Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እያጋጠሙ ያሉ የትራፊክ አደጋዎች በጣም አስደንጋጭ እየሆኑ ነው፡፡ ብዙዎቹ አሽከርካሪዎች ለማመን የሚያዳግት ጥፋት ከመፈጸማቸውም በላይ፣ የማሽከርከር ብቃታቸው በጣም የወረደና እንዴት የማሽከርከር ብቃት ማረጋገጫ እንዳገኙ ጭምር አነጋጋሪ ነው፡፡ ሌሎችን ከበድ ያሉ የችሎታ መመዘኛዎችን ትተን በጣም ተራ የሚባሉ ማለትም አደባባይ ላይ ለማን ቅድሚያ እንደሚሰጥ የማያውቁ፣ የዜብራ ማቋረጫ ላይ ለእግረኛ ቅድሚያ መሰጠት እንዳለበት የማያውቁ፣ ከፊታቸው ያለ አሽከርካሪ ለእግረኞች ቅድሚያ በመስጠት ላይ እያለ ያለ ምንም ማመዛዘን በፍጥነት እየነዱ አደጋ የሚያደርሱና የትራፊክ መብራት ሦስቱን ቀለማት ዓላማ ያልተረዱ ሞልተዋል፡፡ እነዚህ ናቸው እንግዲህ እየተደናበሩ ሕዝብ የሚፈጁትና ንብረት የሚያወድሙት፡፡ 

በቀደም ዕለት የክረምቱ ዝናብ እያካፋ እግረኞችንም በከባዱ የመጣውን ዝናብ ለመሸሽ መጠለያ ፍለጋ፣ ታክሲ የሚሳፈሩም ወደ ታክሲ ለመግባት ይራወጣሉ፡፡ መኪኖችም ከላይ ወደ ታች ይርመሰመሳሉ፡፡ በዚህ መሀል ከኮሜርስ ወደ ፌዴራል ፖሊስ ዋና መሥሪያ ቤት አቅጣጫ የሚጓዙ ተሽከርካሪዎች ሜክሲኮ አደባባይ ላይ ተኮልኩለዋል፡፡ የትራፊክ እንቅስቃሴው ወደ መጨናነቁ ያደላ ቢመስልም፣ ቆመው እግረኞችን ለማሳለፍ የሚጥሩ አሽከርካሪዎች ግን አልታጡም፡፡ ይሁንና በቆሙና በሚንቀሳቀሱ መኪኖች መሀል እየተሽሎከሎኩ በማለፍ ዝና ያተረፉት፣ አንዳንዴም ከአቅም በላይ ሙዚቃ እያስደለቁ የሚነጉዱት ሞተር ብስክሌተኞች እየጋለቡ ሲያልፉ አስደንጋጭ ነገር ተፈጠረ፡፡

አንደኛው ሞተረኛ በዚያ ካፊያ ሲበር መንገድ የሚያቋርጠውን እግረኛ አላስተዋለም፡፡ ምንም እንኳ ተሽከርካሪዎች ቆመው እግረኞችን በማሳለፍ ላይ ቢሆኑም፣ ይህ ሞተረኛ ግን ለዚህ ተግባር ጊዜ የነበረው አይመስልም፡፡ ይህ በመሆኑም በቅፅበት መንገድ በሚያቋርጠው እግረኛ ላይ ጉዳት ከማድረስ አልፎ አሽከርካሪውም ብዙም ባይሆን ለጉዳት የተዳረገ ይመስለኛል፡፡ አወዳደቁ ለጉዳት በሚዳርገው አኳኋን ነበር፡፡ አለባበሱም ቢሆን አናቱ ላይ ካጠለቀው የራስ ቅል ጉዳት መከላከያ በቀር፣ ከአደጋ ለመከላከል የሚያስችለው አልነበረም፡፡ ለቅድመ ጥንቃቄው እግረኛ ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት ባያስቀር እንኳ አሽከርካሪዎቹን ሊረዳ የሚችል የእግር፣ የእጅም ሆነ የሌላ ሰውነት ጉዳትን የሚቀንስ መከላከያ ቢለብሱ ጥቅሙ ለራስ ነው፡፡

በሜክሲኮ አካባቢ ያየነው አደጋ በእርግጥ ከአሽከርካሪው ይልቅ መንገደኛውን ለበለጠ ጉዳት የዳረገ ነበር፡፡ ይሁንና አደጋ የደረሰበት መንገደኛ ዕርዳታ እንዲያገኝ የተደረገበት መንገድ ግን አሳዛኝ ነበር፡፡ በሰዎች ከመከበብ በቀር አፋጣኝ ሕክምና ማግኘት የሚችልበትን ብልኃት ያስገኘ አልነበረም፡፡ ወደ ኋላ ላይ እንደተመለከትነው ገጭው ሞተረኛ ታክሲ ተኮናትሮ ይሁን ወይም ሌሎች ተጋግዘው ያደረጉት ባላውቅም፣ ተጎጂው መንገደኛ እንደ ምንም ወደ ሕክምና ተቋም የተወሰደ ይመስለኛል፡፡ በዚያ ካፊያና ለዓይን በማይመች ዕይታ ውስጥ የሞተረኞቹ ሁኔታ ግን ያበሳጭ ነበር፡፡

በየጊዜው በመንገድ አደጋ ምክንያት እየደረሰ ያለው አደጋ ለሺዎች ሕይወት መጥፋት፣ ለሺዎች አካል መጉደል፣ ለሚሊዮኖች ለሚቆጠር ሀብትና ንብረት መውደም ምክንያት ከሆነና ኢትዮጵያንም በመንገድ አደጋ ምክንያት አደገኛ ከተባሉ ዋና ዋና አገሮች ተርታ እንድትመደብ ዳርጓታል፡፡ በኢትዮጵያ በእያንዳንዱ አሥር ሺሕ ተሽከርካሪ ምክንያት በየዓመቱ 100 ያህል ሰዎች ለሕልፈት ይዳረጋሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ገዳይ ተሽከርካሪዎች ከተንሰራፉባቸው አገሮች ስምንተኛዋ ቀንደኛ አገር ተብላ ለመፈረጅ በቅታለች በማለት ሪፖርተር በአንድ ወቅት ያስነበበውን ዘገባ አስታውሳለሁ፡፡

በአገሪቱ የሚሽከረከሩት መኪኖች ብዛት፣ የሚደርሰው ጉዳትና አደጋ በእጅጉ ያልተጣጣሙ ሆነው መገኘታቸውንም ይኸው ጋዜጣ የዓለም ባንክን ጠቅሶ ጽፏል፡፡ ምንም እንኳ ከሌሎች ከተሞች አኳያ በአዲስ አበባ የሚገኙ ተሽከርካሪዎች ቁጥር አነስተኛ ነው ቢባልም፣ እያደገ የመጣው የትራፊክ መጨናነቅ በከተማው የትራፊክ ፍሰት ማኔጅመንት ላይ ጥያቄ እንዲነሳ ማስገደዱም በጋዜጣው ዘገባ ተጠቁሟል፡፡ ለመንገድ ትራፊክ አደጋ ከሚያጋልጡ ምክንያቶች ተርታ የሚመደበው በተለይ በአዲስ አበባ በቂ የእግረኞች መንገድ አለመኖሩ ሲሆን፣ በዓለም ባንክ መረጃ መሠረት 65 በመቶ የአዲስ አበባ የመንገድ ኔትወርክ፣ እግረኞች የሚረማመዱባቸው መንገዶች እጥረት እንዳለበት ሪፖርተር መዘገቡ፣ በአዲስ አበባም ሆነ በክልሎች እየደረሱ ያሉ አደጋዎች ምን ያህል ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ የሚጠቁም ነበር፡፡

ምንም እንኳ አሽከርካሪዎች ለሚደርሱት የመንገድ ላይ አደጋዎች ትልቁን ኃላፊነት የሚሸከሙ ቢሆኑም፣ እግረኞችም መንገድ ሲያቋርጡና በመንገድ ሲጓዙ ሊጠነቀቁ እንደሚገባ መንገር ለቀባሪው እንደማርዳት ይሆናል፡፡ ጥንቃቄ ለራስ መሆኑን ልብ ማለት ይገባል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ጠጥቶ በማሽከርከርና በችሎታ ማነስ ምክንያት እየደረሰ ያለው አደጋ እዚህ ላይ ትምህርታዊ በመሆኑ መነሳት ያለበት ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም እግረኞች መንገዳቸው በሞት የተሞላ መሆኑን በመገንዘብ መንቀሳቀስ ይገባቸዋልና፡፡

የዛሬ አምስት ዓመት ይመስለኛል ሽንጣሙ የአንበሳ ከተማ አውቶቡስ ንብረት የሆነው ቢሾፍቱ አውቶቡስ ሙሉ ሰው እንደጫነ ከፒያሳ አቅጣጫ ቁልቁል እየተንደረደረ ይመጣል፡፡ እንግዲህ መኪናው ፍሬን እንቢ ብሎት አሊያም መሪ አልታዘዝ ብሎት እንደሁ አላውቅም ብቻ ግን እንዳመጣጡ ቢሆን ስንቱን ጭዳ ባደረገ ነበር፡፡ ይሁንና የሾፌሩ ብርታት፣ የመንገድ ትራፊክ መብራት ከታች የሚመጡትን መኪኖች መያዙ ጥሩ አጋጣሚ ሆነና አውቶቡሱ በመንገድ አካፋይ ተንደርድሮ ሊቆም ችሏል፡፡

እጅግ አሰቃቂ አደጋ ከማድረስ በተዓምር ያመለጠው አውቶቡስ በራሱና በዕፅዋት ላይ ካደረሰው ጉዳት በቀር በተሳፋሪዎችና በእግረኞች ላይ ምንም ጉዳት አለማደረሱ እሰየው ቢያሰኝም፣ የፈጣሪ ጣልቃ ገብነት ተጨምሮበት ባይሆን ኖሮ የዚያን ቀን አደጋ በአዲስ አበባ ታሪክ ውስጥ ተመዝግቦ የሚቀር ሰቆቃ ይሆን ነበር፡፡

እኔ የአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት ቢሮና የመንገድ ማኔጅመንት ቢሮን የማሳስበው ሁለት ነገሮችን ነው፡፡ አንደኛ የአሽከርካሪዎች ብቃት ማረጋገጫ አሰጣጡ መሠረታዊ ለውጥ እንዲደረግበትና በየዓመቱ ፈቃድ ሲታደስ፣ የአሽከርካሪው ችሎታም እግረ መንገዱን ቢለካ እላለሁ፡፡ በተጨማሪ ጠጥተው የሚነዱ ግለሰቦች ጉዳይ ቁጥጥር ተጀምሮ ለምን እንደተተወ ስለማይገባኝ፣ ቁጥጥሩ በፍጥነት ይጀመር፡፡ ሌላው በአዲስ አበባ መንገዶች ላይ ከትራፊክ መብራት አተካከልና ቁጥጥር ጀምሮ የካሜራና የራዳር ቁጥጥር መጀመር አለበት፡፡ መንገዶች ለታለመላቸው ዓላማ ብቻ በሥርዓት እንዲያገለግሉ አስፈላጊዎቹ ሥራዎችና የቴክኖሎጂ ግብዓቶ ይሟሉ፡፡ አደጋን ጨርሶ ማስቀረት ባይቻልም በከፍተኛ መጠን መቀነስ እንደሚቻል ልምድ ተቀስሞ ሥራ ላይ ይዋል፡፡

(ያሬድ አበባው፣ ከአዲስ አበባ)

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...