የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ በውሰን የግብርናና የማኑፋክቸሪንግ ምርቶች ላይ ብቻ በመንጠልጠሉ አገሪቱ በውጭ ምንዛሪ ቀውስ አዙሪት ውስጥ ከገባች በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል።
የውጭ ምንዛሪ ገቢን ለማስፋት መንግሥት በየጊዜው እያደረገ የሚገኘው ጥረት ከአጠቃላይ ፍላጎቱ አንፃር በእጅጉ ያነሰ በመሆኑ ከኤክስፖርት ገቢዎችና ከሌሎች የውጭ ምንዛሪ ምንጮች የውጭ ብድርና ዕርዳታ እንዲሁም ከውጭ አገሮች ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን የሚገኘው የረሚታንስ ገቢ ተደምሮ በየጊዜው እያደገ የሚገኘውን የገቢ ምርቶች ግዥ (ኢምፖርት) ለመሸፈን አልቻለም፡፡ በዚህም ሳቢያ አገሪቱን ለውጭ ምንዛሪ ቀውስ አዙሪት ዳርጓታል።
የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ችግር ለመፍታት የኤክስፖርት ምርቶችን ዓይነትና መጠን ሥር ነቀል በሆነ መልኩ ማሻሻል መሠረታዊ ጉዳይ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት የኤሌክትሪክ ኃይል ኤክክክፖርት ለአገሪቱ ዕምቅ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ሆኖ መታየት ጀምሯል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለጂቡቲና ለሱዳን ኤክስፖርት መደረግ የጀመረው የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ለኢትዮጵያ ያስገኝ የነበረው የውጭ ምንዛሪ ገቢ የዚህ ተስፋ ማሳያ ነው፡፡ ከአምስት ዓመታት በፊት ለሁለቱ አገሮች ከሚቀርብ የኤሌክትሪክ ኃይል ይገኝ የነበረው በ30 እና 40 ሚሊዮን ዶላር ዓመታዊ ገቢ የሚበልጥ አልነበረም ነበር፡፡ በተጠናቀቀው 2013 ዓ.ም. ግን 90.5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ከሁለቱ አገሮች ተገኝቷል።
በ2013 ዓ.ም. የተገኘው ገቢ ከዓመት በፊት ከተገኘው 66.4 ሚሊዮን ዶላር ከፍተኛ ጭማሪ ያሳየ ነው።
በ2013 ዓ.ም ከኤልክትሪክ ኃይል ኤክስፖርት የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ከቀደሙት ዓመታት ጭማሪ ማሳየት የቻለው ለሱዳን የሚቀርበው የኃይል መጠን በተወሰነ መጠን ከፍ በማለቱ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።
ጂቡቲና ሱዳን አሁን ከሚቀርብላቸው የኃይል መጠን በተጨማሪ ከፍ ያለ የኤሌክትሪክ ኃይል ግዥ ለመፈጸም ለኢትዮጵያ ጥያቄ እያቀረቡ ሲሆን፣ በፍላጎት መጠናቸውና በሽያጭ ታሪፍ ላይ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ንግግር እያደረጉ መሆናቸውም ታውቋል።
ሱዳን በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያ ከምትገዛው 200 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል በተጨማሪ 1,000 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለመግዛት ያላትን ፍላጎት ለኢትዮጵያ መንግሥት በማሳወቅ ንግግር መጀመሩን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከጥቂት ሳምንታት በፊት አስታውቋል።
በዚሁ መሠረትም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ባለሙያዎች በጉዳዩ ላይ በዝርዝር ለመወያየት ወደ ሱዳን ካርቱም አቅንተው እንደነበረና ለተጨማሪ ውይይት የሱዳን መንግሥት የባለሙያዎች ቡድን በቀጣይ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡም ተገልጿል።
የጂቡቲ መንግሥትም በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያ ከሚገዛው (ኢምፖርት ከሚያደርገው) 50 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል በላይ ለመግዛት ከመንግሥት ጋር ንግግር መጀመሩም ታውቋል፡፡ ጂቡቲ ለመግዛት የምትሻውን ተጨማሪ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ ይቻል ዘንድም ሁለተኛ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መሠረተ ልማት ለመገንባትም ታቅዷል፡፡ መሠረተ ልማቱን ለመገንባት የሚያስፈልገውን ወጪ ለመሸፈን የአፍሪካ ልማት ባንክ 86.3 ሚሊዮን ዶላር በዕርዳታ ለመስጠት ከኢትዮጵያና ከጂቡቲ መንግሥታት ጋር በሐምሌ ወር 2013 ዓ.ም. ስምምነት ፈርሟል።
የአፍሪካ ልማት ባንክ ከሚሰጠው የገንዘብ ዕርዳታ ውስጥ 69.65 ሚሊዮን ዶላር የሚሆነው ለኢትዮጵያ የሚውል ሲሆን፣ ቀሪው 13.9 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ ለጂቡቲ መንግሥት እንደሚውል ከባንኩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ባንኩ የሰጠው ዕርዳታ ከኢትዮጵያ ወደ ጂቡቲ የሚዘረጋውን ሁለተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ለመገንባት እንደሚያስችልና በዚህም 300 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ከኮምቦልቻ ወደ ጂቡቲ እንደሚዘረጋ ታውቋል።
ባንኩ ከዛሬ 17 ዓመት በፊት ባቀረበው ተመሳሳይ የገንዘብ ድጋፍ የመጀመሪያው የኃይል ማስተላለፊያ መስመር በሁለቱ አገሮች መካከል ተገንብቶ የኢትዮጵያ መንግሥትም ላለፉት አሥር ዓመታት ለጂቡቲ የኤሌክትሪክ ኃይል ኤክስፖርት ሲያደርግ ቆይቷል።
ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥም የኢትዮጵያ መንግሥት ለጂቡቲ ከሚያቀርበው መጠነኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ 275 ሚሊዮን ዶላር ማግኘቱን ያገኘነው መረጃ ያመልክታል።
በዚህም ምክንያት ጂቡቲ ኤሌክትሪክ ኃይል ለማምረት ለዲዝል ጄኔሬተር የምታወጣውን ወጪ በከፍተኛ ደረጃ በመቀነስ 65 በመቶ የሚሆነው የጂቡቲ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታ ከኢትዮጵያ በሚቀርበው የኤሌክትሪክ ኃይል ተሸፍኗል።
ሁለተኛው የመስመር ዝርጋታ ሲጠናቀቅ ተጨማሪ የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚቀርብና ይህም 85 በመቶ የሚሆነውን የአገሪቱን የኃይል አቅርቦት ፍላጎት እንደሚሸፍን ይታመናል።
ከሱዳንና ጂቡቲ በተጨማሪ ኬንያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሌ ላንድና ታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል ግዥ ከኢትዮጵያ ለመፈጸም ከመንግሥት ጋር እየተነጋገሩ መሆኑም ታውቋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘም የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ከኬንያ ኢነርጂ ሚኒስትር ቻርለስ ኬተር ጋር መስከረም 3 ቀን 2014 ዓ.ም. መወያየታቸውን ግልጸዋል።
በውይይታቸውም ኢትዮጵያና ኬንያን በኃይል ማስተላለፊያ መሠረተ ልማት ለማስተሳሰር የተጀመረው ፕሮጀክት አፈጻጸምና የፕሮጀክቱ ማጠቃለያ ትግበራን በተመለከቱ መመርያዎች ላይ መምከራቸው ታውቋል።
የኬንያ መንግሥት እንደ ጂቡቲና ሱዳን መንግሥታት ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ለመግዛት (ኢምፖርት ለማድረግ) ስምምነት ከተፈራረመ በርካታ ዓመታት የተቆጠሩ ሲሆን፣ በስምምነታቸው መሠረትም ኢትዮጵያና ኬንያን በኃይል አቅርቦት ለማስተሳሰር የሚያስችል የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ግንባታ ተከናውኖ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል።
የኃይል ማስተላለፊያ መስመሩ 500 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ኃይል መሸከም የሚችልና ከኢትዮጵያ እስከ ኬንያ ድረስ አንድ ሺሕ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን መሠረተ ልማት ነው።
ለዚህ መሠረተ ልማት ግንባታ 1.3 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ሲጠይቅ፣ ወጪውንም በዋነኝነት የሸፈኑት የአፍሪካ ልማት ባንክና የዓለም ባንክ ናቸው።
ይህ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ከኢትዮጵያ ተነስቶ ኬንያ ከመድረሱ ባለፈ፣ ቀደም ብሎ ኬንያ ላይ የተገነባውን የምሥራቅ አፍሪካ ኃይል ማስተላለፊያ ቋት እንደሚገናኝ ታውቋል።
የምሥራቅ አፍሪካ ኃይል ማስተላለፊያ ቋት (East African Power Pool) በሚል ስያሜ የሚታወቀው የኃይል ማስተላለፊያ መሠረተ ልማት ቋት (ግሪድ) ኬንያን፣ ኡጋንዳን፣ ታንዛኒያንና ብሩንዲን ያስተሳሰረ ነው።
በመሆኑም ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ የሚዘረጋው የኃይል ማስተላለፊያ መሠረተ ልማት መጠናቀቅ ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ኤክስፖርቷን ከኬንያ በተጨማሪ ለታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ፣ ብሩንዲና የተቀሩትን የምሥራቅ አፍሪካ የኃይል ቋት ተጋሪ አገሮች ለመሸጥ ያስችላታል።
ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ ከኬንያ አቻቸው ጋር ሰሞኑን ባደረጉት ውይይት ግንባታው የተጠናቀቀው የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ለአገልግሎት በሚውልበት ሁኔታና ዝርዝር የአተገባበር ሥርዓትን ለመቅረፅ መግባባታቸው ተገልጿል።
ለዚህም ሲባል ከሁለቱ አገሮች የተወጣጣ የቴክኒክ ቡድን ተደራጅቶ ረቂቅ ምክረ ሐሳብ እንዲያሰናዳ እንደሚደረግ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
ኬንያ የተጠናቀቀውን ማስተላለፊያ መስመር በመጠቀም በመጀመሪያዎቹ ዓመታት 400 ሜጋ ዋት ኃይል በዓመት ከኢትዮጵያ ለመግዛት ከዘጠኝ ዓመት በፊት ከኢትዮጵያ ጋር ስምምነት ፈርማ ነበር።
በሒደትም የምትገዛውን የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን ወደ 2,000 ሜጋ ዋት ለማሳደግ ስምምነት እንደተደረሰ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ኬንያ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት የምትገዛው የኃይል መጠን ለኢትዮጵያ በዓመት እስከ 556 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያስገኛል።
ይሁን እንጂ ከዘጠኝ ዓመት በፊት ከኬንያ ጋር የተገባው የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ስምምነት ታሪፍ አነስተኛ ነው። በስምምነቱ መሠረት ኢትዮጵያ አንድ ኪሎ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ለኬንያ ለመሸጥ የተስማማችበት ታሪፍ 0.07 ሳንቲም ዶላር ነበር፡፡ ይህ የታሪፍ ምጣኔ አሁን ካለው የኤሌክትሪክ ኃይል ማምረቻ ወጪ አንፃር እጅግ አነስተኛ በመሆኑ ታሪፉን የማሻሻል ዕቅድ መኖሩ ታውቋል።
ይህም ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ወደ ኬንያ፣ ጂቡቲና ሱዳን ኤክስፖርት በማድረግ የምታገኘውን ገቢ በቀጣዮቹ ጥቂት ዓመታት ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር እንደሚያደርሰው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ዓመታዊ የኃይል ማመንጨት አቅም በነሐሴ ወር 2013 ዓ.ም. ላይ 4,466 ሜጋ ዋት የደረሰ ሲሆን፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ተርባይኖች በጥቅምት 2014 ዓ.ም. ኃይል ማምረት ሲጀምሩ የአገሪቱ ዓመታዊ የአሌሌክትሪክ ማመንጨት አቅም ከ 5,000 ሜጋ ዋት በላይ ይሆናል።
ከህዳሴ ግድቡ ቀጥሎ የአገሪቱ ግዙፍ የኤሌክትሪክ ኃይል ፕሮጀክት የሆነው የኮይሻ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ነው፡፡ ይህ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ለብቻው 2,160 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ይኖረዋል።
የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ግንባታ በአሁኑ ወቅት 46 በመቶ ላይ የደረሰ ሲሆን እስከ 2015 ዓ.ም. ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት በቀረፀው የአሥር ዓመት የኢኮኖሚ ልማት ስትራቴጂ ውስጥ 40 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት የሚጠይቁ 71 የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ለማድረግ አቅዷል።
አጠቃላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ዘርፉ ለኢትዮጵያ ትልቅ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ያስገኛል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ሲሆን፣ ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎቹ ባሻገርም ከምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ጋር የሚፈጠረው የኃይል አቅርቦት ትስስር ኢትዮጵያ በአካባቢው ላይ ለሚኖራት ጠቀሜታና ተሰሚነት ግዙፍ ፋይዳ ይኖረዋል።