የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታ ምክር ቤት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የተፈጠረውን አለመግባባት አስመልክቶ፣ ረቡዕ መስከረም 5 ቀን 2013 ዓ.ም. ፕሬዚዳንታዊ መግለጫ አውጥቷል፡፡
ፕሬዚዳንታዊ መግለጫው በሰኔ ወር 2013 ዓ.ም. በታላቁ የህዳሴ ግድብ አለመግባባት ላይ በፀጥታ ምክር ቤቱ የተደረገው ግልጽ ውይይት ውጤት ወይም ምክር ቤቱ የደረሰበት አቋም መግለጫ ተደርጎ የሚቆጠር ነው፡፡
የፀጥታው ምክር ቤት በየወሩ የሚለዋወጥ ወይም ለምክር ቤቱ አባል አገሮች በየወሩ የሚደርሳቸው ምክር ቤቱን የመምራት ፕሬዚዳንታዊ ሥልጣን አሠራሩን የሚከተል ሲሆን፣ በዚህ ወር ምክር ቤቱን የመምራት ሥልጣን ተራ የአየርላንድ መንግሥት ነው፡፡
በመሆኑም የህዳሴ ግድብ ድርድርን በተመለከተ የወጣው ፕሬዚዳንታዊ መግለጫ የአየርላንድ መንግሥት ተፅዕኖ ያረፈበት እንደሆነ ይነገራል፡፡ ይሁን እንጂ የፀጥታው ምክር ቤቱ ላወጣው ፕሬዚዳንታዊ መግለጫም ሆነ፣ የህዳሴ ግድቡ ውዝግብ በፀጥታ ምክር ቤቱ እንዲታይ የቀዳሚነት ሚናውን የተጫወተችው የዓረብ ሊግ አባል የሆነችው ቱኒዚያ ነች፡፡
ቱኒዚያ በአሁኑ ወቅት በፀጥታው ምክር ቤት የያዘችው መቀመጫ ለአፍሪካ አገሮች ወይም ለአፍሪካ አኅጉር ከተደለደሉ ሦስት መቀመጫዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ በአፍሪካ ኅብረት የአሠራር መርህ መሠረት የአፍሪካ አኅጉርን በፀጥታው ምክር ቤት የሚወክሉ አገሮች፣ አኅጉሪቱን ወይም አባል አገሮቹን አስመልክቶ በፀጥታው ምክር ቤቱ የሚነሱ ጉዳዮች ላይ በአፍሪካ ኅብረት ደረጃ የተያዘውን አቋም ማንፀባረቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ይሁን እንጂ ቱኒዚያ በፀጥታው ምክር ቤት የያዘችውን ተለዋጭ ወንበር በመጠቀም፣ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ውዝግብ በፀጥታ ምክር ቤቱ ውይይት እንዲደረግበት ረቂቅ አጀንዳ በመቅረፅና ሌሎች አባል አገሮችን በማስተባበር ውይይቱ እንዲካሄድ አድርጋለች፡፡
ምንም እንኳን የፀጥታው ምክር ቤት በሰኔ ወር 2013 ዓ.ም. ባደረገው ውይይት የኢትዮጵያ መንግሥትን አቋም የሚደግፉ አመለካከቶች በአብዛኞቹ የምክር ቤቱ አባላት የተንፀባረቀበት ቢሆንም፣ የቱኒዚያ መንግሥት ግን የግብፅን ፍላጎት ለማሳካት በያዘው አቋም በመፅናት የሰኔ ወሩ ውይይትን የተመለከተ የውሳኔ ሐሳብ በፀጥታ ምክር ቤቱ እንዲፀድቅ፣ የውሳኔ ሐሳቡን በማርቀቅና በማስተባበር ጭምር ተግቷል፡፡
ነገር ግን የውሳኔ ሐሳቡን ለማፅደቅ ቱኒዚያ የፀጥታው ምክር ቤት አባል አገሮችን በቂ ድጋፍ ባለማግኘቷ ሳይሳካላት ቀርቷል፡፡
የቱኒዚያ መንግሥት ግን በዚህ ተስፋ ባለመቁረጡ የፀጥታው ምክር ቤት ፕሬዚዳንታዊ መግለጫ እንዲያወጣ ግፊት ከማድረግ አልፎ፣ መግለጫውን አርቃቂ በማቅረብ ጭምር ግንባር ቀደም ሚና ተጫውቷል፡፡
ቱኒዚያ ለመጀመርያ ጊዜ በሐምሌ 2013 ዓ.ም. ያቀረበችው ረቂቅ ፕሬዚዳንታዊ መግለጫ፣ እጅግ ጠንካራና ከውሳኔ ሐሳብ (Resolution) ጋር የሚስተካከል እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
ቱኒዚያ በመጀመርያ ያቀረበችው ረቂቅ ፕሬዚዳንታዊ መግለጫ በምክር ቤቱ እንዳይፀድቅ በማድረግ፣ አራት ጊዜ በረቂቁ ላይ ማሻሻያዎች እንዲደረጉና በመጨረሻም እጅግ ቀለል ያለ መግለጫ እንዲወጣ በማድረግ ረገድ የፀጥታ ምክር ቤቱ ሌላዋ የአፍሪካ ተወካይ የሆነችው ኬንያ ትልቅ ሚና እንደተጫወተች፣ ከተመድ የተገኙ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
በስተመጨረሻም በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት የወቅቱ ፕሬዚዳንት በሆነችው አየርላንድ አምባሳደር ተፈርሞ ታላቁ የህዳሴ ግድብን የተመለከተው መግለጫ፣ ረቡዕ መስከረም 5 ቀን 2013 ዓ.ም. ወጥቷል፡፡
መግለጫው በዋናነት ያስቀመጠው ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን በአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ጥሪ በህዳሴ ግድቡ ላይ ያላቸውን አለመግባባት በድርድር እንዲፈቱ የፀጥታው ምክር ቤት እንደሚያበረታታቸው የሚገልጽ ሲሆን፣ በሚያደርጉት ድርድርም ሦስቱንም አገሮች በእኩል ተጠቃሚ የሚያደርግ ተቀባይነት ያለው ስምምነት አግባብነት ባለው የጊዜ ገደብ ውስጥ እንዲደርሱ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
ሦስቱ አገሮች እ.ኤ.አ. በ2015 የህዳሴ ግድብን አስመልክቶ የመርህ መግለጫ ስምምነት ማድረጋቸውን ምክር ቤቱ ዕውቅና እንደሚሰጠው መግለጫው ይገልጻል፡፡
በቀጣይ በአፍሪካ ኅብረት መሪነት በሚደረገው ድርድር ኅብረቱ የሚጋብዛቸው የድርድሩን ታዛቢዎች፣ እንዲሁም ሦስቱ አገሮች ተስማምተው የሚጋብዟቸው ሌሎች ታዛቢዎች በድርድሩ ወቅት አለመግባባት የሚፈጥርባቸው የቴክኒክና የሕግ ነክ ጉዳዮች እንዲፈቱ የማመቻቸት ድጋፍ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በተጨማሪም ሦስቱ አገሮች ድርድሩን በትብብርና ገንቢ በሆነ መንፈስ እንዲያካሂዱ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
በስተመጨረሻም ፕሬዚዳንታዊ መግለጫ ሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ላይ ለሚነሱ ውዝግቦች እንደ ገዥ መርህ ሊወሰድ እንደሚችል አስገንዝቧል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘም የህንድ መንግሥት ያቀረበውን የልዩነት ሐሳብ በመግለጫው ላይ እንዲካተት የተደረገ ሲሆን፣ የህንድ መንግሥት የህዳሴ ግድቡ ጉዳይ ፈጽሞ ወደ ፀጥታው ምክር ቤቱ መቅረብ የማይገባው አጀንዳ መሆኑንና አገሮቹ ልዩነታቸውን በትብብር መንፈስ ዘላቂነት ያለው የጋራ መፍትሔ በውይይት ማስቀመጥ እንደሚችሉና ትክክለኛው መንገድም ይህ መሆኑን ያመለክታል፡፡
የፕሬዚዳንታዊ መግለጫው አንድምታና የኢትዮጵያ ተቃውሞ
የፀጥታው ምክር ቤት ያወጣውን ፕሬዚዳንታዊ መግለጫ የግብፅና የሱዳን መንግሥታት በአዎንታ ተቀብለው እንደሚደግፉት ሲገልጹ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ግን መግለጫውን ውድቅ አድርጎታል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት ከፀጥታው ምክር ቤት ፕሬዚዳንታዊ መግለጫን መሠረት አድርጎ የሚመነጭ ማንኛውንም ዓይነት ጥያቄ ዕውቅና አይሰጠውም፤›› ብሏል፡፡
የፀጥታው ምክር ቤት ፕሬዚዳንታዊ መግለጫ የወጣው ምክር ቤቱ የህዳሴ ግድቡን አስመልክቶ በቀረበለት አጀንዳ ላይ በግልጽ ከተወያየ ከስምንት ሳምንታት በኋላ የወጣ መሆኑን የኢትዮጵያ መግለጫ በማስታወቅ፣ የምክር ቤቱ አባል አገሮች የህዳሴ ግድቡ የልማት ፕሮጀክት መሆኑን በመጥቀስ ምክር ቤቱ በዚሁ ጉዳይ ላይ መወያየት እንደሌለበት መከራከራቸውን ዕውቅና ሰጥቷል፡፡
ይሁን እንጂ ቱኒዚያ የአፍሪካ አኅጉርን በመወከል በፀጥታው ምክር ቤት ያገኘችውን የተለዋጭ አባልነት አጋጣሚ ባልተገባ መንገድ በመጠቀም፣ ይህ ፕሬዚዳንታዊ መግለጫ እንዲወጣ ግፊት ማድረጓ ታሪካዊ ስህተት እንደሆነ አመልክቷል፡፡
ቱኒዚያ ይህ ፕሬዚዳንታዊ መግለጫ እንዲወጣ ረቂቅ በማዘጋጀትና በማስተባበር ጫና ያደረገች ቢሆንም፣ በዋናነነት በኬንያ መንግሥት ተደጋጋሚ ጥረት በቱኒዚያ የተረቀቀው መግለጫ እንዲለዝብ ተደርጓል፡፡
በቱኒዚያ የተረቀቀው የመጀመርያ መግለጫ አገሮቹ በአፍሪካ ኅብረት መሪነት ተደራድረው፣ ሁሉም የሚቀበሉት አስገዳጅ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ጥሪ የሚያቀርብ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በዋናነነት በኬንያ መንግሥት፣ እንዲሁም በሌሎች የምክር ቤቱ አባላት በጠየቁት ማሻሻያ የፀጥታው ምክር ቤት ለአገሮቹ ጥሪ ከማቅረብ ተቆጥቦ፣ አገሮቹ ልዩነታቸውን በድርድር እንዲፈቱ እንደሚያበረታታ በሚል እንዲቀየር አድርገዋል፡፡
አስገዳጅ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ የሚለውን አገላለጽም በመቃወም፣ ሁሉንም ወገኖች የሚያስማማ ተቀባይነት ያለው ስምምነት እንዲያደርጉ በሚል እንዲለወጥ ማድረግ ችለዋል፡፡
በተለይ የምክር ቤቱ አባል አገሮች በፅኑ የተቃወሙት የረቂቅ መግለጫው አካል የተመድ ዋና ጸሐፊ በጉዳዩ ላይ በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ለፀጥታው ምክር ቤት ሪፖርት እንዲያቀርቡ የሚጠይቀው ክፍል ነው፡፡
ይህ ክፍል ተቃውሞ ሳይቀርብበት እንዳለ ቢያልፍ ኖሮ የታላቁ ህዳሴ ግድብ አጀንዳን የፀጥታው ምክር ቤቱ ይዞት እንደሚቆይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡
ኬንያን ጨምሮ የህንድ መንግሥትና ሌሎች የምክር ቤቱ አባል አገሮች ባቀረቡት ተቃውሞ፣ ይህ አገላለጽ ከመግለጫው ውስጥ እንዲወጣ ከማድረጋቸው በተጨማሪ፣ ይህ የፀጥታው ምክር ቤት መግለጫ ለሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮች እንደ መርህ ሊወሰድ አይችልም የሚል አንቀጽ በመግለጫው እንዲካተትና ጉዳዩም ከምክር ቤቱ አጀንዳነት ውጪ እንዲሆን ማድረግ ችለዋል፡፡
የፀጥታው ምክር ቤት ያወጣው ፕሬዚዳንታዊ መግለጫ አንድምታን በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ባለሙያ እንደሚሉት፣ ለምክር ቤቱ የቀረበው የህዳሴ ግድብ አጀንዳ በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ሥር እንዲወድቅ አድርጓል፡፡ በዚህም የኢትዮጵያ ሙግት ተቀባይነት ማግኘቱን የሚያስረግጥ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ሌላው ጉዳይ የፀጥታው ምክር ቤት ፕሬዚዳንታዊ መግለጫ አወጣ ማለት የሚሰጠው ትርጉም ነው፡፡ እንደ ባለሙያው ገለጻ፣ የፀጥታው ምክር ቤት በአንድ ጉዳይ ላይ ፕሬዚዳንታዊ መግለጫ አወጣ ማለት፣ በቀረበው አጀንዳ ላይ ውሳኔ ለማሳለፍ መስማማት ሳይችል ቀርቷል ማለት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የፀጥታ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንታዊ መግለጫ ማውጣቱ ቀርቶ ውሳኔ አሳልፎ ቢሆን ኖሮ፣ በኢትዮጵያ ላይም ሆነ በሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አገሮች ላይ አስገዳጅ ይሆን እንደነበር ገልጸዋል፡፡
ነገር ግን የወጣው ፕሬዚዳንታዊ መግለጫ በመሆኑ፣ በኢትዮጵያ ላይም ሆነ በሌሎቹ ባለድርሻዎች ላይ የአስገዳጅነት ውጤትን እንደሚያስከትል አስታውቀዋል፡፡