አወራራጆች 1.5 ሚሊዮን ብር የባንክ ዋስትና እንዲያሲዙ የሚያስገድድ መመርያ ወጣ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ተቋርጦ የነበረው የስፖርት ውርርድ ሎተሪ ፈቃድ እንደገና መሰጠት ይጀምራል
  • በ2013 ዓ.ም. ከስፖርት ውርርድ መንግሥት 107 ሚሊዮን ብር ገቢ ተገኝቷል

የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ከዚህ ቀደም በማኅበረሰቡ ውስጥ ከፍተኛ ውዝግብ አስነስቶ የቆየውን የስፖርት ውርርድ ሎተሪ ፈቃድ መመርያ ጥብቅ በሆነ ሕግና ሥርዓት ማሻሻሉን በመግለጽ፣ በአዲሱ መመርያ መሠረት ሕጋዊ ፈቃድ የሚሰጣቸው የስፖርት አወራራጆች 1.5 ሚሊዮን ብር የባንክ ዋስትና እንዲያሲይዙ እንደሚገደዱ አስታወቀ፡፡

አስተዳደሩ በተሻሻለው የስፖርት ውርርድ ፈቃድ መመርያን በተመለከተ ማክሰኞ መስከረም 4 ቀን 2014 ዓ.ም. በኤሊያና ሆቴል ለመገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ መመርያው ከተሻሻለ በኋላ ተቋርጦ ለነበረው የስፖርት ውርርድ እንደገና ፈቃድ መስጠት እንደሚጀምር በመግለጫው ወቅት ተገልጿል፡፡

በብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር የፈቃድ አሰጣጥና ቁጥጥር ዋና ዳይሬክተር አቶ ደሴ ደጀኔ እንዳስታወቁት፣ ቀደም ሲል በነበረው መመርያ ያልነበሩ ተጨማሪ ክልከላዎችን በማካተት፣ እንዲሁም የውርርድ ሥራው ጥብቅ በሆነ ሕግና ሥርዓት እንዲመራ ለማድረግ የሎተሪ ፈቃድ መመርያ ተሻሽሏል፡፡

ከዚህ ቀደም በነበረው መመርያ አወራራጅ ድርጅቶች ምንም ዓይነት የባንክ ዋስትና ሳያስይዙ ሲሠሩ መቆየታቸው የተገለጸ ሲሆን፣ በአዲሱ መመርያ ግን ቀደም ብለው ወደ ዘርፉ የገቡትም ሆነ አዲስ ገቢ ድርጅቶች የአስተዳደሩን ኮሚሽን ክፍያ፣ የበጎ አድራጎት ክፍያ፣ የገቢ ግብር ክፍያና የአሸናፊ የዋስትና ክፍያ ለማስጠበቅ በቅድመ ሁኔታ ያልተመሠረተ 1.5 ሚሊዮን ብር የባንክ ዋስትና እንዲያስይዙ የሚያደርግ መመርያ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የስፖርት ውርርድ  ሎተሪ አጨዋቾች የሚሸልሙት  የሽልማት ጣሪያ ከዚህ ቀደም ወጥ እንዳልነበረና በውርርዱ የተጋነነ ክፍያዎች ይፈጸሙበት እንደነበረ ተጠቁሞ፣ በአዲሱ መመርያ ግን ጣሪያ ሊበጅለት ይገባል በሚል እያንዳንዱ አወራራጅ ድርጅት የአንድ ትኬት ከፍተኛ የሽልማት ጣሪያ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ እንዳይበልጥ መደረጉ ተገልጿል፡፡

ከዚህ በፊት በነበረው የስፖርት ውርርድ ሎተሪ ፈቃድ መመርያ ቁጥር 85/2005 ማንኛውም ዕድሜው 18 የሆነ ሰው በውርርድ ሎተሪ ጨዋታው እንደሚሳተፍ የተፈቀደ ቢሆንም፣ ነገር ግን በኅብረተሰቡ ዘንድ ጥያቄ በማስነሳቱ ሳቢያ፣ በአዲሱ መመርያ መሠረት በጨዋታው መሳተፍ የሚችሉት ዕድሜያቸው 21 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች እንደሆኑ አስተዳደሩ አስታውቋል፡፡

ከዚህ አስቀድሞ አወራራጆች ሽያጭ ሲፈጽሙ ለአስተዳደሩ ቀድመው እንዲያሳውቁ የሚያስገድድ መመርያ እንዳልነበረው ያስታወቁት አቶ ደሴ፣ ሆኖም ከዚህ በኋላ ድርጅቶቹ በባንክ በኩል የሚያርጉትን እንቅስቃሴ ለአስተዳደሩ ማሳወቅ እንዳለባቸውና በየወሩ ለአስተዳደሩ በሚያሳውቁት ሪፖርት ላይ ወርኃዊ የባንክ ስቴትመንታቸውን አያይዘው ማቅረብ እንደላባቸው  መመርያው ያዛል ብለዋል፡፡

የተሻሻለው መመርያ የስፖርት ውርርድ ቦታዎች ከእምነት ተቋማትና ከትምህርት ቤት አካባቢዎች    በ500 ሜትር ርቀት መከፈት እንዳለባቸው የሚያስረዳ ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪም በሬስቶራንት፣ በግሮሰሪዎችና በጫት ቤቶችና መሰል አካባቢዎች የውርርድ ድርጅት እንዳይከፈት ይከለክላል፡፡

የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ገረመው ጋርጄ በበኩላቸው፣ ጥናትን መሠረት በማድረግ የስፖርት ውርርድ ሎተሪ ጨዋታ በአዋጅ ቁጥር 5/35 በ1999 ዓ.ም. እንደወጣ አስታውሰዋል፡፡ መመርያው ደግሞ በ2005 ዓ.ም. የወጣው ውርርድ በስፋት የተጀመረው ከ2011 ዓ.ም. አጋማሽ ጀምሮ እንደሆነ ገልጸው፣ ከዚያ በኋላ ግን በኅብረተሰቡ ዘንድ ይቁምልን የሚል ተቃውሞ፣ በአወራራጆች በኩል ልንሠራ ይገባል የሚል ውዝግብ ሲነሳ እንደቆየ አስረድተዋል፡፡

አስተዳደሩ በሕግ የወጣ ጉዳይ እንዲሻር ለማስደረግ ቢፈልግ እንኳን በጥናት የመጣ ጉዳይ በጥናት መመለስ ስላለበት ለዩኒቨርሲቲዎችና ለኢንስቲትዩቶች በውርርድ ጨዋታው ላይ ጥናት እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቦ፣ የኢትዮጵያ ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ከ2012 ዓ.ም. ጀምሮ ጥናት አከናውኖ ረቂቁን ለአስተዳደሩ እንዳቀረበ አስታውሰዋል፡፡ ጥናቱ በአስተዳደሩ ብቻ የሚወሰንበት ስላልሆነ ለተቆጣጣሪው አካል ማለትም ለገቢዎች ሚኒስቴር ቀርቦ እየታየ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር እስካሁን ድረስ 42 ድርጅቶች የስፖርት ውርርድ ሎተሪ ፈቃድ አግኝተው እየሠሩ እንደሆነ፣ በ2013 ዓ.ም. ከስፖርት ውርርድ ብቻ 107 ሚሊዮን ብር እንዳገኘ አቶ ደሴ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች