Thursday, September 29, 2022
ሌሎች ዓምዶች

  ​​​​​​​የትግራይ ጦርነት የሰብዓዊ መብቶች ቀውስ በተመድ መድረክ

  - Advertisement -spot_img

  በብዛት የተነበቡ

  ጥቅምት 4 ቀን 2013 ዓ.ም. ሌሊቱን የተጀመረው የትግራይ ጦርነት እነሆ አንድ ዓመት ሊሞላው ከሁለት ወራት ያነሰ ጊዜ ብቻ ቀርቶታል፡፡ ጦርነቱ በተለያዩ ጊዜያት መልኩን እየለወጠና አጥቂና ተጠቂው እየቀያየረ ዛሬ ላይ የደረሰ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተናገሩት መሠረት የሁለት ሳምንታት ዕቅድ ቀርቦለት በሦስት ሳምንታት ተጠናቀቀ የተባለው ጦርነት፣ አሁን ግን ማብቂያው ‹‹ላም አለኝ በሰማይ›› መስሏል፡፡

  የአገር መከላከያ ሠራዊት በትግራይ ክልል የነበረውን የስምንት ወራት ቆይታ አብቅቻለሁ ብሎ የተናጠል የተኩስ አቁም አዋጅ አድርጎ ከክልሉ ሲወጣ፣ የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ኃይሎች የተኩስ አቁም አዋጁን አንቀበልም በማለት ወደ አማራና አፋር ክልሎች ጥቃት ሰንዝረዋል፡፡

  የመከላከያ ሠራዊት በትግራይ ክልል በነበረባቸው ጊዜያት የኤርትራ መከላከያ ሠራዊት አባላት በጦርነቱ ተሳትፎ እንደነበራቸው፣ እንዲሀም በሁለቱም ወገኖች ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደተፈጸሙ ተደጋጋሚ ሪፖርቶች ሲወጡ የቆዩ ሲሆን፣ የሕወሓት ኃይሎች ወደ አማራና አፋር ክልሎች ባደረጉት መስፋፋትና በሰነዘሩት ጥቃት ከፍተኛ ውድመት ማድረሳቸውንና አሰቃቂ የሰብዓዊ ጥሰቶችን እንደፈጸሙ በተለያዩ ሪፖርቶች ተመላክቷል፡፡ ከዚህ ቀደምም እንደ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያሉ ተቋማት ባወጧቸው ሪፖርቶች በማይካድራና በተለያዩ አካባቢዎች ግፍ የተሞላባቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን አመላክተው ነበር፡፡ የአክሱም ከተማ ከ100 በላይ የንፁኃን ግድያን በተመለከተ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንም የኤርትራን ወታደሮች ተጠያቂ ያደረገ ሪፖርት አውጥቶ ነበር፡፡

  ይሁንና እነዚህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ከሕግ ውጪ የሆኑ የንፁኃን ግድያዎች በገለልተኛ አካላት ሊጣሩ ይገባል የሚሉ ጥሪዎች ከትግራይ ኃይሎችም ሆነ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ሲደመጡ የቆዩ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ መንግሥትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ጽሕፈት ቤት በመጋቢት 2013 ዓ.ም. በደረሱት ስምምነት መሠረት የገለልተኛ አካል ማጣራት የተጀመረው ጦርነቱ አምስት ወራትን ካስቆጠረ በኋላ ነበር፡፡

  ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ

  ይኼ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ጽሕፈት ቤት በጋራ የሚያደርጉት ምርመራ ከተጀመረ ወራት የተቆጠሩ ሲሆን፣ በእነዚህ ጊዜያት በተለያዩ የግጭቱ አካባቢዎች በመዘዋወር መረጃዎችን ሲያሰባስቡ መቆየታቸውንና የመጨረሻው ሪፖርት ምክረ ሐሳቦች ጥቅምት 22 ቀን 2014 ዓ.ም. ይፋ እንደሚያደረጉ በቅርቡ ተገልጾ ነበር፡፡

  በዚህ ሒደት መካከል ጦርነቱ የቀጠለ በመሆኑና አዳዲስ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችም እየታዩ ሲሆን፣ በየጊዜው በአማራና በአፋር ክልሎች፣ እንዲሁም በትግራይ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች መሰማት የተለመደ ሆኗል፡፡ ነገር ግን የጥምረቱ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ምርመራ የፌዴራል መንግሥት የትግራይን ክልል ለቆ እስከወጣበትና የተኩስ አቁም አዋጁ እስከታወጀበት ጊዜ ያለውን ብቻ የሚሸፍን ነው፡፡

  የትግራይ ክልል ጦርነትና የግጭቱ መስፋፋት ብሎም እያስከተለ ያለው ቀውስ በተለይ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ አሳሳቢነቱ የቀጠለ ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት ተደጋጋሚ መድረኮች እየተዘጋጁ በዚሁ ጉዳይ ላይ ምክክሮች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ በእነዚህ መድረኮች ይህ ግጭት ቀጣናዊ መልክ ሊይዝና የአፍሪካ ቀንድን ሊያናጋ የሚችል እንደሆነ በመግለጽም፣ በርካቶች ሥጋታቸውን ሲያስተጋቡ ይደመጣል፡፡

  እንዲህ ካሉት አንዱ ስብሰባ ሰኞ መስከረም 3 ቀን 2014 ዓ.ም. በጄኔቫ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የተደረገው ሲሆን፣ የተለያየ አገሮችና አካላት በተለይ ጦርነቱ እንዲቆምና በጦርነት የሚፈታ ችግር ስለሌለ ልዩነቶች በውይይት እንዲፈቱ ለማድረግ ንግግር እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በተጨማሪም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የፈጸሙ አካላት ለፍትሕ እንዲቀርቡና የኤርትራ ሠራዊትም ሙሉ በሙሉ ከኢትዮጵያ ግዛት ለቅቆ እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

  በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ቀዳሚውን ንግግር ያደረጉት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚሸል ባሽለት፣ የትግራይ ጦርነት ሀይ ባይ አልባ እንደሆነና ወደ አፋርና አማራ ክልሎች እየሰፋ መምጣቱን በማውሳት፣ ወደ መላው የአፍሪካ ቀንድ ሊዳረስ ይችላልም ሲሉ በሥጋት ንግግራቸውን ጀምረዋል፡፡

  ‹‹ባለፉት ጥቂት ወራት የፍርኃት ድባብን ለመፍጠር ያለሙ የገፍ እስር፣ ግድያዎች፣ ዝርፊያዎችና ወሲባዊ ጥቃቶች እንደቀጠሉ ሲሆን፣ የትግራይ ሲቪል ዜጎች የግድ እንዲሰደዱ ያደረጉ የኑሮ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ ሆኗል፡፡ የንፁኃን ዜጎች ሥቃይ የተንሰራፋ ሲሆን፣ ተጠያቂነት ማጣትም ተስፋፍቷል፤›› ብለው፣ በሁሉም ወገኖች አሰቃቂ የሰብዓዊ መብቶች፣ የረድዔትና የስደተኛ ሕጎች መጣሳቸውን ተናግረዋል፡፡

  ተቋሙ ከሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር ለሚያደርገው ምርመራ ሁለት ሥምሪቶችን በመቀሌ፣ በምሥራቅና ደቡብ ትግራይ እንዳደረገ የገለጹት ባሸለት፣ በተለዋዋጭ የፀጥታ ሁኔታዎች ምክንያት ቡድኑ በማይካድራ የነበረውን ቆይታ እንዲያሳጥር እንደተገደደና አክሱምን ጨምሮ በምሥራቅና ማዕከላዊ ትግራይ ሥምሪት ማድረግ እንዳልቻለ አስታውቀዋል፡፡

  ምንም እንኳን ሪፖርቱ ገና ከወራት በኋላ እንደሚወጣ የተነገረ ቢሆንም፣ ኮሚሽነሯ በምርመራው የተመዘገቡ ጉዳዮች በንፁኃን ላይ የተሰነዘሩ ጥቃቶች፣ ከሕግ ውጪ የሆነ ግድያ፣ ሥቃይ፣ እንዲሁም ሰዎች በግድ እንዲጠፉ የማድረግ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደተፈጸሙ ግልጽ ነው ብለዋል፡፡ ወሲባዊ ጥቃቶች በቡድን አስገድዶ መድፈርን፣ ወሲብ የታከለበት ማሠቃየትና ብሔርን የለዩ የወሲብ ጥቃቶችን ያካትታሉም ብለዋል፡፡

  ‹‹መንግሥት የወሲባዊ ጥቃቶችን ለመመርመርና አጥፊዎችን ተጠያቂ ለማድረግ የገለጸው ቁርጠኝነትን ዕውቅና የምሰጠው ሲሆን፣ የሚወሰዱ ዕርምጃዎችን ውጤት ለመስማት እጠብቃለሁ፤›› በማለትም ተናግረዋል፡፡ በምርመራው ሒደት የታዩ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች የመንግሥት አካላትንና አጋሮቹን ጥፋተኝነት የሚያመላክቱ እንደሆኑም የተናገሩት ኮሚሽነሯ፣ አሁንም ድረስ የትግራይ ተወላጆች እየተወሰዱ የሚታሰሩበት የምዕራብ ትግራይ ሥፍራን ጨምሮ ሌሎች የሰብዓዊ መብቶች የሚፈጸሙባቸው አካባቢዎች መኖራቸው ቀጥሏል ሲሉም ይከሳሉ፡፡

  የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚሸል ባሽለት

  ከዚህ በተጨማሪም የትግራይ ኃይሎች የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እንደፈጸሙ ያነሱት ኮሚሽነሯ፣ የትግራይ ኃይሎች በንፁኃን ዜጎች ላይ ጥቃቶችን በመፈጸምም ተጠያቂ ይደረጋሉ ብለዋል፡፡ ይኼም ያለ መለየት በፈጸሙት ግድያ በአፋር ከ76,500 ሰዎች በላይ፣ እንዲሁም በአማራ ክልል ከ200,000 ሰዎች በላይ እዲፈናቀሉ አድርጓል ብለዋል፡፡ በቅርቡም በተፈጸመ ጥቃት ከ200 በላይ ግለሰቦች መገደላቸውንና ሕፃናትን ጨምሮ ከ88 በላይ ሰዎች ደግሞ ጉዳት እንደ ደረሰባቸው አስታውሰዋል፡፡ በተጨማሪም በጋሊኮማ የትግራይ ኃይሎች በስደተኞች ላይ በፈጸሙት ጥቃት በብዛት ሕፃናት፣ ሴቶችና አረጋውያን መገደላቸውንም ገልጸዋል፡፡

  ‹‹በዓለም አቀፍ ሕግጋት የተከለከለው ሕፃናትን ለጦርነት መመልመል በትግራይ ኃይሎች እየተፈጸመ እንደሆነም የሚያሳዩ ሪፖርቶች ደርሰውናል፤›› ብለዋል፡፡

  የኢትዮጵያ መንግሥት አጥፊዎችን ተጠያቂ ለማድረግ ቁርጠኝነቱን እንደገለጸና ይኼም እንደሚበረታታ የተናገሩት ኮሚሽነሯ፣ የኤርትራ መንግሥትም በትግራይ ክልል የኤርትራ ኃይሎች የፈጸሙትን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ማጣራት አድርጎ ተጠያቂነትን እንዲያሰፍን ጠይቀዋል፡፡

  በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች እየታዩ ያሉ ግጭቶች እንዲቆሙ መንግሥት እንዲሠራ የጠየቁም ሲሆን፣ ወታደራዊ መፍትሔ ግን የለም ብለዋል፡፡

  በመድረኩ ሌላው ተናጋሪ የነበሩት የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የጋራ ቡድኑ የመስክ ሥራውን መረጃ በመሰብሰብ ያገባደደ መሆኑን በመናገር፣ ምንም ዓይነት ግኝትና ማጠቃለያ በዚህ ደረጃ መነገር የለበትም ብለዋል፡፡ ይሁንና በሁሉም ወገኖች ተፈጽመዋል የተባሉና እየተመረመሩ የሚገኙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች በንፁኃንና በሌሎች ጥበቃ በሚረደግላቸው አካላት ንብረቶች ላይ የደረሱ ጥቃቶች፣ ሕጋዊ ያልሆነና ያለ ፍርድ የተፈጸመ ግድያን፣ አስገዳጅ የሰዎች ስደት፣ ወሲባዊና የፆታ ጥቃቶች፣ ማሠቃየትና ሌሎች አስከፊ አያያዞች፣ የዘፈቀደ እስር፣ ጠለፋና አስገዳጅ ሥወራ፣ እንዲሁም በስደተኞች ላይ የተፈጸሙ ጥሰቶችን ያካትታሉ ብለዋል፡፡

  የተኩስ አቁም ሲታወጅ ለሰብዓዊ መብቶች ጥበቃና ለሰብዓዊ ዕርዳታዎች መልካም ጅምር ተስፋን ሰንቆ እንደነበረ በማስታወስ፣ የሰኔ ወር ሦስት ሳምንታት ሳይገባደዱ ወደ አማራና ወደ አፋር ክልሎች የተስፋፋው የትግራይ ኃይል ጥቃት፣ እንዲሁም የተኩስ አቁሙን ለመቀበል ያስቀመጠው ቅድመ ሁኔታ በሁሉም ወገኖች የሠራዊት ክምችት እንዲኖርና አገር አቀፍ ወታደራዊ ምልመላ እንዲከተል ማድረጉ ፈታኝ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ ይባስ ብሎም የግብርናና የመነቃቂያ ጊዜ ሊሆን በሚችለው የዝናብ ወቅት፣ መላ የኢኮኖሚው አምራች ዘርፎች ተናግተዋል ብለዋል፡፡

  ሆኖም በትግራይ ክልል የታየው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ግልጽ ያለና አጥፊውና ተጠቂው በቀላሉ የሚለዩበት አይደለም ያሉት ዳንኤል (ዶ/ር)፣ የተድበሰበሰ ውስብስብነት ያለው መሆኑንና የሁሉም ተዋጊ ኃይሎች ወታደሮችን አልያም ተዋጊዎችን ጨምሮ፣ ሁሉም የግጭቶ አካላትና አጋሮቻቸው የወሲባዊ ጥቃቶችንና ሕፃናትን ለጦርነት ማሠለፍን ጨምሮ በንፁኃንና በመሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት በማድረስ አሳማኝ በሆነ መንገድ ተመላክተዋል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

  የተፈናቃዮች የሰብዓዊ ጉዳዮች አሁንም እንደሚያሳስባቸው የተናገሩት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ዳንኤል (ዶ/ር)፣ ቀስ በቀስ ወደ ድርድር የመሄድ ሙከራና በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ እየቀረቡ ያሉ የድጋፍ ተነሳሽነቶች የሚያበረታቱ ናቸው በማለት፣ ኢትዮጵያውያንም ሆኑ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሰብዓዊ መብቶች ቀውስን ለማስቆም ትርጉም ያለውና ገንቢ ሚና መጫወት ከፈለጉ፣ የዚህን ውስብስብ የፖለቲካ ቀውስ ታሪክና ዓውድ በምሉዕ ለመረዳት ሊጥሩ ይገባል ሲሉም ምክር ለግሰዋል፡፡

  ‹‹አሁንም ቢሆን የዜጎቻቸውን ሥቃይና መከራ ለማቆም ትልቁ ድርሻ ያላቸው ራሳቸው ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ ይኼ ሉዓላዊነትን የሚገልጽ መርህ ሲሆን፣ ሰዎች ሊቆሙለት የሚገባ የሰብዓዊ ደረጃ መለኪያም ነው፤›› ሲሉም ደምድመዋል፡፡

  በመድረኩ የኢትዮጵያ መንግሥትን አቋም ያፀባረቁት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ጌዴዎን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር)፣ መንግሥት በምርመራው የደረሰባቸውን የሰብዓዊ ጥሰቶች በማጣራት ዕርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝና ጥምር ምርመራውም እንዲካሄድ ያመቻቸ መሆኑን በማስታወቅ፣ በሁለቱ ወገኖች የሚደረገው የጋራ ምርመራ ጥልቅ፣ ገለልተኛና ከተፅዕኖ የፀዳ መሆኑን መስክረዋል፡፡ የመጨረሻ ሪፖርቱ ይፋ ከመሆኑ አስቀድሞም የመንግሥት ምላሽና ማብራሪያ እንዲካተትበት ከበቂ ጊዜ ጋር ሪፖርቱን እንደሚያጋሯቸው እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

  ቃና ዓቃቤ ሕጉ የኢትዮጵያ መንግሥት ግኝቶቹንና ምክረ ሐሳቦቹን በአግባቡ እንደሚመለከታቸው በማስታወቅና ተጠያቂነትን ለማስፈን እንደሚያግዝ እምነታቸው መሆኑን በመግለጽ፣ የምርመራ ሥራው ግን እስከ ተኩስ አቁሙ ድረስ ያለውን ጊዜ ብቻ ስለሚሸፍን ምሉዕነት ይጎድለዋል በማለት ተከራክረዋል፡፡ ይኼም የትግራይ ኃይሎች ባደረጉት መስፋፋት በአፋርና በአማራ ክልሎች ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደተፈጸሙ፣ ንፁኃን እንደተገደሉ እንዲሁም ሕፃናት ለውትድርና እንደተሠለፉ ታይቷል በማለት ነው፡፡ ለዚህም የጋሊኮማንና የጭናን ግድያዎች ለአብነት አንስተዋል፡፡

  ሆኖም ሁሉም መሰል ምርመራዎችን የሚያደርጉ አካላት ተመሳሳይ ጥልቀት ያለውን መንገድ ሊከተሉ እንዳልቻሉ በመጥቀስ፣ የአፍሪካ ኅብረት የሰብዓዊና የሰዎች መብቶች ተቋም ያደረገው ምርመራ አጥቂዎችን እንደ ተጠቂ አድርጎ በተናጠል የተከናወነ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የገጠመውን ፈተና ለመወጣት የሚችለውን ሁሉ እያደረገ እንደሚገኝና ከበቂ በላይ የታጠቀውና በገንዘብም የተደራጀው ኃይል ባለፉት ሦስት ዓመታት የተገኙ የዴሞክራሲ ድሎችን ለመቀልበስ እየሠራ ስለሚገኝ፣ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሕወሓት አጥቂው እንጂ ተጠቂው እንዳልሆነ ሊገነዘብ የሚገባው ወሳኝ ጊዜ ላይ እንገኛለን ብለዋል፡፡

  የአውሮፖ ኅብረት አምባሳደር ሎቴ ኑድሰን፣ እንዲሁም የስዊዲን አምባሳደርና የአሜሪካ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተወካዮች የትግራይ ግጭት እያስከተለ ያለው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እጅግ እንደሚያሳስባቸው፣ ግጭቶች ቆመው አጥፊዎች ተጠያቂ እንዲደረጉና ልዩነቶች በድርድር እንዲፈቱ ጠይቀዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ ግዛት ለቅቀው እንዲወጡና የኤርትራ መንግሥትም አጥፊዎችን ተጠያቂ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

  የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚያደርጉት ምርመራ ውጤት ጥቅምት 22 ቀን 2014 ዓ.ም. ይፋ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

  - Advertisement -