በመርሐ ፅድቅ መኮንን ዓባይነህ
በመሠረቱ በመንግሥት ላይ እንዳስፈላጊነታቸው ገንቢ ትችቶችን መሰንዘርና ጥፋት ፈጽሞ ሲገኝ ደግሞ፣ በቅንነት መምከርም ሆነ በያገባኛል ባይነት መንፈስ መገሰፅ አትራፊነቱ አያከራክርም፡፡ እርሱም ቢሆን ታዲያ የምሩን ካልተሳሳተ በስተቀር ቀድሞ ነገር የሰዎች እንጂ የመላዕክት ስብስብ አለመሆኑን ከወዲሁ ተገንዝቦ፣ በፀባዩ ዴሞክራሲያዊና ዜጎችን ለማገልገል ብቻ የተቋቋምኩ ድርጅት ነኝ ብሎ እስካመነ ድረስ በዚህ እንዲከፋ ፈጽሞ አያስፈልግም፡፡
ይሁን እንጂ አበው “ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ ነው” እንዲሉ ከፀሐይ በታች ላሉ የአንድ አገር ሕዝብ ችግሮች ሁሉ በሥልጣን ላይ የሚገኝን መንግሥት አፍራሽነቱ በሚያመዝን የወቀሳ/ዘለፋ ናዳ አብዝቶ፣ መደብደብና ጠዋትና ማታ በአደባባይ ማሳቀል ብቻውን መፍትሔ መስሎ የሚታያቸው ወገኖች አልፎ አልፎ ያጋጥማሉ፡፡ እንዲያውም በጥንካሬው ፋንታ ድክመቱ፣ ከስኬቱ ይልቅ ውድቀቱ በቶሎ የሚከሰትላቸው እነዚህ ህፀፅ አዳኝ ወገኖች አሁን አሁን ቁጥራቸው እየተበራከተ መምጣቱን እንታዘባለን፡፡
እንደሚታወቀው ከውስጥ በኩል አሸባሪው ትሕነግ የእኛው የራሳችን ማዕከላዊ መንግሥት የወሰደውን ተናጠላዊ የተኩስ ማቆም ዕርምጃ እንደ ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም፣ ከሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የትግራይን ወሰን በመሻገር፣ አጎራባቾቹ በሆኑት በአማራና በአፋር ክልሎች ላይ ግልጽና መጠነ ሰፊ ወረራ ከፍቷል፡፡ እርሱ በተላላኪነት እያሠለጠነና እያስታጠቀ የሚያሰማራቸው የኦሮሞ፣ የቅማንትና የጉምዝ ደፈጣ ተዋጊዎች አሳቻ ሰዓት እየጠበቁ ከተለያዩ ማዕዘናት ሰርገው በመግባት፣ ሰላማዊ ዜጎችን በማረድና ንብረት በማውደም ያተራምሱናል፣ ዕረፍት ይነሱናል፡፡
ከውጭ ደግሞ እነርሱን አይዟችሁ ለማለት በወደዱና ኢትዮጵያ የምትባለው አገር ተዳክማ ብቻ ሳይሆን፣ ከናካቴው ፈራርሳ ደብዛዋ እንዲጠፋ አጥብቀው በሚመኙ የቅርብና የሩቅ ባዕዳን ጠላቶቻችን መከበባችን አንድና ሁለት የለውም፡፡ የቱንም ያህል ተዋጊዎች ብንሆን ታዲያ እንዲህ ያለውን የለየለትና ዓይን ያወጣ ከበባና የተቀናጀ ርብርብ፣ ይነስም ይብዛ ያለ ማዕከላዊ ምሪትና የዕዝ ሰንሰለት በተበታተነ ጥረትና ባልተደራጀ የምላሽ አሰጣጥ ሥርዓት ብቻ ልንቋቋመውና በአሸናፊነት ልንወጣው እንደማንችል መታወቅ ይኖርበታል፡፡
እነሆ ወቅቱ አገራችን ለመከራ የተዳረገችበትና ከየአቅጣጫው ተጠራርተው ሊያጠፏት ባሰፈሰፉ ታሪካዊ ጠላቶች የተባበረ ጥቃት ከዓለም ካርታ እንዳትሰረዝ በፍጡነ ረድዔትነት ደርሶ የሚታደጋትን መድኅን አጥብቃ የምትሻበት ነው፡፡ እዚህ ላይ የማያወላውል ስምምነት ካለ ደግሞ ተወደደም ተጠላ በመካሄድ ላይ ያለውን የህልውና ማስከበር ትግል የመምራትና የማስተባበር ኃላፊነት የሚወስድና ሁላችንም ፈቅደን የምንታዘዝለት፣ አንድ ማዕከላዊ አካል ማስፈለጉ ያን ያህል ሊያጠያይቅ አይገባም፡፡
እርግጥ ነው በአሁኑ ወቅት ክፉኛ የተናጋው ሰላማችን ወደ ነበረበት ተመልሶ ቀልባችንን ስንገዛ ‘መንግሥት’ ከተሰኘው ከዚያ አካል ጋር በበርካታ ጉዳዮች ላንስማማ፣ ይልቁንም በአገሪቱ መፃኢ ዕድል ላይ የተለያዩ አቋሞችን ወስደን መሟገታችንን ልንቀጥል እንችል ይሆናል፡፡ “እየዬም ሲዳላ ነው” እንዲሉ ይህ ግን በአሁኑ ወቅት እንደ ቅንጦት መታየትና መቆጠር አለበት፡፡
“ቦ ጊዜ ለኩሉ” ብሎ የለ ጠቢቡ? እንዲያ ያለውን እሰጥ አገባ ነገና ከነገ ወዲያ ስለምንደርስበት ለጊዜው ይቆየንና የህልውና ማስከበር ዘመቻውን በአመርቂ ድል ለመቋጨት፣ አዋጊ መንግሥትና እርሱ በኃላፊነት የሚያሠልፈው ኅብረ ብሔራዊ ጦር ያሻናል፡፡ መንግሥቱ ደግሞ በፋንታው የእኛ ሙሉ ደጀንነትና ያላሰለሰ ድጋፍ ያስፈልገዋል፡፡
ስለሆነም “የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ” በሚል ሰንካላ ዕሳቤ ሥር ወድቆ ፖለቲካዊ ምክንያቶችን እየደረደሩ በአገሪቱ አንድነትና በሕዝቧ ደኅንነት ላይ የተቃጣውን ወረራ ለመቀልበስ መንግሥት ከሚወስዳቸው ዕርምጃዎች ጋር አለመተባበር፣ እንደ ተገቢነቱ በተዋጊነትም ሆነ በደጀንነት አለመሠለፍ አገርን እስከ ማሳጣት ሊዘልቅ የሚችል ከባድ ዋጋ ያስከፍለናል፡፡
ከዚህ በተረፈ አልፎ አልፎ በተቃራኒው ሲፈጸም እንደ ምናስተውለው ጦርነቱን በበላይነት የመምራቱ ታሪካዊ ኃላፊነት በወደቀበት የመንግሥት አመራር ላይ ረብ ያለው አንዳች መፍትሔ የሌለው ውርጅብኝ የማውረዱ ዘመቻ ለትግሉ መሳካት እምብዛም አያግዝም፡፡ መንግሥትና ሕዝብን ይቅርና የራሱን አንድ ነጠላ ቤተሰብ ጉዳዮች እንኳ በቅጡ የመከወን ሐሞት ያልፈጠረበት አቅመ ቢስ የዳር ተመልካች ሁሉ ባፈተተው እየተነሳ፣ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች መሣሪያነት መጠነ ሰፊ የሐሜትና የሽሙጥ ናዳውን ሲያወርድ ውሎ ቢያድር በመካሄድ ላይ ያለውን አገር የማዳን ተጋድሎ ወደ ፊት በማራመድ ረገድ ጠብ የሚል ፍሬ አያስገኝለትም፡፡
ሰሞነኛው የልደቱ ምክረ ሐሳብ
ገንቢ ሐሶችን ከመሰንዘር ይልቅ ጫፍ በረገጠ የጥላቻ ፖለቲካ ከአንድ ጎራ ወደ ሌላው ሲዘል የኖረው ልደቱ አያሌው ሰሞኑን ብቅ ብሎ መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ይካሄዳል ተብሎ ከሚጠበቀው የመንግሥት ምሥረታ በፊት፣ የብልፅግና ፓርቲ ጠቅላላ ጉባዔውን እንዲጠራና የአመራር አባላቱን እንዲመርጥ ሐሳብ አቅርቧል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ሐሳቡ እምብዛም ባልከፋ ነበር፡፡
በእርግጥ አፈ ቅቤ ውልደቱ ሐሳቡን ያቀረብኩት አገሬን ከጥፋት ለመታደግ ነው ሲል በኃይለኛው ተመፃድቋል፡፡ ማዕከላዊ ጭብጡ ግን ከፓርቲውም በላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድን አምርሮ ከመጠየፍ ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ይመስላል፡፡ በእርሱ የግል ግምገማ አቅመ ቢስ ነው ያለው ዓብይ አህመድ በጠቅላይ ሚኒስትርነት እንደ ገና ተሰይሞ ማገልገሉን የሚቀጥል ከሆነ፣ አገሪቱን የገጠማት መከራ እስከ ወዲያኛው ይራዘማል የሚል አፍራሽ ድምፀት ያለው ሆኖ ነው የምናገኘው፡፡
ልደቱ በሚገልጸው ልክም ባይሆን ዓብይ አህመድ የራሱ የሆኑ የአመራር ድክመቶች አይኖሩትም ብሎ መቼም ቢሆን የሚከራከር ሰው የለም፡፡ እንደ እኛው ሰው እንጂ መላዕክ አይደለም፡፡ እንደ ማንኛውም ሰው በከፍተኛው የመንግሥት አመራር ላይ ሆኖ ስህተቶችን እንዲፈጽም ይጠበቃል፡፡ በሥልጣን ላይ በቆየባቸው ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥም ቢሆን አያሌ ስህተቶችን ሲፈጽም እንደታየ ሁላችንም ታዝበነዋል፡፡
ኧረ ለመሆኑ “አልቦ ፍፁም ዘእንበሌዬ”፣ ማለትም ‹‹ከእኔ በቀር ሌላ ፍፁም የለም” ሲል ለእኛ ለፍጡራኑ ከሚያውጀው አንድዬ በስተቀር፣ ከቶ በሥራው ላይ የማይሳሳት ማን አለ? ጥሩ ተናጋሪነቱና ጸሐፊነቱ ባይካድም ልደቱ ሲፈጥረው ተወዛዋዥ ፖለቲከኛ ነው፡፡ ከአቋም የለሽነቱ የተነሳ በአንድ ወቅት በተንሸራታቹ የተንቀሳቃሽ ስልክ ቀፎ ስምና መለያ እስከ መጠራት ደርሶ የነበረው ልደቱ አያሌው፣ የዛሬውን አያድርገውና ከአንድ ዓመት በፊት ጃዋር መሐመድን ከጎኑ አስቀምጦ፣ ‹‹ከመስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥት አይኖርም፤›› ሲል በማወጅ በማንም ሳይሆን፣ በራሱ ላይ ተሳልቆ እንደ ነበር እናስታውሳለን፡፡
ሌላው የልደቱ ችግር በየትኛውም ጉዳይ ላይ እርሱ የሚያቀርበውን ሐሳብ የመፍትሔዎች ሁሉ አናት አድርጎ የመመልከቱ አባዜ ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የመናገር አቅሙ ብቻ ለዚህ ዋስትና የሚሰጠው መስሎ ይሰማዋል፡፡ እነሆ ስድስተኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ ከተካሄደ በኋላ አልዋጥልህ ያለው መንግሥት እንደሚመሠረት ሲያውቅ፣ ልደቱ ሰሞኑን ባቀረበው ሐሳብ መሠረት በመካሄድ ላይ ያለው ህልውናን የማስከበር ዘመቻ ከወራሪውና በአሸባሪነት ከተሰየመው ቡድን ጋር ሊጀመር ይገባል በሚለው ሰላማዊ ድርድርና ዕርቅ እንዲቋጭ ያስፈልጋል፡፡ ምዕራባውያን ጋሻ ጃግሬዎቹም ቢሆኑ ይህንኑ ደጋግመው በማስተጋባት ነው ልባችንን የሚያወልቁት፡፡ ያውም ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ እኮ ነው፡፡
በነገራችን ላይ ልደቱ በኢትዮጵያዊነት ጭንብል ይመላለስ እንጂ በብሔር አማራ ነኝ ነው የሚለው፡፡ ሕወሓት ደግሞ በአሁኑ ወቅት አንድ ሦስተኛ የሚሆነውን የአማራ ክልል እንደ ተቆጣጠረ በሻገተ የፖለቲካ ደዌ የሚሰቃየው ይህ ግለሰብ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ልደቱ ተወልዶ ያደገው በታሪካዊቷ የላሊበላ ከተማ ውስጥ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ከተማዋ ደግሞ እንደ ብዙዎቹ የአማራ ክልል ከተሞች ሁሉ በሕወሓት እጅ ከወደቀች ትንሽ ሰነባብታለች፡፡
ይልቁንም በዚያ የሚገኘውና ንብረትነቱ የራሱ የሆነው ሆቴል በአሁኑ ወቅት ለወራሪው የጠላት ኃይል የጦር ማዘዣ ሆኖ በማገልገል ላይ እንደሆነ የመሰማቱ ዜና ከፍተኛ አግራሞትን የሚጭር ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ሰውዬው ቀደም ባለው ጊዜ በከፍተኛ ስሜት ተነሳስቶ፣ ‹‹ከኤርትራዊው ኢሳይያስ አፈወርቂ ይልቅ ኢትዮጵያዊው ደብረ ፅዮን ገብረ ሚካኤል ይቀርበኛል፤›› ብሎ በአደባባይ ስለመሰከረ፣ ሆቴሉን ለጦር ማዘዣነት ፈቅዶ ያልሰጠና ጠላትን ያልተባበረ ስለመሆኑስ እንደምን ማረጋገጥ ይቻል ይሆን? ይህ በውል ተጣርቶ ከተረጋገጠ ደግሞ ለሽብርተኛ ድርጅት ድጋፍ በመስጠት ወንጀል የሚያስጠይቅ ስለመሆኑ፣ የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ቁጥር 1176/2012 ዓ.ም. አንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ (2) ሥር አስቀድሞ መደንገጉን እዚህ ላይ ልብ ይሏል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በሕግ ሙያ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በ1981 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞው የሕግ ፋኩልቲ ያገኙ ሲሆን፣ በሐምሌ ወር 2001 ዓ.ም. ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በተመድ የሰላም ዩኒቨርሲቲ ጣምራ ትብብር ይካሄድ ከነበረው የአፍሪካ ፕሮግራም በሰላምና በደኅንነት ጥናት የማስተርስ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የርዕሰ መስተዳድሩ ዋና የሕግ አማካሪ ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው፡፡ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡