በነሐሴ 2009 ዓ.ም. ወጥቶ ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ ለሕዝብ ይፋ የተደረገው የመንግሥትና የግል አጋርነት ፖሊሲ እንዲሚያትተው፣ ከማስፈጸም አንፃር የመሠረተ ልማት ሥራዎች የሚጠይቁት አቅም ከፍተኛ ነው፡፡ በተለይ በፋይናንስ ረገድ ከፍተኛ አቅምን የሚፈልጉ ሲሆን፣ ከዕድገት ደረጃ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ውስብስብ መሠረተ ልማቶች በቴክኖሎጂና በሰው ኃይል ዝግጁነት ረገድ ትልቅ አቅም ይፈልጋሉ፡፡ ላለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ኢትዮጵያ ከፍተኛ ድርሻ ያለውን የመንግሥት የፋይናንስ አቅም በመሠረተ ልማት ላይ ለማዋል የቻለች ቢሆንም፣ የመሠረተ ልማት አገልግሎቶች አቅርቦት በስፋትና በጥራት ረገድ ብዙ ሥራ እንደሚቀረው ይነገራል፡፡ መንግሥት በራሱ አቅም ብቻ ተግባራዊ በሚያደርጋቸው የመሠረት ልማት ፕሮጀክቶች ሰፊውን የአገሪቱ ክፍል ማዳረስ ስለማይቻል፣ ከግሉ ዘርፍ ጋር እንዲኖር የሚፈለገውን አጋርነት ዕውን ለማድረግ የፖሊሲና የሕግ ማዕቀፍ አዘጋጅቶ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ በኢትዮጵያ ያለው የመንግሥትና የግል አጋርነት ፕሮጀክቶች (Public Private partnership) ትግበራ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል? ጉዳዩን መሠረት ለማስያዝ የተቋቋመው ዳይሬክቶሬት ምን ዓይነት ተግባራት እያከናወነ ነው? ለምን የመንግሥትና የግል አጋርነት ፕሮጀክቶች በታሰበው ልክ ወደ ሥራ አልገቡም በሚለው ላይ ኤልያስ ተገኝ ከመንግሥትና የግል አጋርነት ዳይሬክቶሬት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጥላሁን ታደሰ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡ አቶ ጥላሁን የተወለዱት በአርሲ ሲሆን እዚያው የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለው ለከፍተኛ ትምህርት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመግባት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በኢኮኖሚክስ አግኝተዋል፡፡ ከዚያም ወደ ውጭ በማምራት የድኅረ ምረቃ ዲፕሎማ ከኔዘርላንድ፣ እንዲሁም የማስተርስ ዲግሪያቸውን ከአየርላንድ አግኝተዋል፡፡ ሙሉ የሥራ ዘመናቸውን በገንዘብ ሚኒስቴር በተለያዩ ኃላፊነቶች ያገለገሉ ሲሆን፣ ላለፉት ሁለት ዓመት ተኩል ደግሞ የመንግሥትና የግል አጋርነት ዳይሬክቶሬት ዋና ዳይሬክተር በመሆን እየሠሩ ይገኛሉ፡፡
ሪፖርተር፡- በገንዘብ ሚኒስቴር ሥር የሚገኘው የመንግሥትና የግል አጋርነት ዳይሬክቶሬት ምን ዓይነት ተግባራትን ለማከናወን የተቋቋመ ነው?
አቶ ጥላሁን:- የመንግሥትና የግል አጋርነት ከተቋቋመ ብዙ ጊዜው አይደለም፡፡ ለማቋቋም የወጣው አዋጅ ይፋ የሆነው በ2010 ዓ.ም. ነበር፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አዋጁ በሚፈቅደው መሠረት ተደራጅቶ እየሠራ ይገኛል፡፡ የመንግሥትና የግል አጋርነት ሲባል በዋናነት በመንግሥትና በግሉ ሴክተር መካከል የሚደረግ የረዥም ጊዜ ውል ያሳያል፡፡ይኸውም በግብዓት ላይ ሳይሆን በውጤት ላይ የተመሠረተ ክፍያ የሚኖረው ዓይነት ነው፡፡ ይህ የሥራ ክፍል በዋናነት ይሠራል ተብሎ የታሰበው የመሠረት ልማት፣ ወይም የሕዝብ አገልግሎት ከመንግሥት ጋር በመሆን እንዲተገብር ነው፡፡ ስሙም እንደሚያመለክተው የመንግሥትና የግል አጋርነት ነው፡፡ ይህ ሲባል መንግሥት ሊያቀርባቸው የሚገባቸውን አገልግሎቶች በተለያየ መንገድ መንግሥት ባለማቅረቡ፣ የግሉ ሴክተር ጭምር ገብቶበት እንዲያቀርብ ስለተፈለገ የግሉ ዘርፍ የሕዝብ ፍላጎትን ለማሟሟላት አጋዥ ሆኖ እንዲሠራ የሚደረግበት አካሄድ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- እንዲህ ዓይነት ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ በማድረግ ሒደት ውስጥ ውስብስብ የሆኑ የሕግ ዝግጅቶች፣ ቅድመ ጥንቃቄዎችና የመሳሰሉትን ማከናወን እንደሚገባ ይታወቃል፡፡ በዚህ ረገድ የሕግ ማዕቀፎችን ከማዘጋጀት አንስቶ፣ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ ወደ ሥራ ከመግባት አኳያ ምን ዓይነት ተግባራት ተከናውነዋል?
አቶ ጥላሁን፡- ዳይሬክቶሬቱ ከተቋቋመ በኋላ በየደረጃው ያሉ የሕግ ማዕቀፎች ተዘጋጅተዋል፡፡ እነኚህ የሕግ ማዕቀፎች ስንል በመጀመሪያ ለማቋቋም ፖሊሲ ይኖራል፣ፖሊሲው ወጥቷል፣ ከፖሊሲው ቀጥሎ የሚኖረው አዋጅ ነው፡፡ አዋጁ ወጥቷል፣ ከአዋጁ ቀጥሎ መመርያ ይኖራል፣ መመርያውም ተዘጋጅቷል፡፡ ሆኖም ደንብ ተዘጋጅቶለት ስላልነበረ በአሁኑ ጊዜ ደንብ በማዘጋጀት ላይ እንገኛለን፡፡ ከዚህ ሁሉ በተጨማሪ የአሠራር ማኑዋል የሚባል አለ፡፡ እርሱም አጠቃላይና በሴክተር የተለዩ (ሴክተር ስፔስፊክ) የሆነ መመርያ ከዓለም ባንክ ጋር በመሆን አዘጋጅተናል፡፡ ይህ እንግዲህ ምንድነው የሚጠቅመው? የመንግሥትና የግል አጋርነት (ፒፒፒ) ፕሮጀክቶችን ለማዘጋጀት ከየትና እንዴት ይጀመራል? ምን ዓይነት መስፈርቶች መሟላት ይኖርባቸዋል? እንዴት ይገመገማሉ? የሚሉትን ጉዳዮች የያዘ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አንዳንድ ሌሎች ተጨማሪ የሕግ ማዕቀፎች ያስፈልጋሉ፡፡
ለምሳሌ የመንግሥት ድጋፍ የሚባል አለ፡፡ ይህም እንዴት ነው መንግሥት ሊደግፈው የሚገባው የሚለውን ያካትታል፡፡ ይህ የሕግ ማዕቀፍ አሁን ላይ በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡ የእነዚህ ሁሉ ጉዳዮች ዝግጅት በፅኑ የሕግ ማዕቀፍ ላይ መሠረት ላይ ተመሥርቶ እንዲደገፍ ያደርገዋል፡፡ እነዚህ ጉዳዮችን ነው የተቋሙ ምሰሶዎች ተብለው የሚወሰዱት፡፡ አንደኛ አጋርነቱ ምንድነው የሚለውን ማወቅ አለብን፡፡ የሠለጠነ የሰው ኃይል ሊኖረን ይገባል፡፡ በተለይም በአስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች በተለምዶ አጠራር ተዋዋይ መሥሪያ ቤቶች የምንላቸው የፒፒፒ ግንዛቤ ያላቸውን ሰዎች ማዘጋጀት አለባቸው፡፡ ለእነርሱ ሥልጠና መስጠት ያስፈልጋል፡፡ እነርሱ ሲሠለጥኑ የፒፒፒ ፕሮጀክቶችን አዘጋጅቶ ለተግባር እንዲደርሱ ማድረግ የሚያስችል ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ እየሠራን ያለነው መሠረቱን ወይም መደላደሉን መሥራት ነው፡፡ ይህም የሕግ ማዕቀፉን ማዘጋጀት፣ አቅም በመገንባት ፒፒፒ ለመተግበር ዝግጁ የሆነ ሰው ማዘጋጀት፣ ይህ እንግዲህ በፒፒፒ ዳይሬክቶሬት ብቻ ሳይሆን በአስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች በሚባሉት ጭምር ነው፡፡ እነኚህ ለፒፒፒ መሠረታዊ የሚባሉ ነገሮች ናቸው፡፡ እነርሱን ሳያሟሉ ፒፒፒ ውስጥ መግባት ምናልባትም ለከፍተኛ ችግር ሊዳርግ ይችላል፡፡
ሪፖርተር፡- እንደ ናይጄሪያ፣ ኬንያና ደቡብ አፍሪካ ባሉ የአፍሪካ አገሮች በመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት የሚሠሩ ፕሮጀክት እንቅስቃሴዎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ይህ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ ላይ ሲተገበር ውጤታማ ሊያደርገው የሚችለው ጉዳይ ምንድነው?
አቶ ጥላሁን፡- በኢትዮጵያ ፒፒፒን በመተግበር ሊገኝ ከሚችለው ጠቀሜታ መካከል አንደኛው ኢትዮጵያ ከፍተኛ የመሠረት ልማት ፍላጎት ክፍተት አለባት፡፡ ባለፉት ዓመታት በመሠረት ልማት ብዙ ነገሮች እንደተሠሩ ይታመናል፡፡ ሆኖም ከፍላጎት አኳያ ተሟልቷል የሚባልበት ደረጃ ላይ አልደረስንም፡፡ እጅግ በጣም ሰፊ ክፍተት አለ፡፡ ፒፒፒን በመተግበር ይህንን ክፍተት በመሙላት የበኩሉን ድርሻ ይወጣል፡፡ ከግል ኩባንያዎች ወይም ባለሀብቶች በሚመጣ ሀብት፣ ፕሮጀክቶችን ወደ መሬት ተተግብሮ በሥራ ላይ ይውላል፡፡ ይህ ከአገር አኳያ ያለውን ፍላጎት በማሟላት የኢኮኖሚውን እንቅስቃሴ የበለጠ ለማሳለጥ ያግዛል፡፡ መሠረት ልማት ሲባል ኢነርጂ አለ፣ መንገድ አለ፣ ባቡር ሊሆን ይችላል፡፡ የተለያዩ የማኅበራዊ ጉዳይ ዘርፎች፣ ቤቶችም ሊሆኑ ይችላሉ፣ የጤና ተቋማት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች ያሉ ክፍተቶችን ለማሟላት ያግዛል፡፡
ሪፖርተር፡- በዚህ ወቅት ያለው የፒፒፒ ፕሮጀክቶች እንቅስቃሴ ምን ይመስላል? ምን ያህል ድርጅቶች ለዚህ የኢንቨስትመንት አማራጭ ምላሾችን ሰጥተዋል? ያሉበትንም ደረጃ ቢያስረዱን?
አቶ ጥላሁን፡- ፒፒፒ ደረጃ በደረጃ የሚተገበር ነገር ነው፡፡ ለትግበራውም ረዘም ያለ ገዜ የሚወስድ ነው፡፡ ይህም ዓለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ የሚሄድ ነገር በመሆኑ ነው፡፡ተጋባዦቹም ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ስለሆኑ ያንን ደረጃ ጠብቆ ካልሄደ ተጫራቹን ማግኘት ከባድ ስለሚሆን፣ ያንን ደረጃ የጠበቀ አሠራር ነው የምንከተለው፡፡ ለዚህም ነው ሒደቱ ረዥም የሚሆነው፡፡ እስካሁን ባለው ወደ 23 ፕሮጀክቶች በሒደት ውስጥ ወይም ለፒፒፒ ይሆናሉ ተብለው በቦርድ ፀድቀው ቀጣይ ሥራቸው እየተከናወነ ነው፡፡ከእነዚህ ውስጥ ሁለት ፕሮጀክቶች በተሻለ ደረጃ ሄደዋል፡፡ ዲቼቶና ጋድ የሚባሉ የፀሐይ ኃይል ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡ ሌሎች ስድስት የፀሐይ ኃይል ፕሮጀክቶች እንዲሁ ለጨረታ ወጥተው የሚተገብሯቸው ኩባንያዎች ልየታ ተደርጓል፡፡ ቀጣዩን በሁለት ከፍለን ጨረታ በማካሄድ ሒደት ላይ እንገኛለን፡፡ ሌሎቹ የአዋጭነት ጥናታቸው በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ የኃይድሮ ፓወር ወይም የውኃ ፕሮጀክቶች አሉ፣ የንፋስ ኃይል ፕሮጀክቶች አሉ፣ የቤቶች ፕሮጀክቶቸ አሉ፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች በአሁኑ ጊዜ የአዋጭነት ጥናታቸው በመካሄድ ላይ ነው፡፡ የአዋጭነት ጥናታቸው ተካሂዶ በዳይሬክቶሬት መሥሪያ ቤቱ ተገምግሞ ለቦርድ ይቀርብና ሲፀድቅ ወደ ጨረታ ሒደት ይገባሉ፡፡
ሪፖርተር፡- ሒደቱ ግን አልዘገየም?
አቶ ጥላሁን፡- በእርግጥ ሒደቱ የዘገየ ቢመስልም አሠራሩ ይህንኑ ረዘም ያለ ጊዜ ስለሚጠይቅ፣ አንዳንድ ዓለም አቀፋዊ ክስተቶችን ጨምሮ (ኮቪድን ማለቴ ነው) መፈጠራቸው በሒደቱ ላይ የበኩላቸውን ተፅዕኖ አድርገዋል፡፡ ፒፒፒን ለመተግበር ኩባንያዎች ወደ አገር ውስጥ መጥተው የፕሮጀክት ቦታ፣ የፕሮጀክት ሁኔታን መገምገም፣ ሰነዶችን ማየትና መሥራት ስላለባቸው ይህንን አላስችል የሚሉ እንደ ልብ የመንቀሳቀስ ዕገዳዎች ስለነበሩ እነርሱም የበኩላቸውን ተፅዕኖ አሳድረዋል፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች ምክንያት በምኞታችን ልክ ፈጥኗል ባንልም፣ ሆኖም እስካሁን ድረስ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡
ሪፖርተር፡- ከዲቼቶና ከጋድ ጋር በተገናኘ እነዚህ ድርጅቶች ወደዚህ ሒደት ከገቡ ትንሽ ቆየት ያሉ እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ ከሁለቱ ድርጅቶች ጋር በተገናኘ ያለው እንቅስቃሴ ምን ይመስላል? በቀጣይስ ያለው ሒደት እንዴት ተግባራዊ ይደረጋል?
አቶ ጥላሁን፡- ከሁለቱ ድርጅቶች ጋር በተገናኘ የሚቀረው ነገር ቢኖር የመጨረሻው የፋይናንስ ስምምነት ደረጃ ላይ መድረስ ነው፡፡ ይህ ማለት ምንድነው? ሁለቱ ድርጅቶች በኢኩቲ መልክ የሚያመጡትን ፋይናንስ ጨርሰው ከአበዳሪዎቻቸው ጋር፣ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር የሚፈረም ስምምነት ነው፡፡ በመሠረቱ የኮሜርሻል ብድር ወይም ክሎዝ የሚባለው ከተፈረመ በኋላ መሟላት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች አሉ፡፡ እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች በቁጥር 17 ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ በኩል ያሉት እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች በአብዛኛው ተሟልተዋል፡፡ ያልተሟሉት ቅድመ ሁኔታዎች ያሉት በአሸናፊው ወገን ነው፡፡ ከእነዚህ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ፣ ድርጅቶቹ አበዳሪዎቻቸውን በአግባቡ ለይተው ብድሩን ይዘው መጥተው ሥራ ለመጀመር የሚያስችላቸውን ስምምነት መፈጸም የሚያስችለው ቅድመ ሁኔታ ባለመሟላቱ ሁኔታውን አዘግይቶታል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የተወሰነ ርቀት እየሄዱ ነው፡፡ ጥረቶችም እየተደረጉ ነው፡፡ በየጊዜው የማራዘሚያ ስምምነት እያደረግን እንገኛለን፡፡ለምሳሌ የተደረገው የማራዘሚያ ስምምነት እ.ኤ.አ. እስከ ጥቅምት 14 ቀን 2021 ድረስ ነው፡፡ እስከ ተጠቀሰው ጊዜ ድረስ የፋይናንስ ክሎዝ ላይ ይደረሳል ብለን ነው ያቀድነው፡፡
ሪፖርተር፡- በመንግሥት ከላይ ከተጠቀሱት ዘርፎች ቅድሚያ ሰጥቷቸው ይሠራባቸዋል የተባሉት የትኞቹ ፕሮጀክቶች ናቸው?
አቶ ጥላሁን፡- እስካሁን ባለው ቦርድ ያፀደቃቸው አብዛኞቹ ፕሮጀክቶች የኢነርጂ ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡ ኢነርጂ ስንል አንድም ከፀሐይ ኃይል የሚመነጭ ኢነርጂ፣ ሁለተኛ ከውኃ ኃይል የሚመነጭ ኢነርጂ ሲሆን፣ በሦስተኛነት ደግሞ ከንፋስ ኃይል የሚመነጭ ኢነርጂ ነው፡፡ እነዚህ ታዳሽ የኃይል ዓይነቶች ስለሆኑ ተፈላጊነት አላቸው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ላይ የተተኮረበት ምክንያት ኢነርጂ ለኢኮኖሚው ከፍተኛ ግብዓት ስለሆነ ነው፡፡ ኢነርጂን የተጠቀመ ኢኮኖሚ ነው አደገ የሚባለው፡፡ የኢነርጂ አጠቃቀማችን የዕድገታችንን ደረጃ ያሳያል፡፡ ይህንን ዕሳቤ ከግምት ውስጥ በመክተት ያለን የኢነርጂ ፍላጎት ከፍተኛ በመሆኑ፡፡ የመብራት ኃይልን በቤት ደረጃ በማዳረስ ያለን ተደራሽነት ዝቅተኛ ስለሆነ፣ ይህንን ፍላጎት አሟልቶ ወደ ልማት ማለትም በኢንዱስትሪው፣ በግብርናውና በአገልግሎት ዘርፉ የሚከናወኑ ልማቶች ከኢነርጂ ውጭ ስላልሆኑ፣ ኢነርጂ በዚህ ምክንያት የቅድሚያ ትኩረት የተሰጠው ዘርፍ ሆኗል፡፡
ሪፖርተር፡- ከ2010 ዓ.ም በኋላ ባለው ጊዜ ውስጥ ስለፒፒፒ ብዙ ሲነገር ቢቆይም፣ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ለዘብ ማለቱ ይስተዋላል፡፡ ይኼ ለምን ሆነ?
አቶ ጥላሁን፡- የመንግሥትና የግል አጋርነት ተብሎ መጀመሪያ ሲጀመር የነበረው ግንዛቤ፣ በቀላሉ ወደ ፕሮጀክት ትግበራ የሚገባ ጉዳይ ተደርጎ ነበር የተወሰደው፡፡ ሆኖም ወደ ዋናው ሥራ ሲገባና ዓለም አቀፍ ልምዶች ሲታዩ ሒደቶቹ የተወሳሰቡና ጊዜ የሚወስዱ ሆነው ተገኙ፡፡ በዚህ ላይ ሌሎች ሁኔታዎች ማለትም የኮቪድ ተፅዕኖ ሲጨመር የበለጠ አራዝሞታል፡፡ ፒፒፒ መንግሥት ከዲዛይን አንስቶ እስከ ግንባታ ድረስ እንደሚተገብራቸው ፕሮጀክቶች ወይም እንደ ኢፒሲ ባሉት አሠራሮች በሚኬድበት የፕሮጀክት ዝግጅት አይደለም ተግባራዊ የሚያደርገው፡፡ ከዚያ ሰፋ ያለና ብዙ ነገሮችን ያካተተ ነው፡፡ እነዚህን ነገሮች አሟልቶ ለማቅረብ ጊዜ ይወስዳል፡፡ ጥናቱን የሚያካሂዱትም የተለያዩ አካላት ናቸው፡፡ የተወሰነ አካል ብቻ የሚሠራው አይደለም፡፡ እነዚህ ሁሉ ከተሟሉ በኋላ ነው ወደ መጨረሻ ሒደት የሚገባው፡፡ ከዚህ አኳያ መጀመሪያ አካባቢ ፒፒፒ ወዲያው ተተግብሮ መሬት ላይ ይታያል የሚል ጉጉት ጭሮ ነበር፡፡ ሒደቱ ግን እንደዛ እንዳልሆነ ሲረጋገጥ አሁን ያለው ረዘም ያለ ጊዜ የጠየቀበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ሆኖም በእነዚህ ሁሉ ሒደት ውስጥ መሠረታዊ መደላድሎችን እያሟላ የሚሄድበት አሠራር ሊፈጠር ችሏል፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ ፒፒፒ የአጭር ጊዜ ሥራ ስላልሆነ ጊዜ ይፈልጋል፡፡ እንበልና በሒደቱ ላይ አንዲት ስህተት ቢሠራ ለረዥም ዓመታት ነው በአገር ላይ ችግር የሚያመጣው፡፡ ለዚህም ሲባል በከፍተኛ ጥንቃቄ ነው መሠራት ያለበት፡፡ በባለሙያዎችና በአማካሪዎች ታግዞ ካልሆነ በስተቀር፣ አንድ ቦታ ላይ ባለማወቅ በሚደረግ ስህተት በአገር ላይ የረዥም ጊዜ ስህተት ጥሎ ሊያልፍ ስለሚችል በሁሉም ደረጃ በጣም ከፍተኛ ጥንቃቄ ይደረጋል፡፡
ሪፖርተር፡- መሠረት ልማት፣ ሰላምና ፀጥታ የማይነጣጠሉ ጉዳዮች ናቸው፡፡ በዚህ ወቅት የአገሪቱን ሁኔታ ስንመለከት መረጋጋቶች የሌሉበት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ወደፊት ሊተገበሩ በታቀዱ ፕሮጀክቶች ላይ ተፅዕኖ አይፈጥርም? ይኼን እንዴት ይመለከቱታል?
አቶ ጥላሁን፡- ሰላምና ፀጥታ ለሁሉም እንቅስቃሴ አስፈላጊ ነው፡፡ በተለይም ደግሞ ከሩቅ ለሚመጡ ባለሀብቶች እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች አሉ ሲባል ፍርኃትና ጥርጣሬ መጫሩ አይቀሬ ነው፡፡ ይኼ ስላለ ግን ሥራ ይቆማል ማለት አይደለም፡፡ ሕይወት ይቀጥላል፡፡ እንዲህ ዓይነት ጉዳዮችም በራሳቸው ጊዜ ይስተካከላሉ፡፡ ሆኖም ሥራዎች ይተገበራሉ፡፡ የፀጥታ ወይም የሕግ ማስከበር ሒደት ባለባቸው ቦታዎች የሚተገበር ፕሮጀክት ካለ ግን ያ ፕሮጀክት መራዘሙ የማይቀር ነው፡፡ ከዚያ ቀጣና ወጣ ያለው ፕሮጀክት ግን የማይተገበርበት ምንም ምክንያት አይኖርም፡፡ ስለዚህ ከዚህ አኳያ ነው መታየት ያለበት፡፡ ሆኖም ባለሀብቶችና የግል ኩባንያዎች እንደ ልብ መጥተውና ዓይተው የተሻለ ዋጋ እንዲሰጡ ሰላም አስፈላጊ ጉዳይ ነው፡፡ የሰላም አለመኖር በፕሮጀክቶች ዋጋ ከፍና ዝቅ ማለት ላይ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን ፕሮጀክቶች ተገቢውን የአዋጭነት ጥናትን ተከትለው መተግበራቸውን ማረጋገጡ መሠረታዊ ጉዳይ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- በተያዘው የበጀት ዓመት የምታከናውኗቸው ዋና ዋና ተግባራትና ወደ ሥራ የምታስገቧቸው አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ቢጠቅሱልን?
አቶ ጥላሁን፡- የተጀመሩት ለምሳሌ የዲቼቶና የጋድ ፕሮጀክቶችን ቀሪ ሒደቶችን ጨርሶ ወደ ተግባር ማስገባት፣ ጨረታ የወጣላቸው ስድስት የፀሐይ ኃይል ፕሮጀክቶችም አሉ፡፡ ጨረታ ወጥቶላቸዋል ስንል በሁለት ዓይነት መንገድ ነው፡፡አንደኛው ኩባንያዎችን ለመለየት የሚወጣ ጨረታ (Request for Pre-qualification) ይባላል፡፡ የምንፈልገውን ሥራ ለመሥራት የሚችሉ ኩባንያዎችን የምንመርጥበት የመጀመሪያ ደረጃ ነው፡፡ በዚህ ጨረታ አማካኝነት አቅም ያላቸውና የተፈለገውን ሥራ ለማከናወን የሚችሉ የተወሰኑ ኩባንያዎች ይመረጣሉ፡፡ ለምሳሌ ለስድስት የፀሐይ ኃይል ፕሮጀክቶች 15 ኩባንያዎች ተመርጠዋል፡፡
ሪፖርተር፡- መቼ ነው ጨረታ ያወጣችሁት?
አቶ ጥላሁን፡- አንድ ዓመት ተኩል ይሆነዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ዝርዝር የአዋጭነት ጥናቶች ሲጠኑ ከስድስቱ ፕሮጀክቱ ውስጥ በተወሰኑት ላይ አንዳንድ ጉድለቶች ታዩ፡፡ የተሟላ ጨረታ ከመውጣቱ በፊት እነዚህን ጉድለቶች ማሟላት አለብን፡፡ ስለዚህ ቅድመ ሁኔታውን ያሟሉትን ፕሮጀክቶች ብቻ መምረጥ ነበረብን፡፡ ስለዚህ አሁን ጋድ ሁለትና ወራርሶ የሚባሉት ፕሮጀክቶች ስላሟሉ ዝግጁ ሆነው ወደ ጨረታ እንዲገቡ አድርገናል፡፡ ቀሪዎቹ አራቱ ፕሮጀክቶች ደግሞ የቀራቸውን የጎደሉ ነገሮች እንዲያሟሉ እየተሠራ ይገኛል፡፡ በያዝነው የበጀት ዓመት አስፈላጊውን ነገር አሟልተዋል ያልናቸውን ፕሮጀክቶች ጨረታ በማጠናቀቅ አሸናፊውን መለየት፣ ከዚያ ወደ ፋይናንስ ክሎዝ ይገባል፡፡ የተቀሩትን ደግሞ የጎደላቸውን በማሟላት ወደ ጨረታው እንዲገቡ ይደረጋል፡፡ በተጨማሪም ሌሎች የንፋስ ኃይል ፕሮጀክቶችን፣ የቤት ፕሮጀክቶችን፣ የውኃ ኃይል ፕሮጀክቶችን ወደ አዋጭነት ጥናትና ጨረታ ማውጣት ሒደት የሚገባ ይሆናል፡፡ የውኃ ኃይል ፕሮጀክትን በተመለከተ አምስት የውኃ ኃይል ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ ከአምስቱ ውስጥ አንድ ወይም ሁለቱን የአዋጭነት ጥናታቸው ያልቃል ብለን እናስባለን፡፡ እነዚህን ፕሮጀክቶች የአዋጭነት ጥናታቸው እንደተጠናቀቀ ወደ ጨረታ ሒደት የማስገባት ሥራ ይከናወናል፡፡ የቤት ፕሮጀክቶችንም በተመለከተ አማካሪ ድርጅት ተቀጥሮ የአዋጭነት ጥናታቸው እየተጠናቀቀ የሚገኙ ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ ይህንን ወደ ጨረታ ሒደት ለማስገባት እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው፡፡ ጎን ለጎንም ተጨማሪ አዳዲስ በፒፒፒ የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች ከተለያዩ መሥሪያ ቤቶች እንዲመጡ እየተደረገ ነው፡፡ በተያዘው የበጀት ዓመት በርካታ ፕሮጀክቶችን ለመጀመር ዕቅድ ተይዟል፡፡