- ትኩረቱን ታዳጊዎችና ወጣቶች ላይ እንደሚያደርግ ባንኩ አስታውቋል
እግር ኳስና አትሌቲክስን ጨምሮ የተለያዩ ስፖርቶችን በማስተዳደር የሚታወቀው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከአምስት ዓመት በፊት ታዳጊዎችን ጨምሮ ያፈረሰውን ዋናውን የወንዶች እግር ኳስ ቡድን እንደገና ለማዋቀር እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ባንኩ በተለያየ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ታዳጊ ወጣቶችን ጨምሮ ዋናውን ቡድን በማቋቋም በ2014 የውድድር ዓመት በከፍተኛ (ሱፐር) ሊግ እንደሚወዳደር ጭምር በስፖርት ማኅበሩ በኩል የወጣው መረጃ ያመለክታል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስፖርት ማኅበር ቀደም ሲል የተለያዩ የመንግሥትና የግል ባንኮችን ስያሜ ይዞ እስከ 2006 ዓ.ም. ድረስ በዋናነት በእግር ኳስ በሁለቱም ፆታ በተለያየ የዕድሜ ክልልና በአትሌቲክስ እንዲሁም በሌሎችም ስፖርቶች ለኢትዮጵያ ስፖርት የበኩሉን ሚና ሲያበረክት ቆይቷል፡፡
የመንግሥትና የግል ባንኮችን ማለትም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ ኮንስትራክሽን ባንክ፣ ከግል ባንኮች ደግሞ አዋሽ ባንክና ንብ ባንክን ስያሜ በመያዝ ‹‹የኢትዮጵያ ባንኮች ስፖርት ማኅበር›› በሚለው መጠሪያ እስከ 2006 ዓ.ም. ድረስ ሲንቀሳቀስ የቆየ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ከ2006 ዓ.ም. በኋላ ግን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የወቅቱ ገዥ በነበሩት አቶ ተክለወልድ አጥናፉ ከሁሉም ባንኮች ፕሬዚዳንቶች ጋር በመነጋገር፣ የስፖርት ማኅበሩ በአንድ ተቋም ማለትም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አማካይነት እንዲተዳደር ከስምምነት እንዲደረስ አድርገዋል፡፡ ስምምነቱን ተከትሎ ማለትም ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ ‹‹የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የስፖርት ማኅበር›› በሚል መጠሪያ አትሌቲክሱና የሴቶቹ እግር ኳስ ቡድን ሲቀር የወንዶቹ ዋናውና የታዳጊዎቹ የእግር ኳስ ቡድኖች ግን በ2009 የውድድር ዓመት መጨረሻ ላይ በስፖርት ማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ሠይፉ ቦጋለ አማካይነት በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ እንዲፈርሱ ተደርገዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስፖርት ማኅበር ከመከላከያ ቀጥሎ የተለያዩ ስፖርቶችን በማቀፍ ሲንቀሳቀስ ይታወቃል፡፡ በአትሌቲክሱ እንደነ ሚሊዮን ወልዴ፣ አሰፋ መዝገቡ፣ መሠረት ደፋርና ሌሎችንም በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልልቅ ስምና ዝና ያተረፉ ታላላቅ አትሌቶችን ያፈራ፣ እስካሁንም በማፍራት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በእግር ኳሱም ቢሆን በተመሳሳይ በቁጥር የበዙ እግር ኳሰኞችን በማፍራት ከሚጠቀሱት ቀዳሚ የስፖርት ማኅበር አንዱ የነበረ መሆኑ የሚዘነጋ አይደለም፡፡
ከ2009 ዓ.ም. ጀምሮ አትሌቲክሱንና የሴቶች እግር ኳስ ቡድኑን በመያዝ የዘለቀው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስፖርት ማኅበር፣ ምንም እንኳን በወንዶቹ ዋናውና ታዳጊዎቹን ቡድኖች ቢያፈርስም በኢትዮጵያ የራሳቸው ማዘውተሪያ ማለትም ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም ካላቸው የስፖርት ማኅበሮች ቀዳሚው ነው፡፡ ሲኤምሲ አካባቢ የሚገኘው የክለቡ ስታዲየም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጨምሮ የተለያዩ ክለቦችና ቡድኖች ለልምምድ እየተጠቀሙበት ይገኛል፡፡ አንጋፋዎቹን ጨምሮ ብዙዎቹ ክለቦች በዚህ ደረጃ የተዘጋጀ ስታዲየም ባለቤት እንዳልሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡
የስፖርት ማኅበሩ ከሰሞኑ እንዳስታወቀው ከሆነ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ ዋናውን ቡድን ጨምሮ ዕድሜያቸው ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ቡድኖች እንደገና ተዋቅረው ወደ ውድድር እንዲገቡ መመርያ አስተላልፈዋል፡፡ ታዳጊዎቹን ቡድኖች የሚያዘጋጁ አሠልጣኞች እስከ ዓርብ መስከረም 14 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ ማስረጃዎቻቸውን አቅርበው ትክክለኞቹ ሙያተኞች እንዲለዩና ወደ ሥራ እንዲገቡ መመርያ ማስተላለፋቸውም ታውቋል፡፡