Sunday, March 26, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የገራድና ገራድነት ታሪክ በኢትዮጵያ

በተሾመ ብርሃኑ ከማል

በሰሜናዊው የአገራችን ክፍል በተለይ በጎንደር በጎጃም፣ በወሎ፣ በትግራይ፣ በሸዋ፣ (አማራ፣ ትግራይ፣ አገው) ልዑላዊ፣ ወታደራዊ፣ ኦፊሴላዊና የሲቪል ማዕረጎች አሉ፡፡ ከሉዑላዊ ማዕረጎች ንጉሠ ነገሥት፣ ንጉሥ፣ አልጋ ወራሽ፣ መስፍን፣ ንግሥተ ነገሥታት፣ ንግሥት፣ ሞገሳ፣ እመቤት ሆይ፣ ወይዘሪት ሆይ፤ ከወታደራዊ ማዕረጎች፣ ራስ፣ ደጃዝማች፣ ፊታውራሪ፣ ቀኛዝማች፣ ግራዝማች፤ ከኦፊሰላዊ ማዕረጎች ጸሐፌ ትዕዛዝ፣ …ሹም፣ በጅሮንድ፤ ከሲቪል ማዕረጎች አቶ፣ ወይዘሮ፣ ወይዘሪት የሚሉት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

በምሥራቃዊ የአገራችን ክፍል ደግሞ፣ ሱልጣን፣ አሚር፣ ኢማም፣ ገራድ ወዘተ የሚባሉት ይታወቃሉ፡፡ የገዳ ሥርዓትን በሚከተሉ የአገራችን ብሔረሰቦችም ኦሮሞዎች፣ ኮንሶዎች፣ ጌዲኦዎች ደግሞ  ደበሌ፣ ጋሜ፣ ፎሌ፣ ራባዶሪ፣ ጋዳ፣ ዩባ፣ ገዳ ሞጂና ጃርሳ የተባለ በዕድሜ የተከፋፈለ ማዕረግ አላቸው፡፡ ሌሎችም ማዕረጎች ይኖራሉ፡፡

ኢሕአዴግ የጓድን፣ የመቶ፣ የሻምበል፣ የሻለቃ፣ የብርጌድና የክፍለ ጦር ስሞችን በመቀየር ሠራዊቱን ጋንታ፣ ቦጦሎኒ፣ ጠርናፊ ሲል፣ በፖሊስ ሠራዊት ደግሞ ኮንስታብል (ወታደር)፣ ረዳት ሳጅንን (አሥር አለቃ) ሳጅን (ሃምሳ አለቃ) ዋና ሳጅን (አራተኛ ደረጃ ባሻ)፣ ረዳት ኢንስፔክተር (ምክትል መቶ አለቃ)፣ ምክትል ኢንስፔክተር (መቶ አለቃ)፣ ኢንስፔክተር (ሻምበል) ዋና ኢንስፔክተር  (ሻለቃ)፣ ምክትል ኮማንደር (ምክትል ኮሎኔል)፣ ኮማንደር (ኮሎኔል)፣ ምክትል ኮሚሽነር (ብርጋዴር ጄኔራል)፣ ኮሚሽነር (ጄኔራል፣ የፖሊስ ጠቅላይ አዛዥ) በሚል ከፋፍሏል፡፡

የዚህ ጥናት መሠረታዊ ዓላማ ግን እነዚህን ሁሉ ለመተንተን ሳይሆን፣ ገራድና ገራድነት ምንድነው? በአገራችን ገራድ የሚለው ማዕረግ በአገልግሎት የዋለው በየትኛው ግዛት ነው? የሥልጣኑ መጠኑስ ምን ያህል ነው? ገራድነት ከመቼ ጀምሮ በአገልግሎት ላይ ዋለ?  በአሁኑ ጊዜ የሚጠቀምበት ማንና ለምንድን ነው? ብሎ በመጠየቅ በዚህ ዙሪያ መልስ የሚፈልግ ነው፡፡ ይሁንና በዚህ ረገድ የተደረገ ጥናት ብዙ ባለመገኘቱ ምክንያት ከልዩ ልዩ መጻሕፍት የተገኘውን ፍንጭ በመገጣጠም አንዳች ተጨባጭ መረጃ ለማቅረብ ጸሐፊው የሚቻለውን ያህል ጥረት አድርጓል፡፡

ለመሆኑ ገራድ ምንድነው?

ገራድ ማለት በጥቅሉ ጠባቂ ወይም ከአደጋ ተከላካይ፣ ሕዝብን፣ አካባቢን፣ ጎሳንና አገርን ለመጠበቅ የሚያስችል ሠራዊት በሥሩ አድርጎ ከሡልጣኑ ወይም ከአሚሩ፣ ወይም ከኢማሙ ሥር የሚመራ፣ የጦር መሪ እንደ ማለት ነው፡፡ ሆኖም በልዩ ልዩ አጋጣሚዎች ራሱ የአገርና ሕዝብ መሪ ሊሆን እንደሚችል ከታሪክ መዛግብት እናገኛለን፡፡ ገራድ በዓረብኛ ጀራድ፣ በሐረሪዎች ገራድ፣ በኦሮምኛ ገራዳ፣ በሱማልኛ ገራድ ይባላል፡፡ በዓረብኛ ጀራድ የሚለው ቃል በብዙ የሚፈታ ስለሆነ ከብዙ ፍች ወታደር፣ ጠባቂ፣ የሠራዊት መሪ የሚለውን ብቻ እንወስዳለን፡፡ በአሁኑ ጊዜ ገራድ እንደ ማዕረግ የሚጠቀሙበት ሶማሌዎች ሲሆኑ በሐረሪም የገራድ ቀጥተኛ ተጠሪዎች እኛ ነን ብለው የሚያሳውቁና ከገራዶች ጋር ዝርያቸውን የሚቆጥሩ ቤተሰቦች አሉ፡፡ ጥንት የሐድያ፣ የወራባ፣ የገንዝ፣ የሐላባ፣ ወዘተ ገራዶች የነበሩ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ በስልጤ ዞን የገራድ ሹመት በመንግሥትም ባይሆን እንዲያው በተለምዶ ሰዎች ለሰዎች የሚሰጡት በባህላዊነቱ ያለ ሹመት ነው፡፡ በስልጤ፣ በሐድያ፣ በጉራጌ ዝርያቸውን ከጥንት ገራዶች ጋር አያይዘው የሚቆጥሩ አሉ፡፡  

ገራድ የሚለው ባህላዊ ሹመት በአሁኑ ወቅት በተግባር የዋለው በሶማሌ ክልልና በሶማሊያ ሪፐብሊክ ሲሆን፣ ወደፊት በዝርዝር እንደምንመለከተው ሁሉም ገራዶች ተሰብስበው ሊቀ መንበራቸውን ይመራሉ፡፡ የሱማሌ ገራዶች ባህላዊ መሪዎች ሲሆኑ ሕዝብን በማስተባበር መንግሥት በአስተዳደር የማይፈታቸውን ችግሮች ለምሳሌ እንደጎሳ ግጭት፣ የግጦሽ መሬቶች አጠቃቀም፣ የውኃ ጉዳጓድ አጠቃቀም፣ የዕርዳታ ስጦታዎች ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ማከፋፈል፣ መንግሥት አንዳች ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕቅዶችን ሲያልም የማማከር ተግባራት ያከናውናሉ፡፡ በምርጫ ጊዜም የጎሳዊ ስብጥሩ የተሟላ እንዲሆን ሐሳብ ሊሰጡ ይችላሉ፡፡ ገራዶች የመንግሥት አስተዳደር በማይደርስበት አካባቢ ማኅበረሰቡን ሰብስበው መፍትሔ ሊሰጡ ይችላሉ፡፡ የሱማሌ ገራዶችን በሚመለከት በዚህ ጥናት ወደፊት በዝርዝር የምንመለከተው ይሆናል፡፡

ገራድነት ከኢስላማዊ ሥልጣን ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ

ኢስላማዊ ሥልጣን ማለት በሸሪዓ ሕግ የሚመራ ማለት ነው፡፡ ስለሆነም አንድ ሰው ገራድ ለመሆን የቤተ መንግሥት ሰው ማለትም በጎሳው፣ በትውልዱ፣ በአስተዳደጉ የሱልጣን ዝርያ መሆን ብቻ ሳይሆን ኢስላማዊ ዕውቀትም ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህም ያስፈለገበት ምክንያት አንዳች ግጭት በጎሳው፣ ወይም ከጎሳው ውጭ፣ ወይም በአገር ደረጃ ቢፈጠር ተገቢ ነው ወይስ አይደለም? ተገቢ ከሆነ እንዴት ይካሄዳል? ተገቢ ካልሆነ እንዴት ይቆማል? ግጭቱ ከውጭ የመጣ ከሆነ በቀጥታ ወደ ጦርነት ከመገባቱ በፊት ጉዳዩ በእርቅ ሊያልቅ ይችላል ወይስ አይችልም? ከተቻለ ችግሩ ኢስላማዊ በሆነ መንገድ እንዴት ይታያል? ካልተቻለ እንዴት ኢስላማዊ በሆነ መንገድ ሊካሄድ ይችላል? ግጭቱ ከውስጥ ወደ ውጭ በአንዳች ምክንያት የሚካሄድ ከሆነ ለምንና እንዴት ይካሄዳል? የሚለው በዝርዝር ማየት አስፈላጊ በመሆኑ ነው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ፣ ገራድነት ራሱ ትልቅ ሥልጣን ነው? ወይስ ገራድ የተባለው ሹም በጉልበቱ ሥልጣኑን ሲያሳድግ አብሮ የሚያድግና እንደ ሁኔታው የሚለዋወጥ ነው?

ከሰሜን ኢትዮጵያ የጦር ሠራዊት ታሪክ የተያያዘው ሹመት ትንሹ ግራዝማች ሲሆን ቀጥሎ ቀኛዝማቸ፣ ፊታውራሪ፣ ደጃዝማች፣ ራስ፣ ቢትወደድ እያለ የሚሄድ ሲሆን ይህ ማዕረግ በአፋር፣ በሱማሌና በሌሎችም ሱልጣኖች በጉልህ አይታይም፡፡ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በሲዳማ፣ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉልና ጉሙዝ እነዚህን ሹመቶች ጎልተው የምናገኛቸው ከአፄ ምኒልክ ዘመን መንግሥት ወዲህ ሲሆን፣ ከዚያ በፊት የተጠቀሱት ማኅበረሰቦች የራሳቸው የሆነ የጦር ሠራዊት ማዕረግ እንደነበራቸው የታወቀ ነው፡፡ ለምሳሌ በመግቢያው ላይ እንደተገለጸው ኦሮሞዎች በገዳ ሥርዓት የሚመራ የጦር አመራር ነበረው፣ አሁንም ባህላዊ በሆነ መልኩ አለው፡፡

ይሁንና ገራድነት ከኢስላማዊ ሱልጣኔት ጋር አብሮ የመጣ በመሆኑ በአሁኑ ጊዜ በዓረብ አገሮች በተለይም በኢስላማዊ ሱልጣኔቶች አለ ወይ? ነበረስ ወይ? ብለን ስንጠይቅ የጦር መሪ፣ ወይም ጠላት ተከላካይ፣ ጠባቂ ከሚል ውሊ ለጊዜው ዝርዝር መረጃ አናገኝም፡፡ በኢስላማዊ ሥነ ጽሑፍ ላይ በርካታ ሥራዎችን ያበረከተውና በኢትዮጵያ በተለይም በሐረር ኢስላማዊ ሥነ ጽሑፍን በሚመለከት ምርምር ያደረገው አሌሳንድሮ ጎሪ ‹‹ኢንሳይክሎፒዲያ ኢትዮፒካ›› ውስጥ እንዳሰፈረው ግን ‹‹ገራድ ለክርስቲያኑም፣ ለሙስሊሙም የሚያገለግል የአካባቢ መሪዎች ሹመት ነው›› ይልና ቃሉ ከየት እንደተገኘ ግን ዎልፍ ሌስላው አይብራራም በማለት ይገልጻል፡፡ ኢንሳይክሎፒዲያ ኢትዮፒካ የተለያዩ የመረጃ ምንጮችን ጠቅሶ እንደሚያቀርበው፣ በአሁኑ ጊዜ ገራድ የሚለው ቃል በብዙ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች በጥቅም ላይ የዋለና የተለያዩ የሥልጣን ደረጃዎች የሚያመለክት መሆኑን ጠቅሶ በስልጢዎች ገራድ ማለት ንጉሥ ወይም ሹም መሆኑን፣ ሳአር ገራድ ማለት ለገራድነት የታጨ፣ ወላብ ገራድ ደግሞ የንጉሡ ወይም የገዥው ቃል አቀባይ ማለት መሆኑን ያስረዳል፡፡ ኢንሳይክሎፒዲያ ኢትዮፒካ ገራድ ዎልፍ ሌስላው ገራድ ማለት ደሚን ከተሰኘው ማዕረግ የሚያንስ መሆኑን አመልክቶ ዓብዱራሕማን ቆራም (ዶ/ር) ደግሞ ‹‹የአካባቢ አለቃ›› እንደ ማለት መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ሆኖም አካባቢ ማለት ምን ማለት ነው? ቀበሌ ነው ወረዳ፣ አውራጃ ነው ዞን ወይስ ምን? የሚለው ጥያቄ አይመልስም፡፡ በሶማሌ በተለይ ደሑልባንሐቴ ጎሳዎች፣ በሶማሌ ሐርላዎች፣ የገራድነት ማዕረግ የነበራቸው የጎሳ መሪዎች እንደነበሩ የሚታወቅ ሲሆን፣ ሪቻርድ ኮክ ሐረርን በሚመለከት ባካሄደው ጥናቱ ገራድ የሚለው ማዕረግ የሚሰጠው ለግብር ሰብሳቢዎች እንደ ነበር ጠቅሶ እነሱም የገራድነት ማዕረግ የነበራቸው የሐረርጌ ኦሮሞዎች እንደሆኑ ይገልጻል፡፡ ወደፊት በዝርዝር እንደምንመለከተው ሁሉ፣ በወሎ ውስጥ ገራዶች ይገዙ የነበር ሲሆን እነዚህም መሪዎች ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ከኢማም አሕመድ ጋር ከሶማሌ የሄዱ አዝማቾች ሊሆኑ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል፡፡

በሐረር ደረጃ ከሆነ የከተማ ወይም የገጠር ቀበሌ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ሐረር በተለይ ከ14ኛው ክፍለ ዘመን እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን ታላላቅ በገራድነት የሚጠሩ የጦር መሪዎች እንደነበሩ ስለሚታወቅ የአካባቢ ሹም ነው ብሎ መውሰድ ያስቸግራል፡፡ ኢንሳይክሎፒዲያ ኢትዮፒካ ኤግናዚዮ ጉዊዲንና ኬንን ጠቅሶ እንደሚያስረዳው ገራድ የሚለው ቃል በጥንታዊ የግዕዝ ጽሑፎች መገኘቱን ጠቅሶ የሐዲያና የጋንዝ ሕዝብ መሪዎች መጠሪያ እንደነበር ያወሳል፡፡ መገኛው ቋንቋም ኦሮሚኛ ሊሆን እንደሚችል አመልክቶ ነገር ግን በአንድም የኦሮሞ መዝገበ ቃላት ቃሉ እንደማይገኝ ያስረዳል፡፡ ሆኖም በአፄ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት ለንጉሠ ነገሥቱ የሚገብር የሐድያ ገራድ ተጠቅሶ እንደሚገኝ አሌሳንድሮ ጎሪ ይገልጣል፡፡ አፄ በዕደ ማርያምም የባሌ ገራድን ከጠላታቸው ጋር ጦርነት እንዲገጥም መታዘዙን ያስረዳል፡፡ ሆነም ቀረ ገራዶች በሰለሞናዊው ሥርወ መንግሥት የሚታወቁት ከ13-14ኛው ክፍለ ዘመን ወዲህ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ጉዊዲ በመጨረሻም ጋዳይቶ ገራድ፣ ጉዳሎ ገራድ፣ ዲሆ ገራድ፣ ሐባቦ ገራድ፣ ጋናዞ ገራድ፣ ሳጋ ገራድ፣ ቃቤን ገራድ፣ ጎጋላ ጋራደ፣ ሐላብ ገራድ፣ ኤረር ገራድ፣ ጌደይ ገራድ፣ ክዋሺም ገራድ፣ ሐርጋይ ገራድ፣ እያለ ይዘረዝራል፡፡

የታወቁ ገራዶች

ምንም እንኳን በአፄ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥትም ሆነ በአፄ በዕደማርያም ዘመነ መንግሥት (1476-1486) ገራዶች ለማዕከላዊው መንግሥት ይገብሩ እንደ ነበረ ቢገለጽም፣ ገራዶቹ እነማን እንደሆኑና በገራድነት ምን እንደሠሩ በዝርዝር የሚታወቅ ነገር የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ለጊዜው አላገኘም፡፡ በርከት ያሉ ገራዶችንና ታሪኮቻቸውን የምናገኘው በ16ኛው ክፍለ ዘመን የኢማም አሕመድ ኢብራሂም አልቓዚ ዜና መዋዓልን የዘገበው ዓብ ፈቂ ‹‹ፉቱሑል ሐበሽ›› በሚል ርዕስ ለንባብ ባበቃው መጽሐፍ ነው፡፡ በዚህ መጽሐፍ ከተጠቀሱት ገራዶች መካከል ገራድ ቢን ባሊ፣ ገራድ ዑስማን ቢን ጀውሀር፣ ገራድ አቡን፣ ገራድ አዲሽ፣ የተሰኙት የኢማም አሕመድ አጋሮች በተሳተፉባቸው የጦር ሜዳዎች ሁሉ ግንባር ቀደም ሚና እንደነበር ተገልጿል፡፡ ፍራንሲስኮ አልቫሬዝ (1536-1541) የተባሉት ፖርቱጋላዊ የሃይማኖት አባት በ1520 በኢትዮጵያና በፖርቱጋል መካከል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲፈጠር ከሌሎች ፖርቱጋላውያን ጋር የልዑክ ቡድን አባላት ጋር ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በነበረበት ጊዜ ከአፄ ልብነ ድንግል ጋራ የተገናኙ ሲሆን በዚህም ጊዜ ንጉሠ ነገሥቱ ከባሌ፣ ከገንዝና ከሐድያ  ገራዶች ጋር ግንኙነት እንደነበራቸው አስፍረዋል፡፡ አፄ ልብነ ድንግል ከኢማም አሕመድ ኢብራሂም ጋር ጦርነት በገጠሙበት ወቅት በክርስቶፈር ደጋማ የሚመራ 400 አባላት ያለው ሠራዊት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እንደነበር ይታወቃል፡፡ ከዚህም ዘማች ጦር ጋር ሙጋል ደ ካስታንያሆ (Miguel de Castanhos) የሚባል ወታርና ወታደራዊ ሪፖርት ዘጋቢ መጥቶ ነበር፡፡ ይህ ሰው የፖርቱጋል ዘማች ጦር  ከ1541 እስከ 1543 በኢትዮጵያ ውስጥ በነበረበት ጊዜ ከአፄ ልብነ ድንግል በኋላ የነገሡት አፄ ገላውዴዎስ ከሐረር ገራዶች ጋር የገጠማቸውን ፈተና ጽፏል፡፡ ካስታነንያሆ ከዚህም በተጨማሪ ጋንዝ ስለነበሩ ገራድ መሐመዶች በዘገባው አስፍሯል፡፡  

ከነዚህም በተጨማሪ የአዳሉ ሱልጣኔት የጦር ሰው ገራድ ማሕፉዝ፣ የሐዲያው ገራድ ሙሐመድ (የንግሥት እሌኒ አባት)፣ የገርዳፉሪው ገራድ ኢብራሂም፣ የሐረሩ ገራድ ዑስማን ኦዳ (የበክሪ ሳፓሎ አባት)፣ የሶማሊ ወረሰነገሊው ጎሳ አባል ገራድ ዲሕ ዲሕ፣ የደራዊሽና የዱሑለባሃንቴ ጎሳ መሪው ገራድ ዲሪዬ ጉሬ፣ የቀቤናው ገራድ አንጃሞ፣ ከኢማም አሕመድ ኢብራሂም በኋላ የጂሀድ ጦርነትን የቀጠለው ገራድ ዓባስ፣ የአውሳ ሱልጣኔቱ ገራድ ዓደን ሳዲቅ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ታዋቂ ገራዶች

አፄ በዕደማርያም በባሌ አካባቢ ጋንዝ ተብሎ በሚጠራው ግዛታቸው ማቴዎስ የተባለ ሰው ገራድ አድርገው ሾመው እንደ ነበር ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት ‹‹ቸርች ኤንድ ስቴት ኢን ኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ እአአ በ1972 (ገጽ 277) ባሳተሙት መጽሐፍ ይገልጻሉ፡፡ ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት በዚሁ መጽሐፍ የግርጌ ማስታወሻ ምንጭ ጠቅሰው እንደጻፉት፣ ማቴዎስ ጃንደርባው ማቴዎስ የጋንዝ ገራድ ከመሆናቸው በፊት በአፄ በዕደማርያም ቤተመንግሥት ተቀባይነት የነበራቸው ከመሆናቸውም በላይ ባለቤታቸው ንግሥት ሮማንንም ይጎበኟቸው እንደነበር አስፍረዋል፡፡ ስለሆነም፣ ጃንደርባው ማቲዎስ የሙስሊሞች መኖሪያ በነበረችው ጋንዝ የተሸሙት ሙስሊሙ የጋንዝ ገራድ ተወግዶ በምትክ መሾማቸውን ያመለክታል፡፡

አፄ ዘርዓ ያዕቆብ (1442 – 1476) ለደብረ ሊባኖስ ገዳም በጻፉት ደብዳቤ ጠላታቸው ከሆነው ከአዳሉ ሱልጣን በድላይ ጦርነት ለመግጠም መወሰናቸውን ባሳወቁበት ጊዜ የሐድያውን ገራድ ሙሐመድ (የንግሥት እሌኒ አባት) ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸው ሪቻርድ ፓንክረስት፣ መርእድ ወልደ አረጋይን (ዶ/ር) እና ፕሩኮን በመጥቀስ ‹‹ኢትዮጵያን ቦርደርላንድስ (1997) ገጽ 116 ላይ ይገልጻሉ፡፡

ሪቻርድ ፓንክረስት በተጨማሪም ገራድ ማሒንኮ የተባሉት የጋንዝ ገዥ የአዳል ገዥ የነበሩት ሱልጣን በድላይ፣ ኢብን ሳዕደዲንን በወገንና ለንጉሠ ነገሥቱ አልገብርም በማለት በአፄ ዘርዓ ያዕቆብ ላይ አምጸው እንደነበር ጠቅሰው፣ ገራድ ባሞና ገራድ ገዳይቶ  ንጉሠ ነገሥቱ እስከ ነበሩበት እስከ ደብረ ብርሃን በመሄድ እንደነገሯቸውና የንጉሠ ነገሥቱ ድጋፍ ካልተለያቸው የወንድማቸውን ልጅ ድል እንደሚያደርጓቸው ነገሯቸው፡፡ አፄ ዘርአ ያዕቆብም የገራድ ባሞንና ገራድ ገዳይቶ ምክር በመስማት ካባ አልብሰው፣ ሹመቱን ሰጥተው፣ በርካታ ጦር ሰጥተው አሰናበቷቸው፡፡ ገራድ ባሞና ገራድ ገዳይቶ  የተሰጣቸው ወታደራዊ ድጋፍ ከፍተኛ ስለነበር ገራድ ማሒኮን ድል አደረጉ፡፡ ገራድ ሐንኮም ሸሸው ወደ አዳል ሄዱ፡፡  ሆኖም ገራድ ባሞ ተከታትለው ‹‹አምባ›› በሚባል ሥፍራ ገደሏቸው፡፡ የመሪዎቹንም እግሮችና እጆች ቆራጠው ለግዳይ ስጦታ አበረከቱ፡፡ እጆቻቸውና እግሮቻቼ ተቆራርጠውም በቤተ መንግሥቱ አካባቢ ተንጠለጠሉ፡፡ ውሾችና ጅቦችም ተከፋፈላቸው፡፡ ገራድ ሐንኮ ከወታደሮቻቸው ጋር በመገደላቸውም በንጉሠ ነገሥቱ ቤተ መንግሥት ፌሽታ እንደሆነ ‹‹ኢትዮጵያን ቦርደርላንድስ፣ ከ143-144 ባለው ገጽ ይገልጻሉ፡፡ በዚህ መጽሐፍ በተለይ በገጽ 143 ገራድ ማሒንኮ ከገራድ ጉዶላ፣ ገራድ ዲሆ፣ ገራድ ሓዳቦ፣ ገራድ ጋንዞ፣ ገራድ ሳጋ፣ ገራድ ጋብ፣ ገራድ ቀቤን፣ ገራድ ጎጎላና ገራድ ሐላብ ማለትም ከዘጠኙ ገራዶች በስተቀር ሌላ ተከታይ ስለሌላቸው ድል ሊሆኑ እንደሚችሉ ገልጠው ሥልጣኑ ለገራድ ባሞ መስጠት ተገቢ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

ከዚህ መግለጫ የምንረዳው መሠረታዊ ቁም ነገር፣ ገራዶች በጦርነት ጊዜ የጦር መሪዎች፣ በሰላም ጊዜ ሕዝብን የሚያስተዳድሩ፣ የመንግሥትን ግብር የሚሰበስቡ፣ በመንግሥት ላይ የሚያምጹትን የመንግሥትን ይሁንታና ድጋፍ በማግኘት የሚደመስሱና የመንግሥት ጸጥታን የሚያስከብሩ፣ ሕዝብ በሰላማዊ መንገድ ሕይወቱን እንዲመራ የሚያስችሉ መሆናቸውን ነው፡፡

ይሁንና ጋራዶች ክንዳቸው ሲፈረጥም፣ ግዛታቸውን ማስፋት ሲያምራቸው በአገሪቱ መሪም ሊያምጹ እንደሚችሉም እንገነዘባለን፡፡ አሚር የነበሩት ሙሐመድ ቢን አራተኛ ቢን ያሲን (1584 – 1586) በሥልጣን በነበሩበት ዘመን በሐድያ አካባቢ ከአፄ ሠርፀ ድንግል ዘመነ (1571 – 1605) ጦር መግጠማቸውና ከመራራ ጦርነት በኋላ ተሸንፈው ከበርካታ ገራዶቻቸው ጋር መገደላቸውን የፕሮፌሰር ፓንክረስት ጥቁም ሥራ በገጽ 249 ሰፍሯል፡፡ ከገራዶቹም መካከል ገራድዛብ፣ ገራድ ሙሐመድ፣ ገራድ ጅብሪል፣ ገራድዷቃር ሙኸመድ፣ የአሚር ኑር ሦስት ልጆች ተጠቅሰዋል፡፡ አፄ ሠርፀ ድንግል ድንግል በሐድያ፣ ዳውሮና በሌሎችም ግዛቶች ገራድ አድርገው ሲሾሙ የንጉሠ ነገሥቱ ጥቅም አስጠባቂና የጦር አዛዥ ‹‹ጨዋ›› በሚል ስም ያስቀምጡ እንደነበር ይታወቃል፡፡

ገራዶች አሚሮችና ሱልጣኖች እንደሆኑ

ገራድ የጦር መሪና አስተባባሪ ቢሆንም ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ሁኔታው ካመቸው ሱልጣንም፣ አሚርም፣ ኢማምም ሊሆን እንደሚችል ልዩ ልዩ ሰነዶች ያመለክታሉ፡፡ ለአብነት ያህልም አቡበከር ቢን ሙሐመድ ቢን አዝሀር፣ አንዳንድ የታሪክ ጸሐፊዎች ኢማም መሕፉዝ ሦስተ ቢን መሐመድ ቢን ገራድ አዲሽ (1519 – 1521) አሚር ገራድ አቦኝ ቢን ሱልጣን መሐመድ ደግሞ 1522 እስከ 1525 አሚሮች እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡ ዋግነር እንደሚለው የዘይላዕ ገዥና የአዳል ሱልጣኔት ኢማም የነበረው ማሕፉዝ ቢን መሐመድ ከአፄ ልብነድንግል ጋር በተደረገው ጦርነት ሲገደል፣ በሃይማኖት መሪዎቹ መካከል የእርስ በእርስ መከፋፈል ስለነበር የተረጋጋ መንግሥት መመሥረት ቀላል አልነበረም፡፡ በዚህ ማሐል ገራድ አቦኝ ቢን አዳሽ የአዳል ሱልጣኔት ኢማም ሆኖ ብቅ አለ፡፡ ገራድ አቦኝ ቢን አዳሽ የአዳል ሱልጣኔት ከተማን ከሐረር ወደ ደከር አዛወረ፡፡ ገራድ አቦኝን እያሞካሸ የጻፈው ዓረብ ፈቂ (ሸሐበዲን) እንደሚለው ‹‹ሕግና ሥርዓትን አስከበረ፡፡ ስህተቱን ከልክሎ ትክክለኛው እንዲከናወን አዘዘ፡፡ የጎዳና ዋልጌዎችን አጠፋ፡፡ አልኮል መጠጥን፣ ቁማርን፣ ከበሮ እየመቱ መጨፈርን ከለከለ፡፡  ግዛቱ በለጸገች፡፡

1567 እስከ 1569 በነበረው ጊዜ ሥልጣን የያዘ አሚር ዑስማን ቢን በድላይ አስተዳደሩ ገራድ አቦኝ ቢን አዳሽ በተቃራኒ የአመራር ሥርዓቱ የተበላሸ ስለነበር ከራሱ ገንዘብ ቤት (ቑፍል ጎይታ) ከገራድ ጂብሪል ሳይቀር ተቃውሞ ተነሳበት፡፡ ገራድ ጅብሪል የኑር ሙጃሂድ አማች ሲሆን፣ በሱ የተጀመረው ተቃውሞ ወደ ሌሎች ተሸጋገረ፡፡ ስለሆነም አሚር ዑስማን ቢን በድላይ ከገራድ ጅብሪል የደረሰበትን ተቃውሞ ለመቀልበስ ገራድ በለው ሙሐመድ ገራድ እንዲወጋ አደረገ፡፡ ሆኖም ገራድ በለውም በተባበረው የሙስሊም ኃይል ሜይ 21 ቀን 1569 ድል ሆነ፡፡ ቸሩሊ እንደሚለው ደግሞ (1931) ምንም እንኳን ገራድ በለው ድል ቢሆንም ገራድ ጂብሪል በጦርነት ላይ ስለሞተ አመራሩን ጣልሐ ቢን ዐባስ ወሰደ፡፡ ጣልሐ ቢን ዐባስ፣ ዑመር በድላይ ሐረርን እንዲጠብቅ የወከለው ገራድ መሐመድ ሐርጋይን ድል ያደረገ ጁን 16 ቀን 1569 የሐረር ገዥ መሆኑን አወጀ፡፡ ይህም ሲሆን አሚር ዑስማን ቢን በድላይ ጦርነት ማድረግ ሰልችቶት አልተሳተፈም ነበር፡፡ 

ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌና ዋግነር እንደሚሉት ደግሞ ገራድ ጂብሪል አልሞተም፡፡ ሆኖም አሚር ዑስማን ቢን በድላይ በገዛ ፈቃዱ ሥልጣኑን ሲለቅ ጣልሓ ሳይሆን፣ ጂብሪል ራሱ የሐረር አሚር ሆነ፡፡ ከሆነም በኋላ አሚር ዑስማን ቢን በድላይንና በለው መሐመድን ገደላቸው፡፡ በኋላም አሚር ዑስማን ቢን በድላይ ዝርያ የሆነው በለው ዑስማን ቢን በድላይ 1571 ቀጥሎም የልጅ ልጁ ሙሐመድ ቢን ናስር ቢን ዑስማን የሐረር አሚሮች ሆኑ፡፡

ምንም እንኳን ለ200 ዓመታት ያህል ስለገራዶች ታሪክ ያነሳልን ለጊዜው ባናገኝም፣ አሚር አሕመድ አቡበከር፣ ቢን አፍተል ዳራድ ዐብዱልመናን፣ ቢን መሐመድ አሚር1834 እስከ 1854 ሥልጣን መያዙንና ሥልጣኑንም ያገኘው ወንድ ልጅ ካልነበረውና ፋጡማ የተባለችው ሴት ልጁ አባት ከሆነው ከአሚር አብዱልከሪም ነው፡፡ የአሚር አሕመድ ቢን አቡበከር ‹‹አፍተል ገራድ›› የተሰኘውን ማዕረግ ያገኘውም አባት የዘይላዕ ገዥ ስለነበረ ነው፡፡ ሴት አያቱ የአላ ጎሳ ኦሮሞ ተወላጅ ስትሆን እናቱ ጊስቲ ፋጢማ ደግሞ የታዋቂው የጋሪ ጎሳ አባል የሆነው የአደም ቢን ካውሻን እህት ናት፡፡ አሚር አሕመድ አቡበከር ቢን አፍተል ዳራድ ወደ ሥልጣን ከመምጣቱ በፊት ጀግና ተዋጊ እንደነበረ ይነገራል፡፡ በጀግንነቱ በመተማመንና ከኦሮሞዎች ጋር በነበረው ዝምድና አካባቢውን ለአንድ ዓመት ያህል ፀጥ ለጥ አድርጎ ለመግዛት ሞክሮ ነበር፡፡ ስለሆነም ገራድነት ትንሽ ሥልጣን ሳይሆን ወደ ሱልጣንነት፣ አሚርነትና ኢማምነት ሊያሻግር የሚችል ሥልጣን ነበር፡፡ ሐቁ ይህ ሆኖ ሳለ፣ የሐረር ሱልጣኔት ከተዳከመ ከብዙ ዓመታት በኋላ የመጡ የታሪክ ተመራማሪዎች ጥልቅ ጥናት ሳያካሂዱ በአጭሩ ይቀጩታል፡፡ ይህም እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ገራዶች በሐረር አቪሻይ ቤን ዶር እንደጻፈው

አቪሻይ ቤን ዶር፣ ‹‹ዒምሬት፣ ሐረር፣ ኢትዮጵያ፣›› በሚል ርዕስ ለፒኤች ዲ መመረቂያው በ218 ገጾች ለኅትመት በበቃው መጽሐፉ፣ (ሞደርን ኢንተሌክቹዋል ኤንድ ፖሊቲካል ሂስትሪ ኢን ሚድል ኢስት፣ ፍሬድ . ሎውሰን፣ ሲሪስ ኤዲተር)፣ በገጽ 87 ባሰፈረው መሠረት፣ ‹‹ዓሚሩ ከዚህም በተጨማሪ ከከተማዋ ውጭ ለሚኖሩ ገራድ የተባለ ተጨማሪ ማዕረግ ፈጥረው ነበር፡፡ ‹‹ገራድ›› የሚለው ስም ከየት እንደተገኘ አይታወቅም፡፡ በሶማሌ ውስጥ ግንድ ገራድ ማለት ከፍተኛ የመንግሥት ሥልጣን የያዘ ሲሆን፣ አንዳንድ ጊዜ ‹‹ልዑል›› የሚለውን ይተካል፡፡ ዓሚሩ ከግንቡ ውጭ የሚኖሩ ታላላቅ የኦሮሞ ልሂቃንን ገራድ ብለው የሾሙ ሲሆን ጋራዱም የመንደር መሪ ናቸው፡፡ የገራዶች ዋነኛ ሥልጣን ከገበሬዎች ግብር መሰብሰብ ሲሆን ለዚህም አገልግሎታቸው 600 ገሪብ ስፋት ያለው መሬት በዓሚሩ ይሰጣቸው ነበር፡፡ የገራድ አለቃ ‹‹ዶጊን›› የሚል ማዕረግ ሲኖረው ይህም በአደርኛ ቋንቋ ‹‹የውጭ አካባቢዎች ገዥ›› ማለት ነው፡፡ ዶጊን ከከተማዋ ውጭ ለነበረው ግዛት ‹‹የዓሚሩ የተገለጠ ዓይን›› የሚል ትርጉም ነበረው፡፡ በዚህም መሠረት ይህ ሹመት እስከ አስራ ዘጠነኛው ክለ ዘመን ድረስ የሚሰጠው ለሐረር ውስጥ ነዋሪዎች ነበር፡፡ ይህም ሆኖ ደግሞ በመለቅና በዶጊን መካከል ስለነበረው የሥራ ግንኙነት የሚገልጽ መረጃ የለም፡፡ እንደሚመስለው ከሆነ ዓሚሩ ጠንካራ በሚሆንበት ጊዜ መለቁ በውስጣዊ ጉዳዮች ላይ ብቻ እንዲሠማራ ይደረጋል፡፡ ዶጊንን በተመሳሳይ ሁኔታ ከሐረር ውጭው የሚገኘውን ጉዳይ ብቻ የሚከታል ይሆናል፡፡

አቪሻይ ቤን ዶር፣ በተጠቀሰው መጽሐፉ ከገጽ 106 እስከ 107 እንደገለጸው፣ ‹‹የግብፃውያን የመጀመሪያው ዕቅድ፣ ቀደም ብሎ እንደተጠቀሰው ሁሉ፣ በጎሳ የተበታተነውን የኦሮሞ ኅብረተሰብ በትልልቅ የሰፈራ መንደሮች ለማሰባሰብ ነበር፡፡ ራዑፍ ፓሻ ኤፕሪል 1877 በጻፈው ሪፖርት መሠረት፣ በከተማዋ ዙሪያ የሚገኙትን ‹‹ቆቱዎች›› በ250 ትልልቅና መካከለኛ መጠን ባላቸው መንደሮች ለማሰባሰብ ዕቅድ እንዳለው አስፍሮ ነበር፡፡ እንዲህ ያለው አብዮታዊ ዕቅዳቸው ጋርም የኦሮሞ ልሂቃንን በ1875 በፊት በነበራቸው የአስተዳደር ማዕረግ እንዲቀጥሉ ለማድረግ አስበው ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ራዑፍ ፓሻ የነበራቸውን የአስተዳደር ሥርዓት እስከ ማዕረጋቸው መልሶላቸዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ኦፊሴላዊ የአስተዳደር ሥርዓቱ በቀጥታ የሚመራው በሐረር ሒኪምዳሪያ አስተዳደር ነበር፡፡ በቱርኮ-ኢጅፕሻን አገዛዝ ሥር፣ የሐረር አካባቢ ኦሮሞ የገራድ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት እንዲቀጥል ያደረገ ሲሆን፣ በትንንሽ የኦሮሞ ወረዳዎቸ መሪ የሚሆኑ ጋራዶችን የሚሾመው ግን ራዑፍ ፓሻ ነበር፡፡ የዋቢነት ቃላቸውን የሰጡ ኦሮሞዎች እንደሚናገሩት በግብፃውያኑ የገራድነት ሹመት ሲሰጥ ይከበር ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ለሹመት የሚታጩት አምስት በሬዎችን በታክስ መልክ ለሐረር ሒኪምዳሪያ አስተዳደር ይከፍላሉ፡፡ በዚህም ለውጥ ቀሚስ፣ ካባና ኮፍያ እንደሹመት ልብስ ይበረከትላቸዋል፡፡ እንደዚሁም ገራድ ሆኖ የሚሾመው ሰው 1000 ፋዳን (4200 ስኩዌር ሜትር) ስፋት ያለው የእርሻ መሬት ይሰጠዋል፡፡ ራዑፍ ፓሻ በላከው ሪፖርት ለኦሮሞ ታላላቅ ሰዎች ሹመት የሚሰጣቸው በከዲቫዊው መንግሥት መመርያ መሠረት ነው፡፡ ግብፃውያን የመሬቱን መለኪያ ከገሪብ ወደ ፋዳን ቢቀይሩትም ከሐረር ከተማ ውጭ ለሚሾሙ ኦሮሞ ልሂቃን የሚሰጠው የእርሻ መሬት መስጠቱ ግን እንዲቀጥል ተደርጓል፡፡ አንድ የኦሮሞ ታላቅ ሰው ገራድ ሆኖ የሚሾመው፣ ለሒኪምዳሪያ የሚሰጠው ድጋፍ እንዲቀጥል፣ በኦሮሞዎች ዘንድ የተከበረ ሆኖ እንዲታይና ግብፃውያኑም የሚገባውን ክብር እንደሰጡት ለማሳየት ጭምር ነው፡፡

ግብፃውያን ከዚህም በተጨማሪ ‹‹መለቅ›› የሚለውን ሹመት ስሙን በመለወጥ እንዲቀጥል አድርገውት የነበረ ሲሆን፣ ቀደም ሲል ሹመቱ የሚሰጠው ለሐረር ከተማ ነዋሪ ነበር፡፡ የዚህም ሹም ተግባር ከገጠር ግብር መሰብሰብ ነበር፡፡ ግብፃውያን ግን ሹመቱን ከከተማዋ ግንብ ውጭ ለሚኖሩ ኦሮሞዎች ከመስጠታቸውም በላይ መለቅ ተብሎ ለሚሾመው ሰው 500 ፋዳን ስፋት ያለው የእርሻ ቦታ ይሰጡ ነበር፡፡ (ሆኖም መለቅ ሆኖ የሚሾመው ሰው እንደገራዱ የሹመቱን ለማመልከት ልብስ አይለብስም ነበር፡፡) 

ግብፃውያን ከተጠቀሱት ሹመቶች በተጨማሪ ‹‹ዳሚን›› የተሰኘ ሹመት ይሰጡ ነበር፡፡ ደሚን የተሰኘው ሹመት ግብፆች ይፍጠሩት፣ ወይም በዓሚሩ ዘመን ሲሰጥ የነበረ፣ ሆኖም ቃሉን በሚመለከት የተለያዩ ትርጉሞች ይሰጣሉ፡፡ መሃዲ ገዲድ የተባለው ሐረሪ ደሚን የሚለው ቃል ዓረብኛ መሆኑን ጠቅሶ ‹‹ዋስትና ሰጭ›› ማለት ነው በማለት ይተረጉመዋል፡፡ ግብፃውያን ይህን ቃል የተጠቀሙበት ሐረርን ከያዙ ከአሥር ዓመት በኋላ ነው፡፡ ‹‹ዳሚን›› ተብሎ የሚሾም የአጠቃላይ የጎሳው ተጠሪ ሲሆን፣ በአብዛኛው ተጠሪነቱ ከከተማዋ ውጭ ላለው የኦሮሞ ጎሳ አስተዳደር ነው፡፡ ዋልድሮን ግን ጥንትም ዓሚሮች ሲጠቀሙበት ሹመት ሲሆን ኃላፊነቱም ለአራት ወይም ለአምስት ጋራዶች ነው፡፡ ያኔ በዓሚሩ አስተዳደር ከከተማዋ ውጭ ላሉ የገጠር መንደሮች ተጠሪ ነበር፡፡ ዋነኛው ሚናውም የዳኝነትና የቡና ግብር መሰብሰብ ነበር፡፡

ሌላው በጥቅም ላይ የቆየ ሹመት ዶጊን የሚባለው ነው፡፡ መላቅ፣ ገራድና ዳሚን ከከተማ ውጭ ላለው መንግሥታዊ ሥራ የሚሾሙ ሲሆን፣ ዶጊን የተሰኘው ሹመት የሚሰጠው ግን ለሐረር ከተማ ሰዎች ነው፡፡ የዶጊን ሹመት ያላቸው ባለሥልጣናትም ተጠሪነታቸው በቀጥታ ለራዑፍ ፓሻ ነው፡፡

ስለዚህ በነአቪሻይ ቤንዶር ገራድ ማለት አንድ ትንሽ የአስተዳደር ማዕረግ መሆኑ ነው፡፡ በመሠረቱ እነአቪሻይ ቤን ዶር ከውጭ የመጡ አጥኚዎች ከመሆናቸውም በላይ በእጆቻቸው በገቡ መረጃዎች ተመሥርተው የሚጽፉ ናቸው፡፡ ችግሩ ያለው ከእኛ ከራሳችን አስረጅዎች በመሆኑ እንደገና በዝርዝር ልንመለከተው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

ጋራዶች አንድም ተሸንፈው፣ ወይም ሥልጣናቸውን ሳይለቁ ለንጉሠ ነገሥቱ አድረውና በሁኔታው አስገዳጅነት ክርስቲያን ሆነው ካልሆነ በስተቀር ገራድነት ከኢስላም ጋር የተያያዘ መሆኑን ያመለክታል፡፡

ገራዶች በወሎ

ምንም እንኳን ከኢማም አሕመድ ኢብራሂም ጋር ከምሥራቅ ኢትዮጵያ እስከ ሰሜን ኢትዮጵያ የተሠራጩት ገራዶች በርካታ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ስማቸውን ያልለቀቁት የወሎ ገራዶች ናቸው፡፡ ሑሴን ሙሐመድ (ዶ/ር) የሐረር-ወሎን ግንኙነት አስመልክተው ጠቃሚ ጥናት እንዳደረጉ የሚታወቅ ሲሆን፣ እሳቸውም ከኢማም አህመድ ኢብራሂም ጋር ገራዶች እንደመጡና እነሱም እስካሁን የዘለቀ ግንኙነት ሃይማኖታዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት እንደመሠረቱ በዚሁ ጥናታዊ ሥራቸው አስፍረዋል፡፡ በወሎና በሐረር መካከል ያለውን ጠንካራ ግንኙነትንም በተጨባጭ መረጃ ሲጠቅሱ፣ ‹‹ለምሳሌ በደቡብ ምዕራብ ደሴ ገራዶ ተብሎ የሚጠራ ሥፍራ ሲኖር ገራዶ የሚለው ስምም የተገኘው ገራድ ከሚለው ገዥ የተገኘ ነው፡፡ ይህም በተቀረው ሙስሊም በዝ በሆኑ የምሥራቅ ኢትዮጵያ ግዛቶች የተለመደ መሆኑን ብራውኻመርን በመጥቀስ ያስረዳሉ፡፡ በተጨማሪም በወሎ በተለይ በቆላ ገራዶ፣ ኮምበልቻል አለፍ ብሎ ደሴ መንገድ ሻሸቢር የምትባል ቀበሌ ስትኖር ስሟን ያገኘችው ሸኽ ሳቢር ከሚባሉ፣ ከኢማም አሕመድ ኢብራሂም ጋር ከመጡና ሸኽ መሆኑን ያወሳሉ፡፡ ዳውዶ የሚባለው ሥፍራም እንደዚሁ በተመሳሳይ ሁኔታ ከኢማም አሕመድ ጋር ከመጡት ከሸኽ ዳውድ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ሑሴን አሕመድ (ዶ/ር) ‹‹ከኢማም አሕመድ ኢብራሂም ቀጥሎ የተከሰተው የኦሮሞ መስፋፋት በሐረርና በወሎ የነበረውን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነትን ቢያላላውም ሃይማኖታዊ ትስስሩ ግን እንደቀጠለ ነው፤›› በማለት በርካታ መረጃዎችን ያቀርባሉ፡፡ 

የሱማሊ ገራዶች

‹‹የሱማሊ ገራዶች›› የሚለው ሐረግ ጥንታዊውንና ዘመናዊውን የሱማሌ ሕዝብ የሚያጠቃልል ሲሆን፣ ይህም ሕዝብ የሱማሊን፣ የኬንያንና የጂቡቲን የሚያካትት ነው፡፡ ይህም ኢትዮጵያውያን አፋሮችን፣ ጂቡቲያውያንንና ኤርትራውያንን እንደሚያካትተው ‹‹ሱልጣን›› የተባለ ማዕረግ መሆኑን ማስተዋል ይገባል፡፡ የሱማሌ ሱልጣናዊ ሥርዓት በተጠቀሱት የአፍሪካ አገሮች የተመሠረተው ከ1,000 ዓመታት በፊት ነው፡፡  የሱማሌ ጎሳ ከሚያካትታቸው ውስጥ ዲር፣ ኢስሐቅ፣ ሃዊዬና ዳሩድ ይገኙባቸዋል፡፡ ዲር የሚባሉት ጎሳዎች ዛሬ ሶማሊ ላንድ ተብላ በምትጠራው በሰሜን ሶማሊያ ግዛት፣ በጂቡቲ ሪፐብሊክ፣ በኢትዮጵያ፣ ብራቫና ጁባ ተብለው በሚጠሩት ወንዞች በምትገኘው በመርካ ቀበሌ ይገኛሉ፡፡ ኢስሀቅ የሚባሉትም በሰሜን ሶማሊያና በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፣ የዳሩድ ዝርያ ከሆኑት ከዲር፣ ከዱልበሐንቴና ከወርሳንገሊ ጎሳዎች ጋር ተጎራብተው ነው፡፡ ሐዊዬ የተባሉት ጎሳዎችም በደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ ሶማሊና በሰሜን ኬንያ በተለይም ከመጀርቲ ዳሮድ ማለትም ሞቃዲሾ አካባቢ በሚገኙት ሙዱግና ሒራን ተብለው በሚጠሩ ሥፍራዎች ነው፡፡ የዚህ ጥናት ዋና ጉዳይ ስለሶማሊም ሆነ ሶማሊያ ዝርዝር መረጃ ማቅረብ ሳይሆን ስለገራዶች መጠነኛ ግንዛቤ ለመስጠት በመሆኑ የአጁራ ሱልጣኔት (ከ13ኛው እስከ 17ኘው ክፍለ ዘመን)፣ የወርሰንገሌ ሱልጣኔት (ከ13ኛው እስከ 19ነኘው ክፍለ ዘመን) እና የዱልበሐንቴ ጎሳ ገራዶችን እንደሚከተለው እንመለከታለን፡፡ 

ወርሰንገሌዎች ከ13ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በዲሕዲሕ ገራዳዊ አመራር የሚመሩ ሲሆን፣ ይኸውም አመራር ገራድ ዲሕዲሕ (1298–1311)፣ ገራድ ሐመር ጋሌ (1311 እስከ 1328)፣ ገራድ ኢብራሂም (1328 እስከ 1340) ገራድ ዑመር (1340 እስከ 1355)፣ ገራድ ማሕሙድ  (1355 እስከ 1375)፣ ገራድ ዒሴ (1375 እስከ 1392)፣ ገራድ ሲዒድ (1392 እስከ 1409)፣ ገራድ አሕመድ (1409 እስከ 1430)፣ ገራድ ሲዒድ ዳግማዊ (1430 እስከ 1450)፣ ገራድ ማሕሙድ ዳግማዊ (1450 እስከ 1479)፣ ገራድ ዒሲ ዳግማዊ (1479 እስከ 1487)፣ ገራድ ዑመር (1487 እስከ 1495)፣ ገራድ ዓሊ ዳብሌ (1495 እስከ 1503)፣ ገራድ ሊበን (1503 እስከ 1525)፣ ገራድ ዩሱፍ (1525 እስከ 1555)፣ ገራድ ማሕሙድ ሣልሳዊ (1555 እስከ 1585)፣ ገራድ ዓብደል (1585 እስከ 1612)፣ ገራድ ዓሊ (1612 እስከ 1655)፣ ጋራድ ማሕሙድ አራተኛ (1655 እስከ 1675)፣ ገራድ ናለይ (1675 እስከ 1705)፣ ገራድ ሙሐመድ (1705 እስከ 1750)፣ ገራድ ዓሊ ዳግማዊ (1750 እስከ 1789)፣ ገራድ ማሕሙድ አምስተኛ (1789 እስከ 1830)፣ ገራድ ዓውል (1830 እስከ 1870)፣ ገራድ ዓሊ ሸሬ (1870 እስከ 1897)፣ ሱልጣን ማሕሙድ ዓሊ ሺረ (1897 እስከ 1960)፣ ሱልጣን ዓብደል ሳላን (1960 እስከ 1997)፣ ሱልጣን ሲዒድ ሱልጣን ዓብዲ ሰላን (1997 – እስካሁን)

የዱባሐንቴ ጎሳዎች የሚገኙት በሰሜን ሶማሊያ፣ በኢትዮጵያ፣ በደቡብ ሶማሊያ በተለይም በኪሲማዮ አካባቢ ሲሆን፣ በተለይ በኢትዮጵያ በዳሎ ዞን በቦሕ፣ ዳኖትና ዋርዴር ወረዳ ይገኛሉ፡፡ የዳሩዶች ዝርያ የሚጀምረው ከዓብዱራሕማ ቢን ኢስማዒል ጀበርቲ ሲሆን፣ ከጀበርቲዎች መካከልም ገራድ ሺርሾር (1530 እስከ 1550)፣ ፋራሕ ገራድ ሺርሾር፣ ገራድ ፋራሕ (1550 እስከ 1590)፣ ገራድ ዓብደላ (1590 እስከ 1600)፣ ገራድ ያሲን (1600 እስከ 1620)፣ ገራድ ባሕርሰሜ (1620 እስከ 1650)፣ ገራድጀባኔ (1650 እስከ 1685)፣ ገራድ ዓሊ (I1685 እስከ 1708)፣ ገራድ ማሕሙድ (1708 እስከ 1734)፣ ገራድ ማሕሙድ ዳግማዊ (1734 እስከ 1760)፣ ገራድ ማሕሙድ ሳልሳዊ (1760 እስከ 1780)፣ ገራድ ዓሊ ዳግማዊ (1802)፣ ገራድ መሐመድ ሳልሳዊ (1802 እስከ 1825)፣ ገራድ ዓሊ ሣልሳዊ (1825 እስከ 1840)፣ ገራድ መሐመድ አራተኛ (1840 እስከ 1863)፣ ሱልጣን ዲሪዬ ጉሬ (1897 እስከ 1918)፣ ዓር ዲሒል (1921 እስከ 1923)፣ ገራድ ጀማ ቀዳማዊ (1923 እስከ 1966)፣ ገራድ ዓሊ አምስተኛ (1966 እስከ 1985)፣ ገራድ ዓብዲቃኒ (1985 እስከ 2006) ገራድ ጃማ ገራድ ዓሊ (ከ2006 እስካሁን) እያለ ይሄዳል፡፡

በዚህ ጥናታዊ ጽሐፍ በመጠኑም ቢሆን ስለገራድ ምንነት፣ በኢትዮጵያ፣ በሶማሊያ፣ በጅቡቲና በኬንያ ስለሚገኙት ገራዶች፣ ገራዶች ወደ ሱልጣንነትና አሚርነት የመውጣት ዕድል እንደነበራቸው ለማውሳት ተሞክሯል፡፡ ሆኖም ይህ የተሟላ መረጃ ነው ማለት አይደለም፡፡ አንዳንዶቹ መረጃዎችም ወደፊት በሚገባ መበጠር ይኖርባቸዋል፡፡ ዋናውና መሠረታዊ ጉዳይ ግን በአገራችን ዛሬም ቢሆን በገራድነት የሚጠሩ የጎሳ መሪዎች መኖራቸውን በማስተዋወቅ ላይ ያተኮረ መሆኑ ነው፡፡ ወደፊት በፈጣሪ መልካም ፈቃድ ጠለቅ ያ ጥናት ተደርጎና በመጽሐፍ መልክ ተዘጋጅቶ ለኅትመት እንደሚበቃ ጸሐፊው ተስፋ ያደርጋል፡፡  

ከአዘጋጁጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛና ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ናቸው፡፡ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles