የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት የአውራ ጎዳና ባለሥልጣን (IHA) ድርጅት በመባል በ1944 ዓ.ም. ተቋቋመ። የተቋቋመው በንጉሠ ነገሥቱ መልካምና ሙሉ ፈቃድ ሲሆን፣ ያቋቋሙትም የዓለም ባንክና የአሜሪካው ቴክኒካል አሲስታንስ ቢሮ ፐብሊክ ሮድ ናቸው። በወቅቱ ድርጅቶቻቸውን ወክለው የፊርማ ሥነ ሥርዓቱን የፈጸሙት ዶናልድ ፌ ባይግሎውና የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር አቶ ዘውዴ ገብረ ሕይወት ነበሩ። ድርጅቱ የተቋቋመበት ዓላማም በአገሪቱ ውስጥ የመንገድ፣ የድልድይ፣ የአውሮፕላን ማረፊያ፣ የወደብ ግንባታ፣ የዲዛይንና የቁጥጥር ሥራዎችን ለማከናወን ነው።
ከንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ውድቀት በኋላ ድርጅቱ ራሱን በሰው ኃይልና በተቋም ደረጃ እጅግ አዘምኖና አጎልብቶ በኮንስትራክሽኑ ዘርፍ በአገሪቱ በአራቱም ማዕዘናት ታላላቅ ተጨባጭ ግንባታዎችን አስመዝግቧል። የአገሪቱን ታላላቅ መንገዶችና ድልድዮች ስናስብ ከአውራ ጎዳና ውጪ ማንምና ምንም ድርጅት እንደሌለ ፍንትው ያለ ሀቅ ነው።
በነገራችን ላይ አውራ ጎዳና መሥሪያ ቤት እስካሁን አራት የተለያዩ ስሞችን በመጠሪያነት ተጠቅሟል። ሲቋቋም የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት የአውራ ጎዳና ባለሥልጣን (IHA)፣ ቀጥሎ የመንገድ ሥራ ድርጅት (ERA)፣ ሲቀጥል የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን (ETCA) አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን (ERA) ሆኗል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ሥር የኮንትራት አስተዳደርና የዲዛይን መምርያ ሆኖ ሲሠራ የቆየውና ከነሐሴ 20 ቀን 1979 ዓ.ም. ጀምሮ፣ በመንግሥት አዋጅ መሠረት በአዲስ መልክ ራሱን ችሎ የትራንስፖርት ኮንስትራክሽን ዲዛይን ድርጅት (TCDE) በመባል ተቋቋመ። የዲዛይን የኮንስትራክሽን ጥራት ቁጥጥር፣ የጂኦቴክኒካል ጥናት፣ የኮንስትራክሽን ማቴሪያሎች ምርመራ ሥራዎች በአንድ አካል በኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት መከናወናቸው በሥራው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረው በመታመኑ ነበር ትኮዲድ የተቋቋመበት ዋናው ዓላማ። ለ70 ዓመታት በጋራና በጥንድ ሆኖ ያገለገለው ሕንፃ ለአገራችን ቅርስ ነው፡፡ ያከናወናቸው ግዙፍ ግንባታዎችም እንዲሁ፡፡
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ድርጅቱ ላለፉት 70 ዓመታት የተገለገለበትን ሕንፃ በ2012 ዓ.ም. አንድ ዓመት ሙሉ በፈጀ የጥገና የዕድሳትና የቅርፅ ማሻሻል ሥራ ሠርቶ እጅግ አስውቦታል። ለዚህም ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ውጪ ወጥቶበታል። ታድያ እንዲ ተውቦ የታደሰው ሕንፃ በ2013 ዓ.ም. ለአንድ ዓመት ብቻ አገልግሎት ከሰጠ በኋላ ነሐሴ 13 ቀን 2013 ዓ.ም. በተደረገው የሠራተኛው ዓመታዊ ስብሰባ፣ የድርጅቱ ቱባ ሹመኛ ይህ ሕንፃ በ2014 ዓ.ም. የመጀመርያ ወር ላይ ይፈርሳል። በእሱም መቃብር ላይ ባለ 22 ፎቅ ግንባታ እንጀምራለን ሲሉ በኩራት ተናገሩ። ሹሙ ይህን ሲናገሩ ያለ ምንም ማመንታት ነበር። በአንፃሩ የስብሰባው ታዳሚዎች አናታቸው በበረዶ ናዳ የተመታ ይመስል ቀዝቅዘው ፀጥ ረጭ አሉ። ተሰብሳቢዎች ከሰመመናቸው ሲነቁ የአገሪቱን የመሠረተ ልማት ዝርጋታ የአምስት፣ ብሎም የአሥር ዓመት ንድፍ አስልቶ ቀይሶና መትሮ የሚያስቀምጥ አንጋፋ ተቋም እንዴት የራሱን ሕንፃ የሚገነባበትን ከሚያፈርስበት የጊዜ ሰሌዳ ጋር ማጣጣም ማስታረቅ አቃተው? ለሚያፈርሰው ሕንፃ 50 ሚሊየን ብር ወጪ አድርጎ ያውም በአንድ ዓመት ብቻ አገልግሎት ሰጥቶ እንዲፈርስ መወሰኑ ለምን አስፈለገ?
ጎበዝ አገራችን እኮ ማፍረስ ቀላል የሆነባት አገር ብቻ ሳትሆን፣ ፈርሶም ዝም የምትባልባት አገር እየሆነች ነውና በብርቱ እናስብበት፡፡
- (አቡቴ ደቦጭ፣ ከአዲስ አበባ)