እናት ፓርቲ በወሎ አካባቢ ያንዣበበው አደጋ እጅጉን እደሚያሳስበውና አፋጣኝ መፍትሔ እንደሚሽ በመግለጽ፣ ‹‹በዚህ ጊዜ የሚታየው የመንግሥት ቸልታ በእጅጉ ያሳስባል፤›› ሲል አስታወቀ፡፡
ፓርቲው ዓርብ መስከረም 7 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹ላለፉት ዓመታት በማንነቱ ምክንያት ግፍ የተፈጸመበት የወሎ ሕዝብ ያለፈው መከራና ሰቆቃ አልበቃ ብሎ፣ በአሸባሪው ሕወሓት በተቀሰቀሰው ጦርነት ዛሬም ለከፋ ችግርና ለመራር ሥቃይ ተዳርጓል፤›› ሲል አስታውቋል፡፡
አካባቢው ከዚህ በፊት ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተፈናቅለው የመጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን የሚገኙበት ቢሆንም፣ ይባስ ብሎ አሁን በተቀሰቀሰው ጦርነት የሕወሓት የክፋትና የበቀል በትር እያረፈበት ነው ብሏል፡፡
‹‹በዚህ ሳቢያ በመቶ ሺዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፣ በግፍ ተጨፍጭፈዋል፣ ንብረታቸው መውደሙን በየአካባቢው ካሉ የዓይን እማኞች አረጋግጫለሁ፤›› ብሏል፡፡
በጦርነቱ ውስጥ እጃቸው የሌለበት ንፁኃን ከነፍስ ወከፍ መሣሪያ እስከ ከባድ መሣሪያ ተጨፍጭፈዋል ያለው እናት ፓርቲ፣ ሴቶች በተለይ ከዋና ዋና መስመሮች ወጣ ባሉ አካባቢዎች መደፈራቸውን፣ በመድኃኒት ዕጦት ብዙዎች መሰቃየታቸውን፣ አለፍ ሲልም እንደሚሞቱና እስከ ጓዳ ድረስ በመግባት የትኛውም ይጠቅማል የተባለ ንብረት መዘረፉን አስታውቋል፡፡
‹‹ሌላው ቀርቶ ውኃ እንኳን ጠጥተን እንሙት እያሉ የዋይታ ድምፅ ያሰማሉ፡፡ ውኃ ለመቅዳት ወደ ወንዝ የወረዱ እናቶች ለምን ውኃ ትቀዳላችሁ ተበለው ሊቀዱ የያዙትን እንስራ እንደተሸከሙ በጥይት ይገደላሉ፤›› በማለት ገልጿል፡፡
በዚህ ጊዜ የሚታየው የመንግሥት ቸልታ በእጅጉ እንደሚያሳስበው በመግለጽ፣ ‹‹ተረባርቦ መድረስ ካልተቻለ መንግሥትም ሕዝብም ታሪክ ይቅር የማይለው የዕዳ በደል በእጃችን እያስቀመጥን ለመሆኑ ጥርጥር የለውም፤›› ሲል እናት ፓርቲ አስታውቋል፡፡
‹‹የትኛውም ዋጋ ተከፍሎ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ከጨካኙና ከጭራቁ ቡድን ነፃ እንዲያወጣው እንጠይቃለን፤›› ሲል ጥሪ አቅርቧል፡፡
መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ የዕርዳታ ድርጅቶች እጃቸውን እንዲዘረጉ፣ በዕቅፍ ያሉና የጣር ድምፅ የሚያሰሙ ሕፃናት ልጆች ድምፅ ተሰምቶ በአፋጣኝ እንዲደረስላቸው አሳስቦ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ችግሩን አርቀን ከተመለከትነው እንደ አገር የምንገባበት ቀውስ ከባድ ስለሆነ፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደ አቅሙ እንዲረባረብ፤›› ሲል መልዕክት አስተላልፏል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች የወሎ ሕዝብ ድምፅ እንዲሆኑ ያሳሰበው እናት ፓርቲ፣ ‹‹መገናኛ ብዙኃንም የወሎ ሕዝብ ላንዣበበበት አደጋ ድምፅ እንድትሆኑ እንጠይቃለን ብሏል፡፡