ወርልድ አትሌቲክስ ዕውቅና ከሚሰጣቸው የጎዳና ላይ ውድድሮች አንዱ የሆነውና ባለፈው እሑድ በዴንማርክ ኮፐንሀገን በተካሄደው ግማሽ ማራቶን፣ ኢትዮጵያውያኑ ፀሐይ ገመቹና ዐምደወርቅ ዋለልኝ ድል ቀንቷቸዋል፡፡ ርቀቱን 1፡05፡08 በማጠናቀቅ የውድድሩ አሸናፊ የሆነችው ፀሐይ፣ እ.ኤ.አ በ2018 በትውልድ ኢትዮጵያዊት በዜግነት ኔዘርላዳዊት በሆነችው ሲፋን ሐሰን ተይዞ የቆየውን የዓለም ክብረ ወሰንን አሻሽላለች፡፡ በወንዶች በተደረገው ተመሳሳይ ውድድር በኢትዮጵያዊው ዐምደ ወርቅና በኬንያዊው ኬኔት ሬንጁ መካከል የነበረው ትንቅንቅ በ0.2 ሰከንድ ልዩነት ርቀቱን በ59፡10 ደቂቃ አሸናፊ የሆነው ዐምደ ወርቅ መሆኑን ወርልድ አትሌቲክስ በድረ ገጹ አስታውቋል፡፡