Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትየበረከት እርግማን - የውጭ ምንዛሪ ንድፈ ሐሳብና በ80 ሺሕ የንግድ ድርጅቶች ላይ...

የበረከት እርግማን – የውጭ ምንዛሪ ንድፈ ሐሳብና በ80 ሺሕ የንግድ ድርጅቶች ላይ የተወሰደ ዕርምጃ

ቀን:

በጌታቸው አስፋው

ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ በፋና ቴሌቪዥን ነሐሴ 19 ቀን 2013 ዓ.ም. ‹‹የኢኮኖሚ አሻጥርና የመሠረታዊ ሸቀጦች አቅርቦት›› በሚል ርዕስ በቀረበ ፕሮግራም ስለወቅቱ የስኳር፣ ስንዴ ዱቄትና ዘይት የመሠረታዊ ሸቀጦች ዋጋ መወደድ ከንግድ ሚኒስቴርና ከአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በመጡ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ለውይይት በተጋበዝኩበት ጊዜ፣ ከተነሱት ጥያቄዎችና መልሶች አስፋፍቼ ለአንባቢያን ለማቅረብ ነው፡፡

ሁለቱ የመንግሥት ባለሥልጣናት የአዲስ አበባንም ሆነ የመላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ የሦስቱ መሠረታዊ ሸቀጦች ፍላጎት ዕቅድ አውጥተው፣ ግማሹን ከአገር ውስጥ ምርት ግማሹን ከውጭ በማስመጣት ለማርካት እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ በአኃዝ አስደግፈው ገለጻ አድርገዋል፡፡ ምንም እንኳ መድረኩ የውይይት እንጂ የክርክር ባይሆንም፣ ክርክር አዘል ውይይት ለማካሄድ ስለፈለግኩ ጥያቄ ማንሳት ተገድጄ ነበር፡፡ ጥያቄዬም ከ110 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ 90 ሚሊዮን የሚሆነው የገጠር ሕዝብ የስኳርም፣ የስንዴ ዱቄትም፣ በአብዛኛው የዘይትም ተጠቃሚ ሳይሆን ሃያ ሚሊዮን ለሚሆነው የከተማ ነዋሪ ፍላጎት ማርካት አቅቶናል፡፡ እንዲሁም ዋጋዎች እንዲህ በየዕለቱ ከተወደዱብን 110 ሚሊዮን ሕዝብ የእነዚህ ሸቀጦች ተጠቃሚ ቢሆን ምን ልንሆን ነው የሚል ነበር፡፡ ለእኔ  የእነዚህ ሸቀጦች ዋጋ መናር ዋናው ምክንያት በየጊዜው ከገጠር ወደ ከተሞች የሚነጉደው ሕዝብ ብዛት ነው፡፡

የሰሞኑን በጥቁር ገበያ የብር ምንዛሪ ሁኔታና የብሔራዊ ባንኩ ዋስትና አስይዞ መበደርን ለጊዜው ማገድ አስመልክቶ፣ እኔ ለብቻዬ አስተያየት እንድሰጥበት በአቅራቢው ተጠይቄም ነበር፡፡ የዋጋ ንረትና የብር ምንዛሪ ዋጋ መውደቅን ተደጋጋፊነት ለበርካታ ጊዜያት የጻፍኩበት ስለሆነ፣ ጥያቄውን ከሌላ አቅጣጫ ለማየት በመፈለግ የብር ምንዛሪ ዋጋ መውደቅ በወቅታዊ ችግሩ ምክንያት ተባባሰ እንጂ ከህልውና ጦርነቱ በፊትም ችግር ያለበት ነው በማለት፣ በ1960ዎቹ በሆላንድ የተከሰተውን በምሳሌ በመጥቀስ አመሳስዬ ገልጬዋለሁ፡፡ የቴሌቪዥን ፕሮግራሙን ያልተከታተሉ ሰዎች ስለሚኖሩና ሰሞኑን አገራችን በምታካሂደው የህልውና ጦርነት ምዕራባውያን ለሕወሓት አግዘው በሚሰጡን ዕርዳታ ጫና አድርገው፣ አንተ ከዚህ ውጣ አንተ እዚህ ግባ እያሉ በርቀት ለማስተዳደር መፈለጋቸው አገራዊ ክብርንና ሉዓላዊነትን ዝቅ የሚያደርግ፣ በሌሎች አገሮች ቁጠባ ላይ የመመርኮዝ ቅሌት ሁኔታ ውስጥ ከመግባታችን ጋር አያይዤ ለማቅረብ ፈለግኩ፡፡

የምንዛሪ መጣኝ በእርግጣዊ መጣኝ (Real Exchange Rate) እና በምሥላዊ መጣኝ (Nominal Exchange Rate) የሚለካ ሲሆን፣ ምሥላዊው ኦፊሴላዊ መጣኝ ከእርግጣዊው ዋጋ በላይ (Overvalued) መሆንና በታች (Undervalued) መሆን ለማብራራት፣ ወደ ሆላንድ የውጭ ምንዛሪ ሁኔታ ልመለስ፡፡ በ1960ዎቹ ሆላንድ ነዳጅ በማግኘቷ የመገበያያ ምንዛሪዋ ጊልደር ዋጋ ወደ ላይ ስለወጣ (Appreciated)፣ በዚያው ልክም የፋብሪካ ምርቶቿ ለሌሎች የኢምፖርት ሸሪኮቿ ከሌሎች አገሮች ምርት ጋር ሲነፃፀር ውድ ስለሆነባቸው መሸጥ አቃታት፡፡ ይህ ሁኔታም የደቾች እርግማን/በሽታ (Dutch Disease) ተብሎ ይታወቃል፡፡ የነዳጁ መገኘት በረከት ሲሆን፣ የፋብሪካ ምርቶቿ ውድ ሆነው ሊሸጡ አለመቻላቸው እርግማን ሆነ፡፡

ሁኔታውን ወደ እኛ አገር ስናመጣው የእኛ እርግማን ከኤክስፖርት ውጪ ለረዥም ጊዜ በድጋፍና በዕርዳታ ወይም ብድርና የውጭ ቀጥታ መዋዕለ ንዋይ መልክ የምናገኘው የውጭ ምንዛሪ በረከት ቢሆንልንም፣ የብራችን የምንዛሪ ዋጋ አተማመን ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጠረ፡፡ በአገር ውስጥ ገበያ በዋጋ ንረት ምክንያት በውድ ዋጋ የሚገዙትን የኤክስፖርት ምርቶቻችንን በዓለም አቀፍ ዋጋ ተወዳድረን መሸጥ አልቻልንም፡፡ ወያኔ በ27 ዓመታት ወስዶ ወደ ውጭ ያወጣው የውጭ ዜጎች ቁጠባ የውጭ ምንዛሪ በረከቱ ባክኖ እርግማኑ ከእኛ ጋር ቀርቷል፡፡ ከዚህ የድህነት አዙሪት አጣብቂኝና በእጅ አዙር በሞግዚትነት እናስተዳድራችሁ ከሚሉን አገሮች ልንወጣ የምንችለው ራሳችንን በራሳችን ስንችል ብቻ ነው፡፡

ወደ መሠረታዊ ፍጆታ ሸቀጦቹ መወደድ ልመለስና የኒዮክላሲካል ኢኮኖሚስቶችን አስተምህሮ ተመርኩዞ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከሕዝቡ ግላዊ ተጠቃሚነትን (Self Centrism) ማዘንበል ሥነ ልቦናዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ባህሪያት ከኬንስ የሰው ልጆች በመረጃ ሳይሆን በስሜት የመነዳት እንስሳዊ መንፈስ (Animal Spirits) ጽንሰ ሐሳብ ጋር አያይዘን መግለጽ እንችላለን፡፡ ኬንስ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች በአክሲዮን ገበያ ውስጥ የሚሳተፉት ስለኢኮኖሚው በቂ መረጃ ይዘው በተማመን ሳይሆን፣ በዕለታዊ ወሬዎችና ዕለታዊ ጥቅሞች ስሜት በመነዳት ባህሪ እንደሆነ አመላክቷል፡፡ በቅድሚያ ከኬንስ በፊት ኢኮኖሚስቶች የኒዮክላሲካል ኢኮኖሚስቶች ከቀዳሚዎቻቸው የክላሲካል ኢኮኖሚስቶች የተለየ አመለካከትን እንመልከት፡፡

አዳም ስሚዝና ሪካርዶን በመሳሰሉ የክላሲካል ኢኮኖሚስቶች አስተምህሮ የሸቀጥ ዋጋ የሚወሰነው ምርቱን ለማምረት በፈሰሰ ጉልበት ልክ የማምረቻ ወጪ መጠን የአቅርቦት ጎን ኢኮኖሚ ትንታኔ ነበር፡፡ ከእነሱ በኋላ በመጡት በእንግሊዛዊው አልፍሬድ ማርሻል፣ በፈረንሣዊው ሊኦን ዎልራስና በኦስትራዊዎቹ ካርል መንገርና ሉድዊግ ቮን ሚስስ፣ በኒዮክላሲካል ኢኮኖሚስቶች አስተምህሮ ግን የሸቀጥ ዋጋ የሚወሰነው ለሸማቹ በሚሰጠው የቀጣይ ጠቀሜታ ሥሌት ሕግ የፍላጎት ጎን ኢኮኖሚ ትንታኔ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ፍልስፍና ላይ ያተኮረው የክላሲካል ኢኮኖሚስቶች ኢኮኖሚ ትንታኔና በካርል ማርክስ የርዕዮተ ዓለም ገጽታ የተሰጠው የዋጋ አወሳሰን ምልከታ፣ በኒዮክላሲካሎች መጠንንና ቀጣይ መጠንን በመለካት የሒሳብ ሥሌት መተንተን ተቀየረ፡፡ የጠቀሜታ  (Utility)፣ የቀጣይ ጠቀሜታ (Marginal Utility)፣ የምርታማነት (Productivity)፣ የቀጣይ ምርታማነት (Marginal Productivity) እና የልጠት (Elasticity) ጽንሰ ሐሳቦች የዋጋ አተማመን ወሳኝ ጉዳዮች ሆኑ፡፡

ኬንስ የሸማቹን የገበያ ወሳኝነት ከኒዮክላሲካል ኢኮኖሚስቶቹ በመዋስ በኅብረተሰቡ ውስጥ ገበያ ውስጥ ባለው የደመወዝ መጣኝ ለመቀጠር ፈልጎ በማጣት ያለ ውዴታና ያለ ሥራ የተቀመጠ የሰው ሀብት (Involuntary Unemployment) ካለ ምክንያቱ በምርት ፍላጎት እጥረት ስለሚሆን ነው በማለት፣ ከአቅርቦት ጎን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ይልቅ ወደ ፍላጎት ጎን ፖሊሲ ያደላበት ምክንያትም ከኒዮክላሲካሎቹ በተቀዳው የጠቀሜታና የቀጣይ ጠቀሜታ ልኬትና የሸማቹ ምርጫ (Consumers Choice) ምክንያት ሆኖ፣ መንግሥት የበጀት ጉድለትም ውስጥ ቢሆን ገብቶ ፍላጎትን በመጨመር አቅርቦትን በማምረት ሙሉ አቅም ላይ ማድረስ ያስፈልጋል በማለት የፍላጎት ጎን ኢኮኖሚ ትንታኔን አስፋፋ፡፡

ይህ ከአቅርቦት ጎን ኢኮኖሚያዊ ትንታኔ ይልቅ ለፍላጎት ጎን ኢኮኖሚያዊ ትንታኔ ዋጋ የሚሰጥ ንድፈ ሐሳብ በምዕራባውያን አገር ኢኮኖሚ ታሪክ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከተከሰተው ታላቁ የኢኮኖሚ ዝቅጠት ጀምሮ፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ትንታኔ ንድፈ ሐሳብ ሆኖ በ1960 እና 1970 ዓ.ም. በምዕራባውያን አገሮች እስካጋጠመው የዋጋ ንረትና የሥራ አጥነት በተመሳሳይ ሁኔታ መከሰት (Stagflation) ድረስ ቀጥሎ ነበር፡፡ ከ1980ዎቹ ዓመታት በኋላ ግን የሥራ አጥነት ክፍተትን (Recessionary Gap)፣ የዋጋ ንረት ክፍተትን (Inflationary Gap)፣ ከማምረት ሙሉ አቅም (Potential Full Employment Production Level) በታችና በላይ መሆን ችግር በተመሳሳይ ጊዜ ሊፈታለቸው ወደ ቻለው ወደ የአቅርቦት ጎን የኢኮኖሚ ፖሊሲ አድልተው ነበር፡፡ ሆኖም በ2008 ዓ.ም. ባጋጠማቸው የገንዘብ ቀውስ ምክንያት ወደ ፍላጎት ጎን ኢኮኖሚ ፖሊሲ ተመልሰው ፕሬዚዳንት ኦባማ የ2008 ዓ.ም. የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ክፍተትን (Recessionary Gap) ቀውስ ያረገቡት በፍላጎት ማነቃቂያ (Stimulus Package) የፍላጎት ጎን ፖሊሲ ነው፡፡

የአቅርቦት ጎን ኢኮኖሚ ፖሊሲው በሁለት የተከፈለ ሲሆን፣ ዝርዝር ሁኔታዎቹ ውስጥ ሳልገባ አንደኛው ለውድድር ምቹ ሁኔታ መፍጠር ገበያ ተኮር (Market Based) ሲባል፣ ሁለተኛው ድጋፍና ቁጥጥር ማድረግ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት (Interventionist) ይባላሉ፡፡

የሌሎች አገሮች ኢኮኖሚ ታሪክን ልናውቅ የሚገባን በእነሱ መንገድ ለመጓዝ ሳይሆን፣ ለልምድ የሚጠቅሙንን ለመቅሰም ከእኛው አገር ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አገናዝበን የሚጠቅመንን ለመውሰድ የሚጎዳንን ለማስወገድ ነው፡፡

በእኛ አገር ከላይ ከተጠቀሱት ዘይት፣ ስኳርና ስንዴ ዱቄት አቅርቦት በተጨማሪ፣ በታደልነው የድንጋይና ሌሎች የማዕድን የተፈጥሮ ሀብቶቻችንና ለደን ልማት ምቹ በሆነው የአፈርና የአየር ንብረት ጥሬ ዕቃ ተጠቅመን የብርጭቆ፣ የሰሐንና የእንጨት ኢንዱስትሪ ፋብሪካዎቻችንን የማምረት አቅም አሳድገን በጣሳ የሚጠጣውንና በሰፌድ የሚመገበውን፣ መመገቢያ ወንበርና ጠረጴዛ የሌለውን 80 በመቶ የሚሆነውን የገጠሩን ሕዝብ የቤት ውስጥ ቁሳቁስ ፍላጎት በማርካት ብቻ፣ የከተማውንም የገጠሩንም ሥራ አጥ ወጣት ሠራተኛ ማድረግ ይቻላል፡፡ በከተሞች የተከማቸው ከፍተኛ የገንዘብ ሀብት ገጠር ሄዶ እንዲሠራ ቢደረግ ለታለመው የብልፅግና ጎዳና ተስፋ ሲሆን፣ ካልተሠራበት ግን የቀውስ ሜዳ ነው፡፡

ንግድ ሚኒስቴር በ80 ሺሕ ድርጅቶች ላይ ዕርምጃ መውሰዱ ለዛሬ ችግር መፍትሔ ሊሆን ይችል ይሆናል፡፡ ለነገ ችግር ግን መፍትሔ ሊሆን አይችልም፡፡ የገንዘብ ሚኒስቴር ከአጭር ጊዜም ይሁን ከረዥም ጊዜ የፍላጎትና የአቅርቦት ጎን አንፃር የግብር ቅነሳና የመንግሥት ወጪ አስተዳደር እየወሰደ ያላቸው ዕርምጃዎች የሚበረታቱ ሲሆን፣ ብሔራዊ ባንኩም ዘግይቶም ቢሆን ለኢኮኖሚስቶች ትርጉም የሚሰጡ የፍላጎት ጎን የጥሬ ገንዘብ ፖሊሲዎችን መተግበር መጀመሩ ተስፋፍቶ መቀጠል ያለበት ነው፡፡

የኢኮኖሚ ችግሮቹ አይደጋገሙም ልንል አንችልም፡፡ ችግሮች ሲደጋገሙም ሰፍተው እንጂ ጠበው አይመጡም፡፡ ምክንያቱም ሕዝብ ከገጠር ወደ ከተማ በፈለሰ ቁጥር የተጠቀሱት መሠረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች ፍላጎት እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አይመጣም፡፡

ከላይ ከተጠቀሱት የምዕራባውያን ኢኮኖሚ ታሪክ ንድፈ ሐሳቦች አንፃር የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ሲገመገም፣ በአንድ በኩል የሸማቹን ኑሮ ስንመለከት ከማምረት ሙሉ አቅም በጣም የራቀ ስለሆነ የማያረካ ፍላጎት በመኖሩ የጥሬ ገንዘብና የበጀት የፍላጎት ጎን ፖሊሲን በመጠቀም ብዙ ችግሮቻችንን ልንቀርፍ እንችላለን፡፡ በሌላም በኩል ከላይ በተጠቀሱት ውድድርንና ገበያን መሠረት ባደረገና ድጋፍና ቁጥጥርን መሠረት ባደረገ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት የአቅርቦት ጎን ፖሊሲ፣ የፍላጎትና የአቅርቦት ጎን ጣምራ ፖሊሲ ዕርምጃ መፍትሔ መፈለግ ይቻላል፡፡

ይህ አመለካከት ከንፁህ ኢኮኖሚክስ ሳይሆን ከፖለቲካል ኢኮኖሚ ርዕዮተ ዓለማዊ መርህ ደረጃ ወዴት ይወስደናል ብለን ልንመረምር እንችላለን፡፡ ገዥው የብልፅግና ፓርቲም ሆነ መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ ራሳቸውን ግልጽ ሳያደርጉ እንደቆዩ ማንም የሚያስተውለው ጉዳይ ነው፡፡ ምርጫው ቀላል አይደለም፡፡ ወደ አቅርቦት ጎን ፖሊሲ ቢያጋድል አክራሪ የገበያ ኃይሎች ተከታይ ሊባል ይችላል፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ችግር መዋቅራዊ ነው የሚሉ ሊደግፉትም ይችላሉ፡፡ ከዚህም አልፎ በኢሕአዴግ ዘመን የተሳሳተ ፖሊሲ ምክንያት ወደ ተጠላው ልማታዊ መንግሥት እያጋደለ ነው ሊባልም ይችላል፡፡ ወደ ፍላጎት ጎን ፖሊሲው ቢያደላም ኢኮኖሚስቶች ራሳቸው በምርምርና በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ እንኳ የሚወዛገቡባቸው ምክንያቶች አሉባቸው፡፡

ለምሳሌ ኬንስና ተከታዮቹ የበጀት አስተዳደር የፍላጎት ጎን ፖሊሲን ሲደግፉ፣ የሚልተን ፍሬድማን ተከታዮች የሆኑ ጥሬ ገንዘባውያን ዋናው የዋጋ ንረት ችግር በኢኮኖሚው ውስጥ በባለሥልጣናት እምነት ብቻ በገፍ የሚረጨው ጥሬ ገንዘብ ስለሆነ፣ ለኢኮኖሚው ችግር መፍትሔው ከምርት ዕድገት ጋር የሚጣጣም፣ በሕግና በመርህ የተገደበ አዝጋሚ የጥሬ ገንዘብ ዓመታዊ ዕድገት መጣኝ ነው ይላሉ፡፡ የጥሬ ገንዘባውያን መፍትሔ በበኩሉ አቅርቦትን ከሚያሳድገው የባንኮችና የገንዘብ ተቋማት መስፋፋትና የብድር ጥሪት (Loanable Fund) ዕድገት ጋር የሚጋጭ ነው፡፡ የዚህ ዘመን ኢኮኖሚስቶችም የአጭር ጊዜውን የፍላጎት ጎንና የረዥም ጊዜን የአቅርቦት ጎን ፖሊሲን የሚያጣምር ቅይጥ ፖሊሲ ነድፈዋል፡፡

የህልውና ጦርነቱ በአጭር ጊዜ መፍትሔ እንደሚያገኝ ተስፋ አለኝ፡፡ በቀናት ውስጥም አዲስ መንግሥት ይመሠረታል፡፡ አዲሱ መንግሥት የኢኮኖሚ ፖሊሲ አቅጣጫውን በግልጽ ይነግረን ይሆን? ወይስ እንደተለመደው ‹‹ሙያ በልብ ነው›› ብሎ በዝምታ ውስጥ ውስጡን እየተብሰለሰለ በሽታውን የሸሸገ መድኃኒት የለውም ዓይነት አካሄድ ይጓዛል?

 

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...