Friday, June 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉይህ ዓመት ካሳለፈነው ዓመት በምን ይለያል?

ይህ ዓመት ካሳለፈነው ዓመት በምን ይለያል?

ቀን:

በተስፋዬ ወልደ ዮሐንስ ኃይሌ

የጊዜ መንጎድ ድንቅ ነው፡፡ በብርሃን የተቀበልነውን አዲስ ዓመት በጨለማ እንሸኘው ዘንድ ተፈጥሮ ግድ ትለናለች፡፡ ስንኖርበት የነበረውን ቁጥር ቀይረን አሮጌውን በአዲሱ ተክተን ቁጥር አክለን፣ በብርሃን፣ በደስታና በፀሐይ መናፈቅ ውስጥ አዲስነቱን በአደይ አበባ አጅበን እንቀበላለን፡፡ የተማረው ወደ የሚቀጥለው ክፍል ተሸጋግሮ፣ ትምህርቱን የጨረሰው ተመርቆ ሥራ ማግኘቱን ተስፋ አድርጎ፣ ሥራ ላይ ያለውም የተሻለ ዕድል እንዲገጥመው የተቀበልነውም አዲስ ዓመት 2014 ዓ.ም. መልካም እንዲሆን በጎ የምናስብበትና የምንሠራበት ሆኖ እንዲያልፍ ሁሉም ባለበት ይመኛል፡፡ አዲስነቱንም በተቀበልንበት ዘመን ውስጥ ቀኑን በፌሽታ እናሳልፈዋለን፡፡ ከዚህ በጎ ምኞት ባሻገር ያለፈው ዓመት እንዴት አለፈ? ይህስ የተቀበልነው ዓመት ካሳለፈነው ዓመት በምኑ ይለያል? ብሎ መጠየቅ እጅግ አስፈላጊ ሆኖ ይሰማኛል፡፡

ዘመንን መቀየር አስፈላጊ ነው፡፡ የጊዜ ሽግግሮሽ በመሆኑም ጭምር ተፈጥሮአዊም ነው፡፡ ክረምት ለበጋ፣ በጋው ለክረምት መልቀቁ በሰው ልጅና በተፈጥሮ መካከል ያለውን መስተጋብር ማሳያ መንገድ ነው፡፡ በሚለዋወጡ ወቅቶች ውስጥ ያለ የስሜት፣ የአካልና የመንፈስ ትምህርት ቤትም ነው፡፡ በእኛ ኢትዮጵያዊያን ዘመን አለካክ ውስጥ ያለፈው 2013 ዓ.ም. እንደ ግለሰብ፣ አገርና ሕዝብ ስኬቱና ፈተናው ለዚህኛውም ዓመት የተሻገረ ነው፡፡ አንዳንድ አገራዊ ጉዳዮቻችንም በያዝነውም ዓመት ብቻ የሚጠናቀቅም አይመስለኝም፡፡ ግን ደግሞ ሕይወት በጊዜ ልኬት እሽክርክሪቷ ትናንት፣ ዛሬና ነገ ብላ መጓዟን ትቀጥላለች፡፡ አንድ ብለን የጀመርነውም መስከረም ተጉዞ ጳጉሜን አሻግሮ ከአዲሱ ዓመት ደጃፍ ያደርሰናል፡፡

- Advertisement -

ያሳለፍነውን ዓመት መጠየቅና መመዘን ይህንን ዓመት መለኪያዎች አስቀምጦ ለመኖር፣ ትርጉም ያለው ለውጥና የአኗኗር ዘይቤ ለማምጣት ዓይነተኛ መንገድ ይሆናል፡፡ ዘመንን በቁጥር ብቻ መቀየር አዲስነቱን በተቀበልነው ዓመት ውስጥ የምንኖርበት አሮጌ ዓመት ነው፡፡ ምን ልንሠራ አቅደን ተነስተን ምንስ ከወንን? ለራስ ለወገንና ለአገር የሚጠቅም ምን አደረግን? የትኞቹ ጉዳዮችስ ሳይሳኩልን ቀሩ? መልካም ውጤት ያስመዘገብንባቸው ጉዳዮች ዋነኛ ምንጮቻችን ምን ነበሩ? ለውስንነቶቻችንስ ዓይነተኛ ሚና የተጫወቱ ምክንያቶች ምንድናቸው? ብሎ መጠየቅ አንድ ብለን ለጀመርነው መስከረም መንገድ መጥረጊያ እንደማንሳት እቆጥረዋለሁ፡፡ ከራስ አልፎ ለሌሎች ሕይወት በመኖር ውስጥ ያሉ ጥያቄዎች ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡

ያለፈውን ዓመት ካልጠየቅን ይህንንም ዓመት በምን ለይተን የተሻለ አድርገን ለመኖር እንደ ወጠንን ማወቅ ከባድ ይሆንብናል፡፡ በየትኛውም የኑሮ እርከንና ደረጃ ቢሆን የሥራ፣ የትምህርትና የዕድሜ ቁጥር ውስጥ መለኪያ የሌለው ሕይወትን መኖር ትርጉም ከሌለው ኑሮ እኩል ነው፡፡ ስኬትን የማንለካበት፣ ድክመትን የማንመዝንበት፣ ብርታትን ዕውቅና የማንሰጥበት ሕይወት ለራሳችምን ሆነ ሌሎች የማይጠቅም የአኗኗር ዘይቤ የሕይወት ታሪክ መጨረሻ ንባብ ነው፡፡

የዓመቱ ትልቁ ግቤ ምንድነው? ምንስ ለማሳካት አስቤያለሁ? ብለን ካልወሰንን፣ “Alice in Wander Land” በተሰኘ አንድ ጽሑፍ ውስጥ የምትገኘው ሜሪ የምትባል ሴት ታሪክ ያስታውሰኛል፡፡ ባለ ታሪኳ ጫካ ውስጥ ስትጓዝ ቆይታ በአጋጣሚ ብዙ መንገዶች ወዳሉት መስቀለኛ መንገድ ትደርሳለች፡፡ መንገዱ ላይ ደግሞ ጥንቸል ታገኛለች፡፡ ግራ ገብቷት ስለነበር ጥንቸሉን እንዳገኘች ዕርዳታ በመፈለግ፣ “እነዚህ መንገዶች ወዴት ይወስዳሉ?” በማለት ጠየቀችው፡፡ ጥንቸሉም፣ “ለመሆኑ አንቺ ወዴት መሄድ ትፈልጊያለሽ?” ብሎ ይጠይቃታል፡፡ ሜሪም፣ “እኔ ወዴት መሄድ እንደምፈልግ አላውቅም፤” በማለት መለሰችለት፡፡ በዚህ ጊዜ ጥንቸሉም፣ “የምትሄጂበትን ካላወቅሽ አንዱን መንገድ ይዘሽ ዝም ብለሽ ሂጂ፣ አንድ ቦታ ያደርስሻል፣” ሲል መለሰላት፡፡ የት እንደምንሄድ ባላወቅንበትና ባልወሰንበት መንገድ የምንደርስበት ቦታ ሁሉ ትክክል ይመስለናል፡፡ ይህንንም እንደ ስኬት እንቆጥረዋለን፡፡ 

የት መሄድ እንዳለብን፣ በሕይወታችን የት መድረስ እንደምንፈልግ የምንወስነውና የምንኖረው እኛው ነን፡፡ ውሳኔያችን ታዲያ ጥረትንና ቁርጠኝነትን ይጠይቃል፡፡ እያንዳንዱ የዕቅዳችን ክፍል አልጋ በአልጋ አለመሆኑንና ይልቁንም በእልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ የሚገኝ የትግልና የመስዋዕትነት ድል መሆኑን መቀበል በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ የክፍላችንን መስኮት መዝጋትና ክፍላችንን ማጨለም እንችላለን፡፡ እንዲሁም የክፍላችንን መስኮት ከፍተን ብርሃን እንዲገባ ማድረግም እንችላለን፡፡ ሁለቱም የምርጫ ጉዳይ ነው፡፡ አዕምሮአችን ማለት ክፍላችን ማለት ነው፡፡ እናጨልመዋለን? ወይስ በብርሃን እንዲሞላ እናደርጋለን? የቱ ውሳኔ ይጠቅመናል? ብሎ መጠየቅ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡

ጃፓናዊያን፣ “ግብ ያለ ድርጊት የቀን ቅዠት ነው፣ ድርጊት ያለ ግብ የማታ ህልም  ነው፤” ይላሉ፡፡ ራሳችንን በስኬታማነት መምራት ከፈለግን ዕቅዶቻችንን በአግባቡ ማስቀመጥ፣ ሊለኩ እንዲችሉ በማድረግ ማሰናዳት፣ ስሜትን የመግራት ብቃትን ሊያጠናክሩ የሚችሉ ሥነ አዕምሮአዊ ሐሳቦችን መረዳትና ዝግጁነት ይጠበቅብናል፡፡ እነዚህ ሐሳቦች ሕይወታችንን የምንቆጣጠርበትንና ትርጉም ባለው ሁኔታ ኑሮአችንን የምናሻሽልበትን ዕድል ይሰጡናል፡፡ ሁሉን አቀፍ ራስን የማሳደግ እንቅስቃሴ የሚያተኩረው አንድ ሰው በሕይወቱ የተለያዩ ክፍሎች ሰውነት (አካል)፣ አዕምሮ፣ መንፈስና ስሜት ስላለው እነዚህን ሚዛኑን በጠበቀ መንገድ ማሳደግ እንዳለበት ነው፡፡ አንድ ሰው አካሉን ወይም አዕምሮውን አሊያም መንፈሱን ብቻ በማበልፀግ ሌሎቹን ከተዋቸው፣ ሙሉ ዕድገት ወይም ሚዛኑን የጠበቀ ዕድገት ሊሆን አይችልም፡፡ ለሁሉም ግን ተገቢ የሆነ ትኩረት ሰጥቶ የሚያሳድግ ከሆነ፣ በአግባቡ የራሱን ሁለንተና ማሳደግ ይቻለዋል፡፡

ለዚህም አሁን ያለንበትን ሁኔታ መቀበል በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ራስን መቀበል ለራሳችን ያለን ግምትና ዋጋ ማወቅ፣ በራስ ዕምቅ የዕድገትና የስኬት ብቃት መተማመንና ራስን ለትልቅ ቁም ነገር ማጨት፣ የራስን ውስጣዊና ውጫዊ ማንነት በማወቅና በመቀበል ሌሎችም ማንነታችን እንደሚቀበሉ ማሳመንና ከሌሎች ሰዎች ሁሉ የተለየንና በመላው ዓለም ብቸኛ ራሳችንን የሚመስል ሰው አለመኖሩን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ በተፈጥሮ የተሰጠንን ዕምቅ ችሎታና ብቃት ግን እኛ ወደ ፈለግነው ደረጃ ማሳደግ እንችላለን፡፡ ነገር ግን የመጀመርያው ሥራ ማንነታችንን መቀበል ነው፡፡

ይህንን የማንነት ጥያቄ ከተቀበልን በራስ መተማመናችንን እናሳድጋለን፡፡ አቅደን ስለመኖር ውሳኔ ላይ እንደርሳለን፡፡ ያለፈው ዓመት ከዚህኛው ዓመት በተሻለ ለመኖርን ምርጫ ማድረጋችንን ለራሳችን መልሰን እናረጋግጣለን፡፡ የተሻለ ለሚለው ቢያንስ ለራሳችን መለኪያ የሚሆን የስኬት አሻራ አስቀምጠን ጉዞአችንን እንጀምረዋለን፡፡ የጀመርነውን ባስቀመጥነው መለኪያ በየወቅቱ በትክክለኛ መስመር ላይ እየተጓዝን መሆናችንን ጊዜ ሰጥተን ራሳችንን እንጠይቃለን፡፡ ትንንሽ ስኬቶቻችንን እናከብራለን፡፡ ክፍተቶቻችንን እንደፍናለን፡፡ የተሻለ ነገን ዛሬ በምርጫችን እንፈጥራለን፡፡

ይህንን ማድረግ ስንችል የትናንትናው ወይም ከዚህ ቀደም ያሳለፍናቸውን ዓመታት በተለየ ዘንድሮን አዲሱን ዓመት መኖር እንጀምረዋለን፡፡ ያኔ ያሳለፍነው ዓመት ከአዲሱ ዓመት በእርግጥም የሚለይ ይሆናል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...