Friday, July 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አገር ለማዳን የታየው አንድነትና መተሳሰብ በግብይት ሥርዓት ውስጥ ይደገም!

አገር በተለያዩ ውስጣዊና ውጫዊ ተፅዕኖዎች በምትፈተንበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያውያን በአንድነት መቆም እንደሚገባን በማመን ይህንኑ በተግባር እያሳዩ መሆኑ ትልቅ ተስፋ ነው፡፡ አገር ከሌለ ምንም ነገር ሊኖር እንደማይችል በመረዳት የገጠመንን ችግር በተባበረ ክንድ መፍታት አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው፡፡

ጦርነት የተከፈተብን ግንባር ላይ ብቻ ሳይሆን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ኢኮኖሚያችን ላይም ጭምር ነው፡፡ ወትሮም የጠነከረ ኢኮኖሚ ያለን ባለመሆኑ አንድ ችግር በተፈጠረ ቁጥር ገበያው መረበሹ የተለመደ ነው፡፡ አጋጣሚዎችን ተጠቅሞ ለብዝበዛ የሚነሳውም ምግባረ ብልሹ ነጋዴ ሠርግና ምላሹ ይሆናል፡፡ ይህም ገበያውን ያናጋል፡፡

በአጠቃላይ ጦርነቱ ኢኮኖሚያችንን በይበልጥ የሚጎዳው መሆኑ ሀቅ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዙ የተፈጠሩ ቀውሶች በርካታ ገንዘብን የሚጠይቁ ናቸውና የመንግሥትን ካዝናና የዜጎችን ኪስ የሚያስዳብስ ጭምር ነው፡፡ እነዚህን ድርብርብ ችግሮች ለመፍታት ለየት ባለ ፖሊስ መራመድን የሚጠይቀን ይሆናል፡፡

የኢኮኖሚ ጉዳይ ከተነሳ አንዱ አሳሳቢ ጉዳይ ኢትዮጵያን ለመጫን ዕረፍት እያጡ ያሉ የውጭ ኃይሎች የተለያዩ የኢኮኖሚያዊ ማዕቀቦችን ለመጣል የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ከተሳካ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ልንጎዳ እንችላለን፡፡ በተለይ ይህ ማዕቀብ ከቀደሙትና ከተከማቹት፣ እንዲሁም አሁን ካሉት ችግሮቻችን ጋር ሲደመር ደግሞ ተጎጂነታችን ሊጨምር ይችላል፡፡

ይህ ደግሞ የዋጋ ንረቱንም ሊያባብስ የሚችል ጭምር ሊሆን ስለሚችል ህልውና ማስከበር ተግባሩ ባሻገር በዚህ ረገድ ሊከፈትብን የሚችለውን ጦርነት ሊመክትና ቢያንስ ከዚህ የባሰ ሁኔታ ገበያ ውስጥ እንዳይፈጠር ወገብን ጠበቅ አድርጎ መሥራት የግድ የሚሆንበት ሰዓት ላይ መድረሳችንን ያመላክተናል፡፡ የውጭ ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖው የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ሊፈጠር የሚችልበትም ዕድል ስለሚኖር ይህንን ለመቋቋም የሚያስችል አቅም መፈጠር አንድ ጉዳይ ሆኖ በጊዜያዊነት መፍትሔ የሚሆኑ አሠራሮችን ከወዲሁ ማሰብ ጠቃሚ ይሆናል፡፡

ተደራራቢ ተፅዕኖዎችና ቀውሶች ተወደደም ተጠላ ገበያውን መንካታቸው የማይቀር ነውና እንዲህ ያሉ ጫናዎች ሊያስከትሉ የሚሉ ተፅዕኖዎችን ለመቋቋም በመንግሥት ሊተገብረው ከሚገባው የመፍትሔ ዕርምጃዎች ባሻገር ገበያውን ለማረጋጋት ትልቅ ኃላፊነት ያለበት የንግዱ ኅብረተሰብ ጭምር ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ሳይፈለጉ የመጡ ጫናዎችን ለመቋቋም የዋጋ ንረቱንም ለመቀነስ የንግድ ኅብረተሰቡ እንቅስቃሴ ጨዋነትን የተላበሰ መሆን አለበት፡፡ የንግዱ ኅብረተሰብ እንደ ከዚህ ቀደሙ የተለጠጠ የትርፍ ህዳጉን ትቶ በመጠነኛ ትርፍ በማስላት ኅብረተሰቡን ማገልገል ታሪካዊ ግዴታው እየሆነም መምጣቱን በማሰብ ለዚህ ራሱን አዘጋጅቶ በተግባር ማሳየት ይጠበቅበታል፡፡

አገር ለማዳን የታየውን አንድነትና መተሳሰብ በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ መታየት ስለሚኖርበት በተመጠነ ትርፍ ሕዝብን ማገልገል በጦር ሜዳ ከሚደረገው መስዋዕትነት ባልተናነሰ ለአገር ዋጋ የመክፈል ያህል የሚቆጠር ይሆናል፡፡ ይህንን አመለካከት በማስፋት ጊዜያዊ ችግራችንን ለመወጣት መተባበር የግድ ይላል፡፡ ጦርነት ላይ በመሆናችን ነገራችን ሁሉ ጦርነቱ ላይ ይሁንም አይባልም፡፡ ባለድል መሆን ካለብን እዚህም ያሉ ችግሮችን በመቅረፍ በጤናማ ኢኮኖሚ በመፍጠር ጭምር ነው፡፡ ጤናማ ኢኮኖሚ የሚፈጠረው ወይም የዋጋ ንረትን መቀነስ ከሚችልበት መንገድ አንዱ  አገር ያለችበትን ሁኔታ በመገንዘብ ሕዝብን በአግባቡ ማገልገል ሲችል ነው፡፡ ጦር ሜዳ ያለው ኃላፊነቱን ሲወጣ እዚህ ያለው ሕዝብ ደግሞ ምርታማ መሆን በሚያስችሉት ሥራዎች ላይ እንዲሰማራ ማድረግም ወቅታዊ ግዴታችን እየሆነ ነው፡፡ ሁኔታዎችም ወደዚያው እንድናመራ እየገፋን ነው፡፡

አሁን ኢትዮጵያን ለመጫን ይጠላሉ የተባሉ ማዕቀቦችን እንደ መልካም አጋጣሚ የሚሆንበት ዕድል ሊኖር ይችላል፡፡ ራሳችን አምርተን ራሳችን ለመቻል እንዲሁም አሁን ያለን የዋጋ ንረት ለመቀነስ ዋነኛ መፍትሔ የሆነውን የምርት ዕድገት ለማምጣት ከተፈለገ ተጨማሪ የሰብል ምርት እርሻችን ማስፋት የግድ መሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ በጦርነት ወቅትም ሆነ አገር በተረጋጋችበት ወቅት ከዚህ በኋላ በብርቱ ሊታሰብበት የሚገባ ነገር ካለ የሰብል ምርታችን በብዛት ማምረት ይሆናል፡፡ እያመረትን ያለነው ምርት በቂ አይደለም፡፡ ወደፊትም ፍላጎታችን እየጨመረ የሚሄድ በመሆኑ ይህንን ታሳቢ አድርጎ ካልተሠራ ነገም ተነገ ወዲያ ዛሬ እያማረረን ያለው የኑሮ ውድነት ነገ ብሶ መከሰቱ አይቀርም፡፡

ዛሬ ላይ የተለዩ ምክንያቶች ታክለውበት እየገሠገሠ ያለውን የዋጋ ንረት ቢያንስ በምንበላውና በምንጠጣው ምርት ላይ እንዳይታይ ብቸኛ አማራጫችን ምርታማነታችንን መጨመር ነው፡፡ ስለዚህ ወቅታዊ የኑሮ ውድነቱንም ሆነ ከውጭ ሊገጥመን በሚችለው ጫና ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን ለመፍታት ከቀድሞ በተለየ ምርትን ለማሳደግ ሥራ ላይ መሰማራት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ምቹ ሁኔታ መመቻቸት የሚያስፈልግ ሲሆን ግብርና እስካሁን እንደምንለው የጀርባ አጥንታችን ነው እያልን ከመዘመር በዘለለ በትክክል የመኖር ዋስትናችንም መሆኑን አውቀን አጥብቀን ልንሠራበት ይገባል፡፡

በነገራችን ላይ ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ የዋጋ ንረቱን ለመከላከል ከሰሞኑ አንዳንድ የንግድ ኅብረተሰብ አባላት ምርቶቻቸውን ዋጋ ቀንሰው ለመሸጥ እያሳዩ ያለው ተነሳሽነት ይበል የሚያሰኝ ሲሆን ሌሎቹም ተከትለዋቸው ይቺን አስቸጋሪ ጊዜ እንዲህ ባለው መተጋገዝ ማሳለፍ ይኖርብናል፡፡

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት