በኢትዮጵያ ፓራሊምፒክ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በቶኪዮ 2020 ፓራሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ያጠለቀችው ትዕግሥት ገዛኸኝ 2.8 ሚሊዮን ብር ተሸለመች፡፡
በ1,500 ሜትር ጭላንጭል በሚያዩት ውድድር ያሸነፈች ፓራ አትሌቷ ትዕግሥት ከገንዘብ ሽልማቱ በተጨማሪ 40 ግራም የወርቅ ሜዳሊያም ተበርክቶላታል፡፡
በቶኪዮ ፓራሊምፒክ ተሳትፈው ውጤታማ ለሆኑት አትሌቶች መስከረም 6 ቀን 2014 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ የሽልማት መርሐ ግብር ሲካሄድ ከትዕግሥት በተጨማሪ ለሽልማቱ ክብር የበቁት፣ በ1,500 ሜትር እጅ ጉዳት T-46 5ኛ ደረጃን በመያዝ ዲፕሎማ ያስመዘገበው ገመቹ አመኑ የ200 ሺሕ ብር፣ በተመሳሳይ በ1,500 ሜትር ጭላንጭል T-13 7ኛ ደረጃን በመያዝ ያጠናቀቀው ታምሩ ከፍያለው የ150 ሺሕ ብር ተሸላሚ ሆነዋል፡፡
የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ንጋቱ ኃይለ ማርያም 400 ሺሕ ብር፣ የቡድኑ ሐኪም ደግሞ 100 ሺሕ ብር ተሸልመዋል።
በቶኪዮ 2020 ፖራሊምፒክ ጨዋታ ኢትዮጵያ በሦስት አትሌቶች የተወከለች ሲሆን፣ አንድ ወርቅ ሁለት ዲፕሎማ በማግኘት ከዓለም 59ኛ ከአፍሪካ 6ኛ ደረጃ በመያዝ ውድድሩን አጠናቃለች።
በሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ላይ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ሒሩት ካሳው (ዶ/ር) ጨምሮ የስፖርት ኮሚሽነር አቶ ኤሊያስ ሽኩርና ምክትላቸው አቶ ዱቤ ጅሎ፣ እንዲሁም የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀብታሙ ሲሳይ ተገኝተዋል፡፡